ዳንኤል ዘነበ
በአዳጊ አገራት ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 15 ባሉ ልጆች ላይ የሚከሰተው የልብ በሽታ (ሪውማቲክ ዲዚዝ) በአግባቡ ካልታከመ የቶንሲል ኢንፌክሽን እንደሚከሰት በቅጡ ያውቃሉን? የቀዘቀዘ ምግብን ወይም መጠጥን አብዝቶ መጠቀም አሊያም በኃይለኛ የፀሐይ ሙቀት በመመታት የቶንሲል ኢንፌክሽን ተብሎ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ የሚታሰበው የቶንሲል ህመም መነሻ ምክንያቱ ከእዚህ በእጅጉ የተለየና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ካላገኘም እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ የጤና ችግር መሆኑን ብዙዎች አይገነዘቡም።
የቶንሲል ህመም መንስኤና የሚያጋልጡ ነገሮች
ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች በፀሐይ ላይ መመገብ፣ እንደ አይስክሬም ያሉ የቀዘቀዙ ምግቦችን በተለይ ለሕፃናት መስጠትና በከባድ ፀሐይ መመታት፤ ከቶንሲል ህመም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው ሲሆን፣ በሽታው በባክቴሪያና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። በጉሮሮአችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል ዕጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡና ሲያብጡ የሚከሰተው ህመም ቶልሲላይተስ ተብሎ ይጠራል፡፡ እነዚህ ቶንሲሎቻችን እንዲቆጡና እንዲያብጡ በማድረግ ህመም እንዲሰማን የሚያደርጉት ባክቴሪያና ቫይረሶች ናቸው፡፡
የቶንሲል ህመም (ቶንሲላይተስ) በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እጅግ የተለመደና በየጊዜው የሚያጋጥም የህመም ዓይነት ነው፡፡ አንድ ልጅ በየዓመቱ በአማካይ እስከ ስምንት ጊዜ ያህል በቶንሲል ህመም ሊጠቃ ወይንም ቶንሲላይትስ ሊይዘው ይችላል፡፡ የቶንሲል ህመም መንስኤ የሆነው ቫይረስ ወይንም በባክቴሪያ በተለያየ መንገድ በዋነኛነት በትንፋሽ ወደ ሰውነታችን ገብቶ ቶንሲሎቻችንን ከበከለ በኋላ ባሉት ሁለትና ሦስት ቀናት በህመምተኛው ላይ የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡ የቶንሲል ህመም ትናንሽ ሕፃናትንና ለጋ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን በብዛት ያጠቃል፡፡ ለዚህ የሚያጋልጡ ነገሮች ደግሞ በተደጋጋሚ ኢንፌክሽኑን ለሚያመጡ ጀርሞች መጋለጥ ሲሆን በትምህርት ቤት የሚውሉ ሕፃናት ከአቻዎቻቸው ጋር ያላቸው የቀረበ ግንኙነት/ንክኪ ለቫይረሶችና ባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡
የቶንሲል ህመም ምልክቶች
• የቶንሲል መቅላትና እብጠት
• የቶንሲል መከርከር
• ምግብ በሚውጡበት ወቅት ህመም መኖር/ መዋጥ መቸገር
• ትኩሳት
• በአንገት ላይ ያበጡና ህመም ያላቸው ዕጢዎች መከሰት
• የድምፅ መቀየር
• መጥፎ የአፍ ሽታ
• የሆድ ህመም (በተለይ በዕድሜያቸው ትናንሽ ሕፃናት ላይ)
• የአንገት ህመም/መጠንከር
• የራስ ምታት ናቸው፡፡
በጣም ጨቅላ በሆኑ ሕፃናትና የህመማቸውን ሁኔታ መግለፅ በማይችሉ ሕፃናት ላይ የሚታየው ምልክት ደግሞ፡-
• ሲውጡ ህመም ስላላቸው የምራቅ/ለሃጭ መዝረክረክ
• ምግብ ለመመገብ እምቢ ማለትና
• ያልተለመደ ድካም የህመሙ ምልክቶች ናቸው፡፡
ልጆች የቶንሲል ኢንፌክሽን እንደያዛቸው ማወቅ የሚቻልበት ዘዴ
ህመምተኛው አፉን እንዲከፍት በማድረግ ጉሮሮው በሚታይበት ጊዜ ከምላሱ ኋላ በግራና ቀኝ የጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ እብጠትና ቅላት ይታያል፡፡ እነዚህ የጉሮሮ ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ የሚገኙ የቶንሲል ዕጢዎች እብጠታቸው አንዳንዴ ከፍተኛ ይሆንና ጉሮሮን ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ ይችላሉ፡፡
ባክቴሪያ ወለዱ ቶንሲላይት ከመደበኛው የቶንሲል ህመሞች ምልክቶች በተጨማሪ ከሚኖረው የበሽታው ምልክት መካከል በጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ በሚኖረው እብጠት ላይ ነጫጭ አይብ መሰል ነጠብጣቦች /ችፍታዎች/ ሊታዩበት ይችላሉ፡፡ የቶንሲል ህመም በትንፋሽ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና ሕፃናትን በይበልጥ የሚያጠቃ የበሽታ ዓይነት ነው፡
የቶንሲል አደገኛው ደረጃና ጉዳቱ
