በአንድ ወቅት አሁን ኢትዮጵያውያንን እየፈተንን ያለው ጽንፍ የረገጠ ብሄረተኝነት ጎረቤታችን ኬንያን ታላቅ ፈተና ውስጥ ከቷትና ከመፈራረስ ጠርዝ ላይ አድርሷት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወጉናል። በኪኪዩ፣ ኦሪዩና ማሳይ ጎሳዎች (ብሄሮች) መካከል የነበረው አለመግባባት ጦዞና አክራሪ ብሄረተኝነቱ ሰፍቶ በቃ ኬንያ አበቃላት እንደ ቅርጫ ሥጋም አስር ቦታ ተከፋፍላ ልታርፈው ነው ተብሎላትም ነበር። በተለያዩ ወገኖች በሚለቀቀው ፕሮፖጋንዳ ህዝብ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ በልዩነት መስመር ይተምም ነበር። የተጋባው፣ የተዋለደውና ክፉና ደጉን አብሮ የተካፈለው የኬንያ ህዝብ በብሄር ልዩነት ጦስ የሀገሪቱ ህዝቦች ቢከፋፋሉና አገሪቱም ብትፈርስ ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ግራ ገብቶት ሁሉም እንደየእምነቱ በጸሎት ተጠምዶ ነገን በስጋት እንዲጠብቅ ተገድዶም ነበር። ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው አንዳንድ የአገሪቱ ፖለቲከኞችም ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ በመጮህ መከፋፈሉ የሚያመጣውን አደጋ ለማሳየት ቢሞክሩም ሰሚ ጆሮ ማግኘት ግን ዘበት ነበር።
ይህን ጊዜ ነበር የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ለሀገሪቱ ችግር የክፉ ቀን ደራሽ ሆነው ብቅ ያሉት። መገናኛ ብዙሃኑ ልጅ ወልደን ማሳደግና ተረጋግተን መኖር የምንችለው እንዲሁም እንዲህ ቁጭ ብለን ሻይ ቡና እያልን የምናወጋው ኬንያ ሰላም ስትሆን ብቻ ነው። ስለዚህ ልዩነትን የሚያንጸባርቁ ሀሳቦችን ለጊዜው ገታ አድርገን ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን ብቻ እንስበክ። አጀንዳዎቻችን ሁሉ የልዩነት ጦሱ ለሁሉም ኬንያውያን አበሳ ብቻ እንደሆነ ያመላክቱ ብለው ወሰኑ። ወስነውም አልቀሩ ለአንድ ወር የሚቆይ የሚዲያ ዘመቻ (media campaign) ለማካሄድ ተነሱ። በከፍተኛ ጥንቃቄና ዕውቀት ላይ ተመስርተው ለዘመቻው የመረጡት መሪ ቃልም “በስተመጨረሻ ሁላችንም ኬንያውያን ነን” (at the end of the day we all are Kenyans) የሚል ሆነ። የማንም ብሄርና ዘር እንሁን የቱንም ያህል የፖለቲካ ልዩነቶች በመካከላችን ይኑሩ አቃፊውና ትልቁ ስማችን ኬንያ ነው የሚል ነበር እሳቤው።
በመረጡት መሪ ቃል በመታገዝም ያለምንም ልዩነት ሁሉም መገናኛ ብዙሃን በተቀናጀ አጀንዳ አንድነትንና ፍቅርን ይሰብኩም ጀመር። መልዕክቶቹም ጥላቻ፣ መከፋፈልና ግጭት ለማንም እንደማይበጅ ጎጂውም ሆነ ተጎጂው የአንዲት እናት የኬንያ ልጆች መሆናቸውን በጉልህ የሚያስተጋቡ ነበሩ። የሚበጀው ተፈቃቅሮና ተካባብሮ በአንዲት ኬንያ ጥላ ስር መጠለል መሆኑም ተደግሞና ተደጋግሞ ተሰበከ። የሚዲያ ጉልበት ምን ያህል ኃያል እንደሆነ በተመሰከረበት በዚህ ዘመቻም በመገናኛ ብዙኃኑ የተላለፉት መልዕክቶች በህዝቡ ውስጥ ሰረጹና ኬንውያኑ ቆም ብለው እንዲያጤኑ አደረጓቸው። አጢነውም አልቀሩ ጥላቻንና መከፋፈልን ወደጎን ብለው ፍቅርንና አንድነትን በጋራ ይዘምሩ ጀመር።
ምስጋና ለችግር ጊዜ ደራሾቹ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ይሁንና በብዙ ዓይነት ልዩነቶች ውስጥ እኛ ሁላችንም ኬንያውያን ሀገራችንም ኬንያ ናት የሚለው ቅዱስ ሀሳብ የበላይነቱን ተጎናጸፈና ኬንያ ከመበታታን ተረፈች። ይህ ማር ማር ከሚለው የሚዲያ ጣፋጭ ባህሪ አንድ ማሳያ ነው።
የወንጀል ድርጊቶች ማነሳሻ፣ የሽብርና ጥላቻ መቀስቀሻ የሆነው ሚዲያ አገራትን እንደሚገነባና የሥልጣኔና ዕድገታቸው ዋልታ እንደሚሆን ደግሞ የቻይናና የአሜሪካ ተሞክሮ ትልቅ ትምህርት ይሆነናል። ሚዲያ የገነባት ቻይና በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ በቅርቡ በወጣ ጽሁፍ ዘመናዊቷንና የበለጸገችውን ቻይና በመገንባቱ ረገድ የቻይና ሚዲያዎች የተጫወቱት ሚና እጅግ የሚያኮራ እንደነበርና ሚዲያዎቹ በዚያ መልኩ ባይንቀሳቀሱ ኖሮ የዛሬዋን ቻይና ማየት አዳጋች እንደነበር ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። የቻይና ሚዲያዎች ሀገሩንና ህዝቡን የሚወድ፣ ሌብነትና ስንፍናን የሚጸየፍ፣ የሀገሩን ብሄራዊ ጥቅም ለማንም አሳልፎ የማይሰጥ ትጉህና ጠንካራ ትውልድ በመፍጠሩ ሂደት የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል።
የአሜሪካም ጉዳይ እንዲሁ ነው። አሜሪካ ትቅደም /America first/ የሚለውን መርህ የሥራቸው ማጠንጠኛ ያደረጉት መገናኛ ብዙሃኗ አሜሪካን ስናስብ ኃያልነቷ፣ ሰላሟና ብልጽግናዋ ቀድሞ አዕምሯችን ላይ እንዲሳል ማድረጉ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ህዝቦቿ የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም እንዲያስጠብቁና አንድነታቸው ከብረት የጠነከረ እንዲሆን በማድረግም የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ሚና ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ስለአሜሪካ ስልጣኔና ዕድገት የተጻፉ ድርሳናት ይመሰክራሉ። የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ሥራዎችም ሆኑ የፊልምና የኪነጥበብ ሥራዎቻቸው ተቀዳሚ ዓላማ የአሜሪካንን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅና አዎንታዊ ገጽታዋን እጅግ ማላቅ እንደመሆኑ መገናኛ ብዙሃኑ ቅዱስ ሚናቸውን በሚገባ ተወጥተዋል ለማለት ያስደፍራል።
ምነው ሚዲያ እንዲህ ብቻ ሆኖ በቀረ ከሚያስብለን ባህሪው ወጣ ብለን ደግሞ መርዛማ ከሆነውና እሬት እሬት ከሚለው ባህሪው አንዱን ጨልፍ አድርገን እንመልከት። በምናብ ወደኋላ እንመለስና ርዋንዳን እንቃኝ። ልክ እንደ እኛዋ ኢትዮጵያ ርዋንዳም ብሄር ብሄረሰቦች ተዛምደው የወለዷት የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ናት። በሀገሪቱ ሌሎች ብሄሮች ቢኖሩም በቁጥር በዛ ብለውና ተጽዕኗቸው ጎልቶ የሚታዩት ግን ሁቱና ቱትሲ የሚባሉት ህዝቦች ናቸው። ልዩነትና አለመግባባት ዓለምአቀፋዊ ባህሪ አለውና በተለያዩ ኃይላት ቅስቀሳዎች የተነሳ በሁለቱ ብሄሮች መካከል በወቅቱ የነበረው ግንኙነት ጥሩ የሚባል ዓይነት አልነበረም። ይህ ሁኔታው እንዲህ ባለበት ወቅት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከውጭ ሀገር ጉብኝት ወደሀገራቸው ሲመለሱ የተሳፈሩባት አውሮፕላን አየር ላይ ይመታና የፕሬዚዳንቱ ህይወት ያልፋል።
