አስመረት ብስራት
በልጆች የስብዕና መደበር ላይ ብዙ ነገሮች ተፅዕኖ ያሳድራሉ። የልጆች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ነገሮች መካከል የዘር ውርስ፣ አካባቢ፣ የወሊድ ቅደም ተከተል፣ የስርዓተ-ፆታ ህግጋት፣ ዕድሜ ወዘተ ናቸው።
የዘር ውርስ፡- ወላጆች ስነህይታዊ በሆነ መንገድ ያለቸውን ባህሪያት፣ ስብዕና ለሚወልዷቸው ልጆች ያስተላልፋሉ። የስነ ህይወትና የስነልቦና ባለሙያዎች በጥናት እንዳረጋገጡት ከሆነ አንዳንድ የልጆች ስብዕና ከወላጆቻቸው የወረሷቸው ናቸው።
የዘር ውርስ በልጆች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም ብቸኛ ግን አይደለም። ሌሎች አካባቢያዊ ምክኒያቶችም ጉልህ ተፅዕኖ አላቸው። ለምሳሌ ወሳኝ በሆኑ የልጅነት ወቅቶች ላይ ያጋጠሙ ነገሮች ለምሳሌ በሞት ወላጆችን ማጣት፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት እና ሌሎችም በልጆች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። የልጆች ስብዕና ስነ ህይወታዊ በሆኑ እንደ የዘር ውርስ እና አካባቢያዊ በሆኑ ምክኒያቶች ይገነባል ማለት ነው።
ወላጆችና አሳዳጊዎች ይበልጥ ትዕግስተኛ በመሆን፣ መረዳትና እንክብካቤን በተለይም መጥፎ የህይወት ገጠመኞች ለደረሰባቸው ልጆች ሊያደርጉ ይገባል። በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና የትምህርት ዝቅተኛነት ምክንያት ለአንዳንድ ወላጆች ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ቢቸገሩም ጉልህ ለውጦችን ወይም ያልተለመዱ ባህሪያቶች በልጆች ላይ ሲያስተውሉ ለምሳሌ ስሜታዊ ለውጥ (በጣም መከፋትና መደበት፣ መደበር፣ ትካዜ ወዘተ) ለሌሎች ባለሙያዎችና መምህራን ጉዳዩን በማማከር ዕርዳታና እገዛን ማግኘት ይኖርባቸዋል።
አካባቢ፡- ልጆች የሚኖሩበት፣ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ለምሳሌ ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ጎረቤት የመጫወቻ ቦታዎች የመሳሰሉት እና የበፊት ልምድ በስብዕናቸው ላይ ተፅዕኖ አላቸው። በቤት ወይም በቤተሰብ ውስጥ ያላቸው ልምድ በልጆች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ምክንያት ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቦታ ስለሆነና የአሳዳጊዎቻቸው አስተሳሰብ፣ ባህሪ፣ አመለካከትና እምነት ቀጥተኛ ተፅዕኖ በስብዕናቸው ላይ ያሳድራል። ለምሳሌ በአሉታዊና በመጥፎ ነገሮች የተሞላ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ደስተኛ ልጆች ወደ ተስፋ መቁረጥ ሊሰማቸው ይችላል። በጥፋትና በቁጣ የተሞላ ቤት ውስጥ ያሉ ልጆች ፈሪና ተናዳጅ ሊሆኑ ይችላሉ።
የወሊድ ቅደም ተከተል፡- ወላጆች ለታላላቅ ልጆችና ለታናናሾች ያላቸው አቀባበልና የሚያደርጉት የተለያየ እንክብካቤና አያያዝ በስብዕናቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል::
የስርዓተ ፆታ ህግጋት፡- ከወንድና ከሴት ልጆች ወላጆችና ማህበረሰቡ የደነገጋቸውና እንዲተገበሩ የሚጠበቁ የተለያዩ ባህሪያት በልጆች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።ለምሳሌ፡-
• ሴት ልጆች ዝምተኛና አንገታቸው የደፉ መሆን አለባቸው!
• ሴት ልጆች በወላጆቻቸው የታዘዙትን ነገር ያለምንም ጥያቄ መፈፀም አለባቸው!
• ማልቀስ ከወንድ ልጅ አይጠበቅም (ምንድን ነው እንደሴት ማለቃቀስ/መነፋረቅ)!
• ወንዶች በጣም ጠንካራና ጉለበታም መሆን አለባቸው (እንደሴት ልፍስፍስ መሆን ከወንዶች አይጠበቅም)!
የልጆች ባህሪያት ወላጆች በሚጠብቋቸው ነገሮች አንፃር ይገነባል ማለት ነው።
ዕድሜ፡- የልጆች ስብዕና እንደየዕድሜ ደረጃቸውና ብስለታቸው እያደገ ይሄዳል።
ወላጆች ይህንን በመረዳት የልጆቻቸው ስብእና ግንበታ ላይ የራሳቸውን መሰመር እያሰመሩ መሄድ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013