ስድስት ልጆችን ከወደቁበት አንስተው አሳድገዋል። አምስቱን አሁንም ድረስ ከሥራቸው አድርገው እየተንከባከቡ ይገኛሉ። ሶስቱን አስተምረው ለቁም ነገር ሲያበቁ ሁለቱን ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አድርገዋል።
‹‹ልጅ የአገር ሀብት ነው›› ይላሉ። ዛሬም ቢሆንላቸው ሌሎችን ከወደቁበት ቢያነሱ እንደሚደሰቱ ይናገራሉ። ሆኖም በህመም ምክንያት ይህንን ማድረግ አልቻሉም። ነገር ግን የእርሳቸውን ፈለግ የሚከተሉ መልካም ዜጎች እንዲኖሩ ይሻሉ። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንና መሰል ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉን ወይዘሮ ጥሩወርቅ ደስታን ለዛሬ ‹‹የህይወት ገጽታ›› እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ!
ልጅነት
በትግራይ ክልል ዓድዋ ከተማ መኮንኖች ካምፕ ውስጥ በ1943 ዓ.ም ህዳር 21 ቀን 9፡00 ሰዓት ላይ ነበር ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ሆነው ወይዘሮ ጥሩወርቅ የተወለዱት። እድገታቸውም በዚያው በካምፕ ውስጥ ነበር።
አባታቸው ወታደር በመሆናቸው ቤት አይውሉም። ግን በመጡ ቁጥር የሚሰጧቸው ፍቅር ዘወትር ከህሊናቸው አይጠፋምናም የቤተሰባቸው ፍቅር እርሳቸውም ሌሎችን በተመሳሳይ እንዲወዱ መንገድ ከፍቶላቸዋል። አባት ቤት አምሽተው ሲገቡ ልጃቸውን ከእንቅልፋቸው ቀስቅሰው አብረዋቸው እንዲመገቡ ያደርጋሉ። ይህ ትዝታ አሁንም በልባቸው አለ። አብሮ መብላትና መጠጣት ባህሪያቸው የሚጀምረው ከዚህ ነበር።
እንግዳችን በባህሪያቸው ዝምተኛ ግን በቁምነገሮች ላይ ቀድመው የሚገኙና መፍትሄ አፍላቂ ናቸው። መመራመር የሚወዱና አዲስ ነገር ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉም ጭምር። የሚሰሯቸው ሥዕሎች በተለይ ለየት ያደርጋቸዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ ደግነት አብዝቶ የተቸራቸውና ያላቸውን ሰዎች ማካፈል የሚወዱም ነበሩ። ወላጆቻቸው ያጡ የእናታቸውም ሆኑ የአባታቸው ቤተሰቦች ከእነርሱ ጋር ስለሚኖሩ እንደ እህትና ወንድም ሁሉን እየተጋሩ ነው ያደጉት።
የእኔ ብቻ የሚሉት ነገር የላቸውም። በቤት ውስጥ ከሠራተኛ ጋር ሳይቀር ልብስ ተጋርተው እንደሚለብሱና አብረው መብላትን እንደሚወዱ ይናገራሉ። እናታቸው በመማር ፣ ንጽህናን በመጠበቅና የተሻለ ነገር ተስፋ አድርጎ በመጓዝ ያምናሉና ልጃቸው ይህንን መርህ ተከትለው እንዲያድጉ አድርገዋል።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ አስተዳደጋቸው በካምፕ ውስጥ በመሆኑ ከሁሉም ብሔር ብሄረሰብ ከመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ለመተዋወቅ እድሉን አግኝተዋል። የአገራችንን የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲችሉም አስችሏቸዋል። ጎረቤቶቻቸው በእነርሱ ህይወት ውስጥ ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል ይህም በመልካም ስነምግባር እንዲቀረጹ እረድቷቸዋል።
‹‹እናታችን አንባቢና አስተዋይ በመሆኗ የምንፈልገውን ከመከልከል ይልቅ በጥበብና በብልሃት እንደማያስፈልገን ታስረዳናለች። ከሰዎች ጋር በገደብ ቀርበን እንዴት ደስተኛ መሆን እንደምንችልም ትነግረናለች። ከዘመኑ ጋር እንዴት መራመድ እንደሚገባን፣ ወቅታዊ ነገሮችን ሰምተን እንዴት መረዳት እንዳለብንም በፍቅር ታስተምረናለች›› በማለት በስነምግባር ታንፀው ለማደጋቸው መሰረት የእናታቸው ጥረት መሆኑን እየጠቀሱ።
እንግዳችን የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው ብዙ ኃላፊነቶችን ይሸከሙ ነበር። በቤት ውስጥ በብዛት ባይፈቅድላቸውም የተለያዩ ሥራዎችን ይሰራሉ። የእጅ ሥራ ውጤቶች እየሰሩ ቤታቸውን ያስውቡ ነበር።
ስዕል መሳልና ማንበብ መለያቸው የሆነው ወይዘሮ ጥሩወርቅ፤ ያዩትን፣ የሰሙትን በስዕል ማስቀመጥ ተሰጧቸው ነበር። ዝምተኛ በመሆናቸው የእድሜ እኩዮቻቸው ሲጫወቱ ማየት፣ የውሃ ዋና ሲሄዱ የእነርሱን ልብስ መጠበቅ ሥራቸው ነበር። በአካባቢው ዘንድ የተለየ አክብሮት ነበራቸው። ይሄ የመጣው ከዝምተኝነታቸውና ከጥሩ ስነምግባራቸው ነበር። ስማቸውም ከግብራቸው እንዲገናኝ ጥሩ መነሻ ነበር፤ አመለ ወርቅ፣ ጥሩ ወርቅ…. የሚል መጠሪያን አግኝተዋል።
እንግዳችን መምህር የመሆን ህልም ነበራቸው።የተቸገረ ማየትን ፈጽሞ አይፈልጉም። በተለይ የተቸገሩ አዛውንቶችን ሰብስቦ የመርዳት ራዕይ ነበራቸው።
ትምህርት
ፊደልን የቆጠሩት በእናታቸው አማካኝነት ቤት ውስጥ ሲሆን፤ ዘመናዊውን ትምህርት ደግሞ በአድዋ ንግስተ ሳባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምረዋል። ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉትን ክፍሎች ደግሞ በሚሲዮን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ዳግም ወደ ንግስተ ሳባ በመመለስም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የቀጠሉት ደግሞ ወደ ኤርትራ በማቅናት አስመራ መምህራን ማሰልጠኛ ነው። በዚህ ምክንያት የልጅነት መምህር የመሆን ህልማቸውና የቤተሰብ ፍላጎት ተሳክቷል። በዚህም በሙያው በዲፕሎማ በማዕረግ አጠናቀዋል። ከዚያ በኋላ ትምህርት አልቀጠሉም። በሙያቸው ወደ ሥራ ዓለም ነበር የገቡት።
ከደብረብርሃን እስከ አሜሪካ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ ዘርዓያቆብ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ የሥራ ምዕራፋቸውን አሃዱ ብለው ጀመሩ። ለ11 ዓመታት በዚህ ሙያ በከተማዋ አገለገሉ። በጊዜው የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያን በመቆጣጠሩና እርሳቸውም አንዳንድ ድርጊቶችን በመቃወማቸው በደብረብርሃን ብዙ መቆየት አልቻሉም። ትግሪኛ ስለሚናገሩ ኤርትራዊ ተብለው ስለተፈረጁም ብዙ ክትትል ይደረግባቸው ነበር። በወቅቱ ለሶስት ቀናት ለእስር ተዳርገው ነበር። በዚህ የተነሳ ነብሳቸውን ማዳን ነበረባቸውና የሚወዷትን ከተማና ሙያ ጥለው ወደ አዲስ አበባ ተሰደዱ።
