የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ከተከሰተ እንሆ ወራት ተቆጥረዋል። ወረርሽኙ የስርጭት አድማሱን በማስፋት በሁሉም ሀገራት በሚባል መልኩ መላው ዓለምን አዳርሷል። በዚህ ወረርሽኝ ምክንያትም ከሦስት መቶ ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሕይወት እንደ ቅጠል ረግፏል፤ስደስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ከበሽታው ማገገም ቢችሉም፣ከባድ ጠባሳ ጥሎባቸው አልፏል።
በሽታው አሁንም የዓለም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። በዚሁ በሽታ ጦስ ምክንያት የሀገሮችና የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ ቆሟል። በርካታ የአውሮፕላን በረራዎቻቸውንም በመቆማቸው ዓለም አቀፍ የሰዎች እንቅስቃሴ ተገቷል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ፋብሪካዎች ተከርችመዋል። ስለትርፍ ሳይሆን ስለህልውና የሚታሰብበት ወቅት ሆኗል።
መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶችም የሥራ ሰዓታቸውን ቀንሰዋል፤ አልያም ዘግተው ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሰሩ አድርገዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ትላልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ኮንፍረንሶችና ጉባኤዎችም በዚሁ ወረርሽኝ ጫና ተሰርዘዋል። በዚህም ከባድ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ኪሳራ አጋጥሟል።
በአጠቃላይ ወረርሽኙ በዓለማችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስን በስፋት አስከትሏል። በሽተኛ ማስታመምና መጠየቅ፣ ቀብር ማስፈጸም እና ማስተዛዘን ጥያቄዎች ውስጥ ገብተዋል። የእምነት ተቋማት ደጃቸውን ለመዝጋት ተገደዋል።
በሀገራችንም ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ሲተግብር ቆይቷል። በመጀመሪያ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጓል። በመቀጠልም የመንግሥት ሠራተኞች እቤታቸው በመሆን ሥራዎቻቸውን እንዲሰሩ አድርጓል። በትራንስፖርት አካባቢ የሚታየውን መጨናነቅ ለመቀነስም ታክሲዎች ከሚያሳፍሩት 50 በመቶን ቀንሰው 6 ሰዎችን ብቻ፣ ሃይገር ባሶች 14 ሰዎች እንዲሁም አውቶቡሶች 30 ሰው ብቻ እንዲጭኑ ተደርጓል።
ችግሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማስወጣት አድርሷል። በኋላ ላይ ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አሳልፏል። የመንግሥት የሥራ ዘመን በመጠናቀቁና ምርጫውን ለማራዘም አራት የሕገመንግሥት አማራጮች ቀርበው የሥገ መንግሥት ትርጓሜ በሕግ ባለሙያዎች ተሰጥቶበታል፤ጉዳዩ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቧል።
መንግሥት እነዚህን ውሳኔዎች ለማሳለፍ የተገደደበት ዋናው ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠውን የሰዎችን ህልውና ለማስጠበቅ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም የበርካታ ሀገራት መንግሥታት ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የተገደዱት የዜጎች ሕይወት ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ነው።
አሁንም የዜጎችን ሕይወት ለመጠበቅ ሲባል በተለያዩ ሀገራትና መንግሥታት ልዩ ልዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው። እርግጥ ነው የቫይረሱ ስርጭት በአንዳንድ ሀገሮች ጋብ ያለበት ሁኔታ ይታያል፤አንዳንድ ሀገሮች ክልከላዎችን ወደማላላት እየገቡ ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ግን ችግሩ ገና እንዳልተፈታ እያሳሰበ ይገኛል። በአንዳንዶች ሀገሮች እንደሚታየው በሽታው እየተስፋፋ ይገኛል። የአውሮፓ ሀገሮች እፎይ ያሉበት ሁኔታ ቢኖርም፣እንደ ብራዚል ያሉት ሀገሮች ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል።
በየሀገሩ ዜጎች ከቤት ባለመውጣትና በጤና ባለሞያዎች የሚተላለፉ መመሪያዎችን እየተገበሩና ጥንቃቄዎችን እየወሰዱ የሚገኙ ቢሆንም ቫይረሱ ስርጭቱን ከማስፋት ያገደው የለም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ የተባሉ የሳይንስ ሊህቃን ቫይረሱን የሚሽር መድኃኒት ፍለጋ ሌት ተቀን ቢለፉም፤ ክትባት ለማግኘት ቢታትሩም እስካሁን የተጨበጠ ውጤት ማግኘት አልቻሉም። አሜሪካንን የመሰሉ የዓለማችን ባለፀጋ ሀገራት ለቫይረሱ ክትባትና መድኃኒት ፍለጋ ረብጣ ገንዘብ ቢመድቡም ጠብ የሚል ነገር አልተገኘም። ተስፋ አስቆራጭ እንጂ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም እየታዩ አይደሉም።
