ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ግንባታ ላይ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ አፈፃፀሙ 74 ከመቶ ደርሷል፡፡ በ2012 ዓ.ም መያዝ የሚገባውን ውሃ ሙሌትም ሙሉ ለሙሉ መያዙን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ብስራት ሲሆን ለግብፅ ልብ ስብራት ሆኗል፡፡ የግድቡ ውሃ ሙሌት በታሰበለት ጊዜ ውስጥ መከናወኑ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ማሳያ መሆኑን የተለያዩ ምሁራን ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት አቶ ገዛኸኝ በርሄ እንደሚሉት፤ ግድቡ በመጀመሪያው ዙር መያዝ የሚገባውን ውሃ በመያዙ የተሰማው ብስራት የኢትዮጵያ ጥንካሬና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እየተሰሩ ያሉ የዲፕሎማሲ ተግባራት የውሃ ሙሌቱ በታቀደው መልኩ ኢትዮጵያ ማከናወን መቻሏ ግብፆች እስካሁን የመጡበትን አካሄድ ዳግም ለማየት እንደሚገደዱና ቀሪውን የውሃ ሙሌት ለማዘግየት የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የኮሙኒኬሽን መምህሩ ያስረዳሉ፡፡
በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምህንድስና አስተዳደር መምህር ኢንጅነር አብዱልዋሃብ አቤ እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበረው አንድ የውሃ ምህንድስና ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት በ12 ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ መሆኑ በቀጣይ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ከዚህ በበለጠ ለመጠቀም ዕድል እንዳላትና ይህም ዓባይን ጨምሮ በሌሎች ወንዞች ላይ የመጠቀም መብቷን ለመጎናፀፍ እውቀት እያካበተች መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ግብፆች ይህም ራስ ምታታቸው ሲሆን ለኢትዮጵያ አይበጅም የሚሉትን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡
እንደ ኢንጅነር አብዱልዋሃብ ገለፃ፤ ግብፅ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ከስትራቴጂክ ጠቃሜታ፤ ወታደራዊ ኃይል፤ አገሪቱ ካላት የተማረ የሰው ኃይል እና በዲፕሎማሲ ረገድ የትኛው አዋጭ ነው ብለው አጢነው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ በብዙ መንገድ ሽንፈት እየገጠማቸው ነው፡፡ አሁን እየተበለጡ ሲሆን ይህንን ለማካካስም ሌላ ተንኮል ላይ መጠመዳቸው አይቀሬ መሆኑን ማጤን አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህ ሁሉ ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
በተለይም በዲፕሎማሲ ሥራ የተናበበ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሥራዎችን ማከናወን፤ በዓለም ላይ ኢ-ሚዛናዊ ዘገባ እያካሄዱ ያሉ ሚዲያዎችም ላይ በመቅረብ እውነታውን ማስረዳት ይገባል፡፡ ግድቡ ውሃ መያዝ መጀመሩ አንዱ ድል ቢሆንም በቀጣይም በርካታ የቤት ሥራዎችም መኖራቸውን በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እጅጉን በተናበበ መንገድ ግድቡ ቀጣይ ምዕራፎች ላይ ማተኮር አለባቸው ብለዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ መምህር የሆኑት አቶ ይበልጣል መሥዕዋት እንደሚሉት፤ የአሜሪካና የአረብ ሊግ ውሳኔን በመፃረር ብሎም የግብጽን ፉከራ በመተው ግድቡ ውሃ ሙሌት መጀመሩ የኢትዮጵያን ተሰሚነት በእጅጉ የሚጨምርና ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ አሸናፊ እየሆነች መምጣቷን አመላካች ነው፡፡
ግብፅ ቀደም ሲል ግድቡ እንዳይገነባ በዲፕሎማሲ ጫና፣ የፋይናንስ ምንጮችን በመዝጋት ብዙ ሄዳ አዋጭ ባይሆንላትም በቀጣይ የዓለም ባንክን፣ ኢንተርናሽናል ሞንተሪ ፈንድንና ሌሎች የገንዘብ ምንጭ የሆኑ ተቋማት ሌላ ቀጣይ ልማት እንዳትሰራ ብድርና እርዳታ ለማስከልከል ብዙ ዕርቀት ልትጓዝ እንደምትችል ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል፡፡
ግብፆች እስካሁን የመጡበት አካሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅ አዙር የብጥብጥ ሤራ አዋጭ እንዳልሆነ በቅርቡ በኢትዮጵያ ታቅዶ የከሸፈው ሴራ ሁነኛ ማሳያ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ ህብረተሰቡም ሴራውን በሚገባ ተረድቷል፡፡ በቀጣይ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ከተስተካከለ፣ ሙስና እና ምዝበራ ከተወገደ እና የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እየተጠናከሩ ከሄዱ በዓባይ ላይ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማከናወን አንዳች የሚያግድ ኃይል እንደሌለም አቶ ይበልጣል ይነገራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር