አብነት አባቡ
(3ኛ ዓመት የካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ድህረ ምረቃ ተማሪ)
በአስተሳሰብና በባህርይ ላይ የሚያተኩረው የንግግር ህክምና (ኮግኒቲቭ ቢሄቭየራል ቴራፒ) በዋነኝነት የሚያተኩረው “አሁናዊ አሰተሳሰብ” ላይ ነው። ይሄ አሰተሳሰብም የአሰተዳደጋችን፣ የማህበረሰባችን እሴት እንዲሁም የእኛ ምርጫ ውጤትም እንደሆነ አይካድም። በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ለሚታዩት ቀውሶች በምክንያትነት የሚያሰቀምጠውም የሰው ልጆችን ምክንያታዊ ያልሆኑ አስተሳሰቦች (Irrational Thoughts) ነው። እነዚህ ምክንያተ ቢስ ሀሳቦችን የምንዋጋባቸውን መንገዶች ከመጠቆሜ በፊት እስቲ ለሰው ልጅ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ምክንያት ይሆናሉ የተባሉ 13 ምክንያታዊ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ከሚባሉት ዋናዎቹን ላቀብላችሁ።
፩. ሁሉም ሰው ሊያደንቀኝ፣
ሊወደኝ ይገባል።
ይሄ አንዳንዶቻችን ምናልባት ካደግንበት ቤተ ሰብ አሊያም ማህበረሰብ የቀሰምነው አስተሳሰብ ነው። በዚህ አሰተሳሰብ መሰረት ሰዎች የምናደርጋትን እያንዳንዷን ነገር በተመለከተ አድናቆት እንጂ ትችት ወይም ተቃውሞ መሰንዘር አይችሉም። የቅርብም ይሁኑ የሩቅ ወዳጆቻችን በሀሳባችን ሊስማሙና ሊያደንቁን ይገባል እንጂ ትችት ሊሰነዝሩ አይገባም። አንድ ሰው እንኳን ይህንን ካደረገ አለቀ ደቀቀ በቃ የማልረባ ሰው ብሆን ነው። ፉንጋ ብሆን ነው። ሁለተኛ ጽሁፍ የሚባል መጻፍ የለብኝም። ሁለተኛ ስዕል የሚባል መሞከር የለብኝም የሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። በዚህ ብቻ ሳንገደብ አጋጣሚውን ካገኘን ይሄንን ሰው በማኩረፍ ፣ አጸፋውን በትችት፣ በመመለሰ እና በንቀት ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን። በዚህ ሂደት ውስጥ ስነልቦናዊ ቀውስ ውስጥ እንወድቃለን። እንሸቀባለን፣ ደስታ ከእኛ ይርቃል! የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔ ያለው አደናቆትን መፈለግ ላይ አይደለም። ከሁሉም ሰው አደናቆትን መፈለግ ላይ ነው።
ሁሉም ሰው እኔን ሊወደኝ ይገባል። ይሄ የአሰተሳሰብ ቫይረስ የብዙ ሰዎችን አስተሳሰብ አዛንፎታል። እንዲህ አይነት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሁሉም ሰው እንዲወዳቸው ይፈልጋሉ። በተለይ በጣም ቁልፍ የሚሏቸው ሰዎች የማይወዷቸው መሆኑን ካወቁ አለቀ ደቀቀ ወይ በስድብ ወይም በኩርፊያ ድራሻቸውን ያጠፉታል። መልከ ቀናዋን ልጅ አያችኋት ይቺን ፉንጋ፣ ሎጋውን ደግሞ አያችሁት ይሄን ጉረኛ ብለን ለማንኳሰስ ይፈጥናሉ። ያም ካልተሳካ ደግሞ ራሳቸውን ያማርራሉ። “አስር ሰዎች አይወዱኝም ሰለዚህ እኔ የማልረባ ውዳቂ፣ መጥፎ ሰው ስለሆንኩ ነው። ተሰፋ የለኝም” ወደሚል ድምዳሜ ይደርሳሉ። የሚወዷቸውን በዙ ሰዎች ችላ ይሏቸዋል።
ይሄ ጤነኛ አሰተሳሰብ አይደለም። ሁላችንም የሚወዱን ሰዎች አሉ ደግሞ ቢቻላቸው የአይጥ መርዝ ሊሰጡን ምቹ ሁኔታ የሚጠብቁ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይሄ ማለት ሰዎች እዚህ አይነት ድምዳሜ ላይ የደረሱት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ነው የሚለው ድምዳሜ ላይ አያደርሰንም። አንዳንዶች በጨረቃ ስለሚነሳባቸው ይሆናል። አለ አይደለ ሙዳቸው አይደለም። ሌሎች ድግሞ አጭር ወፍራምና መነጽር የሚያደርግ ሰው ስለማይወዱ ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ ቀርበው ስላላዩን ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ እኛን የሚጠሉበት አጥጋቢ ምክንያት ስላላቸው ይሆናል። እና ምን ይጠበስ! ጥቂት ሰዎች አይወዱኝም ማለት የዓለም መጨረሻ ነው ማለት አይደለም። ጥቂት ሰዎች አያደንቁኝም ማለት ዘመነ ፍጻሜ በደጅ ነው ማለት አይደለም ።
፪. “የሆንኩትን የሆንኩት ከሌሎች ሰዎች፣ ከቁጥጥሬ ውጪ ከሆኑ ሁኔታዎች የተነሳ ነው።”
“ወድጄ እኮ አይደለም አስተዳደጌን ታውቅ የለ? እዚች ደሃ አገር ላይ፣ ለዚያው ያለ አባት ጋር አድጎ ሰው የሆነ አለ?”
