ያለ ዕድሜ የሚከሰት ሽበት
ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ሜላኒን የተባለ የቀለም መመረት እየቀነሰ ስለሚሄድ ፀጉራችን በተፈጥሯዊ መንገድ ወደ ነጭነት እየተቀየረ ይሄዳል። ስለሆነም ነጭ ፀጉር ከዕድሜ መግፋት ጋር የሚያያዝ ይሆናል። ይሁን እንጂ ያለጊዜው የሚመጣ የፀጉር ቀለም ለውጥ (ሽበት) በአሁኑ ወቅት በለጋ ዕድሜ ላሉ ወጣቶች ጭምር አሳሳቢ ችግር እየሆነ መጥቷል። እናም ይህ ችግር የሚከሰትበትን ምክንያት ማወቅ የመፍትሔ አቅጣጫዎቹን ለመጠቆም ስለሚረዳ መነሻዎቹን እንመልከት።
ከባድ ጭንቀት፡- በመልካም የኑሮ ደረጃም ሆነ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኝ በህይዎት ጉዞው ውስጥ ደረጃው ቢለያይም ለጭንቀት የተጋለጠ ነው። ይህ በበርካታ ሃሳቦች የመዋጥና የመጨናነቅ ስሜት ከፍ ሲልም ያለጊዜው ለሚመጣ ሽበት ይዳርጋል።
ስነ ባህርይ (genetics)፡- ፀጉራችን ወደ ነጭነት የሚቀየርበት ጊዜ በዘርም ይወሰናል። ስለሆነም አባቶቻችን አልያም አያቶቻችን ያለጊዜው በሚከሰት ሽበት ተጠቅተው ከነበረ እኛም በዚሁ ሂደት ውስጥ የማለፍ ዕድላችን ሰፊ ይሆናል።
ያልተመጣጠነ ምግብ፡- የቫይታሚን B.12 እጥረት ለፀጉር ነጭ መሆን ምክንያት ይሆናል። ለዚህም እንደ ዓሣ፣ የበግ ሥጋ፣ ዕንቁላል፣ ቅቤ እና ወተት እና የወተት ውጤቶችን መጠቀም ካልተፈለገና ካለጊዜው ከሚመጣ የፀጉር ቀለም ለውጥ ይታደጋል ተብሏል።
መጥፎ ልማዶች፡- ሲጋራ ማጨስ፣ መጠጥ ማዘውተርና መሰል ያልተገቡ ልማዶች ለፀጉር መንጣት አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ይነገራል።
ፈሳሽ ነገሮችን አብዝቶ መውሰድ፡- ሻይ፣ ቡና እና ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን ከልክ በላይ መውሰድም ለችግሩ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
መፍትሔዎቹስ
የእግር ጉዞ፦ በጠዋት የሚደረግ የእግር ጉዞ ለመላው ጤንነታችንም ሆነ ለፀጉራችን ደህንነት ጠቃሚ መሆኑ ይነገራል። በቀዝቃዛ ሳር ላይ በጠዋት በባዶ እግር መጓዝ ፀጉር ከተፈጥሯዊ ኡደቱ ውጪ ነጭ እንዳይሆን ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።
ጭማቂዎችን መጠጣት፦ትኩስ የአትክልትና ፍራፍሬ ጭማቂዎችን መጠጣት ስኳር ከሚጨመርባቸውና ከተለያዩ ለስላሳ መጠጦች እንድንርቅ ስለሚያደርግ ጥቅሙ የጎላ ነው። በየቀኑ የካሮት ጭማቂ መጠጣት የፀጉርን ቀለም ወደ ነጭነት ከመቀየር ይታደጋል። የበቀለ ስንዴ ጭማቂም ለዚህ ችግር መፍትሔ አለው ነው የሚባለው።
የቫይታሚን ይዘት ያላቸውን ምግቦች መውሰድ፦ ከላይ እንደጠቀስነው የፀጉር ቀለም ካለጊዜው ወደ ነጭነት ለመቀየር የቫይታሚን ቢ12 እጥረት አንዱ ምክንያት ነው። ስለሆነም በቫይታሚን ኤ እና ቢ የበለፀጉ ምግቦችን ማዘውተር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ሙዝ፣ ድንች፣ ጎመን፣ እርጎ፣ ሥጋ፣ ጉበት እና የተለያዩ ጥራጥሬዎችን መመገብ ችግሩን ለመቅረፍ ይረዳል።
በአዮዲን የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ፦ዓሣ ከፍተኛ የአዮዲን ይዘት እንዳለው የሚነገር ሲሆን፤ ሙዝ እና ካሮትም የተወሰነ አዮዲን ስለሚይዙ ብንመገባቸው የፀጉር መንጣትን ለመከላከል ይጠቅማሉ ተብሏል።
ሂና መቀባት፦ሂና ወይም ሜሄዲ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በህንድ የፀጉርን ውበት ለመጠበቅ ጥቅም ላይ የዋለ እስከአሁንም ድረስ የዘለቀ የፀጉር ቀለም ነው። ሂናን ሻወር ከወሰድን ከአንድ ስዓት በኋላ ብንጠቀመው ውጤታማ እንደሚሆን ይነገራል። ሂና የፀጉር ጥንካሬን በማሳደግ ሽበትንም ይከላከላል።
ዘይት መቀባት፦ የዘንባባና የለውዝ ዘይት እንዲሁም የሎሚ ጭማቂ የፀጉር ቀለም መንጣትን ለመከላከል ከድሮ ጀምሮ ጥቅም ላይ ውለዋል። ሰሊጥ መመገብ ወይም ጭንቅላትን የሰሊጥ ዘይት መቀባትም ፀጉርን ጥቁር ለማድረግ እንደሚያግዝ ይነገራል።
ጭንቀትን ማስወገድ፦ ጭንቀት ለምንም ነገር መፍትሔ ሆኖ አያውቅም፤ ለሌላ ከባድ ችግር ያጋልጣል እንጅ። ስለሆነም ላልተገባ የፀጉር ቀለም መለወጥ እና ለሌላ የጤና እክል ከመዳረግ ይልቅ በተረጋጋ ሁኔታ ለችግሮች መፍትሔ መስጠቱ ይበጃል።
ከመጥፎ ልማዶች መራቅ፦ ከላይ እንደጠቀስነው እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጦችን ማዘውተር፣ የአደንዛዥ እፅ የመጠቀም መጥፎ ልማዶችን ማስወገድም ለጤናማ ህይወትና ለፀጉር ደህንነት ወሳኝ በመሆኑ ከእነዚህ ልማዶች መራቅ ያስፈልጋል። በተጨማሪም የሂና ፓውደር፣ የናና ጭማቂ፣ ቡና እና እርጎን በማዋሃድ በየሳምንቱ ለሶስት ስዓታት ፀጉርን በመቀባት እና በሻምፖ መታጠብም ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
ምንጭ፦ስለጤናዎ ምን ያውቃሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2013