በአዲስ አበባ አቃቂ በኪራይ ቤት እየኖሩ በገላን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስተማር ሥራቸውን ቀጠሉ። ለአራት ዓመታትም አገለገሉ። ግን ያ የቀደመ
የመንግሥት ክትትል አሁንም ነበርና በዚህ ምክንያት ማስተማሩን ለመተው ተገደዱ። ኑሯቸውን ለመምራትም ምግብ ቤት ከፍተው መስራት ጀመሩ። ይህን ቢያደርጉም ከደርግ ስለላ ግን አልዳኑም። የህውሃት ሰብሳቢና የፖለቲካ አስፈጻሚ ነች በሚል ለብዙ ጊዜያት ስለላ ሲደረግባቸው እንደቆየም ይናገራሉ።
በዚህ ምክንያት አገራቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ ገቡ። ወደዚያ ያቀኑት በልጃቸው አማካኝነት ነበር። ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሳይሰሩ መኖርና ቁጭ ብሎ መቀለብ በፍጹም የማይወዱት ነገር ነው። በመሆኑም አሜሪካ በገቡ ሦስት ቀናቸው ነበር የሥራ ቅጥር ጋዜጣን ማገላበጥ የጀመሩት። ወዲያው ባያገኙም ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በሄዱ ጊዜ በዘመዶቻቸው አማካኝነት በቀላሉ ሥራውን ማግኘት ችለዋል።
ልጆችን መንከባከብና ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰል የመጀመሪያ ሥራቸው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠሩት አራት ሰዎች ያሉበት አንድ ቤተሰብ ውስጥም ነበር። ስለዚህም ቤተሰቡን ለማገዝ ምንም አልተቸገሩም ነበር። በሥራቸውና በሚሰሩበት ቤተሰብ ደስተኛ ቢሆኑም አገራቸውን ትተው የሰው አገር ሎሌ መሆናቸው ይቆጫቸው ነበር።
‹‹አገር፣ ልጆች ፣ ቤተሰብ ያለኝ ነኝ። በገንዘብም ተቸግሬ አልነበረም ወደ ሰው አገር የሄድኩት። ስለዚህም ይህንን ደስታ እየተነጠቅሁ በዚያ መቆየትን ጭራሹን አልፈለኩትም። እናም በሁለት ነገሮች ማን እንደ አገር ብዬ ተመለስኩ›› የሚሉት ባለታሪኳ፤ የሚሰሩበት ቤት ልጅ የሆነው የአምስት ዓመት ታዳጊ በተለይ ስሜታቸውን የነካ አንድ ንግግሩን እንደማይረሱት ይናገራሉ። ‹‹አንቺን በጣም እወድሻለሁ ሳድግም ማግባት የምፈልገው አንችን ነበር። ግን ጥቁር ስለሆንሽ አይፈቀድልኝም›› ያላቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ ትልቁን ውሳኔ እንዲያሳልፉ መነሻ ሆኗቸዋል።
ይህና ሌሎች ምክንያቶች ምሬት ስለፈጠረባቸውና አገራቸውን ስላስናፈቃቸው የመኖሪያ ፈቃድ እንኳን ሳያወጡ ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱም አድርጓቸዋል። ከውጭ ከተመለሱ በኋላ አዲስ አበባ ቤት ሰርተው ነበርና በዚያ ቆዩ። ሆኖም ደብረብርሃን የነበረው የባለቤታቸው ወንድም ሆቴል በጨረታ ሊሸጥበት ስለነበር በራሱ እጅ እንዲቆይ ቤታቸውን መሸጥ ግዴታ ሆነባቸው። በተረፋቸው ገንዘብ ደግሞ የተለያዩ ሥራዎችን መስራት ጀመሩበት።
ወቅቱ ባለቤታቸውን ያጡበት ጊዜም ስለነበር በጣም እንዲፈተኑ አድርጓቸዋል። ይሁንና በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጡ ስላልሆኑ በሥራ ወደፊት ተጉዘዋል። ምግብ ቤት ከፍተው እየሰሩ ኑሯቸውን ወደነበረበት መመለስም ችለዋል። ከዚያም አልፈው የራሳቸውን ቤት ሰርተው መኖር እንደጀመሩና ለሌሎች መድረስ እንደቻሉም አጫውተውናል።
