አዲስ አበባ ፤ በተለያዩ ሀገራት በስደት ላይ የነበሩ እና በኮሮና በሽታ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ 30ሺህ 87 ኢትዮጵያውያን ወደሀገር ውስጥ መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ዜጋ ተኮር የመንግስት ፖሊሲ ተግባራዊ በመደረጉ በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ እና በስደት የነበሩ 30ሺህ 87 ኢትዮጵያውያንን ወደሀገራቸው መመለስ ተችሏል።
በፍቃደኝነት ወደሃገራቸው የተመለሱ ዜጎች በአብዛኛው ከገልፍ እና ከጎረቤት ሀገራት የመጡ ናቸው።
አምባሳደር ዲና እንደገለጹት፤ በተለይ በአረብ ሀገራት እና በጎረቤት ሀገሮች በስደት የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በኮሮና በሽታ ወቅት ስራ በማጣት ጎዳና ላይ ሲወድቁ በየሀገራቱ የሚገኙ ቆንስላዎች ክትትል አድርገዋል። በተለይ በቤይሩት ከስራ ተባረው እና በመንገድ ላይ ተጥለው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በቆንስላው አማካኝነት ድጋፍ በማድረግ በፍቃደኝነት መመለስ ተችሏል። በዚህ መሰረት ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ከተደረጉ 30ሺ በላይ ዜጎች መካከል ከቤይሩት 656 ዜጎች፤ ከአቡዳቢ 72፤ ከሳዑዲ አረቢያ 3ሺህ 539፣ ከኩዌት ደግሞ 1 ሺህ 23 ዜጎች እንዲሁም በድንበር በኩል ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት 4ሺህ 792 ዜጎች ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
እንደ አምባሳደር ዲና ከሆነ፤ መንግስት በሚከተለው የዜጋ ተኮር ፖሊሲ መሰረት አሁንም በስደት ላይ ለእንግልት የተዳረጉ ዜጎች ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ለአብነት በየመን የቆየ ጦርነት በመኖሩ ምክንያት የት እንዳሉ እና ምን ያክል ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ከተባበሩት መንግስታት እና ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር ክትትል እየተደረገበት ይገኛል። በመሆኑም በቀጣይ ከተለያዩ ሀገራት የሚመለሱ ዜጎች ይኖራሉ። ወደሀገራቸው በፍቃደኝነት ከተመለሱ በኋላም እንዲቋቋሙ ይደረጋል። በዚህ ረገድ ቀጣይነት ባለው መልኩ የማቋቋም ስራው መሰራት እንዳለበት በመንግስት ደረጃ አቅጣጫ ተይዟል።
በሌላ በኩል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በአባይ ግድብ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮው የክረምት ዝናብ ውሃ ከፍተኛ መጠን ነበረው። በዚህም ምክንያት የግድቡን የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ከታሰበው ጊዜ በፊት ማጠናቀቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም