
ቦጋለ አበበ
በ2020 የዓለም ምርጥ አትሌቶች ሽልማት ኢትዮጵያውያን ወንድ አትሌቶች ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ከአስር የመጀመሪያ እጩዎች ውስጥ መካተት ባይችሉም ሴት አትሌቶች ተሳክቶላቸዋል።ከሦስት ሳምንታት በፊት የዘንድሮው ዓመት አስር የሽልማቱ እጩዎች ስም ዝርዝር በዓለም አትሌቲክስ ይፋ ሲደረግ ሁለት ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች መካተት ችለዋል።ከአገር አቋራጭ ውድድሮች አንስቶ እስከ መካከለኛና ረጅም የመም ውድድሮች በአጭር ዓመት ውስጥ ስኬታማ መሆን የቻለችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ እንዲሁም የግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው አባብል የሻነህ ከአስሮቹ እጩዎች መካተት ችለዋል።
ከሳምንት በፊት የመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች ይፋ ሲደረጉም ለተሰንበት ግደይ አንዷ በመሆን የሽልማቱ አሸናፊ ሆና እንደምትፎካከር አረጋግጣለች።የሽልማት ስነስርዓቱ ነገ በሞካኖ ከተማ ሲከናወንም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ከሌሎች አገራት አራት አትሌቶች ጋር ተወዳድራ አሸናፊው የሚለይ ይሆናል።ለተሰንበት ለዚህ ሽልማት ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ የመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌት ሲፈን፣ ከጃማይካዊቷ የመቶና የሁለት መቶ ሜትር የኦሊምፒክ ባለድል ኤሌን ቶምሰን ሄራን፣ ከቬንዙዌላዊቷ ስሉስ ዘላይ ዩሊማር ሮጃስና ከኬንያዊቷ የግማሽ ማራቶን ባለክብረወሰን ፒሬስ ጂፕቺርቺር ጋር ይፎካከራሉ።
አምስቱ እጩዎች በ2020 የውድድር ዓመት ብቻ በአትሌቲክስ ያሳዩት ድንቅ ብቃት በሦስት አይነት መንገድ በሚሰበሰብ ድምፅ ተወዳደረው የሚያሸንፉ ይሆናል።የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ሃምሳ በመቶ የሆነ ድምፅ ለእጩዎቹ የሚሰጥ ሲሆን የአትሌቲክስ ቤተሰቡ በማህበራዊ ድረ ገፅ የሚሰጠው ድምፅ ሃያ አምስት በመቶ ይይዛል።ቀሪው ሃያ አምስት በመቶ ደግሞ ማንኛውም ሰው በማህበራዊ ድረ ገፅ ከሚሰጠው ድምፅ ይሰበሰባል።አምስቱ እጩዎች በ2020 የውድድር ዓመት በየፊናቸው የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግበዋል።ሽልማቱን ለማሸነፍም እኩል እድል አላቸው።የተሻለ የማሸነፍ እድሉ ወደ የትኛው አትሌት እንደሚያዘነብልም ከአትሌቶቹ ስኬት በመነሳት መላ ምቶች ሲቀመጡ ሰንብተዋል።
ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ እኤአ 2015ና 2017 ላይ በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና በወጣቶች ዘርፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ከጨበጠች ወዲህ ፊቷን ወደ መካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ውድድሮች አዙራ በርካታ ስኬቶችን ተጎናፅፋለች።በ2019 የዶሃ ዓለም ቻምፒዮና በአስር ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ለተሰንበት ለዘንድሮው ሽልማት እጩ ባደረጋት የውድድር ዓመት አንድ ታላቅ ስኬት ማስመዝገቧ ሽልማቱን ለማሸነፍ በምታደርገው ፉክክር የጎላ ሚና አለው።