ስድስት ዓመታትን ዳግም በደብረብርሃን ካሳለፉ በኋላ በሁለት ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ የሚያወሱት ወይዘሮ ጥርወርቅ፤ የመጀመሪያው ስድስት ህፃናት እያሳደጉ ስለነበር ልጆቹ በአካባቢው ማህበረሰብ የስነልቦና ጫና እንዳይደርስባቸውና ነጻ ሆነው ያድጉ ዘንድ ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው መጡ።
በዚሁ አጋጣሚ ደግሞ በንግድ ሥራ ላይ መንግሥትንና ነጋዴውን የሚያስተሳስር አንድም ተቋም ባለመኖሩ የተነሳ የንግድ ምክርቤትን ለመመስረት እድሉን አገኙ። ከንግድና ኢንዱስትሪ ሰራተኞች ጋር በመሆን ምክር ቤቱን ለማቋቋም አዲስ አበባ የመግባታቸው ሌላኛው ምክንያት ነበር። በዚህም በጣም የሚያስደስታቸውን ሥራ እንደሰሩም ይናገራሉ። በተለይም የንግድ ምክርቤቱን መመስረትና ለሶስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው ከምንም በላይ ያስደስታቸዋል።
ሌላው በደብረብርሃን ከተማ የከንቲባ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ለሁለት ዓመታት በነጻ ማገልገል ችለዋል። በዚህም ከተማዋን በተለይም በልማትና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በንግድ ዘርፉ የተሻለ አቅም መፍጠር ችለው ነበር። የመጀመሪያውን ‹‹ትንሳኤ ደብረብርሃን›› በሚል ባዛር እንዲዘጋጅ አድርገዋል።
የሚያሳድጓቸውን ልጆች ያገኙዋቸው በደብረብርሃን በሚሰሩበት ወቅት ነበር። ይህም ትልቅ የመንፈስ እረፍትና የሥራ ሰው እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። ከደብረብርሃን ሙሉ ለሙሉ እንደለቀቁ ኮተቤ አካባቢ የለመዱትን የምግብ ቤት ሥራ ነበር የጀመሩት። በዚህም ከምግብ ቤቱ አልፈው አዲስ አበባ ላይ ደረቅ እንጀራ ማከፋፈል ጀመሩ። እውቅናቸው እየሰፋ በመምጣቱም የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ በቀን አምስት ሺህ እንጀራ እንዲያቀርቡ ቢመረጡም አቅርቦቱን ለራሱ ማድረግ የሚፈልግ የዩኒቨርሲቲው ኮሚቴ ነበርና በአልተጠበቀ ሁኔታ ሌሎች አጋሮቹን ሰብስቦ ድንገት ውድቅ አደረገባቸው።
ቤት ንብረታቸውን ሸጠው ሥራውን ለመስራት እየተንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም ‹‹ምንም ዝግጀት አልተደረገም›› በሚል ጨረታው ውድቅ እንዲሆን ኮሚቴው ተፈራርሞ አስገባ። በዚህም የተበደሩት፤ የራሳቸው የሆነ ብዙ ንብረት ነገን ለመኖር ሲባል ወጥቶ ያለምንም ሥራ ውሃ በላው።
ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያሳድጓቸው ማሰብ ተሳናቸው። ከጭንቀታቸው የተነሳም ለህመም ተዳረጉ። በአጥንት መሳሳት ምክንያት አንድ እግራቸው ኦፕራሲዮን ተደረገ። ይህ ደግሞ አሁን ድረስ ለሌሎች ተስፋ እየሆኑ እንዳይቀጥሉ አገዳቸው። መንቀሳቀስ ባለመቻላቸውም የልጆቻቸውን ፍላጎት በሚጠብቁት ደረጃ እንዳያሟሉ ሆኑ። ይህ ሁሉ ቢሆንባቸውም ተስፋ ነበራቸው። የእጅ ጥበባቸውን በመጠቀም ልጆቻቸውን ማስተማርና ለቁም ነገር ማድረስ ይችላሉ። ስለዚህም ቀጥታ ወደ ጥልፍ ሥራ ገቡ።
ልጆቹንም አስተማሯቸውና እንዲያግዟቸው አደረጉ። በዚያ ላይ ችግኝ እያፈሉ ይሸጡ ነበርና ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ቢሆንም ደስታቸው ግን እንዳለ መቆየት ቻለ። በዚያ ላይ የወለዷቸው ልጆች በውጭ አገር ስለሚኖሩ ትንሽም ቢሆን ይልኩላቸው ነበርናም
አገር ስለሚኖሩ ትንሽም ቢሆን ይልኩላቸው ነበርናም ይህም አግዟቸዋል። ዛሬ ደግሞ ልፋታቸው ከግብ ደርሶ ሦስቱ ልጆች ተምረው ሥራ በመያዛቸው የክፉ ቀን መከታ ሆነዋቸዋል። ሁለቱ ልጆች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ናቸው። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አሁን በቤት ውስጥ ስለሆኑ በተለያየ መልኩ እያገዟቸው ይገኛሉ። በዚህም እግዚአብሔርን እያመሰግኑ በደስታ እየኖሩ እንደሆነ አጫውተውናል።
የልጅ ፍቅር
ገና በልጅነታቸው ነበር ልጅን የመውደድ ባህሪን ልምዳቸው ያደረጉት። እናታቸው ለሌሎች መኖርን፣ አጥብቀው ይወዳሉ። በተለይ በእጃቸው ተመግበው ለቁምነገር ሲደርሱ ሲያዩ ይደሰቱ ነበር። እርሳቸውም ያንን እያዩ አድገዋል።
እንግዳችን ወላጅ አልባ ልጆችን ሰብስቦ ለማሳደግ ምክንያት የሆናቸው በደብረብርሃን ከንቲባ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸው ነበር። ማዘጋጃ ቤት ለሥራ በሚመላለሱበት ወቅት የሚያዩት ነገር እንደእርሳቸው ልጅ ወዳድ ለሆነ ሰው በጣም ያማል። በኤች አይቪ ምክንያት ያለ እናትና አባት የሚቀሩ ልጆችን፤ በችግር ምክንያትም የሚጣሉት ህጻናትን እንዲሁም የሚቸገሩትን ሲመለከቱ ዘወትር ያዝኑ ነበር።
በዚህ ምክንያት ከማዘን አልፈው መፍትሄ ማምጣት እንዳለባቸው ያሰላስሉም ጀመር። በየቀኑ ከጓደኞቻቸው ጋርም ያወራሉ። አንድ ቀን ግን ይህንን የሚፈታላቸው ድምጽ ሰሙ። ኤስ ኦ ኤስ ከሚባል ድርጅት ጋር ተገናኙ። ድርጅቱም በቋሚነት እርሳቸውን ወከላቸውና በደብረብርሃን ልጆችን መሰብሰብ ጀመሩ። የእኔም ድርሻ ሊኖርበት ይገባል ሲሉም አንድ ክፍል ቤት ከራሳቸው ቤት ላይ ወስደው ልጆቹን መንከባከባቸውን ቀጠሉ።
ድርጅቱ ወደ ውጭ ልጆቹን በመላክ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ፤ ቤተሰባቸውም እንዲታገዙ የሚያደርግ ሲሆን፤ ከመላው ኢትዮጵያ በማሰባሰብ የሚመጡ ነበሩ። ወደ ደብረብርሃን የሚመጡት ደግሞ በዙሪያው ካሉ ወረዳና የገጠር ቀበሌዎች አልፎ እስከ ሰቆጣ እንደሚደርስም አውግተውናል። በዚያ ላይ በጣም አሳዛኝና ታማሚም የሚሆኑበት አጋጣሚ ስለሚኖር በእነርሱ ሁልጊዜ ይረበሹ እንደነበር አይረሱትም።
ይህ ችግራቸው እንዳይቀጥል ለማድረግ የተቻላቸውን ያደርጉ እንደነበር የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ ብዙ እንክብካቤና ህክምና ስለሚደረግላቸው ወደ ነበረ ማንነታቸው ይመለሳሉ። ወደ ውጭ ሲላኩ ደግሞ ይበልጥ የኑሮ ሁኔታቸው የተሻለ ይሆንላቸዋል ይላሉ።
‹‹ድርጅቱ ከአምስት ዓመት በታች ያሉትን ብቻ ስለሆነ የሚፈልገው በየጊዜው አንዳንድ ልጅ ይተርፍ ነበር›› የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ፤ ስድስት ልጆችን የማሳደጉ ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ ላይ ያረፈው ድርጅቱ አልቀበልም በማለቱ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም አንድም ቀን ተማረው እንደማያውቁና ልጅ ጸጋ ነው ብለው ስለሚያምኑ በቻሉት መጠን ሁሉ ይደግፏቸው እንደነበር ያወሳሉ።
የኢትዮጵያ ልጅ የእኔም ነው
ወይዘሮ ጥሩወርቅ ልጅ ተፈልጎም ሳይፈለግም ይወለዳል ይላሉ። ከተወለደ በኋላ ግን አገር ነው። አገር ማለትም ሰው እንጂ መሬቱና ህንጻው አይደለም። እናም ከማህጸን ከወጣ በኋላ የአገር ልጅ እንጂ የግለሰብ ነው ብሎ ማመን አይገባም። ሁሉም ሰው ልጁ ለቁምነገር እስኪበቃ ድረስ የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት የሚል እምነት አላቸው ።
‹‹ልጅን በፍቅር ተንከባክበን ማሳደግ ከቻልን በምላሹ አገሩን ከመውደድ አልፎ ግለሰብን እስከመለወጥ ይደርሳል›› የሚሉት ወይዘሮ ጥሩ ወርቅ፤ እርሳቸው ቀደም ባለው ጊዜ ልጅ እንደነበሩ ዛሬ ደግሞ እናትና አያት መሆናቸውን እንደ ምክንያትነት ያነሳሉ። ቀጣዩ ትውልድም ‹‹እናት፣አባት እንዲሁም አያት›› ይሆናል የሚለውን እያሰቡ በእነርሱ ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።
ልጅ ነጻነት ሳይሆን ፍቅር ያስፈልገዋል። በልጅነት አዕምሮው ‹‹የፈለገህን አድርግ›› ብሎ መተው አይገባም የሚሉት ወይዘሮ ጥሩ ወርቅ ይህንን ካደረግን የተበላሸ መስመር ይዞ ያድጋል ይላሉ። በኋላ ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልፀውም፤ ማደግ ያለበት በእንክብካቤና በፍቅር እንዲሁም ህግን እያወቀ መሆኑን ይናገራሉ። ሁሉን ነገር እንዲያየው ሲፈቀድለት በገደብ፣ እርሱን በማይጎዳ መልኩ፣ ለአገሩ በሚተርፍበት ሁኔታ፣ የሰውን ክቡርነት እየተረዳም መሆን አለበት የሚል ጠንካራ እምነትም አላቸው።
‹‹እኛ እግር አጥበን፣ የታላቆቻችንን ጉልበት ስመን፣ በምርቃት ከፍ እንደምንል እያሰብን አድገናል›› የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ለዛሬው ማንነታቸው መሰረት የሆነው ይኸው መሆኑን እራሳቸውን ምሳሌ በማድረግ ይናገራሉ። የነገ ትውልድን መፍጠር የሚቻለውም እነርሱ ባደጉበት መንገድ መቅረፅ ሲቻል እንደሆነ ያሳስባሉ።
ወቅት አንድ ቦታላይ አይቆምም፤ ይቀያየራል በማለትም አባቶችና እናቶች በነበሩበት ባህልና ስርዓት እንዲሁም በነበሩበት ዘመን ሁኔታ ልጆቻችንን እንደዘመኑ ሆነን አሳድገናል። ቀጣዮቹም ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተመሳሳዩን ድርጊት መፈፀም እንዳለባቸው ይናገራሉ። ሁሉም አንድ የሚሆንበት የጋራ የፀና ሃሳብና ማንነት ሊኖረው ይገባል የሚል መልእክትም ያስተላልፋሉ። በተለይ በአገር፤ በሰውነት መደራደር የለባቸውም የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። አገር ከሌለ ማንም አይኖርም። የሰውን ክቡሩነትም ማስረዳትና ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም አገርን አገር የሚያደርገው ሰው መሆኑን እንደምክንያት ይጠቅሳሉ።
