
በስፖርት ማህበራት ስራ አስፈጻሚዎች መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመቅረፍ ውይይት እንደሚካሄድ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ። ማህበራቱ በአዋጅና በህግ የተቋቋሙ እንደመሆናቸው ህጉን አክብረው መስራት እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ጠቁሟል። የሁለቱ የስፖርት ተቋማት ስራ አስፈጻሚዎች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ለወራት የቆየ ሲሆን፤ በዚሁ ምክንያት ስፖርቱ በተለያዩ አመለካከቶች ለመንቀሳቀስ መገደዱ ይታወቃል። የስፖርት ቤተሰቡን በሁለት ጎራ የከፈለው ይህ ጉዳይ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ስፖርቱን አደጋ ላይ እንደሚጥለው የብዙዎች ስጋት ነበር።
በቀጣዩ ዓመት እንዲካሄድ ከተራዘመው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጋር ተያይዞ አትሌቶች ወደ ስልጠና መግባት አለባቸው በሚል ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ቢጀምርም ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ዓለም ባለችበት የኮሮና ቫይረስ ስጋት አትሌቶችን ወደ ሆቴል ማስገባት ትክክል አለመሆኑን ገልጿል። ይህንን ተከትሎም የተቋማቱ ስራ አስፈጻሚዎች በየፊናቸው በተለያዩ ጊዜያት ተቃራኒ ሃሳቦችን በመያዝ በመገናኛ ብዙሃን መግለጫዎችን ሲሰጡ ነበር። ተቃርኖው በዚሁ ካልተገታም ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችልም እሙን ነበር።
ኦሊምፒኩ በዚህ ወቅት ይሰረዝ እንጂ፤ በየወቅቱ የሚፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ኮሚሽኑ አመራሮቹን ለማነጋገር ቀጠሮ መያዙን ኮሚሽነሩ ኤልያስ ሽኩር ጠቁመዋል። ተመሳሳይ ድርሻ ባላቸው በስራ ሂደቶች ውስጥ ተቋማዊ፣ የአሰራር አሊያም በግለሰቦች መካከል አለመግባባቶች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው። ነገር ግን ማህበራቱ በአዋጅና በህግ የተቋቋሙ እንደመሆቸው ኮሚሽኑ ያወጣውን ደንብ አክብረው መስራት አለባቸው። ስለዚህም የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በንግግር እንዲፈታ ጥረት ይደረጋል ሲሉ ማረጋገጫቸውን ሰጥተዋል።
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር የነበሩት የስፖርት ምክትል ኮሚሽነሩ ዱቤ ጂሎ በበኩላቸው፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አለመግባባት ከሁለት ዓመታት በላይ የቆየ መሆኑን ያስታውሳሉ። ፌዴሬሽኑም ሆነ ኮሚቴው የራሱ የስራ ድርሻ አላቸው የሚሉት አቶ ዱቤ፤ በቀጣይ ሁለቱም አካላት በየስራ ድርሻቸው እንዲሰሩ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
ብርሃን ፈይሳ