ዳንኤል ዘነበ
የእብድ ውሻ በሽታ ራቢስ በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ አንጎልን የሚያጠቃ በሽታ ነው። የእብድ ውሻ በሽታ በሁሉም የዓለም ክፍል በእንስሳቶች ላይ የሚከሰት በሽታ ሲሆን በበሽታው በተጠቁ እንስሳዎች ምክንያት በሚከሰት ንክሻ ወይንም ምራቃቸው የቆሰለ የአካል ክፍል ከነካ በሽታው ወደ ሰዎች ይተላለፋል። በዓለም ላይ በእብድ ውሻ በሽታ በዓመት 55 ሺህ ገደማ ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ። በሽታው በተለያዩ የዱር እንስሳቶች እንደ ቀበሮ፣ ተኩላ፣ የሌሊት ወፍ፣ የተለያዩ ሥጋ ተመጋቢ እንስሳዎች በብዛት የሚስተዋል ሲሆን አልፎ አልፎ በውሾች፣ ድመቶች እንዲሁም የቀንድ ከብቶች ላይ ይስተዋላል።
የእብድ ውሻ በሽታን የሚያስከስተው ቫይረስ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ የህመም ምልክት ሳያሳይ ከሦስት ሳምንት እስከ ሦስት ወር ድረስ ሊቆይ ይችላል። አልፎ አልፎ በአጭር ቀን እንዲሁም ከዓመት በላይ ዘግይቶ የህመም ምልክት መታየት ሊጀምር ይችላል።
የራቢስ ቫይረስ በበሽታው በተጠቁ እንስሳት በሚያደርሱት የንክሻ ጉዳት ጊዜ በተነከሰው ቦታ ከምራቃቸው የሚወጣው ቫይረስ ወደ ጡንቻዎች ይገባና በዚያን አካባቢ ከሚገኙ ነርቮች ላይ ይጣበቃል። ከዚያም ቀስ በቀስ ቫይረሱ በነርቮች አማካኝነት ወደ ሰረሰርና አንጎል ይደርሳል። ከዚያም ቫይረሱ አንጎልን ማጥቃት ሲጀምር የህመም ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ። እንዲሁም ቫይረሱ ከአንጎል ወደ የምራቅ እጢዎች፣ ልብ፣ ቆዳ እንዲሁም የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይሰራጫል።
የእብድ ውሻ በሽታ የህመም ምልክቶች
የእንስሳቱ ንክሻ በተከሰተበት ቦታ የመደንዘዝ፣ የመነዝነዝና የማሳከክ ስሜት ይኖራል። ከዚያም ሙቀት መጨመር፣ የድካም ስሜት፣ እራስ ህመም፣ ማቅለሽለሽና ትውኪያ፣ የመጨናነቅ ወይንም የመንፈስ መረበሽ ይስተዋላል።
ከዚያም የእብድ ውሻ በሽታን በሁለት አይነት መልኩ ሊስተዋል ይችላል።
- ብዙውን ጊዜ (80%) በሚሆኑት ህሙማን ላይ መደናገር፣ መቃዠት፣ መነጫነጭ፣ መቅበዝበዝ፣ እንፍርፍሪት፣ የምራቅ መዝረብረብ፣ የልብ ምት መዛባት እንዲሁም ውሃና ንፋስ መፍራት ይስተዋልባቸዋል። ከዚያም አንጎልን በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቃ ሲመጣ እራስን መሳትና ሞት ይከሰታል።
- በተወሰኑት ላይ (20%) በሚሆኑት ላይ በበሽታው በተጠቃ እንስሳ ከተነከሰው የሰውነት አካባቢ የመስነፍ ወይንም የሰውነት መዛል ይከሰታል።
የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
ከዚያም ቀስ በቀስ ሙሉ እጅም እግርም ይሰንፋሉ። እንዲሁም ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር ይሳናቸዋል። በመጨረሻም ወደ ሞት ያመራሉ። የእብድ ውሻ በሽታ ተጠቂዎች የህመም ምልክት መታየት ከጀመረ በኋላ የመዳን እድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው።
ምርመራ
ቫይረሱን ከምራቅ፣ ከደም፣ ከቆዳ ላይ እንዲሁም ከአዕምሮ ላይ ናሙና በመውሰድ የቫይረሱን ዘረመል ምርመራ እና ሌሎችም ሰውነታችን ቫይረሱን ለመዋጋት የሚያመነጨውን በመለየት ይመረመራል። ብዙውን ጊዜ ህሙማን በደም ምርመራም ይሁን በሲቲ ስካን ምርመራ የተለየ ለውጥ አይታይባቸውም።
ህክምና
የእብድ ውሻ በሽታ የህመም ምልክት መታየት ከጀመረ በኋላ በህክምና የመዳን እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። ብዙዎች ከቀናት በኋላ ለሞት ይዳረጋሉ። ነገር ግን በበሽታው የተጠቃ እንስሳ ጉዳት እንዳደረሰባቸው የህመም ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ህክምና ካገኙ ብዙዎቹ ይድናሉ።
የሚሰጡ ህክምናዎች
- የንክሻ አደጋ ያጋጠመውን የአካል ክፍል ወይንም ቁስል በሳሙናና በውሃ ከተገኘም በአይወዲን ወዲያውኑ ሙልጭ አርጎ ማጠብ ወደ ሰውነት የሚገባውን ቫይረስ መጠን ይቀንሰዋል። ቁስሉን ወዲያውኑም መስፋት አይመከርም። አንቲባዮቲክና የቴታነስ መከላከያ እንደ አስፈላጊነቱ ይሰጣል።
- ካሁን በፊት የእብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ክትባት ላልወሰዱ ሰዎች RIG (ኢሚኖግሎብሊን) የሚባል ወደ ሰውነት የገባውን የራቢስ ቫይረስ የሚዋጋ የበሽታ መከላከያ መስጠት። የመድሃኒቱ መጠን በህሙማን ክብደት መሰረት የሚሰላ ሲሆን አብዛኛውን በቁስሉ ዙሪያ ይወጋና ቀሪውን ክትባት ከሚሰጥበት በተቃራኒ ባለ ክርን ላይ ይሰጣል። መድሃኒቱ ባስቸኳይ ካልተገኘ ክትባት ከተጀመረ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ መስጠት ይቻላል።
- ክትባት መስጠት፤ ጥቃቱን ያደረሰው እንስሳ የእብድ ውሻ በሽታ ተጠቂ ከሆነ ወይንም ሊሆን እንደሚችል ከተጠረጠረና እንስሳውን መያዝ፣ ካልተቻለ በመጀመሪያው ቀን ከዚያም በሦስተኛው፣ በሰባተኛውና በአስራ አራተኛው ቀን በክርን ላይ መከተብ አለባቸው።
እንስሳው ከተያዘና የእብድ ውሻ ህመም ምልክት ካልታየበት ለአስር ቀን ታስሮ ክትትል ይደረግለትና የህመም ምልክት ካሳየ ለእንስሳው ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ ከተገኘበት የተነከሰው ሰው የመጀመሪያውን ዙር ክትባት በአስረኛው ቀን ከዚያ ቀሪዎቹን ሦስት ዙር ደግሞ የመጀመሪያው ክትባት ከተሰጠበት ከሦስት፣ ሰባትና አስራ አራት ቀን በኋላ መሰጠት አለበት። ማስተዋል ያለብን ነገር ሰዎች የእብድ ውሻ በሽታ ምልክት ካሳዩ በኋላ ክትባትም ይሁን RIG መስጠት ጥቅም የለውም።
የሥራ ባህሪው ለእብድ ውሻ በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያለው ከሆነ ለምሳሌ የእንስሳት ሐኪም፣ ከራቢስ ቫይረስ ጋር የተገናኘ ሥራ የሚሠራ የላብራቶሪ ባለሙያ የቅድመ መከላከል ክትባት በሦስት ዙር ሊሰጣቸው ይችላል። እነዚህ ሰዎች ባጋጣሚ ለቫይረሱ ቢጋለጡ ቁስሉን ማጠብና ሁለት ዙር ክትባት ብቻ መሰጠት በቂ ነው።
የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል
- ውሾችን ጊዜውን ጠብቆ ማስከተብ
- የዱር እንስሳዎች፣ ባለቤት የሌላቸው ውሾች እንዲሁም የተለየ ፀባይ የሚያሳዩ እንስሶችን አለመቅረብ።
- የመነከስ አደጋ ካጋጠመ ቁስሉን በውሃና በሳሙና በማጠብ ያለምንም መዘግየት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንዲሁም ጥቃት ያደረሰውን እንስሳ ከተቻለ መያዝና የሚያሳየውን ለውጥ መከታተል።
ምንጭ ፦ስለጤናዎ ምን ያውቃሉ ገጽ