ለምለም መንግሥቱ
ገለታ ሐይሉ ይባላሉ።በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ደራሼ ወረዳ ነው ተወልደው ያደጉት።ከአርሶአደር ቤተሰብ የተገኙት አቶ ገለታ በቤተሰብ አቅም ማነስ ትምህርታቸውን ከ12ኛ ክፍል በላይ ለመቀጠል አልቻሉም።በሥራ ራሳቸውን መለወጥ ግድ በመሆኑ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።ወደ ንግድ ሥራም የገቡት በ120 ብር ነበር።በትንሹ የጀመሩትን ንግድ ለማስፋፋት በ1985ዓ.ም የንግድ ፈቃድ በማውጣት በአካባቢያቸው በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉ የእህል ንግዶች ላይ ነበር የተሰማሩት።
አቶ ገለታ አሁን በእህል ንግድ ላይ ሳይሆኑ በሀር ልማት ላይ ነው የሚገኙት። ወደዚህ ልማት የገቡበትን አጋጣሚም እንዲህ ያስታውሳሉ ። ‹‹ጊዜውን አስታውሳለሁ።በ1996ዓ.ም ክረምት ወር ነው።ከመልካሳ የምርምር ማዕከል ስለሀር ልማት ቴክኖሎጂ መረጃ ሲተላለፍ ሰማሁ።ለመሞከር ጊዜ አልወሰደብኝም።ከተማ ላይ በነበረኝ ሁለት መቶ ሄክታር መሬት ላይ የሀር ልማት ሥራውን ጀመርኩ ።ወደ ሥራውም እንደገባሁ የተለያዩ ሀገራትን መረጃ ለማሰባሰብ ጥረት አድርጌያለሁ። የቻይናንና የህንድን ተሞከሮ ለማየት ሞክሬያለሁ። መረጃውን ወዳገኘሁበት መልካሳ ምርምር ማዕከል በመሄድ ከእነርሱ ልምድ በመቅሰምና ድጋፍም በመጠየቅ ወደ ሥራ ገባሁ›› ።በዚህ ሁኔታ ወደ ሐር ልማቱ መግባታቸውን ያጫወቱን አቶ ገለታ ልማቱን እያጠናከሩ እስከ 1998ዓ.ም ድረስ ዘለቁ።መንግሥትም ጥረታቸውን በማየት ሶስት ሄክታር መሬት ሰጣቸው።እርሳቸውም በተደረገላቸው ድጋፍ በመበረታታት ሥራቸውን ማሳደግ ቀጠሉ ። በሀር ልማቱ ከራሳቸው አልፈው ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ አርሶአደሮችን አደራጅቶ በማሳተፍ እንዲሁም በዓለምአቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሥነምህዳር(አይ ሲ አይ ፒ) ማዕከል የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው አምስት ሺ ወጣቶች ጋርም አብሮ በመሥራት ሥራቸውን ወደ ፋብሪካ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በቅተዋል።
አቶ ገለታ አንደገለጹልን የሐር ልማቱን የጀመሩት በባህላዊ መንገድ ነው ።ባህላዊ አሰራሩ በጣም አድካሚና ጊዜም ይወስዳል።ወደ ፋበሪካ ካደገ ወዲህ ግን ሥራቸውን አቀላጥፎላቸዋል።በጊዜም ተጠቃሚ ሆነዋል።ይህ ደግሞ ትርፋማ እንዲሆኑ አግዟቸዋል።ከእርሳቸውም አልፎ ለሌሎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏቸዋል።ምርቱን ወደ ውጭ በመላክም ለሀገርም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኢኮኖሚ ምንጭ ሊሆን ችሏል።ከሀገርም አልፎ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ሀገራትም ውስጥ ኢንዱስትሪውን በማቋቋም መስራት የሚቻልበት ዕድል አለ።በተለይ ከእርባታው ጀምሮ ምርት ሆኖ እስኪወጣ ድረስ ያለው ሂደት በዘመናዊ መሳሪያ መታገዙ ነው ለዚህ ሁሉ መብቃት የተቻለው።ለሀር ልማቱ የሚውለውን ማሽን ማድረቂያ፣ማጠንጠኛ፣ማጠናከሪያ በአጠቃላይ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በሚፈልጓቸው ደረጃ አምርቶ ለማቅረብ የሚያስችሉ ናቸው።
