ራስወርቅ ሙሉጌታ
በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት አይዟችሁ ባይ ተቀባይ ካላገኙ መጨረሻቸው ለጎዳና ህይወት መዳረግ ይሆናል። ይህ ዕድል ያልገጠማቸው ከዘመድ አዝማድና ከወላጅ ጋር የመጠጋት ዕድሉን የሚያገኙ ቢኖሩም ለጉልበት ብዝበዛና ለተለያዩ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳቶች መዳረጋቸው አይቀርም። እነዚህን ሕፃናት ለመታደግ በመንግሥት የሚሠሩ በርከት ያሉ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም።
በሌላ በኩል አንዳንድ ከምንም በመነሳት የሰው ችግር የሚቸግራቸው፣ የሰው ጭንቀት የሚጨንቃቸውና ራሳቸውን በመሰዋትና ለሌሎች በመኖር በርካቶችን ለመታደግ የሚበቁ ግለሰቦችም አሉ።
የዛሬ የምግባረ ሰናይ እንግዳችንም ላለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት የእናት ምትክ ለመሆን ማህበር በማቋቋም በርካቶችን ከከፋ ህይወት በመታደግ ለቁም ነገር ያበቁ እናት ናቸው። የዘውዲቱ መሸሻ የሕፃናትና ቤተሰብ መርጃ ማህበር የአስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ የሆኑት ቀሲስ አበባየሁ ፍቃዱ ስለማህበሩ መስራች እናት ህይወትና ማህበሩ አሁን ያለበትን ሁኔታ አስመልክተው የሚከተለውን አጋርተውናል።
ወይዘሮ ዘውዲቱ መሸሻ ይባላሉ፤ የተወለዱት በ1934 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ መንዝ ላሎ ምድር ልዩ ቦታው አባ ሺኖዳ የሚባል አካባቢ ነው። ወይዘሮ ዘውዲቱ በሰፊ ቤተሰብ ወስጥ ያደጉና በዘመናዊ ትምህርት ብዙ ባይገፉም በዘመኑ ፊደል ቆጥረው ዳዊት ለመድገም የበቁ ብለውም ከዓመታት በኋላ ዓይናቸውን ለመታከም ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን የእጅ ሞያ በመማር ተመርቀው የምስክር ወረቀት የተቀበሉ እናት ናቸው።
በልጅነታቸው ኃይለኛ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ያደጉት በዘመድ አዝማድ ተከበው ብዙ ቤተሰብ ባለው ቤት ውስጥ ነበር። ዕድሚያቸው ለአቅመ ሄዋን ሲደርስም በወግ በማዕረግ ትዳር መስርተዋል።
የአብራካቸው ክፋይ የሆነች አንዲት ሴት ልጅ ብቻ ያለቻቸው ሲሆን፤ እሷኑ ሲወልዱ ትልቅ ፈተና ገጥሟቸው ነበር። ችግሩ ደግሞ እንኳን ለዚያን ዘመን አሁንም ድረስ ብዙዎችን የሚያስፈራው ብዙዎችን እንቅልፍ የሚነሳው የካንሰር ህመም ነበር። የተወሰነ ጊዜ በዘመናዊ ህክምና መፍትሔ ሊያገኙለት ደፋ ቀና ሲሉ ከቆዩ በኋላ ችግሩ ስር እየሰደደ በመምጣቱ ለጸበል ወደ አርሲ አካበቢ ያቀናሉ።
እዚያም እያሉ በ1984 ዓ.ም የደርግ መንግሥት መውደቅንና የኢህአዲግ መንግሥት መተካትን ተከትሎ አርሲ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በድንኳን የሚኖሩበትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመመልከት ይበቃሉ። እናም እሳቸው የነበሩበት ቦታ የነበሩትን ሃያ ስድስት ሕፃናትና ሰባት አባወራዎችን የበላሁትን በልታችሁ የጠጣሁትን ጠጥታችሁ እስከቻልኩት አበረን እንኖራለን ብለው ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው ይመጡና አዲሱ ገበያ አካባቢ የነበረው በኪራይ ቤቶች ስር የነበረው ሰፊ ግቢ ያለው ቤታቸው ውስጥ ማኖር ይጀምራሉ።
አባወራዎቹ ሠርቶ ማሳደር የሚያስችል ጉልበት እያላቸው ዘወትር ጥገኛ ሆነው መኖር የለባቸውም በማለት የመቋቋሚያ ገንዘብ እንዲሰጣቸቸው በማድረግ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ። ሕፃናቶቹ ግን ትምህርት ጀምረው ስለነበር ከእርሳቸው ጋር እንዲቀሩ በማ ድረግ ማኖር ይጀምራሉ።
ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሲመጡም በአንድ በኩል ወይዘሮ ዘውዲቱ ለራሳቸው ህመም ፈውስ ፍለጋ በየጸበሉ ሲሄዱ ያገኟቸውን ወላጅ አልባ ሕፃናት ሲያመጡ። በሌላ በኩል ደግሞ ወይዘሮ ዘውዲቱ ወላጅ አልባ ታሳድጋለች የቸገረውን ታስጠጋለች እየተባለ በመወራቱ ወደሳቸው ቤት የሚመጣው ተደጋፊ ቁጥር እየጨመረ ይመጣና በግቢያቸው ያሉት ሕፃናት ቁጥር ሁለት መቶ ሃምሳ ይደርሳል።
በተለያየ መልኩ በቅርብ የሚያውቋቸው ዘመድ አዝማድ ይበቃሻል ከዚህ በኋላ ራስሽን መጠበቅ አለብሽ ከፈለገ ልጆቹን መንግሥት ይንከባከብ የሚል ምክር በተደጋጋሚ ቢቀርብላቸውም እሳቸው ግን የጀመሩትን ለማቋረጥ ፈቃደኛ አልነበሩም። ምክንያታቸው ደግሞ ከነበረበኝ ህመም በሙሉ የዳንኩት እነሱን መንከባከብ ከጀመርኩ በኋላ ነው፤ ይህ ሥራ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለኔም ደህንነት ነው በማለት ይቀበሉታል። ከቅርብ ዘመዶቻቸው አንዲህ ዓይነት ምክር የሚሰጣቸው ቢሆንም ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ግን የሃሳባቸው ደጋፊ ብቻ ሳይሆን የሥራቸውም ሁሉ ተባባሪ ነበሩ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበሩበት ቤት የሰፈረበት ቦታ ቀለበት መንገድ የሚያልፍበት በመሆኑ በከፊል እንዲፈርስ ይደረጋል። በወቅቱ ምንም ማካካሻ ያልተደረገላቸው ቢሆንም የተረፋቸውን ቦታ በመጠቀምና ቤቶቹን በመጠጋገን ሥራቸውን ይቀጥላሉ። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ቦታው ለልማቱ ስለሚያስፈልግ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሱ ይደረጋል። በወቅቱ መንግሥት ምንም ምትክ ቤት ያልሰጣቸው በመሆኑ ያላቸውን ሀብት በሙሉ በመሸጥ ጥሪታቸው ተሟጦ እስኪያልቅ ድረስ ለአንድ ዓመት ያህል የነበሩትን ልጆች በልጃቸውና በባለቤታቸው ድጋፍ በኪራይ ቤት ይዘው ይቆያሉ። ነገር ግን የነበረው የኑሮ ውድነት እንዲሁም የቤት ኪራይ መጨመር ከዚያ በላይ ለመቀጠል የሚፈቅድላቸው አልሆነም።
በመሆኑም እነዚህን ልጆች ለማሳደግ የራሳቸውን ቤት እንዲሁም ሁለት መኪናዎቻቸውን ለመሸጥም ተዳርገው ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም አከራዮቹ የተለያዩ ምክንያቶችን በማንሳት እንዲለቁ ሲያደርጓቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ያላሰቡት ችግር ስለገጠማቸው በጣም በማዘን ልጆቻቸው ተበትነው ወደ ጎዳና ሲወድቁ ማየት ስላላስቻላቸው ወደ ዝቋላ ገዳም በመግባት መኖር ይጀምራሉ። በወቅቱ የሚሠሩት ሥራ እየታወቀ ቤታቸው ሲፈርስ ምትክ ቤት ስላልተሰጣቸው በሌላ በኩል በተገቢው መንገድ ስላላስተናገዷቸው መንግሥት በሠራው ሥራ እጅግ ተከፍተውም አዝነውም ነበር ወደ ገዳም ያቀኑት።
ከዚህ በኋላ ከዚህ ቀደም ወይዘሮ ዘውዲቱ ለአንድ መነኩሴ ከገበሬ ማህበር የገዙላቸው ቤት ነበር እናም ይህ አባት ከዚህ በላይ ምን ችግር ይመጣል ይህንን ቤት መልሰው ወስደው ልጆቹን ይዘውበት ይቀመጡ የሚል ሃሳብ ያመጣሉ። በዚህም መሰረት ለረጅም ዓመት አብረዋቸው የሠሩትና የቦርድ አባላት የነበሩ ወዳጆቻቻው የእየሩሳሌም ድርጅት ባለቤት አቶ ሙሉጌታን ጨምሮ ዝቋላ አቦ ድረስ በመሄድና በመለመን እንዲመለሱ ሃሳብ ያቀርቡላቸዋል። እሳቸውም የቀረበላቸውን ሃሳብ ተቀብለው በ2001 መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቦታው ላይ ጊዜያዊ የቆርቆሮ ቤት በመቀለስ የተበተኑ ልጆቻቸውን ሰብስበው ሥራቸውን ለመቀጠል ይበቃሉ። ኮተቤ አካባቢ የነበረው የራሳቸው ቤት ውስጥ ከዓመት በፊት በደረሰበት የእሳት አደጋ ለከፍተኛ ጉዳት ለመዳረግ ይበቃል።
በዚህ ወቅት ነበር የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በሀገሪቱም ለውጥ መጥቶ ስለነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እቤታቸው ድረስ በመሄድና በማፅናናት አንዳንድ ደጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል የገቡላቸው። በወቅቱ ወይዘሮ ዘውዲቱ «ከሚያፈናቅል መንግሥት አልፈን ለመደገፍ እቤት ድረስ አንኳኩቶ የሚመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር በማየቴ ደስታዬ ወደር የለውም» ብለው ነበር። ከዚህ በኋላ ነበር በቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በኩል በ2012 ዓ.ም እስከአሁን ለሠሩት በጎ ሥራ እውቅና ለመስጠት አሁን ያሉበት አንድ መቶ ሕፃናትን መያዝ የሚችለው ከአስራ ሁለት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና ስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የሕፃናት ማሳደጊያ ሕንፃ ተገንብቶ የተበረከተላቸው።
ይህም ሆኖ በእንጠጦ ፓርክ ስር የተገነባው «የቁስቋም ብርሃን የሕፃናት ማዕከል» የሚገባውን ያህል እየሠራ አይደለም፤ ምክንያቱ ደግሞ የፋይናንስ ምንጩ የተቀዛቀዘ በመሆኑ ነው። ማህበሩ አንድ መቶ ሕፃናትን ለማሳደግ የሚበቃ ሕንፃ ገንብቶ ቢያስረክብም ለዚህ ያህል ወጪ ባለመኖሩ በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ያሉት ሕፃናት ቁጥር ሃምሳ አራት ብቻ ናቸው።
የእዚህም ደጋፍ የሚገኘው በቋሚነት ፊናዶ የሚባል መሰረቱን ቤልጄም ያደረገ በጎ አደራጊ ድርጅት ለሃያ ሁለት ልጆች በወር ከሚያስፈልጋቸው አንድ አራተኛውን ከሚያደርገው ደጋፍ ውጪ አንዳደንድ ለጉብኝት የሚመጡ በጎ አድራጊዎች የሚሰጡት ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት በወር በእያንዳንዳቸው ሁለት ሺህ አራት መቶ ብር ደጋፍ የሚያደርግላቸው በመታጣቱ አርባ ስደስት አልጋ ባዶውን ተቀምጧል። ለልጆች የወር ወጪን በተመለከተ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት የተቀመጡ የትምህርት የጤናና ሌሎች ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ መስፈርቶች በመኖራቸው ከዚህ በታች ብር ቢገኝም ልጆችን ለመቀበል ያስቸግራል።
በመሆኑም አንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ለአንድ ሕፃን የሚል ፕሮጀከት ተቀርጾ በማህበራት መንግሥት መስሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች በዓላትን በተቋሙ እንዲያከብሩም በማድረግ የተደጋፊዎችን ቁጥር ለማሳደግ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ተቋሙ በመንግሥት የተደረገለት ከፍተኛ ድጋፍ ቢሆንም በግቢው አንዳንድ ግንባታዎች ይቀራሉ የሚሉት ቀሲስ አበባየሁ የዕቃ መጋዘን ለሠራተኞች መጸዳጃ ቤትና የእቃ ማስቀመጫ መጋዘንና በግቢው ለወይዘሮ ዘውዲቱ መኖሪያ ቤት አለመኖር ቀዳሚ ችግሮች መሆናቸውን ይናገራሉ።
በተጨማሪ ተቋሙ ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ የሌለው በመሆኑ ለቀለብ ግዢ፤ ልጆች ሲታመሙ ሆስፒታል ለማድረስና ለተመሳሳይ ጉዳዮች በጣም መቸገራቸውንና ከፍተኛ ወጪ እያወጡም መሆኑን በመጠቆም የድጋፍ አድራጊዎችን በጎነት እየጠበቁ መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህ በኩል ድጋፍ ለማድረግ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ለበጎ አድራጎት ማህበራት ኤጀንሲ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት ባለሙያዎች መጥተው ጥናት አድርገው ከሄዱ በኋላ ድጋፉ እንደሚያስፈልግና እንደሚሰጥ ያረጋገጡ ቢሆንም እስከአሁን የተገኘ ነገር የለም።
በዘላቂነት ግን ድርጅቱ የሰው እጅ ከመጠበቅ የራሱን የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ለመሥራት የወፍጮ ቤት፤ የዳቦ ቤት፤ የንብ ማነብና ከብት እርባታ ለማከናወን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በቦርድ አባላቱ ቀርጾ ገቢ ለማሰባሰብ መንቀሳቀስ ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል። በተለይ ፕሮጀክቱ ከውጭ ገቢ ማስገኘትን ብቻ ትኩረት ያደረገ ሳይሆን የሚያመርታቸው ግብአት በቀዳሚነት በድርጅቱ ላሉ ሕፃናት የዕለት ከዕለት ፍላጎት የሚቀርቡ በመሆናቸው አዋጭም ተመራጭም እንደሚሆን ተናግረዋል።
በተቋሙ ያለውንም ሥራ እየሠሩ ካሉት አስራ አራት ሠራተኞች አብዛኛዎቹ እዚያው ያደጉና በትንሽ ክፍያ ለማገልገል በሚል እየሠሩ ያሉ ናቸው። ወይዘሮ ዘውዲቱ ከሰው ጋር ፈጥኖ የመግባባት በተወሳሰቡ ጉዳዮች ውስጥ ሆነው ተረጋግቶ የመወሰን ከፍተኛ የማስተዳደር ብቃት ያላቸው ሲሆን፤ ሁሉንም ልጆቻቸውን ይንከባከቡና ያሳድጉ የነበረው እንደ እናት በመምከርና በመገሰፅ ነበር። ይህንንም በማድረጋቸው ባለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት አርባ ስምንት ልጆችን ከሰርተፍኬት እስከ ማስትሬት ድግሪ ለማስመረቅ የበቁ ሲሆን፤ ሃያ አንድ ልጆችንም በሀገር ባህል መሰረት ሽማግሌ ተልኮባቸው ተቀብለው በመፍቀድ ሦስት ጉልቻ እንዲመሰርቱ አብቅተዋል።
በየአጋጣሚው ለተቸገረ ሁሉ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባለፈ በተለያዩ ጊዜያት ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ ልጆችን ባሉበት በቤተሰብና በዘመድ እጅ ሆነው ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ በማድረግ ለቁም ነገር እንዲበቁ አድርገዋል። ወይዘሮ ዘውዲቱ የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ በርካታ የእውቅና ሰርተፍኬቶችንም ለማግኘት በቅተዋል። ምንም እንኳን በልጅነታቸው ኃይለኛና ቁጡ የነበሩ ቢሆንም ዛሬ ፍጹም ታጋሽና እርጋታ የተሞላባቸው ነገሮችን ሁሉ በአስተውሎት የሚመረምሩ እናት ለመሆን በቅተዋል። በአሁኑ ወቅት በኮተቤ ግቢ የቀሩ የሁለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ተማሪ ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013