ሰሞኑን በቴሌቪዥን ጣቢያዎችና በጋዜጦች የሚታየው ነገር አንድ የአገር ቤት የቃል ግጥም አስታወሰኝ። ይሄን የቃል ግጥም ስካር የተሰማው ሰው ያንጎራጉረዋል። አንዳንዴ ደግሞ የሚሰራው ሥራ ሲሰለቸውም ያንጎራጉረዋል። ነገርየው በፉከራ ዜማ ነው የሚባለው።
ጅንኑ ጂን የወረሰው
ሰርቸው ነበር ደግሞ ላፍርሰው!
ሰውየው ራሱን እያወደሰም እየሰ ደበም ነው። ጅንን ማለት የሚያምር፣ መልከመልካም፣ ኩራተኛ እንደማለት ነው፤ ጂኒ ማለት ደግሞ ሰይጣን ማለት ነው። ‹‹ሰይጣን አሳስቶኝ!›› እንደሚባለው ጂኒ ወርሶኝ የሰራሁትን ላፈርሰው ነው እያለ ነው። ይህን የሚለው የራሱን ቤት ሲያቃጥል ወይም ራሱ የሰራውን (የገዛውንም ሊሆን ይችላል) ነገር ሲያበላሽ ነው። ቤቷን አቃጥላ ‹‹አሁን በራልኝ›› አለች እንደሚባለው መሆኑ ነው።
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የደረሰው ጥፋት የሚጎዳው የአካባቢውን ማህበረሰብ ነው። በጅማ ከተማ ሆቴል የተቃጠለባቸው ባለሀብት በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሲናገሩ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋሚ እና የኮንትራት ሰራተኞች አሏቸው። እነዚያ ሰራተኞች የአካባቢው ወጣቶች ናቸው። አሁን የተቃጠለው የእነዚህ ሰራተኞች እንጀራ ነው።
ልብ ብለን ካየነው ከሰውየው በላይ እነዚያ ሰራተኞች ይጎዳሉ። ሰውየው እኮ ቢያንስ ቢያንስ የዕለት ጉርስ እና የቤት ኪራይ አይቸግራቸውም፤ እነዚያ ሰራተኞች ግን ይቸግራቸዋል። ሞራላቸው ጭምር ነው የሚጎዳው። ባለሀብቱ አካባቢ ቀይረው ንግዳቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፤ ምንም ይሁን ምን የዕለት ጉርስ አያጡም፤ የእነዚያ ምስኪን ሰራተኞች እንባ ግን የአጥፊዎችን ህሊና ይወቅሳል (አጥፊ ህሊና ባይኖረውም!)
ለአካባቢው ማህበረሰብ ሌላም ጉዳት አለው። በዚያ ሆቴል ውስጥ የሚቆይ እንግዳ በከተማዋ ውስጥ ብዙ ነገር ይጠቀማል። ያ የአካባቢው ጥቅም አይደለም? ትልልቅ ስብሰባዎችና ለቀናት የሚቆዩ ሥልጠናዎች የሚሰጡት በእንዲህ አይነት ሆቴሎች ውስጥ ነው። እነዚህ ሆቴሉ ውስጥ የሚቆዩ እንግዶች ከተማዋ ውስጥ ብዙ ነገር ይጠቀማሉ። በተለይም ከሩቅ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች ደግሞ ከተማዋን ለማወቅ ይዟዟራሉ። በእነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎቻቸው ብዙ ነገር ይገዛሉ፤ እንዲያውም ከአካባቢው ተወላጆች በላይ ዕቃ የሚገዙት እነዚህ እንግዶች ናቸው። የአካባቢው ሰዎችማ
ለከተማው አዲስ ስላልሆኑ ብዙ ነገር አይጠቀሙም፤ ሁሉም በየቤቱ ይጠቀማል። የእንግዳ ማረፊያዎች ግን እንዲህ አይነት የንግድ ትስስርን ያሰፋሉ። ይሄን ማስቀረት ለዚያ ከተማ ማህበረሰብ ጉዳት አይደለምን? በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ የራሳቸውን ወገን ነው የጎዱት።
አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ለውጭ መገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን ሲሰጡ የብሄር መልክ ያለው መሆኑን ተናግረዋል። አጥፊዎች ስም እየጠቀሱ እየለዩ ማጥፋታቸውን አይተናል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ደግሞ የብሄር መልክ የለውም፤ የተጎዳው ሁሉም ነው ብለዋል። ትክክል ነው የተጎዳው ሁሉም ነው። የብሄር መልክ ያለው ነው የሚባል ጉምጉምታ ቢኖርም አንድ ወገን ብቻ ይጎዳል ብሎ ማመን የዋህነት ነው። ጥፋት በደረሰበት አካባቢ ሁሉም ተጎጂ ነው።
ቄሮ እና አባ ገዳዎችን ጥያቄ እንጠይቅ
እንደምናየውና እንደምንሰማው የመንግስት ባለሥልጣናት የንግግር መክፈቻ ለውጡ ነው። የለውጡ አካል ደግሞ ቄሮ ነው። የሰላም ተምሳሌቶችም አባ ገዳዎች ናቸው። ቄሮ ለዓመታት ከጥይት ፊት ተጋፍጦ ያመጣው ለውጥ መሆኑን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሁሉ መስክረውለታል። ዶክተር አብይ ‹‹ለውጡ የመጣላቸውና የመጣባቸው›› ሲሉ በገለጹት፤ ጥፋቱን ያደረሱት ለውጡ የመጣባቸው ናቸው።
የእኔ ጥያቄ፤ ቄሮ እነዚህን አካላት (ለውጡ የመጣባቸውን ማለት ነው) ለምን አይከላከልም? አባ ገዳዎች ለምን የጋሞ አባቶችን ጀግንነት አልፈጸሙም? የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ‹‹የጋሞ አባቶች ተንበርክከው አሸንፈውናል›› ብለው ነበር። የኦሮሞ አባ ገዳዎችም እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ተንበርክከው ያሸንፉልን። ቄሮ ተደራጅቶ አጥፊዎችን ይከላከልልን። ቄሮ ጥፋትን ማስቆም እንደሚችል አሳይቶናል። ያንን ይድገምልን!
በመስከረም ወር በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ቄሮ በሰራው ሥራ ምንም ነገር ኮሽ ሳይል በሰላም ተጠናቋል። በወቅቱ በየመንገዱ እንዳስተዋልነው፤ አስተባባሪም፣ ፈታሽም ቄሮዎች ነበሩ። ኃላፊነት ወስደው በሰሩት ሥራ ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል። ታዲያ አሁን ምን ሆኑ?
አሁንም ቄሮ ያንን ሥራ መሥራት አለበት። ቄሮ አመጣው የተባለው ለውጡ ወቀሳ ውስጥ ሲገባ ለምን ዝም ይላል? ምክንያቱም ሲታገለው በነበረው ሥርዓት ይፈጸሙ የነበሩ ጥፋቶች ተደገሙ። የዛሬ ስሜት ለነገ ታሪክ ሆኖ ይቀመጣል። ከለውጡ በፊት የነበረውን ሥርዓት እየወቀስነው ያለነው በሰራው ጥፋት ነው። ጥፋት እንዳይደርስ ቢከላከል ኖሮ ይሄ ሁሉ ወቀሳ ባልደረሰበት ነበር። አሁንም የመጣውን ለውጥ ቄሮ መጠበቅ አለበት። በተለይ ደግሞ ቄሮ ባለበት ኦሮሚያ ውስጥ መሆኑ ነገ ሊያስወቅሰው ይችላል። አባ ገዳዎች ልጆቻቸውን መቆጣትና መምከር አለባቸው።
ይሄን ለማለት የሚያስችለን ቄሮ ማድረግ ስለሚችል ነው። ከአካባቢያቸው የተነሳን አመጽ ምንጩን አያውቁትም? እነዚያን ወጣቶች ማስቆም አይችሉም? ይሄ ነገር ነገ ከነገ ወዲያ ያስወቅሰናል ብለው መወያየት አይችሉምን? የንፁሃንን ህይወት ማጥፋት የሀጫሉን ፍትህ እንደማያስገኝ ማንስ ይስተዋል?
አንድ ግልጽ ነገር አለ። የሀጫሉ ገዳዮች ዓላማ ሀጫሉን መግደል ብቻ አይደለም፤ ቀጥሎ የሚመጣውን ነገር ቀድመው አስልተው ነው። የሚደርሰው ጥፋት የእነርሱ ስኬት ነው። ታዲያ ጥፋቱን አለማስቆም ገዳዮቹን መተባበር አይሆንምን? የገዳዮችን ዓላማ ማሳካት እኮ ነው።
ካለፉ ጥፋቶች እንማር። አሁን ላይ መወቃቀሻ የሆነው ባለፉት ሥርዓቶች የተሰሩ ጥፋቶች ናቸው፤ ስማቸው በበጎ እንዲነሳ የሚያደርጋቸውም በጎ ሥራቸው ነው። ባህሪው ሆነና ከበጎ ሥራ በላይ ጥፋት ደግሞ ይጮሃል። በነጭ ወረቀት ላይ አንዲት ጥቁር ነጥብ ጎልታ ትታያለች። በቄሮ ትግል የመጣው ለውጥ የቱንም ያህል ስኬታማ ቢሆን ጥፋቶች ይሸፍኑታል። እነዚህ ጥፋቶች በታሪክ ሰነድ ላይ ይቀመጣሉ። በአንድ ወቅት እንዲህ ተደርጎ ነበር እያሉ ጮኸው ይናገራሉ። እነዚህን ነገሮች ማስቀረት የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የህዝብ ኃላፊነት ነው። የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ቢሆንም ተሰሚነት ያለውና ለውጡን ያመጣው ቄሮ ደግሞ በጻፈው ደማቅ ታሪክ ላይ አጥፊዎች ጥላሸት እንዳይቀቡበት መጠበቅ አለበት።
በአንድ አካባቢ የሚደርስን ጥፋት የአካባቢውን ህዝብ አይወክልም የሚባል ነገር ብዙም አያሳምንም። ጥፋት ለማድረስ ሲጠራሩ ዝም ማለት ከተባባሪነት አያንስም። ‹‹ያ ሁሉ ጥፋት ሲደርስ የፀጥታ ኃይሎች የት ነበሩ?›› የሚለው ጥያቄ የብዙ መገናኛ ብዙኃን ጥያቄ ነበር። ጓዳ ጎድጓዳ ሁሉ እየተፈለገ በድንጋይ ሲቀጠቀጥ ያልተከላከለ የፀጥታ ኃይል ቢወቀስ አይደንቅም።
ከፀጥታ ኃይልም ሆነ ከማንም በላይ ግን የአካባቢው ወጣቶችና የአካባቢው ሽማግሌዎች የበለጠ ተሰሚነትና ተፈሪነት አላቸው። አባቶች በምክር ወጣቶች በውይይት ይከላከሉ። ቄሮም ያመጣውን ለውጥ ይጠብቅልን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
ዋለልኝ አየለ