ይህን ዕድል እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገሪቱ ከነበሩ መገናኛ ብዙሃን በተለይም የኤፍ ኤም ሬዲዮዎች በቱትሲ ብሄር ላይ ያተኮረ የጥላቻ ቅስቀሳ ማሰራጨቱን ተያያዙት። ወትሮም በቋፍ የነበረውና የፕሬዚዳንቱ መገደል ያስቆጣው ህዝብ በጥላቻ መልዕክቱ በመገፋፋት ግደለውና ጨፍጭፈው በተባለው ብሄር ላይ ገጀራውን ስሎ ዘመተ። የእኩይ ተግባር አነሳሽ የሆኑት መገናኛ ብዙሃንም እነዚህን በረሮዎች እያሳደድክ ጨፍጭፍ አትማራቸው የሚል ሠይጣናዊ ቅስቀሳቸውን ያጧጡፉት ያዙ። ይህ መርዘኛ ቅስቀሳም በዓለም ታሪክ ዘግናኙ የተባለውን ጭፍጨፋ ወልዶ በ100 ቀናት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ርዋንዳውያንን ህይወት ቅርጥፍ አድርጎ በላ።
ምንም የማያውቁ ህጻናት፣ ነፍሰጡር እናቶች በየትኛውም የፖለቲካ አውድ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው ዜጎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አዛውንቶች ያለምንም ሃጢያታቸው በመርዘኛ ሚዲያ ቅስቀሳ ጦስ ይቺን ምድር ዳግም ላያዩ የሰማዕትነት ጽዋን ተጎነጩ። ተፈርተውና ተከብረው ከጭፍጨፋ ያድኑናል በሚል እሳቤ ንጹሃን ርዋንዳውያን የእምነት ተቋማትን መከለያቸው ቢያደርጓቸውም ቅዱሳን ቦታዎቹ እነዚያን ክፉ ቀናት የማስመለጥ አቅም አጡና ክቡር የሆኑት የሰው ልጆች እንደ እባብ በገጀራ ተጨፈጨፉ። ርዋንዳ በደም አበላ ተመታች። ከናዚ ጭፍጨፋ በኋላ አሁንም ድረስ ሲሰሙት የሚዘግንን እልቂትን ምድራችን አስተናገደች። የዚህ ሁሉ እልቂት ምክንያቱ ሚዲያ ነበረና እንዲህ ከሆነማ ሚዲያ በዚህች ምድር ላይ የተፈጠረበት ቀን የተረገመ ይሁን ተባለ።
ከላይ በተከታታይ የተመለከትናቸው ሁለት ተቃርኖዎች የሚዲያን ማርና መርዝ የሆነ ባህሪ ፍንትው አድርገው ያሳዩናል። እንደ ዕድል ሆኖ ሚዲያ በጨዋና ኃላፊነት በሚሰማቸው ሰዎች እጅ ሲገባ መርዝን አርክሶ ፍቅርና ሰላምን ሲያነግስ ቀን ጥሎት በአረመኔዎችና በህሊና ቢሶች መዳፍ ስር ሲወድቅ ደግሞ ጨቅላ ህጻናት፣ ነፍሰጡሮችና አረጋውያንን ሳይቀር አስጨፍጭፎና ህዝብን ከህዝብ አባልቶ ዓይንህን ለአፈር እንደሚባል በደንብ አሳይቶናልና።
ከኮሙኒኬሽን ንድፈ ሀሳቦች (theory) አንዱ ሚዲያን የመርዝ መርፌ ነው ሲል ይፈርጀዋል። ይህ ንድፈ ሀሳብ ወንጀልና ክፉ ተግባራት ከሰው ወደ ሰውና ከአገር ወደ አገር የሚዛመቱት ሚዲያ በሚሉት የጥፋት መሳሪያ ነው የሚል የጠነከረ አቋምም አለው። የዚህ ንድፈ ሀሳብ አራማጆች በአሜሪካ በታጠቁ ሰዎች እየደረሱ ያሉ ጭፍጨፋዎች ለሚዲያ የመርዝ መርፌነት ጥሩ ማሳያ ናቸው ሲሉም ይደመጣሉ። በምሳሌ ሲያስረዱም ከ1980ዎቹ በፊት በአሜሪካ የታጠቁ ተማሪዎች በጓደኞቻቸው ላይ የሚያደርሱት የወንጀል ድርጊት በአሜሪካ ያልተለመደና እንግዳ ነገር ነበር። እ.ኤ.አ በ1988 አንድ ተማሪ መሳሪያ ታጥቆ ወደ ትምህርት ቤት በመግባት የ8 ተማሪ ጓደኞቹን ህይወት ይቀጥፋል። ድርጊቱ በአሜሪካ የተለመደ አልነበረምና አገርን ጉድ አሰኘ። ወሬውን እንደ ጥሩ የገበያ ዕድል በመጠቀምም ሚዲያው እንደ ጉድ አራገበው።
ይህ ዜና በሚዲያ ከተላለፈና በብዙዎች ከተሰማ በኋላ ግን መሳሪያዎችን ባነገቱ ታዳጊ ተማሪዎች ህይወታቸው የተቀጠፈ አሜሪካውያን ተማሪዎችና መምህራን ቁጥር እንደ ጉድ ተመነደገ። ይህ ድርጊት ዕለት ከዕለት እየተዋለደም በአሜሪካ ምርጫ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ መሪዎችን ከሚያጨቃጭቁ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል። የንድፈ ሀሳቡ አራማጆች ይህን ወንጀል የሚሰሩት ሰዎች ይህን መሰል ዜና ባይሰሙ ወይም ባይመለከቱ ኖሮ ድርጊቱን አውቀው አያደርጉትም ነበር የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።
