
በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ አስኳል ሃሳብ ወዳጅነትና መተሳሰብ መሆኑ ይታወቃል። በታሪክ ገጾች እንደሰፈረውም በሰው ልጅ ታሪክ ባጋጠሙ በጎም ሆኑ መጥፎ ክስተቶች ስፖርት በአጋርነት ተሳትፏል። ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ሰላምንና አንድነትን የሚሰብኩ እንደመሆናቸው በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በመግባት ሚናቸውን ሲወጡም ኖረዋል። የወቅቱ የዓለም ራስ ምታት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘም ስፖርት መገኘት ባለበት ሁሉ አጋርነቱን በማስመስከር ላይ ይገኛል።
የቫይረሱ ስጋትነት በዓለም አቀፉ የጤና ተቋም ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ፤ ውድድሮችን ከማቋረጥና ከመሰረዝ ባለፈ የስፖርቱ ተዋንያን በተናጥልም ሆነ በተቋማዊ ደረጃ አበርክቷቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። በእግር ኳስ ጠቢብነታቸው ዓለም የመሰከረላቸው ተጫዋቾችና ስመ ጥር አሰልጣኞችም፤ ለደጋፊዎቻቸው መልእክት ከማስተላለፍና ገንዘብ ከመለገስ ባሻገር ሆቴሎቻቸውን ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉም ጭምር መስጠታቸው ይታወሳል። ክለቦችም በተመሳሳይ ስታዲየሞቻቸውን ቫይረሱን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት እያዋሉት ይገኛሉ። የነጫጮቹ ስታዲየም ሳንቲያጎ በርናባው ለቫይረሱ የሚሆኑ መድሃኒቶችና የህክምና እቃዎች ማከማቻ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየደረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያንቀሳቅሱ ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው ስፖርትም በዚሁ ምክንያት የገንዘብ ችግር በማስተናገድ ላይ ይገኛል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ሙሉ ደሞዛቸውን መክፈል ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በጊዜያዊነት እስከ መጪው ወር መጨረሻ ድረስ መቋረጡ ይታወሳል። ክለቦች ከስታዲየም ገቢ እና ለሌሎችም የሚያገኙት ገቢ ላይ መቀነስ ተከትሎ ከፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ተጫዋቾቹ የደመወዛቸው ግማሽ እንዲከፈላቸው በመስማማት ስፖርት የመተሳሰብ መድረክ መሆኑን አረጋግጠዋል። ጥያቄውን በቅድሚያ ያቀረበው የሊጉ ክለብ የሆነው በርሚንግሃም ሲቲ ሲሆን፤ ለአራት ወራት በዚህ መልክ ደመወዝ እንደሚከፍል ማስታወቁን ዘጋርዲያን በዘገባው አስነብቧል። ቅድሚያ አንዳንድ ተጫዋቾች ሃሳቡን ባይቀበሉም በሂደት በበጎ ፈቃደኝነት መስማማታቸውን አሳይተዋል። ክፍያው ከተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን ባለፈ ያሉ የክለብ ሰራቶችን እንደማይመለከትም ታውቋል።
ወደ ኢትዮጵያ መለስ ስንልም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 2 ሚሊዮን ብር ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲሁም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ መስጠቱ ከትናንት በስቲያ የተሰማ ዜና ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉም በግሏ ለጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በድምሩ 400ሺ ብር መለገሷ ታውቋል። የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማህበርም በበኩሉ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የ 50ሺ ብር ድጋፍ አድርገዋል። የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ምክትል ፕሬዚዳንት የገንዘብ እንዲሁም የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ለመጓጓዣ እንዲውል የተሽከርካሪ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገጹ አስነብቧል።
ብርሃን ፈይሳ