ወርቅነሽ ደምሰው
ወዳጆቼ! እንደምን ከረማችሁ? ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› አለ የሀገሬ ሰው። እድሜ ይሰጠን እንጂ ዘንድሮማ! የማንሰማው ጉድ የለም። የዘወትር ፀሎታችንን ከጉድ ይሰውረን ቢሆንም ያላሰበነውና ያልጠበቀነው ጉድ ከመቅጽበት ከሰማይ ወርዶ ዱብ እዳ እየሆነብን ተቸግረናል!። ይሄው በፈጣኑ በቴክኖሎጂ መረብ እየተምዘገዘገ ጆሮአችን ደርሶ ግራ እያገባ ያፋጥጠን ይዟል። አሁን አሁን እማ! በምንሰማው እንግዳ ነገር የጆሮአችን ታምቡር እንዳይበጥሰው ስጋት ላይ መውደቃችንም አልቀረም። ዘንድሮ ጆሮና አይን መቀለጃ ሆነዋል።
እኛ ያልሰማነውና ያላያነውን እውነት ፤ ሩቅ ሆነው ሰምተውልንና አይተውልን ደግመው ደጋግመው እየነገሩን ሊያስረዱን የሚሞክሩ አካላት በበዙበት በዚህ ዘመን ምን ጉድ ይጠፋል ብላችሁ ነው። እንቅልፍ አጥተው፣ ነጋ ጠባ ተጠበውና ተጨንቀው የሚያስቡልን ‹‹እነእንቶኔ ›› እያሉ ምን እንሆናለን!። ለሀገራችን ሰላምና እድገት የሚበጁ ጠቃሚ መረጃዎችን ከመቅጽበት ለኛው ለማድረስ ሲሉ መቼ ሰንፈው ያውቁና¡።
በሚፈልጉት መጠንና ልክ ሰፍተው በለመዱት መንገድ ማንም ሳይቀድማቸው ተሽቀዳድመው በፍጥነት ሊያደርሱን ሲሯሯጡ መቼ ደከመኝ ሰለቸኝን ያውቃሉ። የዘወትር ልፋታቸው ምስክር ሳይሻው የድርጊታቸው ተከታይ በሆኑት ጀሌዎታቸው እየተመሰከረ ይገኛል። መጮህ በሚፈልጉበት ጉዳይ ጩኸታቸውን ‹‹እንደገደል ማሚቱ›› እያስተጋቡ ሰሚ ፈለጋ ወዲያና ወዲህ ሲሯሯጡ መመልከት የተለመደ ነው።
ሀገራችንን ለረጅም ዓመታት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል በሚለቀቁ ትክክለኛ ያልሆኑ፤ ያልተጣሩ ሀሰተኛ ወሬዎች ስትታመስ ቆይታለች። ህዝብ ከህዝብ በማጋጨት ሀገር እንድትፈርስ ሆን ተብለው በሚፈበረኩ በሬ ወለደ ወሬዎች ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን የሚያደርጉ አካላት ነበሩ። ከወሬው መሠረተ ቢስነት ባሻገር ማነው የተናገረው የሚለውን የማይገልጽ ምንጩ ያልታወቀ፤ የወሬ አዙሪት ተንሰራፍቶ ሀገራችንን ፈታ ነስተው የነበሩ ጉዳዮች ናቸው። ሰሚውም የሰማውን ወሬ የማጣራት ጊዜና ሰዓት ሳያስፈልገው በሰማው ልክ ወይም ከዚያ በላይ አስፋፍቶና አጋኖ ያስተጋባል።
የሰማነውን ወሬ ለማጣራት ሆነ ስለ ትክክለኛቱ ምንም ሳንጨነቅ የሰማነውን ብቻ ስናስተጋባ ምን እያደረግን እንደሆን ያልገባን በርካቶች ነን። ልብ ልንለው ያልፈለግነው ፤ ከቁብ ያልጻፈነው ጉዳይ ብዙዎችን የሚጎዳ ሆኖ ሲገኝ እጅግ ያሳዝናል። ይህንን የወሬ አዙሪት በመጠቀም ሀገር እንዳትረጋጋ የሚያደርጉ እጅግ በርካታ የውስጥና የውጭ ኃይሎች መኖራቸውም እሙን ነው።
ለኢትዮጵያ በጎ የሚመኙ እንዳሉ ሁሉ፤ በመጥፎ አይን የሚያዩአትና ውድቀቷን የሚመኙ ፤ አካላት በየጊዜው እንድትታመስ አጥብቀው በመስራት ሰላሟን ለመንጠቅ አብዝተው ይጥራሉ። ሆኖም ከሚሰማው ይልቅ መሬት ላይ ያለውን እውነት የሚያመነው የሀገሬ ሰው ለዚህ ሳይበገር ቆይቷል። ወሬ በመፈብረክ ታዋቂነት ያተረፉት ‹‹እነእነቶኔ›› የወሬ ማዕበል ተነቅቶባቸው እየከሸፈ ባለበት በዚህ ጊዜ ሌላ የሰማይ ስባሪ የሚያክል ወሬ ከማይጠበቅ አካል ተወልዶ ተገኘ።