የቶንሲል ህመም (ቶንሲላይትስ) በሽታውን በወቅቱ ወይም በዘጠኝ ቀናት ውስጥ አለመታከም አደጋው ስትሬፕቶኮከስ ፓዪጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ በሚመጣው የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው በአግባቡና በወቅቱ ህክምናውን ካላገኘ ከኩላሊት መድከም (ኩላሊት ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆም) እስከ ልብ ህመም ብሎም እስከሞት ሊያደርሱ የሚችሉ መዘዞችን ያስከትላል፡፡ በባክቴሪያ ወለዱ የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው ተገቢውን ህክምና ካላገኘ ቶንሲሎቹ ዙሪያቸውን ያብጡና መግል ይቋጥራሉ፡፡ የህመምተኛው አንገትም ይበልጥ መግል ወደተቋጠረበት አቅጣጫ ያዘማል፡፡ ይህም የማጅራት አለመታዘዝንና መንጋጋን እንደልብ መክፈት አለመቻልን ከማስከተሉም በላይ ታማሚው ህክምና ካላገኘ ባክቴሪያው በደም ውስጥ በመሰራጨት የኩላሊትና የልብን መደበኛ ሥራ በማስተጓጎል ታማሚውን ለሞት ሊዳርገው ይችላል።
ባክቴሪያ አመጣሹ ቶንሲላይተስ ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል አጣዳፊ የኩላሊት መድከም፣ የልብ ህመም፣ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) የቆዳና የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች፣ ጥቂቶቹ ናቸው። ስትሬፕቶከክስ ፓዮዲኒስ በተባለው የባክቴሪያ ዓይነት ሳቢያ የሚከሰተውን እና እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን የሚያስከትለውን የቶንሲል ዓይነት ቫይረስ አመጣሽ ከሆነውና በቀላሉ ከሚድነው የቶንሲል ዓይነት መለየቱ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ሁሉም ዓይነት የቶንሲል ህመሞች በአግባቡና በወቅቱ ህክምና ማግኘት አለባቸው፤ የሚባለውም ለዚሁ ነው።
የህክምና ባለሙያ ማማከር የሚገባን ወቅት
• በ24 ሰዓታት ውስጥ ለውጥ የሌለው የቶንሲል ህመም ካጋጠመዎ
• ምግብ ሲውጡ ህመም ካለዎና
• የድካም/የመዝለፍልፍ ስሜቶች ከፍ ያለ ከሆኑ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
የቶንሲል ህክምናዎች
1. የቤት ውስጥ ህክምና፦ የቶንሲል ህመሙ በቫይረስም ይሁን በባክቴሪያ ምክንያት ቢከሰትም የቤት ውስጥ ህክምናዎችን መከወን ምቾት እንዲሰማዎና ቶንሲሉ ቶሎ እንዲድን ያደርገዋል፡፡ የቶንሲል ህመሙ የተከሰተው በቫይረስ መሆኑ ከተረጋገጠ የህክምና ባለሙያዎ ምንም ፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒት ስለማያዝልዎ ህመሙ እንዲድን የቤት ውስጥ ህክምና ማከናወን የህክምናው ዋናው አካል ነው፡፡ የቶንሲል ህመም በ10 ቀናት ውስጥ ሊሻሻል ይችላል፡፡ በመሆኑም በቤት ውስጥ ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች የሚባሉት፡-
• በቂ እረፍት ማግኘት፡- ብዙ ያለማውራትና በቂ እንቅልፍ ማግኘት
• ፈሳሽ በበቂ መጠን መውሰድ
• ምቾትን ሊሰጡ የሚችሉ ምግቦችን መመገብ፡- ትኩስ ፈሳሾች እንደ ሾርባ፣ ካፊን የሌለው ሻይ፣ የሞቀ ውሃ በማር እንዲሁም ቀዝቃዛ የሆኑ እንደ በረዶ ያሉ ነገሮች የጉሮሮ መከርከርን ሊያክሙ ይችላሉ፡፡
• ጨው ባለው ውሃ አፍን መጉመጥመጥ
• ወደ ውስጥ የሚገባውን አየር እርጥበታማ/ሂሙድፋይ እንዲሆን ማድረግ፡- ወይ የቀዝቃዛ አየር ሂሙድፋየር መጠቀም አለዚያ ደግሞ እንፋሎት መታጠን ደረቅ አየር ጉሮሮ ላይ የሚያመጣውን መከንከን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡
• ሊቆጠቁጡ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ፡- ጉሮሮን ሊከረክሩ ከሚችሉ እንደ የሲጋራ ጭስና የቤት ማጽጃ ኬሚካሎች እራስን መጠበቅ
• ህመምና ትኩሳት ካለ ማስታገሻ መውሰድ፡- እንደ ፓራሲታሞላና አይቡ ፕሮፌን ያሉ መድኃኒቶችን መጠቀም፡፡
2. መድኃኒቶች፦ የቶንሲል ህመም የተከሰተው በባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከሆነ የግድ ፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶችን (አንቲባዮቲክሶችን) መውሰድ ያስፈልጋል። ከአስር ቀናት ሹሮፕ አለርጅ ለሌላቸው አንድ ጊዜ የሚሰጠው መርፌ ይመከራል። በህክምና ባለሙያዎ የታዘዘልዎትን መድኃኒት በአግባቡ ወስዶ መጨረስ የሚያስፈልግ ሲሆን በአግባቡ ካልተወሰደ ግን ባክቴሪያው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰራጭ፤ ሕፃናት ላይ ደግሞ የልብ ህመም እንዲከሰት መንስኤ መሆንና ቀጣይነት ያለው የቶንሲል ህመም (ክሮኒክቶንሲላይትስ) እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
ምንጭ፦ ከጤናችን ማህበራዊ ገጽ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013