“ወንድ ምን ዕዳ አለበት፥ እኔ ሴቷ ልጨነቅበት እንጂ!”
“እስቲ አስበው ማስተርሴን ሰርቼ ቢሆን እኮ ይሄን ጊዜ የት በደረስኩ?”
“እንደ እከሌ ፋስት ብሆን ኖሮ?”
“ይሄን ሰውዬ ባላገባ ኖሮ፣ ልጆች ባልወልድ ኖሮ እኮ ስንት ደረጃ በደረስኩ?”
እነዚህ ከላይ የገለጽኳቸውን ንግግሮች የምታዘወትሩ ከሆነ ለአዕምሮ ጤናችሁ መታወክ በር እየከፈታችሁ ነው። በእነዚህ ንግግሮች ውስጥ እውነት እና ውሸት ተደባልቀዋል። እውነቱ ውጫዊ ሁኔታዎቻችን እና ሰዎች ተጽዕኖ ይፈጥሩብናል። ያደግንበት ሃገር፣ አሰተዳደጋችን፣ የተማርን መሆን አለመሆናችን የጋብቻችን ሁኔታ ተጽዕኖ ያሳድርብናል። ይሄ እውነት ነው። ይህንን የሚክድ ሰው ካለ ሲግመንድ ፍሮይድ እና እስከዛሬ ከወጡ የስነ ልቦናዊ ሀሳቦች ጋር ይጋጫል።
እነዚህን ሁኔታዎችና ሰዎች ላለንበት ሁኔታ ተጠያቂ በማድረግ ራሳችንን ነጻ ለማድረግ የምንሞክር ከሆነ ያ ነገር ውሸት ነው። የራሳችንን ምርጫ (ፍቃድ) ቸል ብለን “አማራጭ የለንም” እያለን የምናላዝን ከሆነ ያ ነገር ቅጥፈት ነው። እኛ እያለፍንበት ባለው ሁኔታ ውስጥ ከዚያም በከፋ ሁኔታ ውስጥ ያለፉና የሚያልፉ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ተቀብለው ለመለወጥ በመስራታቸው ያሰቡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ያለ አባት እና እናት ያደጉ ሰዎች በእናትና በአባት ስር ካደጉ ሰዎች የበለጠ ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል። ፊደል ያልቆጠሩ ሰዎች የሚሰሩትን ተዓምር ለማየት ዙሪያችንን መቃኘት ብቻ በቂ ነው። ሰለዚህ ልንለውጠው የምንችለውን ውጫዊ ሁኔታችንን ምክንያት አድርገን ማለቃቀስ ዋጋ የለውም።
በምንም አይነት ውጫዊ ሁኔታ ውስጥ እንሁን። ላለንበት ሁኔታ ሰበብ አድርገን ልንጠቀምበት አንችልም። ያለንበትን ሁኔታ ለማብራራት ምክንያት አድርገን ልንጠቀምበትና ልናዜመው አይገባም። ያንን እያደረጋችሁ ከሆነ ያላችሁበትን ሁኔታ ባትፈጥሩት እንኳን፣ ውስጡ ለመገኘታችሁ ምክንያት ባትሆኑም እንኳን፣ ውስጡ ስለ ተገኛችሁ መፍትሄ ልትፈልጉለት ይገባል እንጂ ልታላዝኑ አይገባም። የምታላዝኑ ከሆነ የሕይወታችሁን መዘውር የያዛችሁት እናንተ ሳትሆኑ እነዚህ ውጫዊ ሰዎች እና ሁኔታዎች ናቸው።
ይህንን የምታደርጉ ከሆነ ራሳችሁን ያልተገባ ጭንቀት ውስጥ እየጣላችሁ ነው።
– ቀሪዎቹን በሚቀጥለው ሳምንት እናያቸዋለን!
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013