አስመረት ብስራት
ትመጣለህ ብዬ ስንት የትናንት ሌሊት ስንት የዛሬን ማታ ቁጭ ብዬ አነጋሁ። ትመጣለህ ብዬ በቆምኩበት ቆሜ የተውከኝ ቦታ ላይ ሙጃና ቁጥቋጦ እላዬ ላይ በቅሎ ቆሜ እጠብቃለሁ። ትመጣለህ ብዬ በጨቅላው ዕድሜዬ በሴት ማንነቴ ያ ውዱ ጊዜዬ እንደዋዛ ሲከንፍ ዝም ብዬ እያየሁ። ትመጣለህ ብዬ ትላንትን በማሰብ ዛሬ ላይ ቁጭ ብዬ፤ ነገን በመናፈቅ ፍቅርህን አዝዬ በትዝታህ አለሁ።
ልክ እንደትላንቱ ደጁን እቃኛለሁ። ከፍ ባለው ሰማይ ቀን በጨለመበት አስታውስሃለሁ፤ ጥርት ካለው ሰማይ ከዋክብት ሞልቶበት ናፍቆት ባኮሰሰው በዛለው ጉልበቴም አንተን አስባለሁ። በተቀመጥኩበት ከጉልበቴ አጥፍ፤ አንገቴንም አስግጌ ወደሰማይ እመለከታለሁ። የኮከቡ ቁጥር ሰማይን ሞልቶ ለመቁጠር ቢቸግርም እዚያ ውስጥ ትገኝ እንደሁ ብዬ ባይኔ እማትራለሁ።
ደሞ ወዲያው አይኔም ሰማዩ ላይ ከከዋክብት መካከል እየመላለሰ አንተን ማየት ሲሻ ተፈጥሮ ተፈጥሮ ነውና ድካም ይሰማኛል፤ እንቅልፌ ይመጣል፤ አይኔ ይከደናል።
በጨለማው ክፍል ተጋሎ አካሌ ናፍቆት ይቀጥላል። በሙዚቃው ቃና በአስቴር እንጉርጉሮ የፍቅርህን ሃይል በእጥፍ እያከለ ከአልጋዬ ቀስቅሶ ሰርክ ያኳትነኛል፤ እንቀዋለላለሁ……….ትመጣ እንደው ብዬ። በሌለህበት ባልዋልክበት ቦታ ያለህ ይመስለኛል። ሄጄ እፈልግሃለሁ ማፈቀሬንም ሳላውቅ ማፈቀርህን ሳታውቅ ከሄድንበት ቦታ እመላለሳለሁ።
በመናፈሻው ውስጥ አንተን እያስመሰልኩ ያንተን ምስል ስስል የኔን ጉዳይ ሁሉ ወዲያ ግድም ጥዬ ብቻ አንተን እላለሁ፤ ነፍሴ ይቃትታል በቃ ታምሚያለሁ፤ ባንተ ተይዣለሁ። ፍቅርህ ጤና ነስቶኝ ብቸኛ ሆኛለሁ። ትመጣለህ ብዬ…. ቃልህን አምኜ ቀናቶች ቀን ወልደው አመታት ነጎዱ።
አይገርም እኔ ግን ዛሬም እዛው ነኝ። ቃልህን አምኜ በቃል ፍቅር ገመድ የፊጥኝ ታስሬ በትዝታ ገመድ ለፍቅር መንኜ ትመጣለሁ ብዬ እጠብቅሃለሁ። ትዝ ይልሃል ውዴ? ያኔ በፊት ቀድሞ ፍቅርህን ልትነገርኝ የልቤን ላወራ የተቀጣጠርን ለት ማለዳ ላግኝሽ የምነገርሽ አለኝ ብለህ ስታወጋኝ ተወሰህ ውድዬ?
ያን ዕለት ነው ውዴ የሰውነት ንዳደ ከወስጤ ተነሰቶ፤ ላዬን በላብ ጎርፍ ውስጤን እያጠበው አንሶላው ሲራራስ ከገዛ ገላዬ በፈሰሰው ውሃ። ትዝ ይልሀል ውዴ አይን ለአይን ብቻ ቃል ካፍ ሳይወጣ፤ ብቻ በአይን ወሬ ፍቅርህና ፍቅሬ በአንድ የሆኑበት። ብቻ መቃተቱ ብቻ መተያየት ብቻ መደሰቱ…. ያ ሁሉ መከፋት የዛን ሁሉ ኩርፊያ የእንባና ሳቅ ዓለም በትዝታ ሳጥን ቆልፌ ያኖረኩት ትመጣለህ ብዬ የምጠብቅህ እለት። ሲመሽ እየከፈትኩ የተመለከተኩት።
ቀናት በቀናት ላይ ተነባበሩና መቅረትህ አሰጋኝ። ካይን የራቁ ሁሉ ከልብ ላይ ጠፍቶ አንተጋ ያለውን ልቤ መሄጃ አጥቶ ይሆን ብዬ አሰባለሁ። ሀሳቤም ሲበዛ በንዴት እደብናለሁ። አረርኩኝ፤ ደበነኩኝ ከሰው ተነጥዬ ሰውነቴን ናድኩኝ ……………… ትመጣለህ ብዬ። የፈለኩህ ለታ ጠበቃዬ በዝቶ ፀሃይና ዝናብ ሲፈራረቁብኝ ቀሰ በቀስ አለኩኝ።
ስላንተ በማለም ነገን አሻግሬ ባልቀለስነው ጎጆ ህልሜን ባንተ ስዬ መነንኩኝ በከንቱ ትመጣለህ ብዬ ካድማስ ማዶ ባለው ትዝታ ኮብልዬ አንተኑ እንዳልኩኝ ቀርሁኝ ዋልዬ ……….ትመጣለህ ብዬ። በህልም ዓለም ጎጆ ባንተ እንደ ቆረብኩኝ እልፍ ክረምት ሄዶ ሺ በጋ ደገመኩኝ።
የወቅቱ መቀየር የዝናቡ መምጣት የበረደው መጣል የፀሃዩ መውጣት የመስከረም ጥባት ሁሉም በየተራ ሲፈራረቁብኝ ትመጣለህ ብዬ በጥበቃ ጅራፍ እየተቀጣሁኝ እልፍ ዓመት ጠበኩህ…………ትመጣለህ ብዬ ፍቅርህን አዝዬ።
ቀጥ ያለው አቋሜ፣ ደቡጭ ያለው ጉንጬ፣ አጓጊው ከንፈሬ፣ የደረቴ ኳሶቹ ሁሉም ጥለውኝ ሸሹኝ እነሱም እንደኔ ባንተ ተስፋ ማድረግ ስለሰለቻቸው አበባ ጊዜያቸው ጥሏቸው ሳይነጉድ ሮጠው ሊያባረሩት ከልጅነት ውበት ከልጅነት ወዝ ጋር ጥለውኝ ሄደዋል እኔ ግን ቆሚያለሁ ትመጣለህ ብዬ። ዘንድሮም እንዳምና ፍቅርህን አዝዬ በትዝታ ዝዬ፤ እጠበቅሃለሁ።
ልጅነቴን አጣሁ ለፍቅር ታምኜ አንተን በመጠበቅ በናፍቆት ቆስዬ ትመጣለህ ብዬ ህልሜን ባንተ ስዬ የኔን ህልም አጣሁት እመጣለሁ ብለህ የቀረህብኝ ለት እመጣለሁ ብለህ ባትመጣ አንተዬ። ብትመጣልኝ እያልኩ ዛሬም እጠብቃለሁ አድማስ አሳብሬ አሻግሬ እያየሁ ትመጣለህ ብዬ መች ተስፋ ቆርጣለሁ ጀንበሯን ቀድሜ እጠብቅሃለሁ ትመጣለህ ብዬ ከሸኘሁህ ቦታ ቆሜ እጠብቃለሁ አንተኑ በማለም ብቸኛ ሆኛለሁ ትመጣለህ ብዬ………
የአበባዬ ወራት ልጆች የማፍራዬ ወልዶ መሳሚያዬ ዘርቶ መቃሚያዬ የኔ ምለው ዘመን ተጠናቆብኛል። ትመጣለህ ብዬ ጠብቅኝ ካለከው ቃል የቃልህ እስረኛ ከወይኒህ አዳሪ የገዳም እመቤት ሆኜ መንኛለሁ። ለነፍሴ አላደርኩም ልቤ አንተን ይለኛል በሀሳቤ እልፍኝ ብዙ ፍቅር መሰል የመሽት ቀናትን አሳልፌ ነበር ወይ እንደ ሰዎች ለስጋዬ አዳሬ የተፈጥሮን ህግጋት በላዬ መስካሪ ለሆነ አልታደልኩም ባአንተ አይኔ ታወሮ በቃልህ ደነቁሬ በቃልህ ተለጉሜ እነሆ ጾሚያለሁ ሌላ አላየሁም ትመጣለህ ብዬ።
ልጠይቅ አንተዬ የኔኑ ጥበቃ ሲነጋ ሲመሽም አንተን የማለት ሲቃ ቀልብህ እንዴት ቻለ እንዴት አለነገረህ አንተኑ አንተኑ ሲነጋም ሲመሽም የማንሳቴን ነገረ ስቅታው እንዴት ነው ያለደረሰልኝ በገመድከው ገመድ ባሰርከው ቋጠሮ ተሰነካክዬ ስለመቀመጤ እንዴት አልሰማህም ምን ዘመነ በያበቃ ምን ወራት ብነጉዱ ዛሬም ጠባቂህ ነኝ እጠብቅሃለሁ ትመጣለህ ብዬ አንተኑ አልማለሁ።
ውዴ እልፎቹ ዓመታት በላይ በላያቸው እየተነባበሩ ቁንጅናዬ ጠፍቶ ጉልበቴም ሸሽቶኛል ዛሬም ግን ቆሜያለሁ አንተ የነቃህ ለት እኔን ስታሰበኝ የቆመኩበት ቦታ ዘመኔን ጨርሼ ከጉድጓድ ከገባሁ እንዳትደናገጥ ትንሽ ድካም ቢጤ ስለተሰማኝ ነው ከቆምኩበት ቦታ ትንሽ ሸለብ አርጎኝ የሞትኩ መሰሏቸው ሀውልት ቢሰሩብኝ እኔ አልሞትኩም ውዴ እየጠበኩህ ነው ትመጣለህ ብዬ አልጋውን አንጥፌ ቤቱን ጠራርጌ አበባ ይዘህ ና አበባ ወዳለሁ እጠብቅሃለሁ በቁሜም አያለሁ ካነቀላፋሁ ወዲያ እስከዛኛው ዓለም ሌላ ሰው አላይም እጠብቅሃለሁ ትመጣለህ ብዬ እስከ መቃብሬ…………………።
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013