አስናቀ ፀጋዬ
ሁለቱም የተገኙት በኑሮ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኝ ቤተሰብ ነው ።ድህነት በእጅጉ ቢፈትናቸውም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ዩኒቨርስቲ ከመግባት አላገዳቸውም ።
ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በየመረጡት የትምህርት መስክ ትምህርታቸውን ተከታትለው በጥሩ ውጤት በዲግሪና ዲፕሎማ ተመርቀዋል ።በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ የመስራት እድል ገጥሟቸውም በሙያቸው በተቀጠሩበት መስሪያ ቤቶቻቸው በትጋት አገልግለዋል።
ሁለቱም ድህነትን አብዝተው በመፀየፋቸውና ተቀጥሮ መስራትን በመጥላታቸው ከድህነት ለመላቀቅና በራሳቸው ለመቆም በፈርኒቸር አምራችነትና በደብተር አስመጪነት ሥራ ገብተው ለመስራት ሞክረዋል ።
ሆኖም በዚህ ሥራ ብዙም መግፋት ባለመፈለጋቸውና ከዚህ ይልቅ በሌላ አምራች ዘርፍ ላይ የመሰማራት ፍላጎት በውስጣቸው በማደሩ ስራውን አቆሙ ።
በኑሮ ዝቅተኛ ከሆነ ማህበረሰብ የተፈጠሩ መሆናቸውን ባለመዘንጋትና ድፍረት የታከለበት ውሳኔ በማሳለፍ ከትርፍ በፊት ቅድሚያ ህብረተሰቡን እናገልግል በሚል መርህ ተነሳስተው ከውጪ ሃገር ማሽን በማስመጣት ዳቦ ቤት በአዲስ አበባ ከፍተው መነገድ ጀመሩ ።
ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በአንድ ቅርንጫፍ የጀመሩት የዳቦ ንግድ ዛሬ ላይ ወደ ሁለት ቅርንጫፍ አድጓል። ውጤታማ የዳቦ አምራች ለመሆን በቅተዋል። ለገበያ በሚያቀርቧቸው ጥራት ያላቸው ዳቦዎችም ከደንበኞቻቸው አንቱታንና ምስጋናን አትርፈውላቸዋል- የ‹‹ቤክማ›› ዳቦ መጋገሪያ ባለቤቶችና መስራቾች አቶ ከሳቴብርሃን አርአያና ወይዘሮ እፀገነት ብርሀኑ ።
አቶ ከሳቴብርሃን አርአያ ውልደታቸው ደሴ ቢሆንም እድገታቸው ግን እዚሁ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ መነን አካባቢ ነው ።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ናኩቶለዓብ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከገቡም በኋላም በ1991 ዓ.ም በቢዩልዲንግ ኢንጂነሪንግ አድቫንስድ ዲፕሎማ ከህንፃ ኮሌጅ አግኝተዋል ።
በመቀጠልም በዚሁ ዩኒቨርስቲ በቴክኒካል አሲስታንት አስተማሪነት ተቀጥረው እየሰሩ በማታው የትምህርት መርሃ ግብር በሲቪል ምህንድስና ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸ ውን በ1997 ዓ.ም ተቀብለዋል ።በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ዓመታት ያህል በመምህርነት ከሰሩ በኋላም በገፈርሳ ግድብ ፕሮጀክት ከፈረንሳዮች ጋር በመሆን ለሶስት አመት ተኩል ሰርተዋል ።
በአፍሮ ፂዎን ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥም ለተወሰኑ ጊዜያቶች በሞያቸው አገልግለዋል ።ፈረንሳዮች በሰሩት የአሸጎዳ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይም ተሳትፈዋል ።
በመቀሌ አሸጎዳ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለስድስት ወራት የሰሩት አቶ ከሳቴብርሃን በፕሮፌሽናል የምህንድስና ደረጃ በሳሊኒ በኩል ስራ በማግኘታቸው ወደናይጄሪያ አቀኑ ።ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ናይጄሪያ ሲሄዱም በግዜው ከባለቤታቸው አንድ ልጅ አፍርተው ነበር ።
ባለቤታቸው ወይዘሮ እፀገነት ብርሃኑም ትውልድና እድገታቸው ልክ እንደርሳቸው እዚሁ አዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት ተከታትለዋል ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተምረዋል ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በአልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በመግባት በማኔጅመንት ዲፕሎማቸውን በ2007 ዓ.ም አግኝተዋል ።
ወይዘሮ እፀገነት በተማሩት የማኔጅመንት ትምህርት መስክ በጃምቦ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ለሶስት ዓመታት ተቀጥረው ሰርተዋል ።ኤን ኬ ኤች በሚባል የኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ደግሞ ለአራት አመታት በሙያቸው አገልግለዋል ።ተቀጥሮ መስራት ብዙም ፍላጎት የሌላቸው እኚህ ወይዘሮ የራሳቸውን ቢዝነስ እንደሚጀምሩ ሁሌም በውስጣቸው ሃሳቡ ነበራቸውና ቢዝነሳቸውን ለመጀመርም ዘወትር አዳዲስ እቅዶችን ከማውጣት ተቆጥበው አያውቁም ።
በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካለ ቤተሰብ የተገኙ በመሆናቸውና ድህነትን አብዝተው በመጥላታቸው ድህነትን ለማሸነፍ የራሳቸውን ቢዝነስ የመፍጠሩ ሃሳብ ሁሌም በአእምሯቸው ይመላለሳል ።ባለቤታቸው ወደ ናይጄሪያ ለስራ ካቀኑ በኋላም እስኪመለሱ ድረስ የራሳቸውን ቢዝነስ ለመጀመር የሚያስችሉ ሃሳቦችን ሲያወጡና ሲያወርዱ ቆይተዋል ።ሃሳቡን ወደተግባር ለመለወጥም የቢዝነስ ጥናት አካሂደዋል ።
ባለቤታቸው አቶ ከሳቴብርሃን ወደ ናይጄሪያ ከሄዱ በኋላ በሳሊኒ ለተወሰኑ ወራቶች ሰርተው ሴትራኮ ኮንስትራክሽን በተሰኘ ሌላ መንገድ ገንቢ የናይጄሪያ ኩባንያ ውስጥ በመግባት በሙያቸው ለሰባት አመታት ያህል አገለገሉ ። በናይጄሪያ በነበራቸው የሰባት አመታት ቆይታም ከሙያው ጋር በተገናኘ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ቀሰሙ ።ከተለያዩ ሀገራት ከተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የመስራት አጋጣሚው ተፈጥሮላቸው የነበረ በመሆኑም በራስ መተማመንን አዳበሩ ።
ከቤተሰባቸው ተለይተው ለሰባት አመታት በናይጄሪያ መስራታቸው ቀላል ባይሆንም እርሳቸውም ልክ እንደባለቤታቸው ወይዘሮ እፀገነት ድህነትን ለማሸነፍ ካላቸው ብርቱ ፍላጎት አንፃር ገንዘብ ይዘው ወደሀገራቸው በመመለስ የራሳቸው ቢዝነስ ፈጥረው መስራት እንዳለባቸው የዘወትር ሃሳባቸው ነበር ።በጥንካሬና በፅናት ከቆዩበት ናይጄሪያ ባለቤታቸው ለመጀመር ላሰቡት አዲስ ቢዝነስ ሊበቃ የሚችል ገንዘብ ይዘው ከአራት አመት በፊት ወደሃገራቸው ተመለሱ ።
ወደሀገራቸው ከተመለሱ በኋላም ከባለቤታቸው ጋር ተማክረው በፈርኒቸር ማምረት ስራ ዘርፍ ገብተው ከፓኪስታን ዜጎች ጋር ለመስራት ጥናት ሰርተው አጠናቀቁ ።ጥናታቸውንም ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አቀረቡ ።የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም ጉዳያቸውን ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን መራው ።
ኮሚሽኑም ጥናቱን ተመልክቶ ለስራው ቦታ እንደሚያስፈልግና ቦታው ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ እንደሆነ ነገራቸው ።ወደ ኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ቢያቀኑም በግዜው በክልሉ በነበሩ ተቃውሞዎች ምክንያት ቦታውን ሳያገኙ ቀሩ።
ይህ የቢዝነስ ሀሳብ ሳይሳካ በመቅረቱም ከቻይና ደብተር አስመጥተው ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ ።ቀድሞውኑ በአምራች የስራ ዘርፍ የመሰማራት ሃሳብ የነበራቸው በመሆኑና በዚሁ ስራ ለሌሎች ሰዎች የስራ እድል የመፍጠር ፍላጎት ስላላቸው የአስመጪነት ሥራውን በመተው ወደ ዳቦ ማምረት ስራ ለመግባት ወሰኑ፡፡
ለዚህ የቢዝነስ መስክ የሚረዷቸውን የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ስልጠናዎችንም ወሰዱ ።የዳቦ ማሽኖቹ ከየት እንደሚመጡና አጠቃላይ ቢዝነሱ ምን እንደሚመስልም በቂ ጥናት አደረጉ ።
እነዚህ ጥንዶች የሚፈልጓ ቸውን የዳቦ ማሽኖች ካስጠኑ በኋላ ከቱርክ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በ2011 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ በአዲስ አበባ ሾላ ገበያ አካባቢ ‹‹ቤክማ›› የተሰኘ የዳቦ፣ ኬክና ኩኪስ መጋገሪያ በሶስት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታልና በ 30 ሰራተኞች ከፍተው ስራ ጀመሩ ።በጊዜውም ስራውን ሲጀምሩ ዓላማቸው ከትርፍ ይልቅ ለማህበረሰቡ ዳቦ በማቅረብ ነበር ።
በዳቦ ማምረት ስራ ብዙም ልምድ ያልነበራቸው በመሆኑ ሙሉ ስራውን የሚያከናውንና ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ሊያለማምድ የሚችል አንድ ሶሪያዊ ቀጠሩ ።ከ2 ብር ከ 50 ሳንቲም ጀምሮ ዋጋ ያላቸው ትንንሽ ዳቦዎችን ለህብረተሰቡ ማቅረብም ቀጠሉ ።
በሂደትም የተለያዩ መጠን ያላቸው ዳቦዎችን፣ ኩኪሶችንና ኬኮችን በማምረት ለገበያ ማቅረብ ቻሉ ።ለስድስት ወራት ያህል ከሶሪያዊው ጋር ከሰሩ በኋላ የዳቦ ጋገራውና ማሽኑን የመቆጣጠር ስራው በሌሎች ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በመለመዱ ሶርያውን አሰናብተው በኢትዮጵያውያን ተኩ ።
በአሁኑ ወቅት ዳቦ ማምረቻቸው ተጨማሪ ቅርንጫፍ መገናኛ አካባቢ የከፈተ ሲሆን በልዩ ልዩ መስኮች ለ65 ሰራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩን ይናገራሉ ።በሁለቱ ቅርንጫፎቹም በቀን ከ20 ሺህ በላይ ትንንሽ መጠን ያላቸው ዳቦዎች የማምረት አቅም አለው ።ወቅታዊ ካፒታሉም 10 ሚሊዮን ብር ተጠግቷል ። ዓመታዊ ሽያጩም እስከ 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መድረሱን ባለቤቶቹ ነግረውናል ።ይህ ዓመት ሲጠናቀቅም ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑ እስከ 30 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይጠበቃል ።
ዳቦ ማምረቻቸው ጥራትን ለመጠበቅ ብዙ የሚጨነቅ ሲሆን ዳቦዎችን፣ኬኮችንና ኩኪሶችን በተለያዩ መጠኖችና በተለያያ የዋጋ መጠን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል ።በቅርቡ ‹‹ፈጢራና መለዋ›› የተባሉ ምግቦችን አዘጋጅቶ መሸጥም ጀምሯል ።ለሚያመርታቸው ምርቶችም ጥራቱን የጠበቀ ዱቄት ይጠቀማል ።ምርቶቹንም ሳያቆራርጥ በየእለቱ ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል ።ምርቶቹን ለማምረትም ግምታቸው 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሁለት የዳቦና አንድ የኬክ ማሽኖችን ይጠቀማል፡፡
በዳቦ ማምረት ስራ ከተሰማሩ ሁለት አመት ተኩል የሆናቸው አቶ ከሳቴ ብርሃንና ወይዘሮ እፀገነት በቀጣይ የዳቦ ማምረቻቸውን ከማስፋት በዘለለ ለዳቦ ማምረት ስራ ዋነኛ ግብአት የሆነውን የስንዴ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ወደ ግብርናው ዘርፍ በመግባት ስንዴን በራሳቸው የማምረት እቅድ እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
የግብአቱን ችግር በዚህ መልኩ መቅረፍ ከቻሉም የዳቦ ማምረቻ ቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር በማሳደግና የሰው ኃይላቸውንም በመጨመር ዳቦን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ህብረተሰቡን ይበልጥ የመጥቀም ፍላጎት እንዳላቸውም ይገልፃሉ ።ወደ ክልልም ተጨማሪ ቅርንጫፎችን የማስፋትና አሁን ካሉት በተጨማሪ በቀጣዩ አንድ ዓመት ውስጥ ሁለት የዳቦ ማምረቻ ቅርንጫፎች በአዲስ አበባ የመክፈት ውጥን እንዳላቸውም ይጠቅሳሉ ።
ትርፋማነት በብዙ መንገድ እንደሚገለፅ የሚናገሩት ጥንዶቹ ትርፍ በገንዘብ ብቻ የሚገለፅ እንዳልሆነና ከዚህ ይልቅ ማህበረሰብን ያስቀደመ ቢዝነስ መስራት የኋላ ኋላ ለትርፍ እንደሚያበቃ ይስማማሉ ።
