አስመረት ብስራት
ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ልጆች በራሳቸው በርካታ ነገሮችን መሥራት እንደሚችሉ የሚያሳይ አንድ ልጅ ለዛሬ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። ልጆች ዓላማችሁን ተከትላችሁ ለስኬታችሁ የሚረዳችሁን ጥረት ካደረጋችሁ የምትፈልጉትን ነገር መሆን እንደምትችሉ ሮቤል ማሳያ ይሆናችኋል።
ሕፃን ሮቤል በአምላክ በፈረንሳይ ለጋሲዮን የሞንቶሶሪያል ትምህርት ቤት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎችን በማንሳትና ለእያንዳንዱ የተፈጥሮ ሁኔታዎችና ፍልስፍናዎች በቂ ማብራሪያ በመስጠት ይታወቃል። ይህ ልጅ ብዙ ነገር አንብቦ ከትልልቅ ሰዎች የበለጠ ግንዛቤን ስላዳበረ ብዙ ሰዎች በአድናቆት ሲመለከቱት ይታያል።
ከዚህም በተጨማሪ ስለ ስፔስ ሳይንስ ወይም ስለ ስነህዋ ሳይንስ ያለውን እውቀት ከበቂ ገለፃ ጋር በማቅረብ ከመጋቢ ሀዲስ ሮዳስ ጋር በመሆን በጄቲቪ ኢትዮጵያ ላይ ቀርቦ የተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች እየተቀባበሉት የዘመናችን አነጋጋሪ ሕፃን በማለት ብዙ ሰዎች ሲያደንቁትም ታይቷል።
ይህ ልጅ በተፈጥሯዊ ችሎታውና ብቃቱ የተለያዩ ሽልማቶችንም አግኝቷል። በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሕፃን ሮቤልንና ሌሎች መሰል ተሰጥኦና እውቀት ያላቸውን ሕፃናት በተለየ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ እየተማሩ ባላቸው ልዩ የአስተሳሰብ ፍጥነትና እውቀት ሀገራቸውን መጥቀም እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው።
ስለልጁ የሚማርበት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን ነጋሽ ሲናገሩ ሕፃን ሮቤል ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ 1ኛ የሚወጣ ተማሪ መሆኑን ገልጸው ሕፃን ሮቤል ልዩ ጥበቃ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል ብለዋል። አይገርምም ልጆች! ይህ ልጅ በመምህራኖቹም ሆነ በወላጆቹ ስለ ጉብዝናው የተመሰከረለት ነው። እናንተስ እንደ እሱ መሆን አላማራችሁም?
ሕፃን ሮቤል ስለህብረ ከዋክብት ትንታኔ መስጠት የሚያስችል አቅም ያለው፣ ህይወቱን ሙሉ ስለከዋክብት ሲያጠና መኖር የሚመኝ፣ ለዚያውም ለምኞቱ መሳካት ሌት ከቀን የሚተጋ ጠንካራ ልጅ ነው።
በእኛ በትላልቆቹ አዕምሮ ለመገንዘብ የሚከብዱ የምርምሮ ሃሳቦችን በተገቢው ተረድቶ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች ማብራሪያ ሲሰጥ መመልከት በጣም ልብን በደስታ የሚሞላ ነው። በጥቅሉ ሮቤል ሀገር በቀል እውቀትን ከዓለማዊ እውቀት ጋር አቆራኝቶ በንጽጽር የያዘ ሕፃን ነው።
ይህ ልጅ በሚሰጣቸው ገለፃዎች ወደ ራሳችን ወደ ማንነታችን እንድንመለከት ያስተላለፈው መልዕክት በጣም ትልቅ መሆኑን በርካታ ትልልቅ ሰዎች ይናገሩለታል። በተለይ በተለይ ልጅ አስተዳደግ እንዴት መሆን እንዳለበት ከሮቤል ወዲያ ምስክር አለመኖሩ ነው የሚነገርለት።
ወላጆችም ልጆች ያላቸውን ልዩ ተሰጥኦ በመረዳት ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ሀገራችን እንደ ሮቤል ዓይነት በርከታ አስደናቂ ተፈጥሮ ያላቸውን ልጆች ሊያገኙ ይችላሉ።
እናንተም ጎብዙና ራእያችሁን ተከተሉ። ልጆች እወዳችኋለሁ። ቻው።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013