ዳነኤል ዘነበ
በየዓመቱ መጋቢት 15 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው “የአለም ቲቢ ቀን” የሚያስታውሰን የበሽታውን አደገኛነት ሲሆን፤ ቲቢ በባህሪው ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ድንገተኛና አጣዳፊ ከሚባሉት የበሽታ ዓይነቶች ክፍል የሚመደብ አለመሆኑን ነው። የቲቢ በሽታ መንስኤም በዓይን የማይታይ ረቂቅ ተህዋስ ወይም ጀርም ነው። የቲቢ በሽታ ዛሬም የዓለም ሕዝቦች የጤና ችግር ሲሆን ኢትዮጵያም ቲቢ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሁም መድኃኒቶችን የተላመደ ቲቢ በከፍተኛ ሁኔታ ተሠራጭቶ ከሚገኝባቸው የዓለም አገሮች ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች።
የቲቢ በሽታ ሁሉንም ቢያጠቃም የበለጠ የሚያጠቃው ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 50 ዓመት ያሉትንና አምራችና የቤተሰብ ኃላፊነት ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው። ከዚህም የተነሳ በሽታው የሚያስከትለው ሕመም፣ ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።
ለቲቢ ተጋላጭ የሆኑ ክፍሎች
ቲቢ ዕድሜን፣ ፆታን፣ ዘርንና ቀለምን ሳይለይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ነው። ይሁንና ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሚሆኑት፡
- ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት፣
- አረጋውያን፣
- በኤች. አይ. ቪ. የተያዙ ሰዎች እንዲሁም
- በአክታ ምርመራ የቲቢ በሽታ አምጪ ተሕዋስ ከተገኘባቸው ሕሙማን ጋር አብረው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።
ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መንገዶች
- በቂና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት፣
- በቂ የአየር ዝውውር በሌላቸው ክፍሎች ውስጥ ተፋፍጎ መኖር፣
- ሰውነት በተፈጥሮ ያለውን በሽታን የመከላከል አቅም በማዳከም ለሌላ ተደራቢ በሽታ የሚዳርጉ እንደ ኤች. አይ. ቪ./ኤድስ፣ ስኳርና ካንሰር የመሳሰሉት በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- አንድ ሰው ቀድሞ በኤች. አይ. ቪ. ከተጠቃ ቫይረሱ የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅምን ስለሚያዳክም በቀላሉ በቲቢ ሊያዝ ይችላል። እንዲሁም ቲቢ ያለበት ሰው በኤች. አይ. ቪ. ከተያዘ ወይም ከቫይረሱ ጋር የሚኖር ሰው በቲቢ ከተያዘ የበሽታውን ደረጃ በፍጥነት ያባብሳል። ለዚህም ነው የቲቢ ሕሙማን ሁሉ ለኤች. አይ. ቪ. እንዲሁም ኤች. አይ. ቪ. ያለባቸው ሁሉ ለቲቢ እንዲመረመሩ የሚደረገው።
የቲቢ በሽታ መተላለፊያ መንገዶች
• የቲቢ በሽታ በዋናነት የሚተላለፈው በሳንባ ቲቢ የተጠቃና ሕክምና ያልወሰደ በተለይም በአክታ ምርመራ የቲቢ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ የተገኘበት ሕመምተኛ ሲስል፣ ሲያነጥስ፣ ሲነጋገር ወዘተ… የበሽታው አምጪ የሆነው ጀርም ከታማሚው ሳንባ ውስጥ በመውጣት በቀጥታ በትንፋሽ ወይም በአየር አማካይነት ወደ ሌላ ሰው የመተንፈሻ አካል ሲገባ ነው።
• በሽታው አልፎ አልፎ ማይኮባክቴሪየም ቦቪስ ተብሎ በሚጠራ ጀርም አማካኝነት በበሽታው ከተያዙ የቤት እንስሳት የሚገኝ ወተት ሳይፈላ ከተጠጣ ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል።
በሽታው የማይተላለፍቸው መንገዶች
- በመጨባበጥ፣
- አልባሳትን በጋራ በመጠቀም፣
- መመገቢያና ማብሰያ የቤት ዕቃዎችን በጋራ በመጠቀም አይተላለፍም፤
የቲቢ በሽታ ዓይነቶች
ቲቢ ሰማኒያ ከመቶ የሚሆነው የሚያጠቃው ሳንባን ቢሆንም ሌሎችንም የሰውነት ክፍሎችን ሊያጠቃ ይችላል። ስለሆነም በሽታው የሚጠቃውን አካል መነሻ በማድረግ የሳንባ ቲቢ እና ከሳንባ ውጭ የሆነ የቲቢ በሽታ በመባል ለሁለት ይከፈላል።
የቲቢ በሽታ ምልክቶች
- የቲቢ በሽታ ምልክቶች እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል ይለያያል። በሽታው በአብዛኛው የሚያጠቃው ሳንባን ስለሆነ የበሽታው ዋና ምልክት ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የዘለቀ ሳል ነው። ሳሉ አክታ ያለውና ደም የቀላቀለ ወይም ያልቀላቀለ ወይም ደረቅ ሊሆን ይችላል።
- ታማሚው ከሳሉ ሌላ በደረቱ አካባቢ የውጋት ስሜት፣ መጠነኛ የሆነ ትኩሳት፣ ሌሊት በመኝታ ጊዜ ማላብ፣ የክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና የሰውነት መድከም የመሳሰሉ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ከሳንባ ውጪ ያለ የቲቢ በሽታ ምልክቶች እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል ዓይነት ይለያያሉ።
የቲቢ በሽታ ምርመራ ሕክምና
የቲቢ በሽታን መለየት የሚቻለው፣ በታማሚው ላይ በሚታዩ የሕመም ምልክቶች፣ የበሽታው አምጪ የሆነውን ተሕዋስ ከሕመምተኛው አክታ ወይም ከተጠቃው ከሳንባ ውጪ ከሆነው አካል ከሚወሰድ ፈሳሽ በላቦራቶሪ በሚደረግ ምርመራ ነው። በሽታው ዘመናዊና ፈዋሽ የሆኑ መድኃኒቶች አሉት።
ይሁንና የቲቢ መድኃኒቶች በዋጋ ደረጃ ውድ በመሆናቸውና አብዛኛዎቹም ታማሚዎች ከፍለው ለመታከም ስለሚቸገሩ መንግሥት ለሁሉም የቲቢ ሕሙማን ከፍተኛ የመፈወስ አቅም ያላቸውን መድኃኒቶች በነፃ እንዲያገኙ አድርጓል።
ስለዚህ የቲቢ በሽታ ምርመራም ሆነ ሕክምና በመንግሥታዊና ሕክምናውን እንዲሰጡ በተፈቀደላቸው የግል ጤና ተቋማት በነፃ ማግኘት ስለሚቻል ሰዎች የበሽታው ምልክት ሲታይባቸው ወደ ጤና ተቀቋማቱ መሄድ ይኖርባቸዋል።
የቲቢ ሕመምተኛ የታዘዘለትን መድኃኒት ሳያቋርጥ ሙሉ በሙሉ መውሰድ ይጠበቅበታል። ለዚህም ሲባል መድኃኒት በአግባቡ ተወስዶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ታካሚዎች በሚመርጧቸው የቲቢ ሕሙማን ደጋፊዎች የቅርብ ክትትል እንዲወስዱ ይደረጋል።
ሕክምናው ከተቋረጠ ግን በሽታው በፊት ከነበረው ሁኔታ ከመባባሱም በላይ የበሽታ መንስኤ የፀረ-ቲቢን መድኃኒቶችን በመላመድ በመደበኛው የቲቢ ሕክምና ዘዴ መፈወስ የማይችል የቲቢ ዓይነት ይፈጠራል።
የፀረ-ቲ መድኃኒቶችን የተላመደ ቲቢ በሽታ መንስኤዎቹ የአጠቃቀምና የክትትል ጉድልቶች ቢሆኑም በሽታው አንድ ሕክምና ያልወሰደ በተለይም በአክታ ምርመራ የቲቢ ተሕዋስ የተገኘበት ታማሚ ሲስል፣ ሲያስነጥስ፣ ሲነጋገር ወዘተ ከሳንባው በመውጣት በአየር አማካይነት ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋል። ይህም በሽታ እንደ መጀመሪያው ደረጃ ቲቢ የሚፈወስ ነው። ነገር ግን የመድኃኒቶቹ ዓይነትና ብዛት ከመደበኛው የሕክምና የተለየ ሲሆን የሕክምናውም ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት ይደርሳል።
የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከቲቢ ሕሙማን ምን ይጠበቃል?
- የታዘዙ መድኃኒቶችን ባለማቋረጥ ወስዶ መጨረስና በሕክምናው መጨረሻ ላይ መፈወሱን ማረጋገጥ፣
- ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሲስሉም ሆነ ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫዋን በጨርቅ ወይም በመሃረብ በመሸፈን የበሽታው አምጪ ተህዋስያን እንዳይሠራጩ ማድረግ፣
- አክታን በየቦታው ከመትፋት ይልቅ ክዳን ባለው ዕቃ ውስጥ ተፍቶ በመቅበር ወይም በማቃጠል የቲቢ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዳይሰራጩ ማድረግ፣
- የቲቢ ሕመምተኛ አብረው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትን፣ ሌሎች የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ጉረቤቶችንና የሥራ ባልደረቦችን ሁሉ እንዲመረመሩ ማድረግ፣
- የመኝታ ቤት መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖርና የፀሐይ ብርሃንም እንዲገባ ማድረግ፤
- በተቻለ መጠን ገንቢና ተመጣጣኝ የሆነ ምግብ መመገብ፣
- ሲጋራ ከማጨስና ከአልኮል መጠጦች መራቅ፣
ከቲቢ ሕሙማን ቤተሰብ ምን ይጠበቃል?
- የቲቢ ታካሚ የታዘዙለትን መድኃኒቶች ሳያቋርጥ በመውሰድ ከበሽታው እንዲፈወስ ማበረታታትና መከታተል፤
- የቲቢ ሕመምተኛ አክታውን በየቦታው እንዳይተፋ ክዳን ያለው ዕቃ በማቅረብ አጠራቅሞ በተወሰነ ቦታ ማቃጠል ወይም አርቆ ቆፍሮ መቅበር፤
- የቲቢ ሕመምተኛ በሚኖርበት ቤተሰብ በተለይም አስታማሚዎችንና ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች የሆኑትን ሕጻናት ልጆችንና አረጋውያንን ማስመርመር፣
- ለቲቢ ሕሙማን ፍቅር ማሳየትና በተቻለ መጠን ገንቢና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲመገቡ ማድረግ፤
- የመኝታ ክፍል መስኮቶችን በመክፈት በቂ አየር እንዲዘዋወርና የፀሐይ ብርሃን እንዲገባ ማድረግ።
ከሕሙማን ደጋፊዎች ምን ይጠበቃል?
- ከጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛዋ/ባለሙያዋ ትምህርትና ሙያዊ ድጋፍ ማግኘት፣
- ታካሚው የታዘዘለትን መድኃኒት በትክክል መውሰዱን በየቀኑ መከታተልና ማረጋገጥ፣
- ታካሚው የቲቢ መድኃኒት አወሳሰድ ላይ ችግር ሲያጋጥመው መፍትሔ እንዲፈለግለት ችግሩን ለጤና ባለሙያ ወይም ለጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛዋ/ባለሙያዋ ሪፖርት ማድረግ።
ከህብረተሰቡ ምን ይጠበቃል?
- ማንኛውም ሁለት ሣምንትና ከዚያ በላይ የቆየ ሳል ያለባቸውን በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም ሄደው እንዲመረመሩ ማድረግ፤
- የቲቢ በሽታ እንዳለባቸው ተረጋግጦ ሕክምና ላይ ላሉት የህብረተሰቡ አባላት መድኃኒቶቻቸውን ተከታትለው እንዲጨርሱ ድጋፍ መስጠትና ማበረታታት፣
- የመኖሪያ ቤቶች በበቂ ሁኔታ አየር እንዲዘዋወርባቸውና የፀሐይ ብርሃንም እንዲገባ መስኮቶች እንዲከፈቱ ማድረግ፣ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶችም ሲገነቡ በቂ መስኮቶች እንዲኖራቸው አድርጎ መገንባት፣
- የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር መስኮቶችን በመክፈት መተባበርና ማስተባበር፣
- የቲቢ ታማሚን ለመከታተልና ለመርዳት በፈቃደኛነት መሳተፍ፤
- ከቤት እንስሳት የሚገኝን ወተት አፍልቶ መጠጣት፤
- ጎጂ የሆኑ አባባሎችን ማስወገድና ሕሙማንን ባለማግለል ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ በቲቢ በሽታ ቁጥጥር ሥራ ላይ በፈቃደኝነት ተገቢውን የሙያ፣ የጉልበት የቁሣቁስና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ።
ምንጭ፦የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ማህበራዊ ገጽ
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013