አቶ ገለታ ከእርባታው ጀምሮ ምርት እስከማውጣት ያለውን የሥራ ሂደት ሲያስረዱ፤ ለሀር ልማቱ የሚውሉ ትሎች የሚመገቡት ምግብ ቅጠል በመሆኑ በእርሻ ማሳ ላይ ነው የሚመረተው።ትሎቹ ምርት እስኪሰጡ ድረስ በቂ ምግብና እንክብካቤ የሚደረግላቸው ቦታ ያስፈልጋቸዋል።የእርባታ ቦታውም እንዲሁ ሰፊ ቦታና የሰው ኃይል ይፈልጋል።ሥራው በማሽን የሚታገዝ ቢሆንም የሰው ኃይል ያስፈልገዋል።በሀር ልማቱ ኢትዮጵያ ጀማሪ በመሆኗ እንጂ እንደ ህንድና ቻይና ባሉ ሀገሮች ለትሎቹ የሚሆን ምግብ ማለትም ተክሉን የሚያለማ፣ትሎቹን የሚንከባከብ፣መቀባበሉ ቢኖር ሥራውን ለተለያዩ አካላት በመሥጠት በቅብብሎሽ መሥራት ይቻል ነበር።በግብርናው ከሚሳተፉትና በውጭም ምርቶቻቸውን ከሚያቀርቡት በተጨማሪ በፋብሪካው ውስጥ በፈትል፣በሽመናና በሌሎችም ተያያዥ ሥራዎች ከ60 በላይ ሰራተኞች ይገኛሉ።በሥራው ላይ ያሉት በስፋት የቤተሰብ ኃላፊ የሆኑ ሴቶች በፋብሪካው ውስጥ ቤት በማመቻቸት ጭምር ነው የሚያሰሯቸው።
አቶ ገለታ በሥራው ላይ ለ13 አመታት ቆይተዋል።በስድስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ነው ወደ ሥራው የገቡት።አሁን ላይ ግን የመሥሪያ ማሽኑንና ሌሎችንም ንብረቶች ጨምሮ ካፒታላቸው ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ነው።ተቋማቸው ከአርሶ አደሮችና በማህበር ከተደራጁ ወጣቶች ጋር የሚሰራ በመሆኑ በስልጠናና ለትክል የሚሆን ዘር በመስጠት ድጋፍ ያደርጋል።ያመረቱትንም ምርት በመቀበል የገበያ ትስስር በመፍጠርም ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
ከማምረት ጀምሮ እስከ ሽመና ያለውን የአቶ ገለታን የሀር ልማት ሥራ እንዳየነው አካባቢው ላይ እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ ይኖራል ብለን አልገመትንም።እሴት በመጨመር የሚከናወነው ልማት አድናቆትን ፈጥሮብናል።በማንጎና በሞሪንጋ ቅጠል ቀለም እየተሰራ ከሀር ተሸምኖ የሚወጣው አልባሳት ትኩረትን ይስባል።ውጤቱ የሀር በመሆኑና እሴትም ስለተጨመረበት አንድ የአንገት ልብስ እስከ ሁለት ሺ ብር ዋጋ ያወጣል።
ፋበሪካው በአሁኑ ጊዜ በወር 80 ኪሎ ክር የማምረት አቅም ፈጥሯል።ይህ ግን በቂ አይደለም ይላሉ አቶ ገለታ።ክሩን የሚረከባቸው አዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ ሳባ ሀር የሚባል ድርጅት ነው።የድርጅቱን አንድ አራተኛ እንኳን ፍላጎቱን ማሟላት አልቻለም።ድርጅቱ ከህንድ ነው በስፋት የሚያስመጣው።ጃፓን ሀገር የሚገኝ ድርጅት እንዲሁ ምርት ፈልጎ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት አልተቻለም።ሰፊ የሆነውን የሀገር ውስጥና የውጭ ፍላጎት ለማሟላት የአቅም ውሱንነት አለ።‹‹አቅም እንዲፈጠር የመንግሥት እገዛ ያስፈልጋል።በኢትዮጵያ የሀር ልማት ስለማይታወቅ በፖሊሲ ደረጃ የተዘጋጀ ነገር የለም።በዚህ ምክንያት የባንክ ብድር ማግኘት አይቻልም።በቂ መሬት አይሰጥም።እየሰራሁበት ያለው ሶስት መቶ ሄክታር መሬት ሰርቶ ማሳያ እንጂ ከፍተኛ ምርት ለማምረት በቂ አይደለም።አሁን የምናመርተው በእንጆሪና በጉሎ ቅጠል ነው።ግን ከዚህም በላይ ማምረት ይቻላል።በዚህ አነስተኛ መሬት ላይ ለውጪ ንግድ የሃር ልማት ማምረት ህልም ነው››በማለት ያስረዳሉ።
አቶ ገለታ የህንድንም የቻይናንም የሐር ልማት ተሞክሮ ስላዩ አንድ ቀን እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ደርሰው ኢትዮጵያን በሀር ልማት የማስጠራት ራዕይ አላቸው።እኛም ሀሳባቸው እንዲሳካ እንመኝላቸዋለን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013