ምርቱን በጥራት ማቅረብና ለዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ዋጋ ማድረስም የእነሱ ትልቁ ትርፍ እንደሆነም ይገልፃሉ ።ለዚህም በሁለቱ ዳቦ ቤቶች በየቀኑ የሚታየው የሰዎች ሰልፍ ቋሚ ምስክር ስለመሆኑና የዳቦ ቤቱ ደንበኞች የአካባቢው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ከሩቅ ቦታዎችም ጭምር የሚመጡ መሆናቸውንም ያስረዳሉ ።
የዳቦ አምራች ኢንዱስትሪው ትልቁ ችግር የስንዴ ግብአት ነው የሚሉት አቶ ከሳቴብርሃን፤ ግብአቱ በቀጥታ ከግብርና ጋር የሚያያዝ በመሆኑ የስንዴ አቅርቦቱን መጨመር ከተቻለ የዳቦ ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የሚቻልበት ሰፊ እድል እንዳለ ይጠቁማሉ ።ለዚህም ግብርናውን በማሳደግና በማዘመን በሀገር ውስጥ ያለውን የስንዴ ምርት አቅርቦት ማሳደግ እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የስንዴ አቅርቦቱን ለማሳደግ በመንግስት በኩል የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም ገና ብዙ መስራት እንደሚጠይቅም ይገልፃሉ ።ዳቦን ለማምረት የሚያስፈልጉና በብዛት ከውጪ ሀገራት የሚገቡ ሌሎች የዘይት፣ እርሾና ስኳር ግብአቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ ።
ወይዘሮ እፀገነትም የባለቤታቸውን ሃሳብ በመጋራት ከስንዴ ባልተናነሰ የዳቦ ምርቶች ላይ ተፅእኖ የሚያሳድሩት እነዚህ ምርቶች በስፋት ተገብቶባቸው ሊሰራባቸው የሚችሉ ዘርፎች መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ ።ምርቶቹን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ማስፋት በተቻለ ቁጥርም ከውጪ የሚገቡትን መቀነስ የሚቻልበት እድል ስለመኖሩም ይጠቅሳሉ ።
ካለፈው ሁለት አመት ተኩል ወዲህ በዳቦ ንግድ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውን የሚገልፁት የ‹‹ቤክማ›› ዳቦ መጋገሪያ ባለቤቶች አቶ ከሳቴ ብርሃንና ወይዘሮ እፀገነት ፤ በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ጠንካራ ስራ መስራታቸውና አሁን ላይ የያዙት መሰረት በቀጣይ ጥሩ ደረጃ የሚያደርሳቸው በመሆኑ ውጤታቸው ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ ።
በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ 65 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውም የውጤታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ይጠቁማሉ ።ሁለቱም በስራ ላይ አንድ አይነት አቋም መያዛቸውና እንደባልና ሚስት እርስ በእርስ ተደጋግፈው ቀን ከሌሊት ጠንክረው መስራታቸው ለተጨማሪ ውጤት እንዳበቃቸውም ይናገራሉ ።ሆኖም ከዚህ የበለጠ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ያምናሉ ።
ልክ እንደነእርሱ ሁሉ ሌሎችም በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን ከፈለጉ ትርፍ ማግኘትን እንደተቀዳሚ ዓላማቸው ሳይቆጥሩ ስራቸውን ወደውት ሊሰሩ እንደሚገባና ስራቸውንም በቁርጠኝነትና በጥራት ማከናወን እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
በተለይ የዳቦ ማምረት ስራ ገና ያልተሰራበትና ሰፊ ገበያ ያለው ከመሆኑ አኳያ ቢዝነሱን በትንሽ ካፒታልና በአነስተኛ የመጋገሪያ ማሽን ጀምረው ከፍ ወዳለው ደረጃ መድረስ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ ።የዚህ ዘርፍ ዋነኛ ግብአት በሆነው የስንዴ ማምረት ስራ ውስጥ ገብተው ቢሰሩም ውጤታማ የመሆን እድል እንዳላቸውም ይጠቅሳሉ ።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013