አስናቀ ፀጋዬ
የጥቁር አርበኞች የነፃነት ተጋድሎ በሆነው የአድዋ ጦርነት ስማቸው በጉልህ ተፅፎ ከሚገኝባቸው የሀገራችን ክልሎች ውስጥ አንዱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነው። ከዚህ ክልል የፈሩት ስመጥሩ አርበኛ ሼህ ሆጄሌ አልሃሰን ጦራቸውን አስተባብረው ወደ አድዋ በመዝመት ከቀሪ ኢትዮጵያውን ጀግኖች አርበኞች ጋር አብረው ጠላትን በዱር በገደሉ አርበድብደዋል። በዚህ የአርበኝነት ተጋድሏቸውም ሼሁን ታሪክ ሁሌም ይዘክራቸዋል።
በየክልሉ ለኢትዮጵያ ነፃነት ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፤ በተለይ ደግሞ በአድዋ ጦርነት ላይ ተሳትፈው ደማቅ ታሪክ የፃፉ አርበኞችን ለማስታወስም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሰሞኑ ‹‹አድዋ የህብረ ብሔራዊ አንድነት አርማ!›› በሚል መሪ ቃል 125ኛው የአድዋ ድል በዓል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተከብሯል።
የክልሉ መናገሻ በሆነችውና ከአዲስ አበባ በ570 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አሶሳ የክልሉን ነዋሪዎች ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተከባብረው በጋራ ይኖሩባታል። ከተማዋ ጉሙዙን፣ በርታውን፣ ሺናሻውን፣ ኮሞውን፣ ደቡቡን፣ አማራውንና ኦሮሞውን በፍቅር አስተሳሥራ ይዛለች። በማንጎ ፍራፍሬዋና ሰማይጠቀስ የቀርክሃ ምርቷም ትታወቃለች።
ህዝቧም እንግዳ ተቀባይ ነው። ለም አፈሯም የቸሩትን አይነፍግም። በዚች ከተማ ደፋ ቀና ብለው ኑሮን ለማሸነፍ ላይ ታች ከሚሉ ወጣቶች ውስጥ ታዲያ አዲስ ዘመን አንዱን መርጦ የሲራራ እንግዳ አድርጎ ለአንባቢ ጀባ ብሏል።
ዕድገትና ውልደቱ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሃድያ ዞን ሆሳእና ከተማ ቢሆንም እንጀራውን ያገኘው በቤንሻንጉል ክልል አሶሳ ከተማ ነው። የከተማው ሰውም ሥራውን አይቶ ደምስ ብረቱ ይለዋል።
ከሃያ ሁለት ዓመት በፊት ተደርጎ በነበረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ላይም ተሳትፎ የሀገሩን ዳር ድምበር አስከብሯል። ከዚሁ ጦርነት የአሥር ዓመት ቆይታ በኋላ ወደሀገሩ ተመልሶ ትናንሽ ንግዶችንና ተባራሪ ሥራዎችን ዝቅ ብሎ ሠርቷል። የህዝብ ማመለሻ አውቶብስ አሸከርካሪም ሆኖ ኑሮን ለመግፋት ሞክሯ።
ከብዙ የህይወት ውጣውረድ በኋላ ወደ ቤኒሻንጉል ክልል መዲና አሶሳ በማቅናት አነስተኛ የብረታ ብረት ሥራን ጀመረ። አጀማመሩን ያዩ የከተማዋ ነዋሪዎችም ‹‹ዕደግ በርታ›› ሲሉ አሞገሱት። እርሱም በምላሹ ሥራ ለሚያዙት ደምበኞቹ በአነስተኛ ዋጋና በጥራት እየሠራ አስረከበ። ቀስ በቀስ ሥራውን እያሰፋ በመምጣት ዛሬ ላይ የመካከለኛ ብረታ ብረት ድርጅት ባለቤት መሆን ቻለ፡- የአሶሳው ብርቱ ሰውና የብረታብረት ድርጅት ባለቤቱ አቶ ደምሴ በቀለ።
አቶ ደምሴ ውልደቱና ዕድገቱ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሃድያ ዞን ሆሳእና ከተማ በመሆኑ ልክ እንደሌሎቹ የሆሳእና ታዳጊዎች ሁሉ እርሱም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሆሳእና ከተማ ዋቸሞ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚሁ ትምህርት ቤት እየተከታተለ ቢቆይም እስከ አሥረኛ ክፍል ከተማረ በኋላ በ1991 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት በመከፈቱ የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን ወደ ጦር ግምባር ዘምቶ በጦር ሜዳ መሞትም መኖርም እንዳለ ተገንዝቦ የዘመተው የያኔው ብላቴና ሀገሩን ከጠላት ለመከላከል በጀግንነት ሲዋጋ ቆየ።
በጦር ግንባር ቆይታውም ብዙ ኢትዮጵያውያን ከጎኑ ሲወድቁ፤ ከጠላትም በኩል ለቁጥር የሚታክት ወታደር ሲረግፍ ተመልክቷል። ከዚህ አሰቃቂና ሕይወት ቀጣፊ ጦርነት እንደ ዕድል በሕይወት ተርፎ ከአሥር ዓመት ቆይታ በኋላ ከመከላከያ ሰራዊት ተሰናበተ።
በ2001 ዓ.ም ወደ ትውልድ ከተማው ሆሳእና ከተመለሰ በኋላ ኑሮን ለማሸነፍ ሲል የተለያዩ አነስተኛ ንግዶችን ጀመረ። ሌሎች የእህል አየር ባየር ንግዶችንም ሞከረ። ሆኖም እንዲህ በቀላሉ ሊሳካለት አልቻለም። ከራሱ ጋር ሲመካከር ከቆየ በኋላም ከሚኖርበት አካባቢ ወጥቶ መሥራት እንዳለበት አመነ። የአውቶብስ ትኬቱን ቆርጦም ወደ ቤኒሻንጉል ክልል ርእሰ መዲና አሶሳ አቀና።
በ2002 ዓ.ም ወደ አሶሳ ከተማ ከመጣ በኋላ የመጀመሪያ ዓላማው የመኪና ማሽከርከር ሙያን ተምሮ መሥራት የነበረ በመሆኑ ሦስተኛ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ ቅጥቅጥ የህዝብ ማመለለሻ መኪና ተቀጥሮ ማሽከርከር ጀመረ። በዚህ ሙያም ያሰበውን ያህል ሊሳካለት ባለመቻሉ አንድ ዓመት ሰርቶ ሥራውን አቆመ።
የሹፍርና ሥራውን ካቆመ በኋላ በሌላ የንግድ ዘርፍ ገብቶ መሥራት እንዳለበት አስቦ የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ሲያጠና ቆየ። በጊዜው እርሱ ወደ አሶሳ ሲመጣ ከተማዋ ብዙም በንግድ ያልተነቃቃች መሆኗን በመገንዘቡ ከተሳካለት በንግዱ ውስጥ ገብቶ ሊቀጥል ካልተሳካለት ደግሞ ንግዱን አቁሞ ወደሀገሩ ለመመለስ ወሰነ።
ቀደም ሲል የመከላከያ ሰራዊት አባል እያለ ለቴክኒክና ሙያ ሥራዎች ጥልቅ ፍላጎት ነበረው አቶ ደምሴ፤ ወደ መከላከያ ሰራዊት ጋራዥ በተደጋጋሚ በመሄድ የሜካኒክነት ሙያን ይመለከት ነበር። ምንም እንኳን የብረታ ብረት ሥራ ዕውቀቱ እንደሌለው ቢያውቅም የቴክኒክና ሙያ ሥራ ፍላጎቱን ለማርካት ሲል በቅድሚያ በሰው ቤት ውስጥ ገብቶ እጁን አፍታታ።
በጊዜው በከተማዋ በነበሩ አነስተኛ የብረታ ብረት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥሮ በመሥራት ሙያውን ቀሰመ። በሂደትም ራሱን ችሎ በዚህ ሙያ መሥራት እንደሚችል ሲያረጋግጥ የራሱን ብረታ ብረት ድርጅት መክፈት እንዳለበት አመነ።
በ2005 ዓ.ም መሥሪያ ቦታ ተከራይቶ አነስተኛ የብረታ ብረት ሥራዎችን ጀመረ። በጊዜው ሥራውን ሲጀምር በ1 ሺህ 500 ብር ሲሆን አብዛኛውን ሥራዎችንም የሚያከናውነው በራሱ ነበር።
ሥራውን ሲጀምር ለከተማው እንግዳ በመሆኑና ሥራውን እስኪያስተዋወቅ ድረስ ጥቂት የተቸገረ ቢሆንም ችግሮቹን ግን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር አንገቱን ደፍቶ መሥራቱን ቀጠለ። እያደር በሚሠራቸው ግሩምና ጠንካራ የብረታብረት ሥራዎችም የአካባቢውን ሰዎች ቀልብ መሳብ ጀመረ።
በርካቶችም ወደርሱ በመምጣት የተለያዩ ሥራዎችን ያሠሩት ጀመር። በሥራው ረክተውም ‹‹በርታ ዕደግ›› አሉት። እርሱም ከደምበኞቹ ባገኘው ተቀባይነት ሳያኩራራና ለትርፍ ሳይጓጓ ሥራውን ዝቅ ብሎ መሥራቱን ቀጠለ። በትንሹ የጀመረው የብረታብረት ሥራ ይህን ያህል በደምበኞች ተፈላጊነት ካተረፈለት በጥንካሬ ብዙ መሥራት እንዳለበትም ተገነዘበ።
እርሱ በያጅ እርሱ ቆራጭ ሆኖ ያስጀመረው የብረታ ብረት ድርጅቱ በሂደት ሌሎች ሙያውን የሚፈልጉ ወጣቶችን እያሳተፈ መጣ። በእርሱ ድርጅት እጃቸውን ያፍታቱ ወጣቶችም ሙያውን ለምደው የራሳቸውን ብረታ ብረት ድርጅት ለመክፈት በቁ።
እርሱ ሙያውን ለማወቅ ሲል የከፈለውን መስዋትነት ጠንቅቆ ስለሚያቅም አብዛኛዎቹን ወጣቶች በእርሱ ድርጅት ውስጥ በነፃ አለማምዷል። አሁንም አብረውት የሚሠሩ ወጣቶች አሉ።
በትንሽ ካፒታል የብረታ ብረት ሥራን የጀመረው የአቶ ደምሴ ድርጅት በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ከራሱ አልፎ በሥሩ ሦስት ሰራተኞችንም ቀጥሮ ያስተዳድራል። የሥራ መንቀሳቀሻ መኪናም ገዝቷል።
በአሶሳ ከተማም ቤትና ሌሎች ንብረቶችንም አፍርቷል። የቤት በርና መስኮቶችን፣ የብረት አልጋዎችንና ሼልፎችን ጨምሮ አጠቃላይ የብረታ ብረት ሥራዎችንም ያከናውናል። የአብዛኛው ደምብኛ ጥያቄም ጥራት በመሆኑ በተለይ በርና መስኮቶችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ሠርቶ በጊዜው ያስረክባል።
ገና የብረታ ብረት ሥራውን ሲጀምር በርካታ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር የሚያስታውሰው አቶ ደምሴ፤ እነዚህን ፈተናዎች በፅናት በማለፍ ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ይመሰክራል። የኮቪድ 19 ተፅእኖ እንዳለ ሆኖ የብረት ዋጋ መጨመር ሀገር አቀፋዊ ችግር ቢሆንም ችግሩ የእርሱን ድርጅትም ደጃፍ እንዳንኳኳ አይሸሽግም።
በዚሁ የብረት እጥረት ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት መቸገሩንም ይጠቁማል። በዚህም ምክንያት የብረት ሥራው መጠነኛ መቀዛቀዝ ማሳየቱን ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ የህብረተሰቡ የማሠራት አቅም ማነስ እንዳለ ሆኖ የብረታ ብረት ሥራ ገበያው አሁንም እንዳለ ይናገራል።
ሥራው ከዚህም በላይ ከተሠራበት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ይጠቁማል። ጥቂት የማይባሉ ደምበኞች አሁንም ወደ እርሱ ድርጅት በመምጣት የተለያዩ የብረት ምርቶችን የሚያሠሩ እንዳሉም ይጠቅሳል። ለዚህም የሥራዎቹ ጥራት፣ ታማኝነቱና ሥራዎቹንም በጊዜ ማድረሱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተለት ይገልፃል።
በቀጣይም አቶ ደምሴ ከብረታ ብረት ሥራው በዘለለ በንግዱ ውስጥ በመሳተፍ በተለይ ደግሞ ብረት ነክ የሆኑ ምርቶችንና የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት በአገር ውስጥ የማከፋፈል ሃሳብ እንዳለው ይጠቁማል። የብረታ ብረት ድርጅቱን አስፍቶ ከዚህ በተሻለ የመሥራት እቅድ እንዳለውም ይጠቅሳል።
ለጊዜው ለመሥሪያ ቦታ ኪራይ 2 ሺህ ብር እየከፈለ እንደሚሠራም ጠቁሞ፤ በቀጣይ ግን ከቻለ በራሱ አቅም የራሱን ቦታ ገዝቶ ለመሥራት፤ ካልተቻለ ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩ የመሥሪያ ቦታ ጠይቆ የብረታ ብረት ሥራውን አስፍቶ የመሥራት ውጥን እንዳለውም ይጠቁማል።
ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ አሶሳ ላይ ከትሞ ከትንሽ የብረታ ብረት ሥራ ወደ መካከለኛ ደረጃ ላይ የተሸጋገረው ብረቱ ሰው በዚህችው ከተማ ትዳር መስርቶና ሁለት ልጆችንም አፍርቶ እንደሚኖርና እስካሁን ድረስ በሥራው ውጤታማ መሆኑን ይናገራል። በሥራውም ከፍተኛ እርካታ እንዳለው ይገልፃል።
ሥራን ሳይንቅ ዝቅ ብሎ በመሥራቱና ለደምበኞቹም ከፍተኛ ከበሬታ ያለው በመሆኑ ለዚህ ውጤት እንደበቃም ይመሰክራል። ሥራውን ሲጀምር ከጎኑ ሆነው ያበረታቱት ቤተሰቦቹና የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችም እዚህ ደረጃ ለመድረሱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱም ያስረዳል።
ከተማዋ ማንም ሰው መጥቶ ቢሠራባት አመቺና ሰላማዊ ከመሆኗ በርካታ ሥራዎች ሊሰሩባት የሚችሉባት በመሆኑ ሌሎችም መጥተው ቢሠሩባት ውጤታ እንደሚሆኑም ይጠቁማል። በተለይ ደግሞ ወጣቶች ዝቅ ብለውና ሥራን አክብረው ከሠሩ ያሰቡት የስኬት ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉም ይመክራል። በሥራቸው ሂደት ፈተና ቢገጥማቸውም ፈተናዎቹን በመቋቋምና ተስፋ ባለመቁረጥ እስከመጨረሻው ድረስ በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባም መልእክቱን ያስተላልፋል።
እኛም ወጣት ደምሴ ሥራን ሳይንቅ ከትንሽ በመነሳት ከፍ ወዳለው ደረጃ ለመድረስ እያደረገ ያለውን ጥረት እያደነቅን በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም የእርሱን አርያ በመከተልና ሥራን ሳይንቁ በመሥራት ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ እየጠቆምን ዛሬ ነገ ሳይሉ ባሰቡት የሥራ መስክ ውስጥ ገብተው ሊሠሩ ይገባል የዕለቱ መልእክታችን ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013