ጤና አዳም ብዙ የጤና በረከቶች እንዳሉት ሁሉ መጠኑ ሲበዛ ፅንስ እስከማስወረድ የሚደርስ አደገኛነት እንዳለው ያውቃሉ?። በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ጤና አዳም ለሆድ ሕመም፣ ለተቅማጥ፣ ለጆሮ፣ ለልብ ሕመም፣ ለኪንታሮት፣ ለኢንፍልዌንዛና ከአንጀት መታወክ ጋር ለተያያዙ አገልግሎት ላይ ይውላል፤ የደረቀው ፍሬ ከተፈጨ በኋላ ተፈልቶ በመጠጣት ለተቅማጥ ሕክምና ሲውል፣ ቅጠሉ ከተከተከተ በኋላ በውኃ ተደርጎ ለሕፃናት ሆድ ሕመም ይሰጣል፤ ተክሉ ተድጦ ሲልም ደግሞ ለኪንታሮት በሽታ እንደመድሃኒት ይወሰዳል።
በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ አገሮች ደግሞ ከተክሉ ተዘፍዝፎ የሚገኘው ፈሳሽ ለጉንፋን፣ ለጆሮ ሕመምና ለአንጀት መታወክ ይወሰዳል። የጤና አዳም ሽታ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ሰዎች ጊንጦችን ከአካባቢያቸው ለማራቅ ይጠቀሙታል።
በአልጀሪያ ሰዎች ተክሉ ከተዘፈዘፈ በኋላ የሚገኘውን ፈሳሽ በጠብታ መልክ በአፍንጫ ይወስዳሉ፤ በተለይ ለሕፃናት ይህ ሕክምና የሚሰጠው ለሚያስመልስና ትኩሳት ላለበት ነው። በመሆኑም ጤናአዳም እንደ ቀንድ አውጣና ሦሥት አፅቄ ያሉ ነፍሳትን የማራቅ አቅም ስላለው በጓሯችን ቢኖር ተመራጭ ነው፤ ለቁንጫ መድኃኒትም ያገለግላል።
የጤና አዳም የተለያዩ የጤና ጥቅሞች
ጤናአዳም በጡንቻ ላይ የሚያጋጥም ሕመምን፣ ውጥረትንና በወር አበባ ወቅት የሚያጋጥም ሕመምን የማርገብ ሁኔታ ያለው ሲሆን መጠቀም ያለብን ግን የእፅዋት ባለሙያን በማማከር መሆን አለበት።
በሻይ መልክ መጠቀም ለሽንት ቧንቧ፣ ለአንጀትና በአጠቃላይ ለደንዳኔ ኢንፌክሽን መድኃኒት መሆን ይችላል፤ ጤናአዳም ለምግብ መመረዝ በተለይ ደግሞ ሳልሞኔላ የተባለውን ባክቴሪያና ሌሎች አደገኛ ተህዋስያን ሊከላከልልን ይችላል፤ ከዚህ በተጨማሪ ጤናአዳም የፀረ ባክቴሪያ ባሕሪ ስላለው ልንጠቀመው እንችላለን።
ይህ እጽ ነርቮችን የማረጋጋት ኃይል ማለትም የአራጌነት (sedative) ባሕሪ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ፤ በመሆኑም የእንቅልፍ ማጣት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ብንጠቀመው ሊያረጋጋን ይችላል።
ጤና አዳም በአንዳንድ መርዛማ እንስሳት (ለምሳሌ በእባብ) ከተነደፍን ማርከሻ የሚሆንበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ይኸውም የተነደፍነው የነርቭ ስርዓት ላይ እክል በሚፈጥሩ የመርዝ ዓይነቶች ከሆነ ነው። ጤናዳም በአንጓ ላይ የሚያጋጥም ብግነትን ሰከን የማድረግ ኃይል ስላለው ችግሩ ያለበት ሰው አንድ ወይም ሁለት ብርጭቆ በሻይ መልክ ቢጠጣ እፎይታን ሊያገኝ ይችላል።
የጤና አዳም ዘይት በዘመናዊው ዓለም ለሳሙናዎችና ለኮስሞቲክስ ምርቶች ጥሩ መዓዛ ጥቅም ላይ ይውላል፤ ይህ ዘይት መጠኑ ሲበዛ የመርዛማነት ባሕሪ ስላለው በቀጥታ በቆዳ ላይ ጥቅም ላይ አይውልም፤ ነገር ግን ተመጥኖ ለቆዳ የተለያዩ ጥቅሞች እንዳስገኘ ጥናቶች ያሳያሉ፤ ይኸውም የፀረ-ፈንገስ ባህሪ ስላለውና ቆዳን የማጥራት አቅም ስላለው ነው።
የጤና አዳም የጎንዮሽ ጉዳት
ከጤና አዳም የሚወጣው ዘይት በሰውነት ላይ በቀጥታ ከተጠቀምን ሰውነት ውኃ ሊቋጥር እንዲሁም ሊቀላ ይችላል፤ በከፍተኛ መጠን ከተጠቀምነው ደግሞ የሰውነት መመረዝ ሊያስከትል ይችላል፤ በተለይ ደግሞ ፅንስ ያላቸው እናቶች በከፍተኛ መጠን ከተጠቀሙት ፅንሳቸውን ሊያስወርድ ይችላል፤ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የጨጓራ ሕመም ሊያስከትል ይችላል።
በተጨማሪም ከጤና አዳም የሚገኘው ዘይት በብዛት ከተወሰደ ውርጃ ሊያስከትል ይችላል። ይህም በመሆኑ በዘመናዊው ዓለም የጤና አዳም የሕክምና አገልግሎቱ የተገደበ እየሆነ መጥቷል።
ምንጭ፡- ሜዲካል ኤንድ ስፕሪቿል
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013