
የኮሮና ወረርሽኝ በድንገት ተከስቶ ዓለምን እንዳልነበር ባያደርግ፤ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የዛሬ ወር ጅማሬውን ያደርግ ነበር፡፡ ከሰው ልጅ ቁጥጥርና ዕውቀት በላይ ሆነና ግን የታቀደው ቀርቶ ስለ መካሄድ አለመካሄዱ ማረጋገጫ ሳይኖር ጊዜው ሊነጉድ የግድ ሆኗል፡፡ በቀጠሮው መሰረት ውድድሩን ማስኬድ ባይቻልም ግን ኦሊምፒክን ስለ መልካም እሳቤውና ሰላማዊነቱ ማክበሩ አስፈላጊ በመሆኑ ትናንት በመላው ዓለም ሲከበር ውሏል፡፡ ለዓመታዊው ክብረ በዓሉም እንደ ከዚህ ቀደሙ በአካል ሳይሆን በቴክኖሎጂ እገዛ የስፖርት ቤተሰቡ በአንድነት ቆሞ ነበር::
በእርግጥም አንድነቱ በተለየ መንገድ መታየት የጀመረው በወረርሽኙ ምክንያት ዓለም ደጁን በዘጋበትና ኦሊምፒክ ኮሚቴውም መራዘሙን ካሳወቀበት ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡ ከ50 ሃገራት የተወጣጡ 5ሺ የሚሆኑ ኦሊምፒያኖች እንዲሁም 243 ሚሊዮን የስፖርቱ ቤተሰቦች በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የማህበራዊ ገጾች ከቤታቸው ሆነው የሚያደርጓቸውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲያጋሩም ቆይተዋል፡፡ ትናንት በተከበረው የኦሊምፒክ ቀንም ከመላው ዓለም የተውጣጡ ኦሊምፒያኖች ለ24 ሰዓት ታላቅ የዲጂታል ንቅናቄ ፈጥረዋል፡፡ ይኸውም 23 የኦሊምፒክ ባለድል አትሌቶች ካሉበት ሆነው በ20 ሰከንዶች የሚሰሯቸውን አካላዊ እንቅስቃሴዎች በተንቀሳቃሽ ምስል አስቀርተው በቀጥታ ስርጭት በመቀባበል በኮሚቴው ድረገጽ በማጋራት ነው፡፡
በዓለም ትልቁ በሆነው በዚህ ዲጂታል እንቅስቃሴ ላይም ኬንያዊቷ የ1ሺ500 ሜትር ቻምፒዮና ፌይዝ ኪፕዬጎን፣ ፈረንሳዊው የምንጊዜም የኦሊምፒክ ቻምፒዮን
ማርቲን ፎርሳዴ፣ በፓራሊምፒክ ውሃ ዋና 13 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችው አሜሪካዊት ጄሲካ ሎንግ፣ የኦሊምፒክ ስደተኞች ቡድንን የምትወክለው ኢራናዊቷ የቴኳንዶ ስፖርተኛ ዲና ፖርነስ እንዲሁም ሌሎች ቻምፒዮኖችም ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ከአትሌቶችና ኮሚቴው ባሻገር የ2020 ቶኪዮ፣ 2024 ፓሪስ እና 2028 ሎስአንጀለስ ኦሊምፒክ አዘጋጆች፣ ብሄራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች፣ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት፣
የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የኦሊምፒክ አጋር ተቋማት የንቅናቄው አካላት እንደነበሩም ታውቋል፡፡
‹‹ኦሊምፒክ ለሰው ልጆች ጤንነት መልሶ መቋቋም እና ትብብር›› በሚል ሃሳብ በተከበረው በዓል፤ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹የዚህ ዓመቱ የኦሊምፒክ ቀን ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ ነው፡፡ ቢሆንም በትክክለኛው ወቅት የስፖርትን ኃይል የሚያሳይ፣
ተስፋን፣ መልካም እሳቤንና ጥንካሬን የሚያላብስ መልዕክት አስተላልፈናል:: አሁንም በህብረት በመሆን የኦሊምፒኩ መራዘም መላውን የሰው ዘር ከወረርሽኙ በፍጥነት እንዲያገግም መሆኑን እናሳይ›› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም ‹‹ዓለም በተመሳሳይ ሁኔታ በቫይረሱ በምትጨነቅበት በዚህ ወቅት የወደፊቱን ማወቅ ከባድ ነው፡፡ በጥንካሬ፣ በንቃትና በጤና ቆዩ፤ መልካም የኦሊምፒክ ቀን›› በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያም በኦሊምፒክ መድረክ በርካታ ድሎችን ካጣጣሙና በሜዳሊያዎች ካሸበረቁ ሃገራት መካከል ተጠቃሽ እንደመሆኗ ቀኑን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ ከሰሞኑ በዓለም አቀፉ ኮሚቴ እውቅና ያለው የምስክር ወረቀት የሚያስገኝ በቤት ውስጥ የሚደረግ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ውድድር ሲያካሂድ ነበር፡፡
ዕለቱ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሲከበርም፤ የስፖርት አመራሮች፣ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ብሄራዊ ቡድን የተመረጡ አትሌቶች፣ አንጋፋና የኦሊምፒክ ባለድል አትሌቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ ‹‹የጀግናው የአበበ ቢቂላን የኦሊምፒክ ጽናት ይዘን የኢትዮጵያን ስፖርት ትንሳኤ እናበስራለን›› በሚል ሃሳብም የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የስፖርት ማህበራት ለተወጣጡ 60 የቀድሞ ስፖርተኞች የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል፡፡
የኦሊምፒክ ቀን በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን፤ ዓላማውም ዘመናዊው ኦሊምፒክ የተጀመረበትን ወቅት (እአአ 1948) ለማስታወስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
ብርሃን ፈይሳ