አስመረት ብስራት
ልጆች ሰላም ነው? እንዴት ናችሁ? ሁልጊዜ ስትገናኙ ሰላም ነው? ሰላም ሰላም ትባባላላችሁ አይደል? ለመሆኑ ሰላም ምንድነው? ስለሰላም ምን ታውቃላችሁ? በኤቢ አካዳሚ ተገኝቼ ያነጋገርኳቸው ልጆች ስለሰላም እንዲህ ይነግሩናል።
ተማሪ ዘካሪያስ ስለሺ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ̋ሰላም ማለት አለመጣላት፤ አለመጨቃጨቀ ማለት ነው። ሰውና ሰው ሲጣላ በጣም ብዙ ነገር ስለሚጠፋ ሰዎች በሰላም መኖር አለባቸው። ሌላው የሰላም ትርጉም ደግሞ ሰዎች ሳይጨነቁ ሳይታመሙ መኖር ማለት ነው።”
“ለምሳሌ ኮሮና መጣ ሲባል ተጨንቀን አልነበር? እሱ ከጠፋ ደግሞ ሰላም እንሆናለን ማለት ነው። ኮሮናን ለማጥፋት ትምህርት ቤት ስንገባ ሙቀታችንን ተለክተን፤ እግራችንን በኬሚካል ነክረን፤ እጃችንን ታጥበን በክፍላችንም ውስጥ ለየብቻችን ተቀምጠን እርሳስ ላፒሳችንን ይዘን መጥተን፣ ሳንዋዋስ እየተማርን ነው” ብሏል።
በተጨማሪም ተማሪ ዘካሪያስ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችንና ስእል መስራት እንደሚወድ ነግሮናል። “ይህንን ሁሉ እንድሰራ ግን ቤተሰቦቼ ሰላም ስለሆኑ ያግዙኛል። ስለዚህ ሰላም ለልጆች በጣም አስፈላጊ ነገር ነው” ሲል አጫውቶናል።
የአምስተኛ ክፍለ ተማሪ የሆነችው ኤልዳና ብርሀኑ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ኤልዳናም እንደ ዘካሪያስ ስእል መስራት፤ የወረቀት ስራ ፈጠራዎች መሞከር ትወዳለች።
ኤልዳና ሁልግዜ የምትመኘው ሀገራችን ሰላም ሆና ማየት ነው። ሁልግዜ ትልልቅ ሰዎች ስለጦርነት ሲያወሩ እፈራለሁ የምትለው ይህች ልጅ ህፃናት ሳይጨነቁ እንዲኖሩ ትልልቅ ሰዎች መጣላት ማቆም አለባቸው ትላለች።
ሰላም ማለት ምንም ሳይጣሉ ማንም ሳይፈራ መኖር ነው። ሰላም ማለት መሳቅ መደሰት አብሮ መብላት መተቃቀፍ ነው ትላለች ህፃን ኤልዳና። ሌላው እነዚህ ልጆች ያስተላለፉት ነገር እኛ ልጆች በሰላም እንድንኖርና አላማችን እንዲሳካ ሁሉም ሰው እንዳይጣላ፣ ሰላም… ሰላም እንዲባባል ነው።
እኔም ደግሞ ሰላም ለግለሰብ፣ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብና ለሃገር ህልውና እጅግ አስፈላጊ የሆነ ምቹና ጤናማ የአኗኗር ሁኔታዎች የሰፈኑበትና በየዕለቱ የሰው ልጆች ኑሯቸውን ለማሻሻል ከተፈጥሮና እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት የማያቋርጥ ትግል፣ የመተጋገዝና አብሮ የመኖር ሂደት ነው።
ሰላም የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች ከሆኑት ምግብ፣ መጠለያና ልብስ በበለጠ ዋጋው እጅግ የላቀ ነገር ነው። የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች ሊሟሉ የሚችሉት በቅድሚያ የሰው ልጅ በሰላም በህይወት መኖር አለበት። ሰላም ለሰው ልጆች እጀግ በጣም የሚያስፈልገን ነገር ነው። ልጆች ሰላማችሁ ይብዛ ሰላም ሁኑ። እባካችሁ የሀገሬ ሰዎች ሰላም ውለን ሰላም በማደር ለልጆቻችን የሰላም አየር እናስተንፍሳቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013