ንድፈ ሃሳቡ እውነታነት እንዳለው በሀገራችን ከተከናወኑ አስከፊ ድርጊቶች አንዱን መዘን በማውጣት መረዳት እንችላለን። የዛኔዋ ወይዘሪት የአሁኗ ወይዘሮ ካሚላት መህዲ ፊትና አካል ላይ አሲድ የመድፋት ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት የዚህ ዓይነት የወንጀል ድርጊት ለሀገራችን እንግዳ ነበር። ይህ አረመኔያዊ ወንጀል በካሚላት ላይ ሲፈጸም ግን መገናኛ ብዙሃን ከግራም ከቀኝ ነገሩን አራገቡት። የዚያን ሰሞኑ የመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋንም በካሚላት ላይ ስለተደፋው የአሲድ ወንጀል ሆነ። ይህን የመገናኛ ብዙሃን ክንውን ተከትሎ ከልጅ እስከ አዋቂ ያለምንም የብሄር፣ የጾታና የሃይማኖት ልዩነት ድርጊቱ ሰይጣናዊ ተብሎ ተወገዘ። ወንጀል ፈጻሚው “ይገደል” “ይሰቀል” እየተባለ ሰልፍ እስከመወጣትም ተደረሰ። ይሁንና ከዚያን ጊዜ በኋላ በርካታ እህቶቻችን ፊታቸውና አካላቸው ላይ አሲድ እየተደፋ የአሰቃቂ ወንጀል ሰለባ ሲሆኑ ተመልክተናል። ለዚህም ነው ከላይ የተጠቀሰው ንድፈ ሀሳብ አራማጆች ሚዲያ እንደመርዝ መርፌ ወንጀልና ክፋትን አስፋፊ ነው የሚሉት።
ዘመኑ መረጃ የእህል ያህል ለህይወት አስፈላጊ የሆነበት ነውና መገናኛ ብዙሃን ለሰይጣናዊ ተግባራት መሳሪያ ስለሚውሉ ከእነአካቴው ይቅሩብን ማለት አይቻልም። ዓለም እንዴት ውላ እንዴት እንዳደረችና በዙሪያችን ምን እየተከናወነ እንዳለ በማወቅ ራሳችንን ከሁኔታው ጋር አስማምቶ ለመሄድ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ተኪ የለሽ ነውና። ስለሆነም ዋናው ጉዳይ ይህን ማርም መርዝም የሆነውን መሳሪያ እንዴት እንጠቀመው የሚለው ይሆናል ማለት ነው። ካለው ትልቅ የተጽዕኖ ኃይል የተነሳ አራተኛው የመንግሥት አካል የሚል ስያሜን የተጎናጸፈው ሚዲያ በራሱ ምንም (nothing) ነው። ልክ እንደ ቢላዋ አጠቃቀሙ በተጠቃሚው ሰው ፍላጎትና አስተሳሰብ ይወሰናል። ለበጎ ስንጠቀመው ፍሬው ሰናይ ለክፉ ስናውለው ደግሞ ፍሬው እሬት ይሆናል።
የሰብአዊና ዴሞክራሲ መብቶች ታፍነዋል በሚል መነሻ በሀገራችን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥን ወልዶ ሀገራችን በሁሉ መስክ በለውጥ ጎዳና ወደፊት በመራመድ ላይ ትገኛለች። ሀሳብ በነጻነትን የመግለጽ መብት በተሟላ መልኩ እንዲተገበርም በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችንን ከመልቀቅ ጀምሮ ታግደው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ተጨባጭ እርምጃዎች ተወስደዋል።
አሁን የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ የሚል ምክንያት ቦታ የለውም፤ ኳሷም በመገናኛ ብዙሃኑ እጅ ናት። ‘ቅዱስ መጽሐፍ ፍልና በራድ ውሃ ከፊትህ ቀርቦልሃል እጅን ወደወደድከው መስደድ ያንተ ድርሻ ነው’ እንዲል ያለው ምርጫ ማህበራዊ ኃላፊነትን ዘንግቶ ገበያን ለማሳደድ ጥላቻን ማራገብ፣ አገርን ማተራመስና ማፍረስ በዚህም የታሪክ ተጠያቂ መሆን ወይም ስህተትን ገንቢ በሆነ መልኩ በማሳየት ህዝቦችን በማቀራረብና ፍቅርን በመዝራት ምድርን ተሻጋሪ ዋጋ ማግኘት ይሆናል!
ፍቃዱ ከተማ
ፍቃዱ ከተማ