ዳንኤል ዘነበ
አጥንት ከሰውነት ክፍል ጠንካራው አካል ነው። እንደ ጥንካሬው ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት በሚዳረግበት አጋጣሚ ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ቀላል አይሆንም። አጥንት ከአካል እድገትና ከእድሜ መጨመር ጋር እያደር እያደገና እየጠነረ ሄዶ በጉርምስና እድሜ ማብቂያ ላይ እድገቱን ያቆማል። አጥንት ጠንካራ የሰውነት አካል መሆኑ ቢታወቅም በተለያዩ ምክንያቶች አቅም የሚያጣበትና ለስብራትም ሆነ ለመሰንጠቅ የሚጋለጥበት ሁኔታ አለ። በተለምዶ የአጥንት መሳሳት የምንለው አጥንታችን ጥንካሬውን አጥቶ ሲሳሳና በዚህም ምክንያት የአጥንት መድከም ሲኖር ነው።
በአብዛኛው ጊዜ ህመሙ ቢኖርም እንኳን ምንም ምልክት ስለማያሳይ እንዲሁም አንድ ሰው አጥንቱ ቢሳሳ እንኳን አጥንቱ መሳሳቱን ሊያውቅ ስለማይችል “ዝምተኛ ህመም” እንደሆነ ይታሰባል። የዚህ በሽታ ተጠቂዎች አጥንታቸው በቀላሉ የመሰበር አጋጣሚው ከፍተኛ ሲሆን ስብራት ካጋጠማቸው በኋላም ወደ ቀድሞ የተለመደ የእለት ተዕለት ተግባራቸው ለመመለስ ጊዜ ይፈጅባቸዋል፡፡ በአጥንት መሳሳት ምክንያት የሚፈጠር የአጥንት ስብራት በአብዛኛው የሚፈጠረው በዳሌ አካባቢ፤ በአከርካሪ አጥንት ላይ እንዲሁም የሰዓት ማሰሪያ አንጓ ላይ ነው፡፡
የጥንካሬውን ያህል ታዲያ እክል ሲገጥመው በቀላሉ ላይጠገንም ይችላል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ከወንዶች ይልቅ የሴቶች የአጥንት ጥንካሬ ከእድሜ አኳያ እየቀነሰ ይሄዳል። ጥንካሬው የቀነሰ አጥንት ደግሞ ለመሰበርም ሆነ ለመሰንጠቅ አደጋዎች እጅግ የተጋለጠ ነው። ስለዚህ እግር ወይም እጅ የመሠበር አደጋ ሊያጋጥም ይችላል፤ በእርግጥ ይህ በተገቢው ህክምና ሊጠገንና ወደ ቦታው እንዲመለስ ሊደረግ ይችላል። እንዲህ ያለው ችግር የሚወሳሰበው ግን አንድም አጥንቱ ሲሳሳ አለያም አቅም አጥቶ ለመሰንጠቅ ሲዳረግ ነው።
ለዚህ በሽታ በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው
• እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች እና ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች
• 45 ዓመት ሳይሞላቸው ያረጡ ሴቶች
• ከዚህ በፊት የአጥንት ስብራት በተደጋጋሚ የገጠማቸው ሰዎች
• ስቴሮይድ የሚባሉ የመድሃኒት አይነቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች
• የጠና ህመም ያለባቸው ሰዎች ለምሳሌ እንደ ኩላሊት ህመም
ምርመራ
ሰዎች የዚህ ህመም ተጠቂ መሆናቸውን ለማወቅ DEXA (Dual Energy X-Ray Absorp Hometry) የሚባል መሳሪያን በመጠቀም የአጥንት እፍጋትን መለካት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህን ልኬት በመጠቀምም በዳሌ አጥንት፤ አከርካሪ አጥንት እንዲሁም የሰዓት ማሰሪያ አንጓ አካባቢ ያለ የአጥንት እፍጋትን መለካት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህ ምርመራ የአጥንት ስብራት ሳይከሰት በፊት አጥንት መሳሳት መኖሩን የምናይበት ነው፡፡
የአጥንት መሳሳት ለምን ያጋጥማል ?
