ዳንኤል ዘነበ
ስንፈተ ወሲብ (Impotence) ወይም የወንድ ብልት አለመቆም ችግር ለወንዶች አሳሳቢ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ችግር የወንዶችን በራስ መተማመን የሚቀንስና ፍርሃት የሚያሳድር ነው። ስንፈተ ወሲብ (Impotence) ማለት በፆታዊ ግንኙነት ወቅት የወንድ ልጅ ብልት በደንብ መቆም አለመቻል ነው።
ብዙ ወንዶች ጠዋት ላይ ብልት አለመቆምን ማስተዋል፣ ብልትን ለማቆም መቸገር ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነት ለማድረግ በሚያስችል መልኩ መቆም አለመቻል፣ ወይም የግብረስጋ ግንኙነት ፍላጎት መቀነስ አይነት ችግሮችን ያስተውላሉ። እነዚህ የስንፈተ ወሲብ (Erectile Dysfunction) ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ወንዶች ያማረ የወደፊት ህይወት እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ አመላካች ነው።
የስንፈተ ወሲብ ችግር (Erectile Dysfunction) እድሜያቸው ከ20-30 ከሚሆኑት ወንዶች ውስጥ 8% የሚሆኑትን እንደሚያጠቃና እድሜያቸው ከ70-75 ከሆኑት ላይ ደግሞ ወደ 37% ከፍ እንደሚል ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ ስንፈተ ወሲብ (Erectile Dysfunction) በአሁኑ ሰዓት በደንብ የሚታወቅና የተለያዩ የህክምና አማራጮችም ያሉት ችግር ነው።
ስንፈተ ወሲብ (Erectile Dysfunction) በምን ይመጣል?
• የእድሜ መግፋት
• ዝቅተኛ ቴስቴስትሮን
• ጭንቀት፣ ፍርሃት ወይም ድብርት
• በቂ እንቅልፍ አለማግኘት
• ሲጋራ ማጨስና አልኮል መጠጥ እንዲሁም፤ ሌሎች የጤና ችግሮች በተለይ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ ኮሌስትሮል ናቸው
ስንፈተ ወሲብን ማስወገድ የሚችሉባቸው መንገዶች
• ብዙ ስኳርንና ከፍተኛ ካርቦሀይድሬት ያላቸውን ምግቦች ማስወገድ። ምክንያቱም እነዚህ ስኳር የበዛባቸው ምግቦች የወሲብ መነሳሳትን ወይም የወሲብ ፍላጎትን ሊቀንሱ ይችላሉ።
• የኮሌስትሮል መጠናችን ጤነኛ በሚባለው ደረጃ መቆጣጠር።
• የደም ፍሰትን ለመጨመር ከፍተኛ አሚኖ አሲድ (Arginine) ያላቸው ምግቦችን መጠቀም።
• በዚንክ የበለፀጉ ምግቦችን መጠቀም እንዲሁም የቴስቴስትሮን ሆርሞን እንዲመረት የሚረዱ ሰፕልመንቶችን መውሰድ።
• ከፍተኛ ፍላቮኖይድ ያላቸውን ምግቦች መመገብ፣ ይህ ንጥረ ነገር በታይላንድ ከዕፅዋት በተለይም የታይላንድ ጥቁር ዝንጅብል (Kaempferiaparviflora) ላይ እናገኛለን። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፍላቮኖይድ ብዙ የጤና ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ብልት ላይ ያሉ የደም ስሮች ከእንደገና እንዲያገግሙ ይረዳል።
• በየቀኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያድርጉ፣ ክብደትዎን ይቀንሱ፣
• ሲጋራ ማጨስ ያቁሙ፣ የአልኮል መጠጥ ይቀንሱ፣ ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ያስወግዱ፣
• ጤናማ ምግቦችን ይመገቡ፣ ጭንቀትን ይቀንሱ።
በህክምና ማስተካከል እንዴት ይቻላል?
ስንፈተ ወሲብ ያለብዎት ከመሰለዎ ዶክተር ማማከር በጣም አስፈላጊ ነው። ማፈር የለብዎትም! የስንፈተ ወሲብ ህክምና እንደ ችግሩ መንስዔ እና እንደችግሩ ክብደት ይለያያል። የህክምና አማራጮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
• የመድሃኒት ህክምና፡ መድሃኒቶች የደም ፍሰትን ይጨምራሉ እንዲሁም የፆታዊ ፍላጎት በሚኖርበት ጊዜ ብልት በምላሹ እንዲቆም የሚያደርጉ ናቸው። አብዛኛዎቹ የስንፈተ ወሲብ መድሃኒቶች ስራቸውን ለመጀመር 30 ደቂቃ አካባቢ ይወስድባቸዋል። ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችም ራስ ምታት፣ አፍንጫችን ድፍን የማድረግ፣ የቆዳ መቅላት፣ የእይታ መቀየር ወዘተ ሊኖሩ ይችላሉ።
• ኤክስትራኮርፖሬል ሾክዌቭ ህክምና (Extracorporeal Shockwave Therapy): ይህ ህክምና ለስንፈተ ወሲብ አዲስ የህክምና አማራጭ ነው። ይህ የህክምና ዘዴ ታካሚው ብልቱን በበቂ ሁኔታና በራሱ ሰዓት ማቆም እንዲችል ያደርገዋል። የሾክዌቭ ህክምና ሂደት የደም ዝውውርን በመጨመርና የደም ስሮች በአዲስ መልኩ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ በማነቃቃት የተሻለ የደም ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል፤ ይህም የፆታዊ ግንኙነት አቅም እንዲመለስ እንዲሁም እንዲሻሻል ያግዛል።
• ቴስቴስትሮንን የመተካት ህክምና (Testosterone Replacement Therapy)፡ ዝቅተኛ የቴስቴስትሮን መጠን ያላቸው ወንዶች ቴስቴስትሮን የመተካት ህክምና በማግኘት ወንዶች የተሻለ ፆታዊ መነሳሳት እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። የሆርሞን ህክምና አብዛኛውን ጊዜ ዳሌ አካባቢ በመርፌ መልኩ ይሰጣል። ቴስቴስትሮንን ለመተካት ከሚደረጉ ህክምናዎች በብዛት የተለመዱት የቴስቴስትሮን አይነቶች ‘Cypionate’ እና ‘Enanthate’ ናቸው። የቴስቴስትሮን cypionate የተባለው መድሃኒት ግማሽ ላይፉ (half-life) 2 ሳምንት ሲሆን በአንፃሩ ቴስቴስትሮን enanthate የሚባለው ከ10-12 ሳምንት half-life አለው። ሌላኛው ቴስቴስትሮንን የሚተካ መድሃኒት የሚወሰድበት መንገድ ደግሞ ቆዳን ሰርጎ መግባት በሚችል ቅባት በመቀባት መልኩ ነው። ይህም ሆርሞኑ በቆዳችን ሰርጎ ከገባ በኋላ በደማችን ውስጥ ስራውን ያከናውናል።
ምንጭ ፦ከቬጂታኒ ሆስፒታል ድረገፅ
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013