አስመረት ብስራት
ስብዕና ማለት በአንፃራዊነት ቋሚ የሆነ የስሜት፣ የሃሳብና የባህሪ ድምር ውጤት ሲሆን እንድን ግለሰብ ከሌሎች የሚለይ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ልዩ ስሜት፣ አስተሳሰብና ባህሪ አለው፡ ፡ ነገር ግን የልጆች ስብዕና እንደ አዋቂዎች ቋሚ ሆኖ የሚዘልቅ ሳይሆን በሂደት የሚያድግና የሚሻሻል ነው፡፡
ስብዕና አወንታዊና አሉታዊ ገፅታዎች አሉት፡፡ አዎንታዊ የምንላቸው እንደ ተጫዋችነት፣ ሳቂታና ቀልድ አዋቂነት ሲሆኑ ትግስት አልባነት፣ ተናዳጅነት፣ ቁጡ፣ ግልፍተኛነትና ስሜታዊነትን አሉታዊ የምንላቸው ናቸው፡፡
የስነልቦና ባለሙያዎች የልጆችን ስብዕናን በአምስት ይከፍሉታል፡፡ ከአምስቱ የመጀመሪያው በጣም ንቁ የሆኑ ልጆች የተለያዩ ነገሮችን ለማወቅና ለመስራት ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው ሲሆኑ በጣም ንቁ ሆኖ መገኘትን የሚወዱ፣ ባሉበት
ተረጋግተው መቀመጥ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት እነዚህ ልጆች ለነገሮች ያላቸው ትኩረት ዝቅተኛ ስለሆነ ቶሎ የመርሳት ችግር ይታይባቸዋል፡፡ ከነዚህ ልጆች ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ማውራትና ንግግር ማድረግ በጣም ያስቸግራል፡፡
ለዚህ አይነት የልጆች ስብዕና ወላጆች ሊያደርጉዋቸው የሚገባቸው ነገሮች የልጆችን ትኩረት ማጣት ላይ ትኩረት አለማድረግና አለመጨነቅ፤ መልካም ነገር ሲያከናውኑ ማድነቅና ማበረታታት፤ ልጁ ስለባህሪው እንዲያስብበት ማድረግ፤ አንድ ነገር በአንድ ጊዜ እንዲያከናውኑ ማገዝ፤ ቀስ በቀስ ልጆች ረዘም ላለ ጊዜ አንድን ተግባር እንዲያከናውን ማገዝ ነው።
ሁለተኛው ቁጡና_ግልፍተኛ_ልጆች ናቸው። ይህ ስብዕና ያላቸው ልጆች በአብዛኛው ስሜታቸውን መቆጣጠር የሚቸገሩ ሲሆን ሰዎች ለሱ ጥሩ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው ናቸው፡፡ በቀላል ነገሮች የሚበሳጩና የሚናደዱ ሲሆኑ የሚፈልጉትን ነገሮች ሃይልን በመጠቀም ለማግኘት ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ
ነገሮችን ሳያስቡ ማከናወን የሚቀናቸው ሲሆኑ በአጠቃላይ ችግር ፈጣሪ የሚል ስያሜን ሊያገኝ ይችላል፡፡
ለዚህ አይነት የልጆች ስብዕና ወላጆች ሊያደርጉዋቸው የሚገባቸው ነገሮች ለሚያሳዩት ባህሪያት ትዕግስተኛ መሆን ግን ግልፅ ገደብ ማበጀት፤ ስሜቱን እንዲያቀዘቅዝ እንክብካቤና እምነት መስጠት፤ መልካም ነገር ሲያከናውኑ ማድነቅና ማበረታታት፤ ከቁጣቸው ጀርባ የሆነ ምክንያት ሊኖር ስለሚችል በመረጋጋት ለማወቅና ለመረዳት መሞከር፤ ስሜታቸውን በንግግር እንዲገልፁ ማገዝ፤ ልጁ ከመናደዱ በፊት እንዲያስብበት ማስተማርና ቀስ በቀስ ስሜቱን መቆጣጠር እንዲችል ማገዝ ይኖርባቸኋል።
ሶስተኛው አመፀኛ_ግን_ነፃ_የሆኑ_ልጆች ናቸው። እነዚህ ልጆች ምን መስራትና ማድረግ እንዳለባቸው በሌሎች ሲነገሯቸው የማይወዱና እልህኛ የሆኑ ናቸው፡፡ ሆን ብለው ጥፋትን እና አመፃን የሚያነሳሱ ናቸው፡፡ አንዳንዴ የመሪነትን
ሚና የሚጫወቱ ቢሆንም ሌሎች ልጆችን አሉታዊና መጥፎ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር ይጠቀሙበታል፡፡ በወላጆችና በታላላቆች የሚታዘዙትን ስራ በተቃራኒው ያከናውናሉ፡፡
ለነዚህ አይነት የልጆች ስብዕና ወላጆች ሊያደርጉዋቸው የሚገባቸው ነገሮች ለሚያሳዩት ባህሪያት ትዕግስተኛ መሆን ግን ግልፅ ገደብ ማበጀት፤ የተረጋጋና ሰዎችን ማክበር እንደሚያስከብረው ማስተማርና መምከር፤ መልካም ነገር ሲያከናውኑ ማድነቅና ማበረታታት፤ ከአመፀኝነታቸው ጀርባ የሆነ ምክንያት ሊኖር ስለሚችል በመረጋጋት ለማወቅና ለመረዳት መሞከር፤ መልካም የሆኑ አማራጮችን ማቅረብና ምክንያታቸውን በማስረዳት እንዲመርጡ ማድረግ፤ ለውጥ ማሳየት ሲጀምሩ ድጋፍ መስጠትና በማበረታታት ተባባሪና መልካም እንዲሆን ማደረግ ይኖርባቸዋል። የስነልቦና ባለሙያዎች ድረ ገፅ ላይ ካሰፈሩት ያገኘነውን ተከታይ ክፍል ለሳምንት ይዘን እንቀርባለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013