የኮሮና ቫይረስ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው በቀላሉ ሊዛመት የሚችል በመሆኑ ንክኪና መቀራረብ አይፈልግም። በተለያዩ ቁሶችና በአየር ላይም ለተወሰኑ ደቂቃዎችና ሰዓታት ስለሚቆይ ያለንክኪ በቀላሉ በሰዎች አፍና አፍንጫ አማካኝነት ወደ ሰውነት ሊገባ ይችላል። አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ተደርጎ በትንሽ አጋጣሚ በቫይረሱ የመያዝ ዕድል እንደሚኖር የጤና ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ። በአጭሩ ከባድ ጥንቃቄ ካልተደረገ በስተቀር ከቫይረሱ ለማምለጥ ያዳግታል።
እዚህ ጋር ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ታዲያ ኮሮና ቫይረስ እስኪያበቃ ድረስ በሰዎች ዘንድ እየተደረጉ ያሉ ጥንቃቄዎችን አሁን ባሉበት ደረጃ ማስቀጠል ይቻላል ወይ? ለዚሁ ጥንቃቄ የሚረዱ ትክክለኛ ግብአቶችን ሁሌም ሳይቋረጥ ማሟላትስ ይቻላል? የሚሉት የበርካታ ወገኖች ጥያቄዎች ሆነዋል። በመንግሥት የሚተላለፉ መመሪያዎችንና በጤና ሚኒስቴር የሚተላለፉ ምክሮችን እንዲሁም ራስን ከበሽታው ለመከላከል የሚረዱ ማናቸውንም ጠቃሚ መልዕክቶችን እስከ መቼ ድረስ ሳይሰለቹ በአግባቡ መፈፀም ይቻላል? የሚለውም አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል።
ከዚሁ ጉዳይ ጎን ለጎን ታዲያ የኮሮና ቫይረስ ማብቂያ መቼ እንደሆነ አይታወቅም፤ሰዎች ከቤት ወጥተው ሳይሳቀቁ እንደልብ ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ጊዜ በግልፅ አይታወቅም። ኮሮና ቫይረስ ካደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ ሀገራት መቼ እንደሚያገግሙም በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። ነገሮች ወደ ቀደሞው መልካቸው ተመልሰው ዓለም የአውሮፕላን በረራዎችን የሰዎች እንቅስቃሴ መቼ እንደሚጀመርም አልተረጋገጠም። በአጭሩ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የቀጣዩን ዓለም አቀፍ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ ከወዲሁ ለመተንበይ እያዳገተ ነው።
አሁንም ቢሆን ኮሮና ማብቂያው አልታወቀም። በመሆኑም ወረርሽኙ እስኪያበቃ ድረስ መደረግ ያለበት ብቸኛ አማራጭ አሁንም ከመንግሥትና ከጤና ባለሞያዎች የሚተላለፉ መመሪያዎችን ሳይሰለቹ ሁሌም ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ነው። ይህም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በዋናነት ደግሞ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገዢ መሆን ይገባል።
መቼም ጨልሞ አይቀር ዳግም ይነጋልና ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፤በሳይንሱም በመንፈሳዊ መንገድም መታገል ያስፈልጋል። የተለያዩ ሀገራት የሳይንስ ሊህቃን የቫይረሱን ክትባትና መድኃኒት ለማግኘት ሌት ተቀን እየለፉ ናቸው። አንድ ቀን ማግኘታቸው የማይቀር በመሆኑ እስከዚያው ድረስ ራስን ከበሽታው በመከላከል በተስፋና በትዕግስት መጠባበቁ ይበጃል።
ያን ጊዜ ታዲያ ሁላችንም በየእምነት ተቋማችን ስር ሆነን በሽታው ከአጠገባችን እንዲርቅ የጸለይነውን ያህል ምስጋናችንን እናደርሳለን። በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ተራርቀን የቆየንም ተገናኝተን በመተቃቀፍ ናፍቆታችንን እንወጣለን። ርቀተን ለመጠበቅ በተወሰደው እርምጃ የላላው አካላዊ ትስስር ወደነበረበት ይመለሳል። ልጆቻችንም ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው የናፈቁትን ትምህርት ይማራሉ።
የመንግሥትና የግል ሠራተኞችም በጥርጣሬ ሳይተያዩና ሳይሳቀቁ ለራሳቸውና ለሀገረቸው ተግተው ይሰራሉ። ሲኒማ ቤቶች ተከፍተው ሰዎች ይዝናናሉ። የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም ለተመልካቾች በራቸው ወለል ይደረጋል። በአጠቃላይ በቫይረሱ ምክንያት ተገድቦ የነበረው የሰዎች አካላዊ ግንኙነት ትንሳኤ ይመጣል። እናማ ወገኔ ሆይ ኮሮና እስኪያበቃ ጥንቃቄ ይብዛ፤መዘናጋት ይብቃ!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
አስናቀ ፀጋዬ