አዲስ አበባ፡- የኮሮና በሽታ ከተከሰተ በኋላ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የመንገደኞች በረራ አገልግሎት መነቃቃት በማሳየቱ ሰባት የውጭ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ መብረር መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የኤር ናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ከተከሰተ በኋላ በርካታ ሀገራት በረራቸውን አቋርጠው ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ግን በአየር ትራንስፖርት የመንገደኞች በረራ አገልግሎት መነቃቃት በማሳየቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ሀገራት አየር መንገዶች ሰባት ደርሰዋል። በአማካይ በቀን ሰባት የውጭ ሀገራት አየር መንገድ አውሮፕላኖች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ላይ ናቸው።
እንደ ኤር ናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሽመልስ ገለጻ፤ ኮሮና በሽታ በዓለም ላይ ከተስፋፋ በኋላ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መብረር ከጀመሩ አየር መንገዶች መካከል የዱባይ ፣ የቱርክ፣ የኳታር፣ የግብጽ፣ የሱዳን፣የኬንያ እና የጅቡቲ አየር መንገዶች ይገኙበታል። በአሁኑ ወቅትም በአማካይ ሁለት መደበኛ በረራ እና አምስት መደበኛ ያልሆኑ የመንገደኛ አገልግሎት የሚሰጡ አውሮፕላኖች ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እየበረሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንም እየጨመረ የመጣውን የአየር በረራውን አገልግሎት እና የአውሮፕላኖች ቁጥር መሰረት በማድረግ የቁጥጥር ስራ ለማከናወን የሚችሉ በቂ ሰራተኞችን ማሰማራቱን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው፤ በኮሮና በሽታ መስፋፋት ምክንያት እረፍት ላይ የነበሩ ሰራተኞቹን ጭምር በመጥራት በ24 ሰዓት ውስጥ በሶስት ፈረቃ የሚሰሩ 45 የአየር በረራ ቁጥጥር ባለሙያዎችን በአሁኑ ወቅት ተሰማርተዋል። በቀጣይ ቀናትም ወደ ኢትዮጵያ የሚበሩ እና ከኢትዮጵያ የሚነሱ አውሮፕላኖች ቁጥር እንደሚጨምር በመገመቱ ተጓዳኝ በሽታ ከሌለባቸው ሰራተኞች ውጪ ያሉ እና 90 በመቶ የሚሆኑትን የባለስልጣኑ ባለሙያዎችን በማሰማራት የቁጥጥር ስራውን ለመከወን ታቅዷል።
የኮሮና በሽታ በተስፋፋበት ወቅት እንኳን ኢትዮጵያ የአየር ክልሏን እንዳልዘጋች የተናገሩት አቶ ሽመልስ፤ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያን አየር ክልል አቋርጠው ወደሌሎች ሀገራት የሚያልፉ አውሮፕላኖች ላይ ቁጥጥር ሲደረግ እንደነበረ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ወደአቋረጠባቸው ቦታዎች ዳግም መብረር በመጀመሩ በየቀኑ ወደአውሮፓ እና ሌሎች ክፍላተ ዓለማት የሚያደርገውን በረራ 50 ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል። በመሆኑም ባለስልጣኑ ከ50 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አውሮፕላኖች እንቅስቃሴ ላይ በየቀኑ ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መረጃ የኮሮና በሽታ ከመስፋፋቱ በፊት ወደ ኢትዮጵያ የሚበሩ 22 የውጭ ሀገራት አየር መንገዶች ሲኖሩ በየቀኑ ከ300 በላይ በረራዎች በኢትዮጵያ ይስተናገዱ ነበር።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም