ጤንነቱ የተጠበቀ የስራ ፍላጎቱ እና ታታሪነቱ የተረጋገጠ በቂ ትምህርት እና ስልጠና ያለው እርሶ አደር መፍጠር ለግብርና ልማት ወሳኝ ነው። ታዲያ የዚህን ሃይል ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያስችለው የቴክኖሎጂ አቅርቦት ካላገኘ፣ ቴክኖሎጂው በሚፈለገው መጠን ካልተባዛ እና በአግባቡ ወደ አምራቹ ካልተሰራጨ የሚፈለገው እድገት ሊገኝ አይችልም። በመሆኑም የቴክኖሎጂ አቅርቦት የብዜት ስርጭትን የማሻሻል ጉዳይ የህዝቡን የማምረት አቅም ከማጎልበት ተግባር ተነጥሎ የማይታይ ጉዳይ ነው ።
በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኘው ወጣት ተምሮ አርሶ አደር ለመሆን ፣ በግብርና ሙያ ሰልጥኖ በዚህ መስክ ለመሰማራት ፍላጎት አይታይበትም። የግብርና ስራን የድህነት እና የኋላቀርነት መገለጫ አድርጎ የሚወስደው ወጣት ተማሪ ብዙ ነው። የጉልበት ስራን የሚጠየፍ ተምሮ እንደግብርና ባሉ የጉልበት ስራን በሚጠይቁ የስራ መስኮች ለመሰማራት የማይፈልገው በርካታ ክፍል ነው። በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት እና የሚያሳድገው ባህል፣ የጉልበት ስራን ጨምሮ የስራ ክቡርነትን የሚያሳምንና የግብርና ሙያም እንደሌላው ክቡር መሆኑን የሚያስገነዝብ አለመሆኑ አንዱ መሰረታዊ ምክንያት ነው። በግብርና ስራ ላይ ተሰማርተው የሚያየው አርሶ አደርም በድህነት እና በኋላቀርነት የሚገረፍ መሆኑ ተጨባጭ ልምዱ እና ተሞክሮው የሚያረጋግጥለት ነገር በግብርና ስራ መተዳደር ለድህነት እና ለኋላ ቀርነት የሚያጋልጥ መሆኑ ይታመናል።
ወጣቱ ትውልድ በግብርና ሙያ የመሰማራት ዝግጁነት እና ስራን በታታሪነት የመስራት ፍላጎት እንዲያድርበት ካልተደረገ በስተቀር ቀጣይነት ያለው ፈጣን የግብርና ዕድገት ሊታሰብ አይቻልም። ከዚህ አኳያ ወጣቱ ትውልድ ያለበትን ችግሮች ከምንጫቸው ማድረቅ መቻል ይኖርብናል። ትምህርት ቤቶች የስራ ክቡርነት የሚያሳምኑ፣ ለግብርናም ሆነ ለሌላ የስራ መስክ የሚያዘጋጁ የስራ ታታሪነት ባህልን የሚያዳብሩ ሊሆኑ ይገባሉ።
ትምህርት ቤቶች አሁን እንዳለው በአጠቃላይ የጉልበት ስራን በተለይ የግብርናን ስራ የሚጠየፍ ወጣት በመፍጠር እስከተሰማሩ ድረስ ፋይዳ ያለው በገጠርም ሆነ በሌላ የልማት ስራ መስክ ውጤት ማምጣት ሊታሰብ አይችልም። ከዚህ አኳያ የትምህርት ቤቶች በተለይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሰራር፣ የትምህርት አሰጣጥና የሚያሰርጹበት ባህል ተፈትሾ መስተካከል ይገባዋል።
በአጠቃላይ የሰው ሃይልን የማምረት አቅምን ለማጎልበት በግብርና ስራ ላይ ለመሰማራት ዝግጁነት ያለው ታታሪ ሰራተኛ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ከቦታ ቦታ ቢለያይም በነባሩ አርሶ አደር ትውልድ አካባቢ ከዚህ አኳያ ከፍተኛ ችግር አለ ሊባል የሚችል አይደለም። አርሶ አደሩ በግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ ኑሮውን በቀጣይነት የሚያሻሽልበት እና ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠር የግብርና ስራ ዝግጁነትንና ተነሳሽነቱን መጠበቅ እና ማሻሻል የሚገባ ቢሆንም ከዚህ አኳያ ልዩ ትኩረት የሚጠይቀው የወጣቱ ትውልድ ጉዳይ ነው። ወጣቱ ትውልድም በግብርና ስራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት በትጋት የመስራት ዝግጁነት እንዲኖረው ለማድረግ ትምህርት ቤቶች ታታሪ አምራች ዜጋን የሚያፈሩ እንዲሆኑ ማድረግ ፣ የተማረውና በግብርና ስራ ላይ የሚሰማራው ወጣት ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ ይዞ በሌላ የስራ መስክ ከሚሰማራው የማይተናነስ ገቢ የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
በዚህ ዘመን ሁሉም ወጣት ግብርናን የተጠየፈና እና በዚያ ለመተዳደር የማይፈልግ አይደለም። ወጣትነቱን ከታታሪነት እና ከዝግጁነት ጋር በማጣመር በግብርና ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ የሆነ ወጣት ተሞክሮን ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
ወጣት አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ ይባላል። በአዋሳ ከተማ በቱላ ክፍለ ከተማ ኮተጀብሳ በተባለ ቀበሌ ነዋሪ ነው። አርሶ አደር ክፈለ ድጋፍ ሳያገኝ በፊት በማሳው ላይ ቢለፋም የልፋቱን ያክል ውጤት ሳያገኝ ኖሯል። ይህም ከሳይንሳዊ የግብርና አሠራር ዘዴ አውቀት ማነስ የተነሳ ነው።
እውቀት ታታሪነት እና ዝግጁነትን ያለው ወጣቱ አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ በጋራ በመሆን የጎደለውን እየሞሉለት አርሶ አደሩ ያልደረሰበትን የሳይንሳዊ አሰራርን እንዲከተል እየደገፉት በጋራ ባሳዩት ትጋት በምርት እና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል። የተገኘውም ውጤት በዚያው ቀበሌ እና በአጎራባች ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ በጎ ተጽዕኖ በመፍጠር ብዙ የአሰራር ለውጦች እንዲመጡ አድርጓል። ለብዙ አርሶ አደሮችም ለለውጥ መነሳሳት እና መበረታታትም ምክንያት ሆነዋል። ወጣት አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ የስራ ውጤት ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደመማሪያ እና ማሳያ እንዲሆን ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ልምዳቸው
ተቀምሮ ከተሰራጨላቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው፤ አርሶ አደሩ የሚኖርበት እና የሚሰራበት ቀበሌ የአየር ፀባይ ቆላማ ሲሆን የመሬቱ ከፍታ ደግሞ 1 ሺህ 708 ሜትር ነው። የአካባቢው የአፈር አይነት አሸዋማ ሲሆን ቅመራው የተሰራባቸው የሰብል ዓይነቶች ጥቅል ጎመን፤ ቃሪያ እና ፎሶሊያ ናቸው።
ዝግጅት
መሬት በግል ተያዘም በመንግስት አጠቃቀሙ የተስተካከለ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፤ እያንዳንዱ ሜትር መሬት ለልማት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት በምትችልበት ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለች መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለቤት እና ለከተማ ልማት ማዋል የሚገባው መሬት የግጦሽ መሬት ከሆነ የደንና የግጦሽ መሬት መሆን የሚገባው ከታረሰም መታረስ የሚገባው መሬት ከተማን ከተስፋፋበት ወይም ግጦሽ መሬት እንዲሆን ከተደረገ ከመሬቱ ማግኘት የምንችለውንና ማግኘት የሚገባንን ልማት ስለማናገኝ አጠቃላይ ልማቱ መሰናከሉ እና መጓተቱ የማይቀር ይሆናል። እያንዳንዳንዱ ሜትር መሬት የበለጠ ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት ስራ ላይ መዋሉ ዋነኛ ምክንያት ነው።
ወጣት አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ ያለውን መሬት በአግባቡ ያለአንዳች ማባከን በማረስ የሚጠቀም ትጉህ አርሶ አደር ነው። ታዲያ ያለውን መሬት ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ባደረገለት የትምህርት እና የዘር ድጋፍ መሰረት ለዘር ምቹ አድርገዋል።
ወጣቱ አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ ያለው የማሳ ስፋት 1 ነጥብ 04 ሄክታር ሲሆን እርሱንም የማሳ መሬት መምሪያው በሰጠው ትምህርት መሰረት ሳይንሳዊ በመሆነ መንገድ ለሚፈልገው የዘር ዓይነት ቦታውን አከፋፍሏል። አርሶ አደሩ ከመምሪያው በአገኙት የእውቀት ድጋፍ መሰረት
ያለውን መሬት በመከፋፈል ለጥቅል ጎመን ዜሮ ነጥብ ሰባት አምስት ሄክታር፤ ለፎሶሊያ 0 ነጥብ 05 ሄክታር፤ ለቃሪያ ዜሮ ነጥብ ሁለት አራት በማከፋፈል አዘጋጅቷል።
በአጠቃላይ በማሳው ላይ ጥቅም ላይ የዋለ የአፈር ማዳበሪያ በሄክታር ኤን ፒ ኤስ 4 ነጥብ አምስት ኩንታል፤ ዩሪያ 5 ነጥብ 5 ኩንታል እና ኮምፖስት 60 ኩንታል የተጠ ቀሙ ሲሆን የተዘራው የአትክልት ዓይነትና ሁሉንም ኪሎ ግራም በማድረግ ዘርቷል ነበር። ይህም የማሳ ዝግጅት እና የግብዓት አጠቃቀም ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደ ማሳያ የቀረበ እንዲሁም ተቀምሮ እንዲጠቀሙበት የተደረገ የአርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ የትጋት ስራ ውጤት ነው። ዝግጅቱም ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ በሆኑ ምርታማነት በመጨመር ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ነው።
የዘር አዘራርና የአፈር ማዳበሪያ አጨማመር
አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ የዘር አዘራር ወይም የተከላ ሂደት መጠን እንደ ሰብሉ ዓይነት መስመሮችና ዘሮች ተክሎች መካከል ርቀቱን ጠብቆ መዝራትን አከናውነዋል፤ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀሙም ሁሉንም ኤን ፒ ኤስ በማሳ ዝግጅት ጊዜ ያደረጉ ሲሆን ዩሪያ ከተከላ ጊዜ ጀምሮ እስከሚቀጥሉት 7 ቀናት የሚጨመር ነው።
ዘመናዊ የግብርና መሳሪያ ባይኖራቸውም ብርቱ እና ታታሪው አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ የኩትኳቶ ክንውናቸውን በእጅ በመኮትኮት የሚሰሩ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ እየተከታተሉ አረምን የማስወገድ ስራ ይሰራሉ። የአረም ቁጥጥር ክንውኑም በተሰጠው ስልጠና መሰረት እንደዘራው የዘር ዓይነት የሚለያይ ሲሆን ፎሶሊያ 4 ጊዜ፤ ለጥቅል ጎመን 3 ጊዜ፤ ለቃሪያ ደግሞ ስምንት ጊዜ አድርጓል። የውሃ አጠቃቀም በየሁለት እና ሶስት ቀን የሚያጠጣ ሲሆን አርሶ አደሩ የአረም ቁጥጥር በጊዜ መከናወን ለምርት መጨመር ከፍተኛ አዋጭነት ስላለው ከሶስተኛው ሳምንት ጀምሮ አረም ቁጥጥር ያደርጋሉ። አርሶ አደሩ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ጋር በመተባበር ደግሞ የተባይ መከላከልና ቁጥጥር ክንውን እንደ ማንኮዜብ ዱቄት ፤ ዳይመቴኤት፤ አግሮታይት፤ ኮሳይድ እና የመሳሰሉትን ተጠቅመዋል። ሌላው አርሶ አደሩ የተጠቀሙባቸው ቴክኖሎጂ ዓይነቶች የውሃ አማራጭ ሲኖሩ የመጀመሪያው ዓይነት ዘመናዊ ጉድጓድ ብዛቱም 2 ሲሆን 2 የውሃ መሳቢያ ሞተር ተጠቅመዋል፤ ጉልበት አንዱ ግብዓት ሲሆን ይህም አርሶ አደሩ ብዛታቸው ሶስት የሚሆን የቤተሰብ ጉልበት የተጠቀሙ ሲሆን ወደ 10 የሚሆኑ ወንድ እና ሴት የቀን ሰራተኞችንም ጉልበት ተጠቅመዋል። ይህም ሌላኛው የአርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ተሰውዶ የተቀመረ የወጣቱ የልማት አርበኛው የትጋት ውጤት ነው።
ውጤት
አርሶ አደሩ በአደረገው ከፍተኛ ትጋት ያገኘው ምርት እጅግ መልካም ነው። በዚህም ቃሪያ 16 ነጥብ 8 ኩንታል ፣ጥቅል ጎመን እንዲሁም ፎሰሊያ 4 ኩንታል ለማግኘት ችለዋል፤ ትጋት፣ ላብ ጥንካሬ እና ዝግጁነት መልሶ ይከፍላል የሚባለው በአርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ ቤት እና ማሳ ላይ ይታያል።
በአገኙትም ምርት እና ትርፍ ቤተሰብ መርዳት ችለዋል፤ በተለያዩ የድጋፍ ዓይነቶች ጎረቤቶቻቸውን ጠቅመዋል ፤ ለከብት መኖነት ጥቅም የሚውል ተረፈ ምርት ያገኙ ሲሆን ይህንን ሁሉ ተጠቅመው ትርፍ ካፒታል ማስመዘገብ ቁጠባ ማስቀመጥ ችለዋል ።
ልክ እንደ ወጣት አርሶ አደር ክፈለ ጋትሶ ወጣቶችን ወደ ግብርና ስራ በማስገባት ያላቸውን አቅም እውቀት በመጠቀም ስኬታማም እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ታላቅ የልማት ድል ፣ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ እና ህዝቡም ከዚሁ ልማት በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል።
ችግር
አርሶ አደሩ ያጋጠመው ችግር ምርቱን ከአመረተ በኋላ የሚሸጥበት ቦታ አሊያም የገበያ ትስስር ሲሆን በአካባቢው ከአለው የሸማቾች ህብረት ጋር በማስተሳሰር ይህ ችግሩ እንዲፈታ የምርምር ማዕከሉ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል። በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ ትጉህ አርሶ አደሮችን እየደገፍን ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ራሷን የቻለች አገር መፍጠር ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2012
አብርሃም ተወልደ