ይህም ለአስራ ሁለት ዓመታት በረጅም ርቀት ፈርጧ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የአምስት ሺ ሜትር ክብረወሰን በአራት ሰከንዶች ማሻሻል መቻሏ ነው።በቅርብ ዓመታት ያውም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ውድድሮች ባልነበሩበት ወቅት ይሰበራል ተብሎ ያልተጠበቀውን ክብረወሰን 14፡06፡62 በሆነ ሰዓት ከወር በፊት ቫሌንሲያ ላይ ማሻሻል የቻለችው ለተሰንበት ይህ ስኬቷ በውድድር ዓመቱ አንደኛው ቢሆንም ቀላል ክብደት የሚሰጠው አይደለም።ለተሰንበት በውድድር ዓመቱ በሞና ዳይመንድ ሊግ ሁለተኛ ሆና ባጠናቀቀችበት ውድድርም በአምስት ሺ ሜትር ስኬታማ ነበረች።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ጥቂት በማይባሉ ባለፉት ዓመታት በመካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪነቷን በተለያዩ አጋጣሚዎች አስመስክራለች።በተለይም ለተሰንበት ግደይን አስከትላ በገባችበት የዶሃው ቻምፒዮና ከአስር ሺ ሜትር በተጨማሪ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ያስመዘገበችው ስኬት በ2020 የውድድር ዓመት ምርጥ አትሌት ሆና ለመታጨት ላበቋት ስኬቶች መንደርደሪያ ሆነዋል።ሲፈን በውድድር ዓመቱ የአንድ ሰዓት ሩጫን 18፡930 በማስመዝገብ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ስትጨብጥ በአስር ሺ ሜትር 29፡36፡67 የሆነ የአውሮፓ ክብረወሰንን መያዝ ችላለች።ይህም ሰዓት በርቀቱ ታሪክ አራተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ኬንያዊቷ ፒርስ ጂፕቺርቺር ከወር በፊት የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮናን በፖላንድ ጊዲኒያ ማሸነፍ የቻለች ሲሆን የርቀቱን የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረወሰን 1፡05፡34ና 1፡05፡16 በሆኑ ሰዓቶች ሁለት ጊዜ ማሻሻል ችላለች።የዓለም የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በተደጋጋሚ በሌሎች አትሌቶችም የሚሰበር እንደመሆኑ ሽልማቱን ለማሸነፍ ይህች አትሌት የተጋነነ እድል ባይኖራት እንኳን የዓለም ቻምፒዮን ጭምር መሆኗ የአሸናፊነት ሚዛኑ ወደ እሷ ሊያደላ እንደሚችል ብዙዎች እምነት አላቸው።ምክኒያቱም ሌሎች ተፎካካሪዎቿ በውድድር ዓመቱ የዓለም ቻምፒዮን የመሆን አጋጣሚው አልነበራቸውምና።
በእርግጥ ከአምስቱ እጩዎች መካከል አንዷ የሆነችው ቬንዙዌላዊቷ ዩሊማር ሮጃስ በውድድር ዓመቱ በቤት ውስጥ ውድድር የዓለም ስሉስ ዝላይ ክብረወሰንን 15፡43 በሆነ ሰዓት ማሻሻሏ አይዘነጋም።ሆኖም በዓለም ምርጥ አትሌቶች ሽልማት የቤት ውስጥ ውድድሮች ስኬት ከቤት ውጪ እንደተመዘገቡት ስኬቶች እኩል የማይታይበት እድል ሰፊ እንደሆነ ከባለፉት ዓመታት ልምዶች መገንዘብ ይቻላል።ይሁን እንጂ ሮጃስ በውድድር ዓመቱ በቤት ውስጥም ከቤት ውጪም ባደረገቻቸው አራት ውድድሮች አንድም ሽንፈት አለማስተናገዷ ሽልማቱን ለማሸነፍ ሰፊ እድል ካላቸው ተፎካካሪዎች አንዷ እንደሚያደርጋት ጥርጥር የለውም።
ጃማይካዊቷ ኢሌን ቶምሰን ሄራን በውድድር ዓመቱ በመቶ ሜትር ባደረገቻቸው ሰባት ፉክክሮች አንድም ሽንፈት አልገጠማትም።በርቀቱ የዓመቱን መሪ ሰዓትም 10፡85 አስመዝግባለች።ይህ ስኬቷ ቀላል ባይሆንም ከሌሎቹ ተፎካካሪዎቿ አንፃር ሽልማቱን ለማሸነፍ አነስ ያለ እድል ያላት አትሌት ሊያደርጋት እንደሚችል ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም