(ክፍል 2)
አይን አፋር ልጆች፡- እነዚህ ልጆች በጣም ስሜታዊነት የሚሰማቸው ናቸው። በዚህም ምክንያት ከሰዎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ፍርሃት ይሰማቸዋል። ሌሎችን ሰዎች የሚጠራጠሩና እምነት የሌላቸው ናቸው። ምናልባት ባለፈው ህይወታቸው ከሰዎች ጋር የነበራቸዉ ግንኙነት በመበላሸቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በቀላሉ አዳዲስ ነገሮችንና ቦታዎችን ለማወቅና ለመላመድ ፍላጎት የላቸውም።
ለነዚህ አይነት የልጆች ስብዕና ወላጆች ሊያደርጉዋቸው የሚገባቸው ነገሮች ለሚያሳዩት ባህሪያት ትዕግስተኛ በመሆን ቀስበቀስ ማስተማርና እንዲደፋፈሩ ማድረግ ሚዛናዊና የተረጋጋ እንዲሆኑ ማስቻል መልካም ነገር ሲያከናውኑ ማድነቅና ማበረታታት ያስፈልጋል።
ከአይናፋርነታቸው ጀርባ የሆነ ምክንያት ሊኖር ስለሚችል በመረጋጋት ለማወቅና ለመረዳት መሞከር ከልጆቹ ጋር በመሆን አዳዲስ ነገሮች እንዲለማመዱ አብሮነትን ማሳየት ተገቢ ነው።
ዝምተኛ ልጆች፡- እነዚህ ልጆች በጣም ዝምተኛ ከመሆናቸው የተነሳ በዙሪያቸው ለሚከሰቱ ነገሮች ግንዛቤ የላቸውም። በሃሳብና በቅዠት መብሰልሰል ይመርጣሉ። አዳዲስ ነገሮችን ማወቅና መፈለግ የማይወዱ ናቸው።
በቀላሉ የሚሰላቹና የሚደክማቸው ሲሆኑ ምናልባትም የምግብ እጥረት አሊያም ይህን ተከትሎ በሚመጣ በሽታ ተጠቅተው ሊሆኑ ስለሚችል ወላጆች አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና እንዲያደርጉላቸው ይገባል።
ለዚህ አይነት የልጆች ስብዕና ወላጆች ሊያደርጉዋቸው የሚገቡ ነገሮች ግርማ ሞገስን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማሳየት መልካም ነገር ሲያከናውኑ ማድነቅና ማበረታታት ጥሩ ነው። ከዝምተኝነታቸው ጀርባ የሆነ ምክንያት ሊኖር ስለሚችል በመረጋጋት ለማወቅና ለመረዳት መሞከር አስፈላጊ ነው።
ለየት ያሉ ነገሮችን በማድረግ የልጁን ፍላጎትና ትኩረትመሳብ በሚያስችል ቀላልና ብዙ አድካሚ ያልሆኑ ተግባራትን እንዲያከናውኑ በማድረግ ዝምታቸውን እንዲሰብሩ ጥረታቸውን ማጉልበት ይገባል።
ልጆች የተለያዩ ስብዕናዎች ሊኖራቸው እንደሚችል ግንዛቤን እንዳገኛችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ ልጆችን መጥፎ ናቸው ብለን እንዳናስብ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የልጆችን ባህሪ በአንድ በኩል ብቻ ተመልክተን ሙሉ ስብዕናቸውን ከመግለፅ መቆጠብ አለብን። ምክንያቱም የልጆች አሉታዊ ባህሪያቶች ምን አልባት ጥሩ ምክንያት ሊኖራቸው ስለሚችል ነው።
ለምሳሌ በቤት ውስጥ በደረሰበት ጥቃት ምክንያት አንድ የስድስት አመት ልጅ ቁጡና ግልፍተኛ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ ልጅ ቁጡ የሆነ ስብዕና አለው ማለት አይደለም። ነገሮች ሲሻሻሉ ለምሳሌ ወደ ምቹና የተሻለ ቤተሰብ ጋር ቢሆን የልጁ ስብዕና እንደሚለወጥ መገንዘብ አለብን።
የልጆች ስብዕና ባለበት ፀንቶ የሚቀር አይደለም፤ ምክንያቱም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ባህሪያትን ሊያሳዩ ስለሚችሉና ስብዕናቸው ተሟልቶ ያልዳበረ ስለሆነ ነዉ። እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲመጣ ስብዕናቸውም እያደገና እየተለወጠ ይመጣል። ስለዚህ ወላጆች እነዚህን ነገሮች ሊረዱ፣ ሊቀበሉና ሊቆጣጠሩ ይገባል።
ወላጆች የልጆችን አወንታዊ የስብዕና ባህሪያቶችን እያበረታቱ አሉታዊ የሆኑትን ደግሞ ሊቆጣጠሩ አልያም ወደ አወንታዊ ወደሆኑ ባህሪያቶች በመቀየር ልጆችን ሊያግዟቸው ይገባል። ለምሳሌ ቁጡና ግልፍተኛ ባህሪያቶችን የሚያሳዩ ልጆችን ወደ ስፖርትና የተለያዩ የፈጠራ ተግባራት እንዲያከናውኑ በማድረግ ሊቆጣጠሯቸው ይችላሉ።
ወላጅ ወይም አሳዳጊ ሁልጊዜም የልጆችን አዕምሯዊም ሆነ አካላዊ እድገት ላይ የቻለውን ሁሉ ሲገነባ ሀገርን በቤቱ እንደሚያሳድግ ይቁጠረው እላለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013