አስናቀ ፀጋዬ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለው ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ142 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። በዚሁ ወረርሽኝ ጦስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥርም ከሶስት ሚሊዮን ተሻግሯል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዜጎች በኩል ከፍተኛ መዘናጋት መታየቱን ተከትሎ የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በየቀኑ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በአስደንጋጭ ሁኔታ አሻቅቧል።
የኮሮና ወረርሽኝ ሊያሳድር የሚችለውን ሁለንተናዊ ተፅእኖ በመቋቋም ምጣኔ ሃብታዊ እድገታቸውን ባሰቡት ልክ ማሳደግ ባይችሉም ባለበት እንዲቀጥል ካደረጉ ጥቂት ሀራት መካከል ቻይና አንዷ ናት። ቻይና ቫይረሱ እንደገባ ለሁለት ወር የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ በማበጀቷና ዜጎቿም ይህንኑ አውቀው ለገደቡ ተገዢ በመሆናቸው በሽታው ሊያደርስ የሚችለውን ሰብአዊ ቀውስ መቀነስ ችላለች።
ከክልከላ ገደቡ በኋላም ዜጎቿ የኮሮና መከላከያ መንገዶችን ሳይሰለቹ በአግባቡ በመፈፀማቸውና ከጥንቃቄ ጋር ስራዎችን በመስራታቸው የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዳይዋዥቅ የድርሻቸውን ተወጥተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሀገሪቱ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ የኮሮና ክትባት እንዲከተቡ በማድረግ የወረርሽኙን ተፅእኖ ለመቀነስ ጥረት እያደረገች ነው ።
,ይህ ሁሉ ጥረት ታዲያ ፍሬ አፍርቶ የቻይና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ከባለፈው የመጀመሪያ ሩብ አመት ጋር ሲወዳደር የ 18 ነጥብ 3 ከመቶ እድገት ማስመዝገቡንና ይህም ኮቪድ ከገባ በኋላ ከፍተኛ መሆኑን ቢ ቢ ሲ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።
አሃዙ ቻይና ከ1992 ጀምሮ የሩብ አመት ምጣኔ ሃብታዊ እድገቷን ማስመዘገብ ከቀጠለችበት ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ላይ ትልቅ እምርታ ያመጣ መሆኑ ተነግሮለታል።
እንደዚም ሆኖ ግን አሃዙ ከተጠበቀው በታች እንደሆነና የኢኮኖሚ ተንታኞች ከተነበዩት የ19 ከመቶ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ያነሰ መሆኑ በዘገባው ተገልጿል። ካለፈው አመት የምጣኔ ሃብት መኮማተር ጋር ሲወዳደር የአሁኑ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የተዛባና ጠንካራ እድገትን በደምብ ያመላከተ እንዳልሆነም ተጠቁሟል።
በመላው ሀገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት በ2020 የመጀመሪያ ሩብ አመት የቻይና ምጣኔ ሀብት በ6 ነጥብ 8 በመቶ መኮማተሩ በዘገባው ለትውስታ የተቀመጠ ሲሆን የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት መረጃ ይፋ ያደረገው የቻይና ብሔራዊ ስታተስቲክስ መስሪያ ቤት ‹‹ብሔራዊ ኢኮኖሚው ጥሩ ጅምር አደረገ›› ሲል ገልጿል።
መስሪያ ቤቱ አክሎም ‹‹የኮሮና ወረርሽኝ አሁንም ዓለም አቀፍ ስርጭቱ እየጨመረ መሆኑና ዓለም አቀፍ ምህዳሩም የተመሰቃቀለና በከፍተኛ ጥርጣሬና አለመረጋጋት የተሞላ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል›› ብሏል።
በቻይና የስታተስቲክስ መስሪያ ቤት የተለቀቁ ሌሎች ቁልፍ አሃዞች ቀጣይ የኢኮኖሚ ሽግግርን እንደሚያመለክቱ፤ ይሁንና አሃዞቹ ካለፈው ዓመት ጋር ከነበሩ እጅግ ደካማ ቁጥሮች ጋር በመወዳደራቸው ባልተለመደ ሁኔታ ጠንካራ መሆናቸው በዘገባው ተገልጿል። ከአመት በፊት የቻይና የመጋቢት ወር የኢንዱስትሪ ግብአት 14 ነጥብ 1 ከመቶ ከፍ ያለ መሆኑና የችርቻሮ ሽያጭ ደግሞ 34 ነጥብ 2 ከመቶ ማደጉ ለምጣኔ ሃብቱ እድገት ማሳያ መሆኑም ተጠቁሟል።
የቻይና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ከአየር ንብረት ለውጥ ችግር ጋር ተዳምሮ ከዓለም ቀዳሚ መሆኑ ትንሽ ግራ አጋቢ እንደሆነም በዘገባው የተመላከተ ሲሆን፤ ከታሪክ አንፃር የኢኮኖሚ እድገቱ ሙሉ በሙሉ የድንጋይ ከሰል፣ጋዝና ነዳጅ በማቃጠል በበካይ ጋዝ ልቀት የተሞላ መሆኑም ተነግሯል። ቻይና እአአ በ2030 የበካይ ጋዝ ልቀቷን በ 2030 ለመቀነስ እንዲሁም በ 2060 ሙሉ በሙሉ ልቀቱን በማቆም ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ለማስቀጠል ቃል መግባቷንም ዘገባው አስታውሷል።
ይሁንና የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ቺም ፒንግ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤር ማክሮንና ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጄላ መርኬል ጋር ተገናኝተው ባወሩበት ወቅት ቻይና የካርበን ልቀቷን ምንአልባት በ2025 ሙሉ በሙሉ እንደምታቆም መናገራቸውም በዘገባው ለትውስታ ቀርቧል።
የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ መሪዎችም ቻይና ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› በተባለው ኢኒሺዬቲቭ በተለይ ለታዳጊ ሀገራት አዳዲስ የድንጋይ ከሰል እሳት ሃይል ፋብሪካዎች የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ግፊት ማድረጋቸውም በዘገባው ተነግሯል። የአፍሪካ ሀገሮች በድንጋይ ከሰል የበለፀጉ ሀገሮች ያስቀመጡትን የብክለት መንገድ ተከትለው ቢሄዱ ዓለም ከባድ መከራ ውስጥ ልትዘፈቅ እንደምትችል ማሳሰባቸው ተጠቅሷል።
የቻይና ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዩ ሱ ፤ የቅርብ ጊዜዎቹ መረጃዎች የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ማገገም ሰፊ መሠረት ያለው መሆኑን ያሳያሉ ብለዋል። አንዳንድ የምርት እና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴዎች ከመጀመሪያው ሩብ ዓመት በፊት ጫና እንደነበረባቸውና ይህም የወደፊቱ እድገት ቀርፋፋ ስለመሆኑ ጠቋሚ መሆኑን አስቀምጠዋል።
‹‹የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት የሚያስችሉ እርምጃዎች ባለመኖራቸው የንግድ ስራ አፈፃፀምና የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች ለቀጣዮቹ ዓመታት እንዲህ ዓይነቱን ጠንካራ የእድገት ፍጥነት ሊጠብቁ አይችሉም›› ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዋ ገልፀዋል።
ቻይና አሁንም ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቷን እንደቀጠለች አኃዛዊ መረጃዎች እያሳዩ እንደሚገኙ በዘገባው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከባለፈው 2020 የመጀመሪያ ሩብ አመት ጋር ሲወዳደር የቻይና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ዜሮ ነጥብ ስድስት ከመቶ ብቻ ስለመሆኑም ተነግሮለታል። ጥብቅ የቫይረስ መከላከያ እርምጃዎች መኖራቸውና ለንግድ ድርጅቶችም የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መደረጉ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ኢኮኖሚው ያለማቋረጥ እንዲያገግም ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉም ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013