ወዳጆቼ! ዘንድሮማ ጉድ ፈልቷል። እጅግ አስገራሚ ወሬ ተሰምቷል። ‹‹ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው›› ያሰኘንን እንግዳ የሆነ መረጃ ። በኛ ሀገር በሀገረ ኢትዮጵያ በጥንታዊ ከተማ አክሱም ተፈጸመ የተባለ ድርጊት ዱብ እዳ ሆኖብን ሰንብቷል። ይህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊት በወገኖቻችን ላይ ሲፈጸም እንዴትስ መስማት አቃተን ? ‹‹ ለሀገሩ ባዳ ለሰው እንግዳ የሆነ ›› የሆነው አካል መረጃን ፈልፍሎ ከነምንጮቹ እንካችሁ ሲለን ለምን ግራ አንጋባ ። ከሀገር ውጭ ለሚኖረው ለዚህ አካል ቅርብ የሆነው ለኛ እንዴት ድብቅ ሆነ ?። ወይስ የነሱ ጆሮና አይን የተለየ ብቃት ተችሯቸዋል።
‹‹ሳያጣሩ ወሬ ሳይገድሉ ጎፈሬ›› እንዲሉ አበው በአንድ ሀገር ላይ ያልተጣራና ያልተጨበጠ መረጃ አገኘሁ ብሎ ማቅረብ ምን የሚሉት ገድል ነው። ሊያውም ለሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ጥብቅና ቆሜያለሁ ከሚል ዓለም አቀፍ ተቋም።
ተቋሙ መንግሥት በትግራይ ባካሄደው ህገ የማስከበር ዘመቻ ወቅት በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በአክሱም ከ200 በላይ ሰዎች በጅምላ መገደላቸውን ገልጿል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ላይ በኅዳር 19 እና 20/2013 ዓ.ም የተፈጸመው የጅምላ ግድያን የዓይን እማኞቹን ጠቅሶ ይፋ አድርጓል። ከኅዳር 10 እስከ 21 ባሉት ቀናት ውስጥ በአክሱም ከተማና ነዋሪዎቿ ላይ የቦንብ ድብደባን፣ ግድያ፣ የአካል ጉዳት እና ዘረፋን ጨምሮ ከባድ የመብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን ገልጿል።
ይህ ዓለም አቀፉ ተቋም ለዚህ ዘገባ በመረጃ በምንጭነት የተጠቀማቸው አካላት በምሥራቃዊ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞችና አክሱም ውስጥ ካሉ ግለሰቦች በስልክ የተሰበሰበ መረጃ እንደሆነ ገልጿል።
ድንቄም መረጃ አሉ! እማማ ! ‹‹የአይጥ ምስክር ድንቢጥ›› እንዲሉ አበው። ተቋሙ ለምስክርነት የጠቀሳቸው ምንጮች በትኩረት መመልከት የግድ ይላል። ተቋሙ ከአክሱም በስልክ አነጋገርኳቸው ብሎ ያቀረባቸውን የዓይን እማኝ ግለሰቦች ገለልተኛ ወገን መሆናቸው የሚያሳይ ሪፖርት አልቀረበም። ይልቁንም በጥቃቱ ላይ ተሳተፊ የ ሆነውን ወጣት የዓይን እማኝነት አድርጎ አቅርቧል።
ከሁሉም በላይ ግን የመረጃውን ታአማኒነቱን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተው ስልክ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንዴት አድርጎ መረጃውን በስልክ መሰብሰብ ተቻለ? የሚለው ትልቁ መጠየቅ ያለበት ቁልፍ ጥያቄ ነው። ተቋሙ መረጃ ሰበሰብኩ ባለበት ወቅት በአክሱም አካባቢ የስልክ አገልግሎቱ መቋረጡን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። ይህ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተላለፈና ሁሉም ሰው መረጃውን የሚያውቀው ነው።
መቼም ወገኖቼ! ለእነዚህ ምስክሮች ብቻ የተለቀቀ የስልክ መስመር ይኖር ይሆን? ወይስ መኖርና መሞታቸው የማይታወቀው ቀሪ የጁንታው ርዝራዞች፤ የነሱ ይሆን አይሁን በማይታወቅ ጽምፅ አንዳንዴ አለን እያሉ እንደሚለቁት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ አይነት ይሆን? እንዴ ነገሩ ‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ›› ነውና መጠርጠር አይከፋም።
ወዳጆቼ! መቼው መንግሥት በትግራይ ክልል ባደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ የተጎዱ ወገኖች ስለመኖራቸው ግልጽና ከማንም የተሰወረ ሚስጥር አይደለም። ነገር ግን በአክሱም ተፈጸመ ተብሎ የቀረበው የጅምላ ጭፍጨፋ ሰምተን በግዴለሽነት ልናልፈው የምንችለው ጉዳይ አይሆንም።
በትግራይ መረጋጋት እንዳይሰፍን በሚፈልጉ አካላት ሴራ እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባል። እነዚህ አካላት ይፋ ያደረጉት መረጃ በመረጡት አካል በሰበሰቡት መረጃ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት በማለም ነው። ያም ሆነ ይህ ፤ እዚህም ነፈሰ እዚያ ተቋሙ አገኘሁት ብሎ ያቀረበው ሪፖርት ከእውነት የራቀ ‹‹ ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ ›› አይነት መሆኑን አመላካቾች በርካታ ናቸው።
ሌላው አስገራሚ ነገር ግን ደግሞ ለምስክርነት የቀረቡት የሱዳን ስደተኞች ጉዳይ ነው። በሞቴ! በአክሱምና በሱዳን መካከል ያለው ርቀት ደግሞ ምነው እንደዚህ ቀረበ። የሪፖርቱ ምንጮች የሆኑት በምሥራቃዊ ሱዳን የሚገኙት ስደተኞች በምን ያህል ፍጥነትና ጊዜ ተጉዘው ነው ከአክሱም ተጉዘው ሱዳን የገቡት። አክሱም ላይ የተፈጸመው ግድያ አይተው ሸሽተው ሱዳን ገቡ። ከዚያም ለዓይን ምስክር የሚያበቃ መረጃ ለመስጠት ቻሉ። ሊያሳምን የማይችል ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ›› የሆነ ነገር ነው። እናም እነዚህ አካላት ምንጮች አድርጎ የቀረበው ሪፖርት በጥልቀት ሊመረምረው ይገባል። የተቋሙ ፍላጎት ምንም ይሁን ምን ከዚህ ጀርባ ያሉ የማይታዩ እውነታዎች ፈልፈሎ ማግኘት የግድ ይላል። ከህዝብ አይን የሚያመልጥና የተሰወረ አንዳችም ነገር ሚስጥር የለምና። የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ ሁሉም በጊዜው ይገለጣል።
ሌላው በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው የዚህ ሪፖርት ማበልፀጊያ የሆኑት አነጋጋሪ ቄስ ጉዳይ ነው። ቄስ ነኝ ያሉት ግለሰብ እንደሚገልጹት በህዳር ወር በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ስፍራ በጥንታዊቷ ከተማ አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያ በጸሎትና ቅዳሴ ላይ እያለን የተኩስ ጽምፅ ሰማን ፤ ስንወጣ የአማራ ልዩ ኃይልና የኤርትራ ወታደሮች እየተኮሱ ነበር።
በፈጣሪ ስም እየተማፀንን ብንለመናቸውም መተኮሳቸውን አላቆሙም ። የእናንተ አምላክ የኛ አምላክ አይደለም እያሉ እየተኮሱ ሰዎችን ሲገድሉ መመልከታቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ይህ እራሱን ቄስ ወልደማሪያም እያለ ሲጥራ የነበረ ሰው ያሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑ ተደርሶበታል። በአሜሪካን ቦስተን የሚኖር ሚካኤል በርሄ በመባል የሚታወቅ የህወሓት ካድሬ የነበረ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ ሆኗል። ይህ ጉዳይ ሆን ተብሎ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማደናገር ታስቦ እየተፈነቀለ ያለ ድንጋይ መሆኑ ከዚሁ መረጃ መገንዘብ አያዳግትም። ቄሱ ሲነቃበት ደግሞ በቦታው ላይ ባልገኝም አስመስዬ የመስራት መበት አለኝ ብሎ ሲናገር ያለምን ሃፍረት ነው። ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር ይሏል እንዲህ ነው።
‹‹ወደው አይስቁ ›› አሉ እማማ! ታዲያ ዛሬም ድረስ ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያላነሱ የጁንታው ርዝራዦች ድርጊት ይፋ የወጣበት ነው። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሪፖርቱ ባሻገር ያሉ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ አስፈላጊውን ጥናት በማካሄድ በጥልቀት መመርመር ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ። የሆነው ሆኖ የሀሰት መረጃ በመስጠት በወገኖቻቸው ላይ መቀለድ ተገቢ አይደለም። የጁንታው የጥፋት ኃይሎች እንኳን የትግራይ ህዝብ ሊጠቅሙት ያተረፉለት ስቃይና መከራ ነው። የጥፋት ኃይሉ ርዝራዦች እነሱ በመረጡት ሀገር ተንድላቀው እየኖሩ ለችግርና ለመከራ የተዳረገው ህዝብ ላይ ሌላ ምሬት በመፍጠር ህዝቡ ለኀዘንና ለእንግልት መዳረግ በምንም እሳቤ ተቀባይነት አይኖረውም። ህዝቡ የጁንታው የጥፋት ኃይሎች ካደረሱበት ጉዳት እያንሰራራ ባለበት በዚህ ወቅት መረጋጋትና ሰላም እንዳይሰፍን የሚፈልጉ ኃይሎች በተዘዋዋሪ የሚሰሩት ሴራ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል።
አበው ‹‹ ጦርከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል›› እንዲሉ ፤የወሬ ቀስታቸውን ሰብቀው ኢትጵያውያን በመበታተን ሀገር እንድትፈርስ የሚሰሩ አካላት ዓላማቸውን ማክሸፍ ያስፈልጋል። ሁሉም የኢትዮጵያ ጠላቶች የጥፋት በትራቸውን አነስተው ሀገራችንን ሊያዳክሙ ቢጥሩም መቼም ቢሆን ተሳክቷላቸው አያውቅምና። ምንም እንኳን እነሱ በሰላም ውለን እንድናደር ባይፈቅዱልንም በፈጣሪ ከዛም በታች ደግሞ በደጋግ ኢትዮጵያውያን ብርታት ሀገር ሳትፈርስ እንድትቀጥል ሆናለች።
ዛሬም ሀገርን ማፍረስ ቀላል መስሎ የታያቸው አካላት ያለ የሌለ ኃያላቸው ተጠቀመው በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተፅዕኖ ለመፍጠር ይጣጣራሉ። በተለይም አለን የሚሉት ጀግንነትና ልዩ ኃይል በ15 ቀናት ውስጥ እነደ ጉም በኖ ሲጠፋ የቀራቸውን በመርዝ የተለወሰ ምላስ መሳርያ አድርገው እየተጠቀሙ ነው። በጦር ሜዳ ያልተገኘ ድል በምላስ ይገኛል ብሎ ማሰብ ቂል ከማሰኘት ውጪ ምን የሚያስገኘው ትርፍ የለም። ህውሓት ሞቶም ቢሆን ምላሱ አያርፍም ያለው ጄኔራል አበባው እውነቱን ነው ለካ።
ወዳጆቼ እስኪ ልብ ብላችሁ አድምጡኝ! ለደቂቃዎች ጆሮአችሁን አውሱኝ! በድህነት ውስጥ እየማቀቅን ያለን እንደኛ አይነት ሚስኪን ህዝብ ድህነት ከላያችን አሽቀንጥረን ለመጣል ከመሯሯጥ ይልቅ ለምን ይሆን በፖለቲከኞች ቁማር ተበልተን ኪሳራ ውስጥ የምንገባው። እስከመቼ ይሆን ልብ ገዝተን ከመገፋፋት ወጥተን እርስ በእርሳችን ተደጋግፈን ሳንለያይ በአንድነት ለሀገር ሰላም የምንሰራው። እኛ ለሌላ አካል አሳልፈን የሰጠነውን የውስጥ ሰላም ማን ይመልስልን ይሆን ?። ጥንታዊት ቀደምት ሀገር እንዳለን እየተናገርን ታሪክ ሰሪ ሳይሆን ታሪክ ዘካሪ ትውልዶች ሆነንን መቅረታችን ሊያሳስበን ይገባል።
‹‹በሬ ሆይ! ሣሩን አይተህ ምነው ገደሉን ሳታይ ›› እንደተባለ እንዳንሆን ለወገኖቻቸው ደንታ የለሽ የሆኑ አካላት የራሳቸውን ጥቅም እንጂ ሌላው ለማመልከት የሚያስችል ተግባር የላቸውም። ዞሮ ዞሮ ህዝብ ከህዝብ ለመለያየት የሚያደርጉት ሴራ ባይሳካላቸውም ፤ ጥለውት የሚያልፉት ጠባሳ ግን ሊያሳስበን ይገባል። እነዚህ የጁንታ ርዝራዥ የሆኑ የጥፋት ኃይሎች በተባባረ ክንድ በአንድነት በመሆን ልናስቆማቸው ይገባል። እጁን በሀገራችን ላይ የቀሰረን የጥፋት ኃይል ሁሉ እጁን እንዲሰበሰብ በማድረግ የጥፋት መንገዱን ማኮላሸት የኛ ድርሻ ነው። ወደድንም ጠላንም የኛ የመኖር ህልውና ሀገራችን ላይ የተመሠረተ ነው።
በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኘውን ሀገር በመደገፍ ወደ ከፍታው ማማ ለመውጣት የምናደርገውን እርምጃ የሁላችንን ጥረት ይጠይቃል። ለዚህም ሁሉም በተሰማራበት መስክ በብርታትና በጥንካሬ ከሰራን የጠላትን አፍ ማሲያዝ እንችላለን። ድር ቢያብር አንበሳ ያስርን ነውና በተባበር ክንድ እጅ ለእጅ ተያያዘን በአብሮነት ወደፊት እንገሰግሳለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013