የዘንድሮው ምርጫ የዘመናት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት ቁልፍ እንደሆነ መዘንጋት ሞኝነት ነው። በአገራችን ለበርካታ ዓመታት የሕዝቦችን ጥያቄ ወደ ተገቢው የዴሞክራሲ ባሕል መንገድ ማስገባት አልተቻለም ነበር። ጉዳዩን ወደኋላ አርዝመን ካየነው ምናልባትም ከታኅሣሡ ግርግርና ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የሕዝባችን የፖለቲካ ጥያቄዎች በዋናነት የሚንጸባረቁት አንድም በጎዳና ላይ ዐመጽ፣ ሁለትም በጦር መሣሪያ አማካኝነት ነበር። ሁለቱም መንገዶች እጅግ ኋላቀርና አውዳሚዎች እንደነበሩ እስኪበቃን አይተናል። አገራችን ኢትዮጵያ በድኻ ወገቧ አስተምራ ለከፍተኛ ደረጃ ያደረሰቻቸው አያሌ ተማሪዎች እና ምሁራን በገፍ አልቀውበታል። ለዓመታት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች በቀናት ልዩነት ወደ ትቢያነት ተለውጠዋል። እንዲያም ሆኖ የዘመናት ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ አላገኙም። ለምን?
በአንድ በኩል ነጻ አውጭ ድርጅቶች፣ ጠብመንጃ አንሥተው በገቡበት ጫካ «ራስን በራስ የማስተዳደር የብሔሮች መብት ዛሬውኑ ይከበር» ሲሉ፤ በሌላ በኩል የከተማ ሽምቅ ውጊያ የጀመሩ ኃይሎች «ሕዝባዊ መንግሥት ዛሬውኑ» እያሉ ሲፋለሙ ነበር። ከፍልሚያው በኋላ፣ የጭቆና ቀንበር ጫነ የተባለው ድርጅት ከመንበረ ሥልጣኑ ሲገለል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቅርጥፍ አድርገው የበሉ ጥያቄዎች በወጉ መልስ ሳይቸራቸው፣ «የሞግዚት አስተዳደር» እንዲያበቃ ዳግም ወደ ጫካ፣ ዳግም ወደ ጎዳና ተወጥቷል። ለምን?
«ምርጫ 97» የሕዝብን ጥያቄ ወደ ካርድ ማምጣት የቻለ ቢሆንም፣ ሂደቱ በአግባቡ ባለመቋጨቱ ምክንያት ውጤቱ የድሮው ዓይነት የጎዳና ዐመጽና የበረሃ ትግልን ወልዷል። በጎረቤት አገራት ተደብቀው ኢህአዴግን በጦር መሣሪያ ለመጣል ሲታገሉ የነበሩት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ምንጩ ያንን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ ባለመጠቀም የተፈጠረ እንደሆነ አይካድም። መቀመጫቸውን አሜሪካና አውሮፓ ያደረጉ፣ በሳይበርና በሜንስትሪም ሚዲያዎች ታግዘው ሲከናወኑ የነበሩ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች በአገር ውስጥ ካሉ የተቃውሞ ኃይሎች ጋር በመጣመር ዜጎች ድምፃቸውን በየጎዳናው እንዲያሰሙ በመገፋፋታቸው፣ ለብዙዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። ለምን?
የእነዚህ ሁሉ «ለምን» ጥያቄዎች መልሱ የሚያጠነጥነው የሕዝብ ድምፆች ተገቢውን ቦታ አግኝተው መሰማት አለመቻላቸው ነው። በሌላ አማርኛ ፓርላማችን እውነተኛ ፓርላማ የሚያደርገውን ባህሪ እንዲላበስ ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት የተፈጠረ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ልዩ ልዩ የሕዝብ ድምፆች የሚሰሙበት ፓርላማ ኖሯት አያውቅም። ሕዝብ ድምፁ በፓርላማ የሚሰማለት ከሆነ በምን ምክንያት ሕይወቱ በየጎዳናው ወይም በየዱር ገደሉ እንዲቀጠፍ ይፈልጋል? በምንም።
በዓለማችን ላይ በዴሞክራሲ ከፍ አድርገን የምንጠቅሳቸው አገራት የሕዝብ ጥያቄዎች የሚደመጡት በየጎዳናውና ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ሳይሆን በምክር ቤቶቻችው ነው። ለአገርና ለሕዝብ የሚበጁ ውሳኔዎች ሁሉ የሚወሰኑት በምክር ቤቶቹ አማካኝነት እንጂ በሌላ አካል አይደለም። ውሳኔውም በአገሬው ሕዝብ ሙሉ ተቀባይነት አለው። ይሄንን ያደረገው ወደ ውሳኔው ያደረሱት ሐሳቦች የእውነት የሕዝብን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሂደቱ አሳማኝ ስለሚሆን ጭምር ነው።
ለዚህም ሕዝቡና መንግሥት ያልተጭበረበረና የዜጎችን ድምፅ በትክክሉ የሚገልጽ ምርጫ እንዲካሄድ ከምንም በላይ የተለየ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። በዚህ መልኩ አንዴ ምርጫው የተሳካ ሆኖ ከተከናወነ ሕዝቦች ወደ ጎዳና መውጣት ሳያስፈልጋቸው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ድምፃቸው ስለሚሰማላቸው፣ ዜጎቻቸው ሰፊ ጊዜያቸውን በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አውለው፣ ራሳቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል።
የዘንድሮው የአገራችን ምርጫ ለኢትዮጵያውያን ይሄንን ወርቃማ ዕድል የሚፈጥር ነው። በተሳካ መልኩ ማከናወን ከቻልን በእርግጥም የሕዝባችንን ድምፅ ከጎዳና ወደ ፓርላማ፣ ከጫካ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ይመልሳል። ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በተሳካ መልኩ ማከናወን ቢቻል፣ መንግሥት የመመሥረቻ የሚያስችል መቀመጫ (ሃምሳ ሲደመር አንድ) ካገኘው ፓርቲ ባለፈ ሌሎች ፓርቲዎች ቁጥራቸው የማይናቅ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያገኛሉ። ይህ ማለት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ማለት ነው።
የአገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ውሳኔዎች በጥቂት ግለሰቦች/ቡድኖች የሐሳብ የበላይነት ተፈጻሚ መሆናቸው አብቅቶ ብዙ ድምጾች ተሰምተው፣ ብዙ ክርክሮች ተደርገው፣ ብዙ ሐሳቦች ተሰጥተውበት ይወሰናል። ለዚህ መሳካት የምርጫው ሂደት ላይ የተአማኒነት ጥያቄ ሊያስነሱ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ርምጃዎች ቀድመው ተወስደዋል። ከየትኛውም ፓርቲ ፍላጎት ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ በታሪካችን የመጀመሪያው አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ ሁላችንንም ያስማማል የሚል ግምት አለኝ። ያም ሆኖ፣ ሁላችንም ካርድ ወስደን ፍቃዳችንን ሊሞላልን የሚችለውን ተወካይ እስካልመረጥን ድረስ የተሠራው ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆናል። አገራችንም የኖረችበት አዙሪት ውስጥ ትወድቃለች። ስለዚህ የዕለት ተዕለት ችግርን በዕለት ተዕለት መፍትሔ ከመጋተር፤ ዋናውን መሠረታዊ ችግር በመሠረታዊ መፍትሔ ማስወገድ አዋጭ ነው።
አንዳንዶች ምርጫውን በዚህ ሰዓት ማድረግ ቅንጦት እንደሆነ አድርገው የተለያዩ ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። በማንነታቸው ሰዎች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሽምቅ ተዋጊዎች ሰላማዊውን ሕዝብ እረፍት እየነሡት ስለ ምርጫ መጨነቅ ተገቢ አይደለም ይላሉ። አገራዊ ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ ጥቃቶች ከውጭ አገራት እየተሰነዘሩብን፣ በዚህ በኩል የኑሮ ውድነትና የኮሮና ወረርሽኝ የዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ አደጋ እየጋረጠብን፣ ሌላ ራስ ምታት የሚሆን፣ ተጨማሪ ቀውሶችን ሊጋብዝ የሚችል ምርጫ ማድረግ እብደት እንደሆነ ይገልጻሉ።
እነዚህ ምክንያቶች ከላይ ከላይ ሲታዩ አሳማኝና የሰዎችን ልብ የሚገዙ ቢመስሉም፣ ከላይ በሰፈሩት መነጽሮች ሲፈተሹ ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይወድቃሉ። መከራከሪያዎቹ በአገራችን የሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለውጭ አገራት ኃይሎች እና የግል ፍላጎታቸውን ለሚያሳድዱ የውስጥ ኃይሎች ካልሆነ በቀር ደካማ መንግሥት ስለኖረን አገራችን ምንም ነገር እንደማታተርፍ ግልጽ ነው። ሁላችንም በንቃት በምንሳተፍበት የዘንድሮው ምርጫ የሕዝቦች ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ መግባቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መመሥረት በመቻሉ አገራችን የምታገኘው ጥቅም ከላይ ለቀረበው መከራከሪያ በቂ መልስ መሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 17፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013