አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ ማንኛውም ተቋምም ሆነ ስፍራ ለታሰበለት አላማ መዋል ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ በኪሳራ ይመዘገባል። አሊያም ደግሞ ጭርሱኑ መሰራት አይኖርበትም የሚል ድምዳሜ ላይ ሊያስደርስ ይችላል። ወደ አንድ ስፍራ ጉዳያችሁን ለመፈፀም ሄዳችሁ በቀላሉ እንድትስተናገዱ ታስበው የተዘጋጁ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚጠበቅባቸውንና የቁመናቸውን ልክ ሆነው ሳይገኙ ሲቀሩ ምን ይሰማችኋል? ተስፋ መቁረጥ? ብስጭት? ወይስ ሌላም ሌላም ደስ የማይሉ ስሜቶች? እውነቱን ለመናገር ከጠቀስኩት አንደኛው ሀሳባችሁን መስረቁ የማይቀር ነው።
ለዚህ መሰል ስሜት ደግሞ ዛሬ በስፋት የማነሳላችሁ የአገራችን ባንኮች ጥሩ ማሳያ ይሆናሉ። እንደሚታወቀው በአገራችን የሚገኙት የገንዘብ ጎተራዎቻችን ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ በየቦታው ቅርንጫፎቻቸውን በመሽቀዳደም ይከፍታሉ። በተጨማሪ በነዚሁ በከፈቷቸው ማቀላጠፊያ ሱቆች የደንበኛ ማስተናገጃ መስኮቶችን በብዛት ዝግጁ ያደርጋሉ። መስኮቶች እንደየ ባንኮችና እንደ ደንበኞቻቸው ብዛት ታይተው እንደሚዘጋጁ ልብ ይሏል። በዚያው ልክ ደግሞ የሰው ሀይል ይመደብላቸዋል። አጀብ ነው ሽር ጉዱ!
ሁሌም ግን በነዚህ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንድ ነገር እናስተውላለን። በአንድ የባንክ ቅርንጫፍ ውስጥ ከሚሰሩ ይልቅ የማይሰሩት(ሰው አልባ) መስኮቶች መብዛታቸውን አስተውላለሁ። እንደ እድል ሆኖ ይሄ ጉዳይ በስፋት ያጋጥመኛል። ለመሆኑ እነዚህ መስኮቶች ተግባራቸው ምን ይሆን? በእኛ በኢትዮጵያን ባህል ባንክ ቤት ሄዶ ያለ ወረፋ መስተናገድ ቅንጦት ነው። የሚገርመው ደግሞ አስተናጋጁ መስኮቶቹን በኩራት ከፍቶ እየተመለከትን እኛ ስንቁለጨለጭ ማየት ነው። በዚህ ቅሬታዬ ላይ የሰነዘርኩትን ሃሳብ ተመልክታችሁ ‹‹ልክ ነህ የልቤን ነው የተነፈስክልኝ›› እንደምትሉኝ አልጠራጠርም።
በአንድ ባንክ ውስጥ ከአስር በላይ የመስኮት ብዛት ቢኖርም ደንበኞችንና አገልግሎት ሰጭዎችን የሚያገኙት ከሁለትና ከሦስት አይበልጡም። የተቀሩት ‹‹አገልግሎት አይሰጡም›› የሚል ነጭ ወረቀት ተለጥፎባቸው፤ አሊያም ክፍት ሆነውም በአስተናጋጁ ግልምጫ ተስተናጋጅ በስፍራው እንዳይደርስ ይደረጋል። እነዚህ ክፍት የስራ መስኮቶች እያሉ ደንበኛ ግዜውን ማቃጠሉና ረጅም ሰአት መጠበቁ ብስጭት ይፈጥራል። የሚገርመው እንደ ተስተናጋጁ ሁላ እነዚህ ክፍት መስኮቶች ማንን መጠየቅ እንዳለባቸው ባያውቁ ነው እንጂ ለምን ተሰራሁኝ ብለው መሞገት የሚፈልጉ ይመስላሉ። የደንበኞች መጉላላት ብቻ ሳይሆን ከመስኮቱ ጀርባ ያለው የሰውን ብዛት ለተመለከተ ከፍተኛ የሆነ ንዴትን ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው። ምንድነው ይሄ ሁሉ ሰራተኛ የሚርመሰመሰው? ከጀርባ ያለው የሰው ሀይል ወጥቶ መስኮቶችን አገልግሎት እንዲሰጡ ካላደረጋቸው በስተቀር ‹‹ደንበኛ ክቡር ነው›› የሚለው የተለመደ አባባል ምን ትርጉም ይሰጣል?
ምን ይሄ ብቻ! ‹‹ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ››፤ ‹‹የምን ጊዜም አጋሮ››፤ ‹‹አብረን ሰርተን አብረን እንደግ›› የመሳሰሉ የባንክ ማስታወቂያዎች አንድ ቦታ ወረፋ በመጠበቅ ቆመው ውዱን ጊዜያቸውን ለሚያጠፉት ደንበኞች ምናቸው ነው? ያለውን በትክክል ማስተናገድ ያልቻለ ባንክ እንዴት ነው በባንኩ ሊተማመንበት የሚችል ተጨማሪ ደንበኛ ለማፍራት በየቴሌቪዥን መስኮቱ የተጋነነ ማስታወቂያ የሚያስነግረው? ወገን ስራችንንና ምግባራችን አንድ እናድርገው እንጂ። ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ይላል ወንዱ አያቴ። እንዴት ነው ነገሩ የባንክ ሲስተም፣ የሰራተኛውም ሞራል በጠፋ ቁጥር እኛ ደንበኞች ወረፋው ገደለን እኮ !።
ከላይ ደጋግሜ እንዳነሳሁት በነዚህ ባንክ ቤቶች በርካታ መስኮቶች ቢኖሩም አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው ጥቂቶች በመሆናቸው የተነሳ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ ‹‹220›› የሚል የወረፋ መጠበቂያ ቁጥር ደርሶኝ ያውቃል። በቀላሉ ከቢሮ ወጥቶና በአጋጣሚ ጎራ ብሎ የባንክ አገልግሎት ማግኘት የማይታሰብ ነው። ይህ ችግር በየቀኑ ከተለመደው ‹‹ሲስተም የለም›› ፣ ‹‹ኮምፒውተሩ አልከፍት አለ›› ውጭ ያለ የዕለት ተዕለት ችግር ነው። የመስኮቶች ዝግ መሆን የሰው ሀይል እጥረት አይደለም። ጠይቄ የተረዳሁት ግን ‹‹መስኮት ላይ እንዲሰሩ የተመደቡ ሰራተኞችን ከግንባር ወደ ጀርባ በማዛወር ከስራቸው ውጪ የአለቆቻቸውን ተግባር እንዲያከናውኑ ያደርጓቸዋል››።
ሰሞኑን ከኮሮና ጋራ ተደማምሮ የንግድ ባንክ ደንበኞች ሰልፍ ከአንዱ ቅርንጫፍ የተነሳው ሌላኛው ቅርንጫፍ ደርሷል። ይሄ ሰልፍ የመረረው አንዱ‹‹ ባንኩ ስኳርና ዘይት ማከፋፈል ጀመረ እንዴ? ››ብሎ ተሳልቋል። የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት ደግሞ አብዛኛው ሰራተኛ የጦሩ ጀነራሎች ወይም የኋላ ጀግኖች እንጂ የግንባር ተዋጊዎች አለመሆናቸው ነው።
በየቅርንጫፉ ያሉ ማናጀሮች ከራሳቸው አልፈው ከስር ያሉ ሰራተኞችን ስራ በመሸፈን አርአያ መሆን፤ ደንበኛን ማርካትና መሳብ የሚችል ስራ መስራት ሲገባ ሰራተኛን ከመስኮት ማሸሽ ምን የሚሉት ፋሽን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የስራ ኃላፊነት ከፍ ባለ ቁጥር ብዙ መስራት እንደሌለባቸው የሚያስቡ ሞልተዋል። መሆን የነበረበት ግን የሀላፊነት ቦታ ላይ መቀመጥና ከፍተኛ ተከፋይ መሆን የሥራ ሀላፊነትም በዛው ልክ እንደሚጨምር ማሰብ ነበር። የአደጉ አገሮች ተመክሮም ከኛ በተገላቢጦሽ ነው።
‹‹ደንበኞች ምን ያህል ይጉላሉ›› በቴክኖሎጂ ተለይቶ አጥፊው ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ይደረጋል። ‹‹አገልግሎት አይሰጡም›› የሚባሉ መስኮቶች በፍፁም አይኖሩም። ሃላፊዎች በሚያስተዳድሩት ባንክ ውስጥ የሚሆነውን ሁሉ በአንክሮ ስለሚከታተሉ ስህተት ሲኖር በፍጥነት ያስተካክላሉ።
ታዲያ ይህን ሳስብ ለአገሬ ባንኮች ይሄን ተመኘሁላቸው። ደንበኛ ክቡር ነው የሚለውን የግርግዳ ላይ ጥቅስ በልባቸው እንዲሆን። ሰራተኞች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ መስኮቶች ስራ እንዳይፈቱ፤ በቴክኖሎጂ ዘምነው ለአገር እንዲተጉ። ይሄ ምኞቴ ቅዥት ብቻ እንዳይሆን እየፀለይኩ ሃሳቤን ልቋጭ ። ከዚያ በፊት ግን አንድ መፈክር። ‹‹ስራ የፈቱ መስኮቶችን ተባብረን እናስወግዳለን!›› ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ሞገስ ፀጋዬ