• ሴቶች በእርጣት ምክንያት የበለጠ ይጠቃሉ። ይህም የራሱ ምክንያት አለው።
• ቀጭንና ቀላል መሆን
• በቤተሰብ የአጥንት መሳሳት ችግር ያለበት ሰው መኖር
• ሲጋራ ማጤስ
• አልኮል ጠጭ መሆን
• አነቃቂ መጠጦችን ማብዛት
• የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ
• በምግብ ውስጥ በቂ ካልሲየም አለመኖር (ከሶስት ስኒ በላይ ቡና መጠጣት)
• የቫይታሚን ዲ መጠን ማነስ
• ባጠቃላይ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ
• የሆርሞን ችግር
• ኮርቲሶን መድሐኒቶችን ለብዙ ጊዜ መጠቀም እንዲሁም እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የአጥንት መሳሳት እድሉም እየጨመረ ይሄዳል።
የአጥንት መሳሳት የሚያስከትላቸው አካላዊ ጉዳቶች
የአጥንት መሳሳት ለስብራት ማጋለጥ ይችላል:: በተለይ ለዳሌ አጥንት፡ ለጀርባ አጥንት፡ ለእጅ አባር አካባቢና ሌሎችም ላይ በሚወድቁ ሰአት በቀላሉ የመሰበር እድሉ ከፍ ያለ ነው። አንዳንድ ጊዜ አጥንት ያለምንም ምክንያት ሊታጠፍና ሊሰበር ይችላል። መሳል በራሱ ለጎን አጥንቶች መታጠፍና መሰበር ምክናያት የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ከአጥንት መሳሳት የተነሳ በጀርባ አጥንት ላይ የሚያጋጥም የአጥንት መታጠፍና መሰበር ሰዎች እድሜያቸው ሲገፋ እንዲጎብጡ ይዳርጋቸዋል። የአጥንት መሳሳት ችግር በአጋጣሚ በተደረገ የራጅ ምርመራ ካልሆነ እስከ ሀምሳ አመት ድረስ ላይታወቅ ይችላል።
የአጥንት መሳሳት ህክምና
᎐የአጥንት መሳሳት ችግር ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ህክምና አማራጮችን ስንመለከት መድሃኒት መውሰድ እንዲሁም ጤነኛ የኑሮ ዘይቤን መከተል፤ በቂ የካልሲየም፤ የቫይታሚን ዲ እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል።
᎐በአጥንት መሳሳት ምክንያት የአጥንት ስብራት ቢገጥምዎ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርብዎታል።
᎐የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንዲሁም በቂ ካልሲየም እና ቫይታሚን ዲ ማግኘት፤
᎐በየእለቱ መደበኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፤
᎐ሲጋራ ማጨስ እና አልኮል መጠጥ የመውሰድ ልምድን መቀነስ፤
᎐የአጥንት እፍጋት ምርመራን ያካተተ መደበኛ የጤና ምርመራ ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ።
መድሀኒቶች
• Bisphosphonates
• Selective oestrogen receptor modulators
• Strontium ranelate
• Calcitriol
በአጥንት መሳሳት ዙሪያ ከሚከታተለዎት የጤና ባለሙያ ጋር ስለሚመገቡት ምግብ፣ ስለሚሰጠዎት ተጨማሪ ካልሽየም፣ የአጥንት መሳሳቱ ቀጣይ ሊያመጣ የሚችለው ችግር መኖር አለመኖሩንና ካለም ስለ ቀጣይ የምርመራ አይነቶች መነጋገር ያስፈልጋል። በተለየ መንገድ የሚታዘዙ መድሐኒቶችም ሊኖሩ ይችላሉ።
ምንጭ ፦ስለጤናዎ ምን ያውቃሉ ገጽ
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013