‹‹በመማር መለወጥም እንዳለ ማስገንዘብና አዕምሯቸው ላይ መስራት ያስፈልጋል›› የሚል ሃሳብ ያላቸው ወይዘሮ ጥሩወርቅ በተለይ ይህ አይነት ተግባር ከእናቶች በስፋት ይጠበቃል ይላሉ። ችግሮችን እንዲያዩና በራሳቸው እንዲፈቱ እድል መስጠትም ይገባል የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃሉ። የነበራቸውን ልምድ በማንሳት በእያንዳንዱ ነገር የእኔነት መንፈስ እንዲፈጠርለት እያደረጉ እንዲሰራ ማበርታትም ተገቢ ነው ይላሉ።
ገጠመኝ
የብሊሀርዝያ በሽታ ታማሚ ነበሩ። በዚህም የሐኪም ማስረጃ ይዘዋል። እናም ስፖርት መምህራቸው በትምህርት ክፍለጊዜው ‹‹የተግባር ልምምድ ካልሰራሽ›› በሚል ያስቸግሯቸዋል። ‹‹አይ መስራት አልችልም ታማሚ ነኝ›› ብለው የተሰጣቸውን ማስረጃ ሊያሳዩት ሲሉ ‹‹ቁጭ በይ›› አሏቸውና አርጩሜ ይዞ በመምጣት ደበደባቸው። በጊዜው እርሳቸው ዝም ስለሚሉ ምንም አላሉም ነበር።
ጓደኞቻቸው ለቤተሰብ ሄደው በመናገራቸው አባታቸው ወታደሩን አሰልፈው፣ ሽጉጣቸውን አቀባብለው መምህሩን ለመግደል መጡ። በዚህ ጊዜ እርሳቸው ርዕሰ መምህሩ ጋር ሄደው እያለቀሱ ለመኑት። አባታቸውንም እንዲያሳምናቸው ላኳቸው። አባብለውና ለምነውም እንደመለሷቸው አይረሱትም። ይህን አጋጣሚ መለስ ብለው ባስታወሱ ቁጥር ሁኔታው ፈገግ ያሰኛቸዋል።
ቤተሰብ
ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙት በማስተማር ሥራ ላይ ነበር። አዲስ አበባ ሲመላለሱ መኪና ያለው ሰው በመሆናቸው አብረው ይመጡ ነበር። በዚህም ቀረቤታቸው ጠነከረና ወደ ትዳር ተቀየረ። ሦስት ልጆችንና አራት የልጅ ልጆችን ማፍራትም ቻሉ። በፍቅርና በደስታ ዓመታትን አሳለፉ። ሆኖም በአንድ ጥቁር ቀን የቤተሰቡን ፍቅር ሳይጠግቡት የልጆቻቸው አባት ባለቤታቸው በህይወት ተለዩዋቸው።
ጠንካራ እናት በመሆናቸው ምክንያትም ልጆቻቸውን በሚገባ አሳደጓቸው። በዚህ ብቻ በቃኝ ሳይሉ አምስት ልጆችን ወስደውም በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈው አሳድገዋል። አስተምረዋል ለቁምነገር አብቅተዋልም። አሁንም እያስተማሯቸው ያሉ ሁለት ልጆች አሏቸው። እናም ለእነዚህ ልጆች መማርና ዛሬ ላይ መድረስ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ቤታቸውን ሸጠው እስከማሳደግ ደርሰዋል። ከሚወዱት ከተማ የወጡትም እነርሱን ነጻ ለማድረግ እንደነበር ያወሳሉ። ይህንን በማድረጋቸው ደግሞ አንድም ቀን ቆጭቷቸው አያውቅም። እንደውም ችግርን አይተው ማደጋቸው ለቀጣይ ህይወታቸው ጠንካራ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ይላሉ። ሰው ማዳን ቅድሚያ ስለሰጡና ልጆቹ ለአገራቸው እንዲደርሱ ስላደረጓቸውም ደስተኛ መሆናቸውን አጫውተውናል።
መልዕክት
