ጽጌረዳ ጫንያለው
ዶክተር ኢዳሶ ሙሉ ይባላሉ።አይነስውር ቢሆኑም ለመስራት የሚከብዳቸው ነገር እንደሌለ በተግባር የሚያሳዩ ናቸው።በተለይ በተማሪዎች ዘንድ ያላቸው ተወዳጅነት ብዙዎችን የሚያስቀና ነው።ምክንያቱም እርሳቸው ሲያስተምሩ ክፍሉ ሞልቶ በመስኮት የሚከታተለው ብዙ እንደነበር ተማሪዎቻቸው ይናገሩላቸዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ በአመራር ጥበባቸውም በሁሉም የሚመሰገኑ ናቸው።ለዚህም በሊቀመንበርነት ቀበሌ ላይ ሲያስተዳድሩና የምክር ቤት አባል ሆነው ሲሰሩ እንዲሁም በሌሎች ሃላፊነቶች ላይ ሲቀመጡ ያመጧቸው ለውጦች ምስክር ናቸው።
መጀመሪያ አካባቢ ብዙዎች ቦታውን እንዲይዙ አይፈልጉም።ተቃውሟቸውንም በተለያየ ነገር ያሳዩባቸው ነበር።ሆኖም ቦታው ላይ ሲሆኑ ብዙዎች በተናገሩት ይጸጸታሉ።እርሳቸው አይነስውር መሆናቸው ብቻ ነው ልዩነታቸው የሚለውንም ያረጋግጣሉ።እንደውም ለሌላ ነገር እጩ ሲፈለግ ቅድሚያ ጠቋሚዎች የሆኑላቸው ብዙዎች እንደነበሩ ይናገራሉ።
በቤተሰብ አመራርም እንዲሁ የተሻሉ እንደሆኑ በልጆቻቸው ጭምር አሳይተዋል።እናም አይነስውርነት አይን ማጣት እንጂ አቅም ማጣት እንዳልሆነ በተግባር ያሳዩ በመሆናቸው ለዛሬ ለብዙዎች ትምህርት ሰጪ እንዲሆኑ በ‹‹ ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገን አቅርበናቸዋልና ልምዳቸውን ቃርሙ ስንል ጋበዝን።
ልጅነት
የተወለዱት በቀድሞ ሲዳማ ዞን በአሁኑ ሲዳማ ክልል ውስጥ በነበረችው እንታዬ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ነው።ቦታዋ በኦሮሚያና ሲዳማ መሀል አካባቢ ስለምትገኝ የሁለቱንም ባህልና ቋንቋ በደንብ አውቀው እንዲያድጉ አድርጓቸዋል።ግን የልጅነት እድገታቸውን በደንብ እንዲያጣጥሙባት እድሉ አልሰጣቸውም።ምክንያቱም እናትና አባታቸውን ገና በልጅነታቸው በማጣታቸው ወንድማቸው ቤት በመሆን ነበር ጊዜያቸውን ያሳለፉት።
ይህ ደግሞ ምንም እንኳን ወንድማቸው የፈለጉትን እያደረገና አባታቸው ሆኖ እየተንከባከባቸው ቢያድጉም ሁለት ጊዜም ያገባቸው ሚስቶች ለእርሳቸው ምቹ አልነበሩም።በዚህም ከዚያ ቦታ መሄድን ይፈልጉ ነበር።ማንንም መውቀስና ማጋጨት ስለማይፈልጉም ምንም ሳይሉ ነበር ፈጣሪ ያመጣላቸውን የውጪ ዜጋ ነርስ ተከትለው ወደ ባኮ ያመሩት።
በእርግጥ ምክንያታቸው ይህ ብቻ አልነበረም።በአካባቢያቸው ፈንጣጣ የሚባል በሽታ በመግባቱ የእነርሱ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ቀጥፏል። የእንግዳችንም ታናሽ እህት በዚህ በሽታ ነው የሞተችው።በበሽታው አንድ አይኑ የጠፋ ወንድምም አላቸው።እርሳቸውን ደግሞ ሁለቱም አይናቸው እንዲጨልም አድርጓቸዋል።
ስለዚህም ይህንን ችግራቸውን የሚፈታና የመማር እድል የሚሰጣቸው መኖሩን ሲሰሙም ነው የተከተሏት።ስለዚህም በዚያ ቦታ ላይ ብዙም የልጅነት ጊዜያቸውን አላሳለፉም።ብዙ የልጅነት ትዝታም ያላቸው ባኮ ላይ በነበሩበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከወንድማቸው ጋር ሲኖሩ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውኑ ነበር።በተለይ ገመድ በመግመድ የሚያክላቸው አልነበረም።ኑሯቸው ገጠር አካባቢ በመሆኑ ለጥጃ ማሰሪያ ጭምር በእርሳቸው የተገመዱ ማሰሪያዎች አገልግሎት ላይ ይውሉ እንደነበር አይረሱትም።
ከዚያ ባሻገር አገዳና በቆሎ የመሳሰሉ እህሎችን እንዲሁም የጓሮ አትክልቶችን በመትከልና በመዝራት እየኮተኮቱና እየተንከባከቡ የድርሻቸውን ለቤተሰቡ ይወጣሉ። ሥራቸውን ሲሰሩ በቻሉት ልክ አድምተውም ነበር።እንደውም እርሳቸው ማሳ ውስጥ ማን ገባ የሚለውን ጠንቅቀው ያውቃሉም፤ ይጠይቃሉም።ሆኖም ከአራት ዓመታቸው በኋላ ግን አይነስውርነታቸው ይህ ሁኔታቸውን የተለየ ኑሮ እንዲኖሩ አደረጋቸው።
በአካባቢው ዘንድ አይነስውር ይማራል የሚል እሳቤ ባለመኖሩና እንደሚማሩም የማያውቁት ባለታሪካችን፤ ነርሷ መጥታ ይህንን ስትነግራቸው ማመን እንደከበዳቸው፤ ጊዜም ሳይፈጁ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ የትውልድ ቀያቸውን እንደለቀቁ ያስታውሳሉ።ባኮ የአይነስውራን ትምህርት ቤት በአዳሪነት መግባታቸውን ሲረዱና ያለውን ምቹ ሁኔታ ሲያዩ ደግሞ የበለጠ ስንቅ እንደሰነቁም አይረሱትም።
ምክንያቱም ጨዋታና ሥራን በደንብ ያዩት በዚህ ቦታ ነው። እዚህ እንደገቡ ልዩ ትኩረታቸው ትምህርት ቢሆንም የእጅ ሥራ ሙያ ለምደውበታል።ማንም የማይቀድማቸውን የቡርሽ ሥራ እየሰሩም በወር 30 ብር ይከፈላቸው ነበር።በተለይ በጥራት መስራታቸው የበለጠ ጉርሻ ያስገኝላቸው እንደነበር አይረሱትም።
ቀደም ሲል በነበረው የልጅነት ጊዜ ዶክተር ኢዶሳ ልጆች እንዲጫወቱ ቢጋብዟቸውም እርሳቸው ግን ከእነርሱ ጋር ተቀላቅለው መጫወትን አይፈልጉም ነበር።ምክንያታቸው ደግሞ ተሸናፊ መባልን አለመፈለጋቸውና እናት አባት ስለሌላቸው ከእነርሱ የተለየሁ ነኝ ብለው ስለሚያስቡ ነው።በዚህም ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በገመድና መሰል የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በመስራት ነበር።ይህ እንዳይሰማቸው ወንድማቸው ብቻ ሳይሆን አክስትና አጎቶቻቸው እንዲሁም የአካባቢው ሰው በጣም ይጥራል።ነገር ግን እርሳቸው ከአዕምሯቸው ውስጥ ይህንን ማስወገድ ባለመቻላቸው አያደርጉትም።ፈታ ብለው ከጨዋታ ጋር በደንብ የተተዋወቁት አዳሪ ቤት ሲገቡ ነው፡፡
በአዳሪ ቤቱ ውስጥ የተለየ ሥጦታቸውን ጭምር አግኝተውበታል።ይህም ጎበዝ የእግር ኳስ ተጨዋች መሆናቸው ነበር። በዚህ ቤት አይነስውራን እኩል የመጫወት እድል አላቸው።እናት አባትም ለሁሉም እዚያ ያለው ማህበረሰብ ነው።እናም ምንም ሳይሰማቸው የፈለጉትን እንዲያደርጉ አግዟቸዋል።በዚህም እንግዳችን የጨዋታ ጥማቸውን ለመወጣት በሚያስችል መልኩ እግር ኳስን በሚገባ ተጫውተውበታል።ይህ የሚሆነው ደግሞ ኳሷ ውስጥ ቃጪል ገብቶ የሄደችበትን አቅጣጫ እየተከተሉ እንዲጫወቱ ይደረጋሉና ሳይቸገሩ ይጫወታሉ።
እርሳቸውም በጨዋታው ኢሊጎሬ የማይስቱ ተጨዋች ሆነውበታል።ዛሬም ቢሆን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሳይቀር እግር ኳስ እንዲከታተሉና የቡድናት አድናቂ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።እንደውም የአዋሳ ከነማና የቸልሲ ደጋፊ መሆናቸውን አውግተውናል።እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በጭላንጭል ያዩ ስለነበር ጥሩና የተዋጣላቸው ተጨዋች መሆን እንዳስቻላቸውም አውግተውናል።
እንግዳችን ዘማሪም ናቸው። ኦርጋንና ፒያኖ በደንብ ይጫወታሉ።ነርሷ ደግሞ የአካባቢውን ሰው ታግዝና ታገለግል ስለነበር የበለጠ ውጤታማ ወደሚሆኑበት ቦታ ማለትም ወደ ባኮ አይነስውራን ትምህርት ቤት በአዳሪ ተማሪነት ስትወስዳቸው ይህንን ክህሎታቸውን የበለጠ አዳብረውታል።ዛሬም መሳሪያዎቹን በደንብ ይጫወታሉ፤ ያገለግላሉም።
በባህሪያቸው ምስጉን፣ ተጨዋችና ከሁሉ ጋር መኖር፣ መብላት፣ መስራት የሚወዱ ናቸው።ብቻዬን የሚሉት አንድም ነገር የላቸውም።በጋራ የሚባል ነገር ከሁሉ ይልቅባቸዋል።በተለይ ግን ለየት የሚያደርጋቸው ሥራን ለነገ ማለት የማይወዱ መሆናቸው ነው።በጥራት በጊዜ ማጠናቀቅ፤ መሸነፍ መሞት እንደሆነ የሚያስቡ አይነት ልጅም ናቸው።ከዚህ አንጻር የልጅነት ህልማቸው ጠንካራውን መምህር መሆን ነው።ምክንያታቸውም የሚወዷቸውና አርአያ የሚያደርጓቸው ብዙ መምህራን በዙሪያቸው መኖራቸው ሲሆን፤ እንደእነሱ መሆን አለብኝ በሚል ከጉብዝናቸው እስከ ንግግራቸው እነርሱን ለመሆን ይጥሩ ነበር።
ደረጃውን ያለቀቀው ተማሪ
ከትምህርት ጋር የተገናኙት በአንዲት አማኝ ፈረንጅ ነርስ አማካኝነት ሲሆን፤ እርሷ በሰፈራቸው ክሊኒክ ከፍታ ትሰራ ነበር።እናም ስታገለግል እርሳቸውን ደጋግማ በማግኘቷ አይነስውራን እንደሚማሩ ስለምታውቅ ባኮ አይነስውራን ትምህርት ቤት እንዲገቡ ረዳቻቸው።በወቅቱ ሰባት ወይም ስምንት ዓመት ቢሆናቸው ነው።እናም በዚህ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተማሩ።በሦስት ዓመት ውስጥም ትምህርቱን ማጠናቀቅ ቻሉ።አምስተኛንም ሳይማሩ ስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ በመውሰድና 100 በማምጣት ሰባተኛ ክፍልን ተቀላቀሉ።
ከመንግስት ትምህርት ቤት ጋር የተዋወቁት ስድስተኛ ክፍል ሲገቡ እንደነበር የሚያወሱት ባለታሪካችን፤ የገቡበት ትምህርት ቤት በአምቦ ከተማ የሚገኘው አምቦ መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።እስከ 12ኛ ክፍልም በዚህ ቦታ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።ስለዚህም ምንም ሳያቆራርጡ ነው የተማሩት።ለትንሽ ጊዜ የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ የእድገት በህብረት ዘማች ሆነው አጋርፋ ላይ ዘምተው ከማቋረጣቸው በስተቀር።
እናም በዚህ የትምህርት ጉዟቸው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያቸው ከፍተኛ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።ከዚያ በቀጥታ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቀኑ።በእንግሊዝኛ ቋንቋ የትምህርት መስክም 3 ነጥብ 9 በማምጣት በከፍተኛ ውጤት ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ቢሆን በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የተማሩት ዶክተር ኢዳሶ፤ ትምህርቱ በሥራቸው ጠንካራ በመሆናቸው ያገኙት እድል ነው።ማለትም የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት በገቡበት ሁሉ ፍሬያማ ሥራ የሚሰሩ በመሆናቸው እንዲማሩ ሙሉ ወጪአቸውን ለመቻል ቃል ገባላቸው።በዚህም የመግቢያ ፈተናውን ወስደው በከፍተኛ ውጤት አልፈው የእድሉ ተጠቃሚ ሆኑ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ገብተው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መስክ በማዕረግ ተመረቁ።
ሌላኛው የትምህርት ጉዟቸው የሚወስደን አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የሚመራው ዩኒሳ ውስጥ ሲሆን፤ የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት እድልም ሲመጣ በአንደኝነት አልፈው እንዲገቡ የሆኑበት ነው።እዚህም ቢሆን በተሻለ ውጤት ነው መመረቅ የቻሉት።ከዚያ በትምህርት ጉዟቸው በተለያዩ ስልጠናዎች አቅማቸውን ማጎልበት ችለዋል።በእርግጥ በእርሳቸው እሳቤ ማስተማር ሁልጊዜ መማር ነው።መመራመርና ሌሎችን ማማከርም እንዲሁ የተሻለ እውቀት ለማግኘት ወሳኝ ተግባር ነው።ስለዚህም በዩኒቨርሲቲው በሚሰሯቸው አጠቃላይ ተግባራት የሁልጊዜ ተማሪ ሆነው እየቀጠሉ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።
አይነስውርነታቸው ደግሞ የበለጠ ለመስራት እንዳገዛቸውም ያወሳሉ።ምክንያቱም ጉብዝናቸው፤ አልችልም የሚል ፍራቻ በውስጣቸው ያለመኖሩ፤ ተጨዋችና ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር መኖራቸው የሚወዱ መሆናቸው ይህንን ስሜት እንዳቀዳጃቸው ይናገራሉ።መምህራን ጭምር ይወዷቸውና ጓደኛቸው ይሆኑላቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።ከዚያም አልፈው በሚቸግራቸው ሁሉ ይደግፏቸው እንደነበር አይረሳቸውም።ይህ ደግሞ አይነስውር መሆናቸው በትምህርት ጉዟቸው ተሰምቷቸው እንዳያውቅ አድርጓቸዋልና ነው። ስለዚህም ለትምህርታቸው ውጤታማነት የሁሉም ድርሻ አለበትም ይላሉ።
የሰው ልኬቱ ብቃቱ
ዶክተር ኢዳሶ የሰው ልኬቱ ብቃቱ እንጂ የአካል ጉዳቱ ሊሆን እንደማይገባ አበክረው የሚታገሉና የማይወላውል አቋም ያላቸው ናቸው።እናም እኔ ስመዘንበት የነበረው አይነስውርነት ሌላው ላይ ሊከሰት አይገባውም ይላሉ።ምክንያቱም እርሳቸው ዳይሬክተር ለመሆን አይነስውር አይችልም ይባሉ ነበር።ለትምህርትም ቢሆን በጽሁፍ ጭምር ተፈትነው ሌሎችን ሲበልጧቸው ድጋፍ እንደተደረገላቸውና የተለየ ሻጥር እንደተሰራላቸው ተደርጎ ይወሰድባቸው ነበር።እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ዳግም ፈተና እንዲወስዱ የተደረገበትን ሁኔታ አይረሱትም።ስለዚህም የሰው ልጅ ከብቃቱ ባሻገር ሌላ የሚለካበት መስፈርት መኖር እንደሌለበት በጽኑ ያምናሉ።
የመጀመሪያ ሥራቸው የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ገና ሲጀምሩም ነበር እንቅፋትም ተቃውሞም ይገጥማቸው የነበረው።እርሳቸው ግን ይህንን ታግለው በማሸነፍና ብቃታቸውን በማሳየት አሸንፈውታል።የእንግሊዝኛ ቋንቋን በማስተማር ስለነበር ሥራው የተጀመረው ደግሞ ብቃታቸውን በሚገባ ለማሳየት አግዟቸዋል።ከዚያ በቋሚነት ተቀጥረው ከሥራው ጋር ሲገናኙ ማለትም ከምረቃ በኋላ አሁንም ላይታለፉ የሚችሉ የሚመስሉ ፈተናዎች ገጥመዋቸው ነበር።ይሁን እንጂ ይህንንም በብቃት አልፈውታል።እንደውም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ከእርሳቸው የተሻለ መምህር እንዳልነበር ይነገርላቸዋል።
ማስተማር የጀመሩት በይርጋለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ በትምህርት ቤቱ ለ18 ዓመታት ያህል አገልግለዋል።በእርግጥ በመምህርነት ብቻ አልነበረም የሰሩት።የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል።ፈተናው የበለጠ የነበረውም በዚህ ቦታ ላይ እንደነበሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።እንዴት አይነስውር ሀላፊ ይሆናል ተብለዋል።ምክንያታቸው ደግሞ ለአመራር አይበቃም የሚል ነበር።ነገር ግን በሚሰሩት ሥራ ብዙዎች እንዲደመሙባቸው አድርገዋል። እንደውም ረጅሙ ጊዜ በኃላፊነት የሰሩበት በዚህ ቦታ ላይ ባሉበት ጊዜ ነው።ይህም 13 ዓመት ከመንፈቅ ተቆጥሮበታል።
ቀጣዩ የሥራ ጉዟቸው ሀዋሳ ላይ የሚወስደን ሲሆን፤ በሥራቸው የረካውና ለከተማው አስፈላጊ ሰራተኛ መሆናቸውን ያመነው የትምህርት ጽህፈት ቤቱ በቀጥታ በዝውውር ወደ ሐዋሳ አስገባቸው።አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን እንዲቀላቀሉም አደረጋቸው።
በዚህም እንደገቡ በኃላፊነት ላይ አልነበረም የተቀመጡት።የይርጋለሙን የመምህርነት ተሞክሮ በዚህም እንዲተገብሩት በመፈለጉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ሆነው መስራታቸውን ቀጠሉ።በእርግጥ ኃላፊም ሆነ መምህር ሆነው መቼም ማስተማራቸውን አቋርጠው አያውቁም።ሰዓት መድበውና ክፍለ ጊዜ ይዘው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በቋሚነት ያስተምራሉ።ሀዋሳም ከመጡ በኋላ የትምህርት ቤቱም ዳይሬክተር ሲሆኑም ይህንን ነበር ያደረጉት።እናም ለእርሳቸው መምህርነት ከደም ሥር ጋር የተሳሰረ ሙያ ነው።
ዶክተር ኢዳሶ ሹመት የሚባል ነገር አይወዱም።ሰው በብቃቱ ተወዳድሮ እንደሚችል አሳይቶ አልፎ ስራዎችን መስራት አለበት የሚል እምነት አላቸው።በዚህም ሀዋሳ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በዳይሬክተርነት ለማስተዳደር ሲበቁ በሹመት ሳይሆን ተወዳድረው በማሸነፍ ነው።በወቅቱ አይነስውር እንዴት ዳይሬክተር ይሆናል ተብለው እንደነበር አይረሱትም።ብዙ አንባጓሮም እንደተፈጠረ ያስታውሳሉ።እንደውም ዳግመኛ ፈተናው የወሰዱበትም ይህ አጋጣሚ እንደነበር ይናገራሉ።
‹‹አይነስውር ዓይኑ ታወረ እንጂ አዕምሮው አልታወረም።ስለዚህም የሚመራው በአዕምሮ እንጂ በዓይን አይደለም›› የሚሉት ባለታሪካችን ፤ ፈታኞቹ ሳይቀሩ ስለእርሳቸው ብቃት የመሰከሩና በአቅም ከእርሳቸው የሚበልጥ እንደሌለ የተማመኑባቸው ነበሩ።አንዱ ብቻ ነው ይህንን መቀበል ያዳገተው።
ሆኖም እርሱም ቢሆን በምስክሮቹ ሀሳቡን ሊቀይር ችሏል።በዚህም በሥራው ላይ ለሦስት ዓመት ተኩል መቆየት ችለዋል። ይህ ጊዜ ደግሞ ለሌሎቹ መምህራን ጭምር ምሳሌ ሆነው ያሳለፉበት እንደነበር ያስታውሳሉ።ከዚያ ባሻገርም ቅዳሜና እሁድም ቢሆን ሜካብ እየጠሩ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የጣሩበት እንደነበርም አይረሱትም።
አዲስ ከተማ ትምህርት ቤትን በዳይሬክተርነት ሲመሩ የተለያዩ ነገሮችም ተፈጥረዋል።ከእነዚህ መካከልም በትምህርት ቤቱ ታይቶ የማይታወቅ ውጤት መምጣቱ አንዱ ነው።63 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉበት ጊዜም ነበር።አጥር ያልነበረው ትምህርት ቤትም ከውጪ ረጂ ተቋማት ጋር በመነጋገር ሥራውን አስጀምረዋል።
የተለያዩ ልማታዊ ሥራዎች እንዲኖሩም ሰርተዋል።ከዚያ ልቆም ማንም የማያውቀው ትምህርት ቤቱ በሁሉም ዘንድ ተመራጭ ሆነ።ታዋቂነትን በማግኘቱ ደግሞ በግል የሚያስተምሩ ወላጆች ጭምር ልጆቻቸውን ወደዚያ ማስገባት ጀመሩ።ይህ ደግሞ የእርሳቸው ስኬታማ ሥራ ውጤት እንደነበር አይረሳቸውም።
እንግዳችን በይርጋለም እና ሀዋሳ ከተማ ላይ የሚማሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማትሪክ እንዲዘጋጁ የሲዳማ ልማት ማህበር ቀጥሮ በክረምት እንዲያስተምሩ በትልቅ ብቃት የመረጣቸውም ናቸው።ምክንያቱም ብዙዎቹ በስም ያውቋቸዋል።እንዲያስተምሯቸውም የሚፈልጉት እርሳቸውን ነው።ስለዚህም ተማሪም ወላጅም መርጧቸው ከተቀጠሩት መካከል አንዱ ነበሩ።ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲጨርሱ ደግሞ በቀጥታ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ።
ሥራ መስራት ለብቃት ምስክር ነው የሚሉት እንግዳችን፤ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥምም ያሻግራል ባይ ናቸው።ለዚህም ማሳያው የሚያደርጉት አሁን በማስተማር ሥራና በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ መስራታቸውን ነው።እንደውም በማስተማር ብቻ 39 ዓመታትን ለማሳለፋቸው፤ በሥራቸው በሁሉም ነገር አንቱታን ያተረፉበት ምስጢር ይህ እንደሆነም ይናገራሉ።እርሳቸው ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ባደረጉት የማስተማር ጉዞ ብቃታቸውን ሁሉም ተማሪ የሚያደንቅላቸው አይነት ናቸው።ለዚህም ማሳያው ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚመጣው ተማሪ ቀላል አለመሆኑ ነው።ክፍሉ ጢም ብሎ ሞልቶ በመስኮት ጭምር የሚማረው ብዙ ነው።
ከተማሪዎች ጋር ያላቸው ቅርበትም ቢሆን አጃኢብ ያሰኛል።የዩኒቨርሲቲው መምህራንን ጭምር የሚያስቀና እንደሆነ አብረዋቸው የሚያስተምሩ መምህራን ይመሰክሩላቸዋል።በተመሳሳይ በሥራ አድምተው እንጂ ደምተው እንደማይወጡም ይነገርላቸዋል።በአይነስውርነታቸው ይህ ፈትኖኛልን ለማስተማሪያ እንጂ ለወቀሳ አያቀርቡትም።በዚያ ውስጥ ሆነው መቆዘምና አለመስራትንም በፍጹም አይፈልጉም።ከዚያ ይልቅ አይነስውር መሆንን በብቃት አሸንፈው ማሳየትን ይወዳሉ፤ ያደርጉታልም።
ዶክተር ኢዳሶ ከመምህርነት ውጪም በተማሪነት ህይወታቸው ሳይቀር ሌሎችን ያግዙ ነበር።ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ በባህሪያቸው ተጨዋችና ሰው ወዳድ በመሆናቸው ብዙ ጓደኞች ማፍራታቸውና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አይነስውራን ጭምር አንባቢና ጸሐፊ ጭምር እንዲቸሩ መሆናቸው ነው።
ከዚያ ሻገር ስንል ደግሞ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተው ያውቃሉ።ከእነዚህ መካከል ደግሞ የመምህራን ማህበር ተወካይ ሆነው የሰሩት፤ የዳሌ ወረዳ ምክር ቤት በመሆን ያገለገሉት፤ በይርጋለም ከተማ ከፍተኛ አንድ ቀበሌ 05 የፍትህ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነውም የሰሩበት ተጠቃሽ ነው።በተመሳሳይ የቀበሌው አስተዳደር ምክትል ሊቀመንበር በመሆንም አገልግለዋል።ሀዋሳ ከገቡ በኋላ ደግሞ ከፍተኛ ቀበሌ 01 ሥራ አስፈጻሚ አባልና ሊቀመንበር በመሆን ሰርተዋል።
ኤሊት ማለትም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራም ማዕከልን ከይርጋለም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እስከገቡበት ድረስ አስተባባሪ በመሆን መስራት የቻሉም ናቸው።ሌላው የሰሩት የደቡብ ክልል የእንግሊዝኛ መምህራን ሂልተልኔት የሚባለውንም በአስተባባሪነት በአገር አቀፍ ደረጃ መርተዋልም።አሁን ደግሞ የሚገኙት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስፖክን እንግሊሽ መምህርና ማህበረሰብና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ውስጥ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አመራርነት በአይነስውር በመምህሩ እይታ
ማየት መቻል ሙሉ ለሙሉ ሲቆም ከመሞት እንደማይተናነስ የመገመት ያህል ይከብዳል።ምክንያቱም በምናብ መስራትን ይጠይቃል።ስለዚህም ይህንን ለማድረግ ደግሞ ብዙ ይዳከራል።ጥረቱም ቢሆን ቀላል ፈተና አይኖርበትም።
ብዙ መገለሎች ይኖራሉ።ግን ይህንን ለማለፍ ደግሞ ብዙ መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን ዋነኛ ተግባር ነው የሚሉት እንግዳችን፤ ሁሉም ነገር በአዲስ መልኩ ሲጀመር ግራ ያጋባል።ሥራው ምንም እንኳን ቀላል ቢሆንም ከአዲስነቱ አንጻር ብቻ ይከብዳል።ይህ የሚሆነው ደግሞ ለአይነስውራን ብቻ ሳይሆን ማየት ለሚችለውም ነው።እናም ይህ ተስፋ ባለመቁረጥ ብቻ እንደሚመለስ ከነበራቸው ልምድ በመነሳት ይመክራሉ።
ለአካል ጉዳተኛው በማህበረሰቡም ሆነ በተማሩ አካላት ጭምር የሚሰጠው ግምት አይሆንም ነው።እንደሚሆን ለማሳየት ደግሞ በልጦ መታየትና እነርሱን ማሸነፍን ይጠይቃል።ከመገልገያ ግብዓት ጀምሮ በቀላሉ የሚገኝም አይደለም።ለመጻፍ፣ ለማንበብ ወዘተ ሁሉን ነገር በትግል ማግኘትን ይፈልጋልም ይላሉ።
‹‹አይነስውር ሆኖ ማስተማር በብዙዎች ዘንድ የሚታሰበው ለተማሪዎች መጫወቻ መሆን ነው።ይታለላል ተብሎ ይታመናልም።ለእኔ ግን ይህ የተለየ ቦታ አለው።የተለየ ሥራን ቢጠይቅም ሲሆንብኝም አላየሁም።ምክንያቱም እኔ ሰዓት አከብራለሁ፤ ሰዓቴንም ለማንም መስጠት አልፈልግም።የሚፈልጉትንም በሚገባ አስተምራለሁ።ሳርም እንኳን ከአንድ ሰው ጋር በመሆን ብቻ አይደለም።
ብዙ ሰው እንዲያይልኝ እዟዟራለሁ።በዚያ ላይ ተማሪዎቼን በስም ብቻ ሳይሆን በመቀመጫቸውና በድምጻቸው ጭምር አውቃቸዋለሁ።በእርምጃና በመዳሰስም ቢሆን ብዙ የመለየት ብቃት አለኝ።ይህ ደግሞ ምን አይነት ተማሪ እንደሆኑም እለካበታለሁ።ስለዚህም ስህተት የተማሪዎች ውጤት አይሆንም።እነርሱንም እኔን ስህተት ውስጥ መክተት አይፈልጉም።ከዚያ ይልቅ ራሳቸውን መፈተኛ ነው የሚያደርጉኝ።እናም መምህርነት በአይነስውርነት እንዲህ ነው መሆን ያለበት›› ይላሉ።
አይነስውራን የሚያቅታቸው ነገር አለ ብዬ አላምንም።መጻፍና ማንበብ ካልሆነ በቀር።ይህም ቢሆን በመሳሪያ በመታገዝ ተግባራዊ የሚደረግበት ላይ ስለደረስን የሚከብድበት ሁኔታ ቀሏል።እናም የአመራርነት ቦታቸውን በአዕምሯቸው ብቃት ለመምራት ምንም አይፈትናቸውም።
እንደውም የበለጠ የሚታዩበት ነው የሚሆንላቸው።ምክንያቱም ሲገቡ በፈተና ስለሆነ ሲወጡ በክብርና ሰዎችን በመብለጥ ይሆንላቸዋልና ነው።ቦታው በእነርሱ ጊዜ የተሻለ ሆኖ እንዲታይላቸው ለማድረግ የሚታትሩበት ጊዜ ቢኖር ሀላፊነት ሲሰጣቸው ነው።እናም በማንኛውም ቦታ እችላለሁ ብለው ገብተው ማሳየትን መልመድና ለሌሎች አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋልም ምክራቸው ነው።
ቤተሰብ
ዶክተር ኢዳሶ የአራት ልጆች አባት ናቸው።ሁሉንም ከሁለት በላይ ዲግሪ እንዲኖራቸው አድርገው አስተምረው ለቁምነገር አብቅተዋል።በዲቪ አንዷ ልጃቸው ውጪ የሄደች ሲሆን፤ አንዱ ደግሞ የጥርስ ሀኪም ሆኖ ከስራቸው ሳይለይ ይሰራል።ሁለቱ ሴት ልጆቻቸውም ቢሆኑ በሀዋሳ ከተማ ስለሚኖሩ እርሳቸውን ከመንከባከብ አልራቁም።አሁን የአስር ልጆች አያትም ሆነዋል።ለእርሳቸው የትምህርት ጉዞ ብዙ የለፋችው ባለቤታቸውም ይህንን በማየቷ ደስተኛ ሆና ከቤተሰቡ ጋር በቅርበት እየተገናኙ በፍቅር ይኖራሉ።
መልዕክት
አይነስውር ሆኖ ትምህርት መማር፣ መሥራትና ለስኬት መብቃት እጅግ ፈታኝ ነው።ነገር ግን ይህንን ፈተና በድል ከተወጡ በኋላ ያለን ወርቅ ማንም ዝቆ አይጨርሰውም።ስለዚህም ብዙ የተሻሉ ነገሮችን ለማግኘት ብዙ ችግሮችን ማለፍ ግድ ነው።ይሁንና አንዳንድ አይነስውራን የአካል ጉዳታቸውን ተንተርሰው ከመስራትና ስኬታማ ከመሆን ራሳቸውንም ያገላሉ።ልመናና መሰል ተግባራትንም መፈጸም ይፈልጋሉ።ይህ ነገር በፍላጎትና በተስፋ መጠን ይመዘናልና እነዚህ አካላት በዚህ የተገቱም ይመስለኛል።እናም ጊዜ ቆሞ አይጠብቅምና በጊዜው በፍላጎትና በተስፋ ችግራቸውን ያሸንፉ ማለት እፈልጋለሁ ይላሉ።
አካል ጉዳተኝነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ጥቃት ወይም ስጦታ አይደለም።በጊዜ ሂደት ጭምር ሊፈጠር የሚችል ቅጽበታዊ ነገር ነው።ስለዚህም አካል ጉዳተኝነቱን አምኖ በመቀበል ያንን የሚያሸንፍበትን መንገድ መቀየስ ነው ያለበት።አልችልም በማለትም ነገውን ማጨለም አይገባም።ምክንያቱም ነገን ማየት የሚችሉት በመቻል ካልሆነ በምንም አይደለም።ተስፋን ማንገብ፣ የቀረውን ማሰብ፣ የተሻለውን ማለም ያስፈልጋል።አካል ጉዳተኝነትን እያሳበቡ ለመኖር አለመፈለግና በሰዎች ጫንቃ ላይ መቆም ከመውደቅ አይተናነስም።እናም አልችልም ባዮች አካል ጉዳተኞች ከዚህ ስህተታቸው በእውቀትና በተስፋ መሻገር አለባቸው።
አይችልም ባዮች ደግሞ ሁኔታው ቅጽበታዊ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ በመኖሩ ያንን እያሰቡ መኖር አለባቸው።ምክንያቱም የነገ እነርሱነታቸውን ከአምላክ በቀር የሚያውቀው የለም።ስለሆነም ‹‹አይችሉም›› ሲሉ ይህንን እያሰቡና ስለሰው ምንነትና ማንነት ተረድተው መሆን ይገባዋል።
ሰውን በሰውነቱ እንጂ በአካል ጉዳቱ መመዘን የለባቸውምም።በእርግጥ ካለማወቅና ከተለመደው ባህል አንጻር ይህ ሊከሰት ይችላል።ነገር ግን ለእነርሱ ነገ አካል ጉዳተኛውን በማገዝ መስራት ይኖርባቸዋል።ማንም ሙሉ ተደርጎ አልተፈጠረም።ጎዶሎውን ሊሞላለት ሰው ያስፈልገዋል።እናም አይነስውራንም ጊዜ፤ ምቹ ሁኔታን እንዲያገኙ ማገዝ አለባቸው እንጂ አይችሉም ሊሏቸው አይገባም፤ ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013