አብርሃም ተወልደ
ሴኔጋል ከምዕራብ አፍሪካ አገራት አንጻራዊ የቆዳ ስፋት ያላት ሀገር ናት። በውበቷ ግን የሚስተካከላት እንደሌለ ይነገራል። በፈረንሳይ ቀኝ ግዛት ውስጥ ስለነበረች የአውሮፓውያን ተጽዕኖ ያለባት አገር ናት። በአገሪቱ የሚመረቱ የትኛቹም ምርቶች ማዕከል የሚያደርጉት እነኚህኑ አውሮውያኑን ነው።
ሴኔጋል ከቀኝ ግዛቱ በ1960 ነጻ ከወጣች በኋላም ከአውሮፓውያን ተጽዕኖ አልተላቀቀችም። አፍሪካዊ በሆኑት ባህላዊ አልባሶቻቸው ላይ የአውሮፓውያን ጥበብ ተቀይጦ ይቀርብ ነበር። አንድ አባባል አለ፤ በአፍሪካ አንድ ዲዛይነር አዲስ ነገር መሞከር ከፈለገ ሴነጋል የሚሰሩ ዲዛይን የተደረጉ አልባሳትን ማየት እነሱንም መሞከር አለበት ይባላል።
በሴነጋል የሚሰሩ ዲዛይኖች በአለም ላይ ያለውን ማህበረሰብ የዲዛይን አምሮት እና ፍላጎት ለማርካት የሚዘጋጁ ናቸው። በተለይ በታዋቂ የአገሪቱ የልብስ ዲዛይኖች ላይ እነዚህ ጥበቦች ጎልተው ይታያሉ።
ታዲያ እንዲህ ከደረጁ እና አፍሪካዊ ጣዕምንና ባህልን ሳይለቁ ባህላዊ አልባሶቿን ከአውሮፓውያን አልባሳት ጋር በማዋሃድ የፋሽኑን ኢንዱስትሪ ከተቆጣጠረችው ሴነጋል አያሌ እና ቱባ ባህል ያላት ኢትዮጵያ ትምህርት መቅሰም ይኖርባታል። ኢትዮጵያ ሰሞኑን በአልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ገበያ ሰብሮ ለመግባት የሚረዳትን እውቅ ባለሙያ ከሴኔጋል በማምጣት ለፋሽን ባለሙያዎችና ዲዛይነሮች ስልጠና ሰጥታለች። ተጋባዡ ሴኔጋላዊው ዓለም አቀፍ አርቲስት.፣ የፋሽን ዲዛይንና ግራፊክስ አርት ጥበብ ባለሙያ ነው።
የኢፊዲሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት እና ዘርፉን ለማሳደግ ካለው ራዕይ በመነሳት ስልጠናው የተዘጋጀው። ስልጠናው የተዘጋጀው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማህበር ጋር ሆነው ነው።
ይህ እውቅ ባለሙያ የፋሽንና ግራፊክስ ዲዛይነር እንዲሁም ዓለም አቀፍ አርቲስት ሲሆን ስሙም ሚስተር አል ሓጂ ባባካር ሲላ ይባላል። በኢትዮጵያ የባህል ኢንዱስትሪ እና በቀጣይ አብሮ መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለምክክር በሚልም ጭምር ነው ስልጠናው የተዘጋጀው ።
በዚህ ምክክር የኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማህበር አመራሮች እና አባላት እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት ተሳትፈዋል። ከተለያዩ ቦታዎች የተወጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።
ሓጂ ባባካር ሲላ በሴኔጋል አገር አቀፍ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከል የዲዛይን እና ግራፊክስ ስነ ጥበብ አሰልጣኝ እና ዋና የህዝብ ግንኙነት በመሆን ይሰራል። ዲዮግ አፕ የተባለ ፕሮጀክት ቀርጾ ከሴኔጋል ባህልና ኮሚኔኬሽን ሚኒስቴር እና ንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር እየሠራ ይገኛል። ይህንኑ ፕሮጀክት ለማስተዋወቅና በኢትዮጵያ ከሚገኙ የዘርፉ ሙያተኞች ጋር በጋራ ለመሥራት እንዲቻል ከዘርፉ ማህበራት ጋር በመወያየትና የመስክ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል።
አርቲስቱ የቆዳ አልባሳት፣ ጫማ ዲዛይንና ፋሽን ድርጅት ባለቤት ሲሆን፣ ቀደም ብሎም በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ሙያውን በማስተዋወቅ ቆይቷል። ይህንኑ የስራ ፈጣሪነት (ኢንተርፕረነር) ፣ፋሽንና ግራፊክሰ አርት ከኢትዮጵያ ሙያተኞች ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል። ሴኔጋላዊው በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክብር አምባሳደር ሆኖ አየር መንገዱን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ እስከአሁን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች። አሁን ግን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በሰጠው ትኩረት በዘርፉ ላይ መነቃቃት እየታየ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ምርት ፤ለምርቶቹም የሚያገለግል ተዝቆ የማያልቅ ጥሬ አለ፤ እነዚህም በማዋሃድ እንደ ሴኔጋል ያሉ አገራትን ልምድ በመቅሰም ለአውሮፓ ገበያ የሚመጥኑ ምርቶችን በማምረት አገርን በማስተዋወቅ ገቢ ማግኘት ይቻላል።
ከዚህ ቀደም ለየትኛውም የአገር ውስጥ ምርት ትኩረት አይሰጥም ነበር። አሁን ማህበረሰቡ ወደ ራሱ ወደ ልቡ እና ማንነቱ የተመለሰ ይመስላል፤ በእለት ተዕለት እንቅስቃሴው የአገሪቱን ምርት እየተጠቀመ ባይሆንም ከቀድሞ ይሻላል። እንደሚታወቀው የሀብት እና የዘመናዊነት መለኪያ የተለያዩ የአውሮፓ እና የኢሲያ ምርቶችን መጠቀም ሆኗል። ስልጣኔ የራስ የሆነን ነገር መውደድ መቀበል ነው።
ስልጣኔ ራስን መቀበል የራስን መውደድ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ማሳየት ነው። ብዙዎቻችን የሀገር ውስጥ ምርትን እንደ ተራ ነገር በማየት ለውጪ ምርት ትኩረት በመስጠት በሞኝነት ኖረናል። እኛ ለራሳችን ምርት ክብርና ፍቅር ከሌለን ማንም ከየትም መጥቶ አያከብርልንም። ሰዎች የእኛ የሆነውን ነገር እንዲወዱ በመጀመሪያ እኛ ወደን ማሳየት አለብን። ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ እንደሚባለው እኛ ያልተቀበልንውን የእኛ የሆነ ነገር ማንም አይቀበለውም።
በተለያዩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ቻይናውያንን ብንመለከት በሰው አገር ላይ ሆነው እንኳ ከራሳቸው ምርት ሌላ የሌላ አገር ምርት አይጠቀሙም። ይህ አንዱ ምክንያት ይመስለኛል አገሪቱ በስልጣኔም በኢኮኖሚም ከፊት የተሰለፈችው።
ሀገራቸውን የሚወዱ ዜጎች የሀገራቸውን ምርት በመጠቀም ፍቅራቸውን የሚገልጹ ናቸው። የራስን ምርት መጠቀም በተዘዋዋሪ መንገድ ራስን መጥቀም ነው። ለሀገር ብልጽግና አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። የሀገር ፍቅር ከሚገለጽባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ የራስን ምርት መጠቀም ነው።
ታዲያ የራሳችንን ምርት እንውደድ ስንል ደግሞ ልብሱ በተሻለ ውብ በሆነ ዲዛይን መሰረት ይኖርበታል። ልክ እንደ ሴነጋል ያሉ በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላቸውን አገራት በመጋበዝ እና ልምዳቸውን በመቅሰም ምቹ እና ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች ሊመረቱ ይገባል።አሁን በአገር ደረጃ የተጀመረው ስራ እና ዘርፉን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013