ልጆችን ስናሳድግ በተለይ ያልወለድናቸውን ምንም እንዲሰማቸው ማድረግ የለብንም። የማንነት ጥያቄ እንዲኖርባቸው ልናደርግ አይገባም። ይልቁንም በፍቅር ማሸነፍ ልምዳችን ማድረግ አለብን። እኔ ይህንን በማድረጌ ከቤተሰባቸው ይልቅ እኔን መርጠው ከእኔ ጋር ተሳስረው እንዲኖሩ ሆነዋል ይላሉ። ሰዎች አልወለድኩም ብለው ከሚጨነቁ ልጆችን በጉዲፈቻ ተቀብለው በስነ ምግባር ኮትኩተው ቢያሳድጉ ትውልድን ከመቅረፅ አልፈው ለራሳቸው ደስታን ስለሚፈጥሩ ይህን በጎ ምግባር እንዲከተሉ ይናገራሉ።
‹‹መንግሥት ቢያደርገውና ቢፈታው ብዬ የማስበው በጉዲፈቻ ወደ ውጭ መላኩ ቢቀጥል የሚለውን ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ፤ ምክንያቱም ነጮች ባይወስዷቸው እንኳን በውጭ አገር የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን በልጅ ናፍቆት እየተሰቃዩ መሆኑን እንደ ምክንያት ያነሳሉ። በብዙ ችግር ውስጥ አገራቸው ላይ እያደጉ መልሰው ለአገር እዳ ከሚሆኑ ይህ ሁኔታ ተፈቅዶ ማንነታቸውን እየተረዱ በተሻለ መንገድ የሚያድጉበት አማራጭ ቢሰጣቸው ተስፋቸው ይለመልማል የሚል የግል ምልከታም አላቸው። ካደጉ በኋላ ደግሞ ለአገርና ለወገናቸው መድረስ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
‹‹በጣም በርካታ ህጻናትን ወደ ውጭ አገር ልኬ ብዙዎቹ የተሻለ ኑሮ እየኖሩና አገራቸውን በተለያየ ዘርፍ እያገዙ ይገኛሉ ለሌሎችም እነርሱን እየደረሱ ነው›› የሚሉት እንግዳችን፤ ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ጉዲፈቻ መስጠቱ እንዳለ ሆኖ ይህንን እድል ለማያገኙት ልጆች ደግሞ ወደ ሞትና ስቃይ ከምንመራቸው እንዲያልፍላቸው ወደ ውጭ አገር ብንልካቸው ይበጀናል የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ።
‹‹እኔ የምፈልግና የምሰጣቸው ይመስል በሚዲያ በቀረብኩበት ጊዜ ብዙ ሰዎች እየደወሉ ልጅ እንደሚፈልጉ ይነግሩኛል። ከ50 በላይ ሰዎችም ተመዝግበዋል። ግን መንግሥት መስመሩን ካልከፈተ ይህ ሊሆን አይችልም። እኔም ብሆን በአገር ውስጥ እንኳን ይህንን ማድረግ የምችልበት ሁኔታና አቅም የለኝም›› የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ፤ ስለዚህም መንግሥትን በጉዳዩ ላይ ሊያስብበት ይገባል ይላሉ።
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ልጅ በፍቃዳቸው ለማሳደግ ሲወስዱ አርአያነትን እንዳሳዩ አምናለሁ›› በማለትም፤ ሁሉም ሰው አንዳንድ ልጅ በአቅሙ መውሰድ ቢችል ህጻናት ሲንገላቱ አድገውም እዳ ሲሆን አናይም ነበር ይላሉ። በመሆኑም ልጆቻቸው ተምረው ለወግ ማዕረግ የበቁላቸውና ባዶ ቤት ታቅፈው ያሉ እናቶች የተቸገሩ ህጻናት ጉዳይ የእነርሱ መሆን አለበት ይላሉ። ልጅ ከማህጸን ከወጣ ሰው ነውና የእከሌ ነው የእከሌ ነው ሊባል አይገባውም። ልጁ የአገር ልጅ ነውና መራብና መጠማት የለበትም። በችግር ውስጥ ማደግም ግዴታው ሊሆን አይገባም። ስለዚህም እያንዳንዱ አገሬን እወዳለሁ የሚል ለዚህ ልጅ ተስፋ መስጠት ይኖርበታል በማለት ሃሳባቸውን ጠንካራ መልክት ባዘለ ጉዳይ ደምድመዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው