
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ህዳር 17 ቀን 2012 የወጣ ፅሁፍ ፤ ዴሞክራሲ ስርዓት በተገነባባቸው አገራት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜው የሚጠይቀውን ለውጥ በማድረግ የማህበረሰቡን ተቀባይነትን እያገኙ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ የለውጥ ምክንያቶችን በመቀበል ረጅም ርቀት መጓዝ ችለዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ራሳቸውን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመውና ለውጠው የማይጓዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የሚዳከሙበት ወይም የሚጠፉበት እድል እንደሚኖርም ያለው ልምድ እንደሚያሳይ ጠቅሷል፡፡ የዜጎቻቸውን ፍላጎትና ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ራሳቸውን እያስተካከሉ የሚሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘለግ ያለ ጊዜ መጓዝ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከግብጽ እስከ ቺሊና ታይላንድ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተግዳሮት የፈጠሩባቸው ሲሆን፤ በተለይም ዜጎች የሚወከሉበትን አዳዲስ መንገዶች እንዲፈልጉና የዴሞክራሲ ተሳትፎ መንገዶች ቀጥተኛ እንዲሆን ያደረጉበት ሁኔታ ተከስቷል። አዳዲስ የመረጃና የቴክኖሎጂ ውጤቶችም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠሩት ተጽዕኖ ከፍተኛ ሲሆን፤ እንደ ማህበራዊ ሚዲያ የመሳሰሉት የዜጎችን የፖለቲካ ሀሳብ መግለጫ ያቀላጠፉ ለውጦች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰሩበትን መንገድ እንዲቀይሩና እንዲያሻሽሉ ያስገደዱበት ሁኔታ መፈጠሩ በፅሁፉ ተመልክቷል።
በፖለቲካ ድርጅት የሪፎርም ሥራዎች ላይ ሶስት መነሻ የሆኑ አብይት ጉዳዮች በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህም፤ አንደኛው በፖርቲው ውስጥ ያለውን እርካታ ለማሻሻል ከመጣ ፍላጐት የመነጨና የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ ከመጣ ተቋማዊ ዕቅድ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ በድርጅቱ ውስጥ የሰፈነውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል ካለመ ስልታዊ ፍላጐት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፤ የግለሰቦችን የተጽዕኖ አቅም ለመጨመርና የሌሎች ቡድኖችን ኃይል ለመቀነስ ያለመ ይሆናል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ፤ በድርጅቱ ታሪክና በርዕዮተ ዓለሙ አውድ ዙሪያ መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን የማስመዝገብ ፍላጐትን ያነገበ የተደራጀ ኃይል መኖሩ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በውስጣቸው ያለውን ዴሞክራሲ ለማበልጸግ በጣም ጉልህ የሆኑ ሪፎርሞችን ያደርጋሉ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በርከት ባሉ አገሮች የውሳኔ ሰጭነትን አቅም በተመለከተና የዕጩና የአመራር ምርጫዎችን ሂደት በተመለከተ ለአባሎቻቸው የበለጠ ክፍት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይገለጻል፡፡ በዚህም ምክንያት መደበኛ አባላት ከዚህ በፊት በፓርቲው ልሂቃንና ጦማሪያን ተይዘው የነበሩ ሚናዎችን የመያዝ እድል እንደተፈጠረላቸውና በፓርቲው ጉዳዮች ላይ በንቃት የመሳተፍ እድል እንደተከፈተላቸው ይታወቃል፡፡
የሽግግር ወቅት ሁሌም በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ በርግጠኝነትም ትላንትን ለኖረ ዛሬ ከትናንት የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን፤ ምንም ከትናንት የተሻለ ተስፋ ቢሰነቅም፤ ከሁሉም ጊዜ ይልቅ ስለ ነገ እርግጠኛ አይደለንም፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሳቢያ እየተሻሻለ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር በአግባቡ ለመጠቀም አዳጋች ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በለውጡ ያገኘቻቸውን የህዝብ አንድነትና መረጋጋት የመጠቀም ሰፊ ዕድል ቢኖራትም በየአካባቢው የሚነሱትን ግጭቶች ማስቆም ባለመቻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት ለመንቀሳቀስ ተቸግረናል ሲሉ ይደመጣል፡፡
በተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ መልካም ጅምሮች የታዩ ሲሆን እስረኞች ተፈትተዋል። መገናኛ ብዙሃን ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት በነጻነት መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ መንግስት በለውጡ እነዚህን መልካም ጅምሮች ያሳየ ቢሆንም፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱትን ግጭቶች ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አልቻለም ፡፡ በዚህም ሳቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመሃል ከተማ ውጪ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ አጀንዳቸውን ለማስተዋወቅና ከደጋፊዎቻቸውና ከአባሎቻቸው ጋር ነጻ ውይይት እንዳያደርጉ ተገድበዋል እየተባለ ይወቀሳል፡፡
በሌላ በኩል፤ በአገሪቷ በተገኘው ለውጥ የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዓላማ በነጻነት ለማስተዋወቅ ያለጥያቄ ለመንቀሳቀስ መደላድሎች ተፈጥሮላቸዋልም ይባላል፡፡ ይሁንና ፓርቲዎች ከመታገድ፤ አባሎቻቸው ከመታሰርና ከመደብደብ ስጋት ነጻ ቢሆኑም በአገሪቷ የሚታዩ የሰላምና መረጋጋት ችግሮች የነገ ህልማቸውን ከወዲሁ እየተፈታተኑ መሆኑን ታይቷል፡፡ ፓርቲዎች በአሁን ወቅት ስለመታሰር ሳይሆን የሚያስቡት የሰለጠነ ፖለቲካ ስለማራመድና በሃሳብ ብልጫ በማሸነፍ አገርን የሚጠቅም መሪ ማፍራት ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሌም መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን የተገኘውን ነጻነት በአግባቡ ለመጠቀም የዚህችን አገር ህልውና እየተፈታተኑ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች በጊዜው መፍታት አለመቻል ስጋት ላይ እንደጣላቸው ይጠቀሳል፡፡
በአሁን ወቅት ግን መንግስት በግልጽ የራሱን አቋም ገልፆ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዓላማቸውንና ግባቸውን በአግባቡ አስተዋውቀው እየተንቀሳቀሱ አይደለም፡፡ በዚህና በሰላም እጦት ሳቢያ የተጀመረው ለውጥና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በተፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ ገደብ ሊያደርግ እንደሚችል ስጋት ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ፓርቲዎቹ ጥቆማ መንግስት በአገሪቷ እየታየ ያለውን የሰላም መደፍረስ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች በመውሰድ ዜጎች ያለስጋት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡
የለውጥ ኃይል በአንፃሩ ሕልውናውን የሚፈታተኑና የአገርንና የሕዝብን ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ከዚህ ቀደም ባልተስተዋለ መልኩ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ፤ ‘በቂ እርምጃ አልወሰደም’ የሚሉ ምክንያታዊ ጥያቄዎች፣ ተቃውሞዎችና ቅሬታዎች እየቀረቡበት ይገኛል፡፡ ወቅቱ የለውጥ እንደመሆኑ መንግሥት መቀመጫውን እስኪያደላድል እዚህም እዚያም መንገጫገጮች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፤ አካልን የሚሰባብሩ፣ የሰውነት ክፍልን የሚያጎድሉና ለሕይወት የሚያሰጉ መንገጫገጮችን በዋዛ ማለፍ ግን፤ የኋላ ኋላ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይሆንም።
ከዚህ አንፃር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንጹሕን ላይ የደረሱ እንግልቶችና መፈናቀሎች በአብዛኛው በዝምታ የመታለፋቸው ጉዳይና፤ አገሪቱን ሲያደሙ የኖሩና አሁንም ከማድማት ወደኋላ ያላሉ ከፍትሕ ዕይታ ተሰውረው መቅረታቸው የማያቋርጥ እሮሮ ከሚቀርብባቸው ችግሮች ቀዳሚ ናቸው፡፡ መንግሥት የሕዝብን መፈናቀል ሲያወግዝ ቢሰማም፤ የተፈናቀሉ ሰዎች ሙሉ በሙሉና በዘላቂ ዋስትና ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ አለመደረጉ ሌላው የቅሬታ ምንጭ ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚወጡ ያልተማከሉ መረጃዎችና ውሳኔዎች መበራከት፣ በቅርቡ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ሴራ መድበስበስ፣ እንዲሁም ‘የለውጡ ባለቤት እኛ ነን’ በሚል እብሪት በየአካባቢያቸው አዛዥ ለመሆን የሚቃጣቸው ጉልበተኞች እንደአሸን መፍላት ከዚሁ ጋር ይጠቀሳሉ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጣውን የመንግስት ለውጥ ተከትለው የተከሰቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለውጡ በህዝቡ ላይ ተስፋና ስጋት እየጫረ ሁለት ዓመታት ዘልቋል። በነዚህ ሁለት ዓመታት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እራሳቸውን በአግባቡ አደራጅተው እንዲቀርቡ፣ በውጭ የሚገኙ አመራሮቻቸውና አባሎቻቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እና ውህደትና ትብብር ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል፤ የመንግስት ተቋማትን አሰራርና ህጎች እንዲስተካከሉ በማድረግ መንግስት ውስጣዊ ለውጦች አካሂዷል። በተጨማሪም በመጡ ለውጦች በውጪ አገራት ያሉ ዳያስፖራዎች መነቃቃት ፈጥረዋል፣ ከተለያዩ አገራት የትብብርና የወዳጅነት ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ቀድሞ ከነበራት ክብር ከፍ ብላ መታየት ችላለች፡፡ አጠቃላይ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በመንግስት የውስጥ ለውጥ ወይም የተቋማት ሪፎርም፤ እንዲሁም በውጪ አገራት መፍጠር የተቻለው ተፅዕኖ ምን ይመስላል?
ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ማሳተፍ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም በውጭ ይገኙ የነበሩ ወደ ሃገራቸው ገብተው እንዲወያዩና ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት ሁሉም ፓርቲዎች ለዶክተር አቢይ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ወደ አገራቸው ገብተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ባጠቃላይ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦና ተመካክሮ እንደሚሰራ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ በኋላ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ውይይት ላይ ከለውጡ በኋላ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ አለም ተበታትነው ስለሚገኙ በተሟላ ሁኔታ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ሲባል፤ በርካታ ሊሻሻሉ የሚገባቸው አዋጆችና አሰራሮች ስለነበሩ እነሱን መነካካት እና የፍትህ ሪፎርሙን ማሳለጥ ያስፈልግ ስለነበር፤ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም ተብሎ ስለሚታማ እሱን ለማሻሻል ቢያንስ የመጀመሪያ ርምጃ መውሰድ ስለሚገባ እና መሰል ስራዎች ቀደም ብለው መሰራት ያለባቸው ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ገብረ ክርስቶስ ኑርዬ እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ የሚኖሩት ፓርቲዎች ምን ላይ ናቸው የሚለው ሲታይ ተፎካካሪ የሚለው ሰም በቅርቡ የተሰጠ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብሎ “ተቃዋሚ” ተብለው ይጠሩ የነበሩ ፓርቲዎች በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ ምክንያት እንደ ጠላት መቆጠር የለባቸውም በሚል ስማቸው እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጥሩ ሁኔታ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን፤ ዴሞክራሲ ካዳበሩ አገራት ጋር ሲነፃፀር ይህ ሁሉ ደካማ ነው። ያም ሆኖ፤ በኢትዮጵያ ከነበረው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ አንፃር ከተገመገመ ጥሩ ለውጦች መጥተዋል ተብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል አሁን መንግስት የህዝብ ሀብቶችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከታየ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዥው መንግስት እኩል የፖለቲካ ምህዳሩን እየተጠቀሙ ነው ማለት አይቻልም፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁን ላለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ብቁ አይደሉም ማለት ይቻላል የሚሉት ዶክተር ገብረ ክርስቶስ፤ በአሁን ወቅት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማሟሟቅ ካልሆነ በስተቀር ምንም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፈው ከደጋፊዎቻቸው ጋር የመነጋገር ሁኔታ እንደማይታይ ያብራራሉ፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች በሚያስብል ሁኔታ በየቢሯቸው ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ይህም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ማለት ይቻላል። በመርህ ደረጃ ግን እስካሁን የተፈጠረ ችግር የለም። በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉና እየተሰበሰቡ እንደሚገኙ ይገልፃሉ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጃፋር በድሩ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በሁለት አመታት የለውጥ ጉዞ በአገሪቱ ውስጥ በተቃዋሚነት ሲሳተፉ መድረኩ ጠብቧቸው በሚፈለገው ደረጃ ለአገሪቱ ዴሞክራሲ ግንባታ አስተዋፅኦ ማድረግ ያልቻሉ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በትጥቅ ትግል ለአርባ ዓመታት የቆዩ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ እነዚህን ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበትና አጀንዳቸውን ለህዝብ አቅርበው የሚወዳደሩበት ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ተደርጓል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ በርካታ ስራ ተከናውኗል፡፡ በሰዎች ላይ ይደርሱ ከነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማስቆም፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን ለህግ ለማቅረብ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀምባቸው የነበሩ ተቋማትን በመዝጋት ሙዝየም የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ በሌላ በኩል አፋኝ የነበሩ ህጎችን የማሻሻል ርምጃ ተወስዷል። በዚህ ረገድ መጠነ ሰፊ የህግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። በተለይ የፀረ ሽብር፤ የሲቪክ ተቋማት እና የመገናኛ ብዙሀን ህግ ተሻሽለዋል፡፡
እንደ አቶ ጃፋር ማብራሪያ፤ ከለውጡ በፊት አፋኝ በተባሉ ህጎች ምክንያት አገሪቱ እርዳታ ታጣ የነበረ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት አፋኝ የተባሉ ህጎች ተሻሽለው ወደ ተግባር እየተገባ ይገኛል፡፡ የፍትህ አካላት ዘመናዊና ከፖለቲካው ጥገኝነት ለማላቀቅ በተሰራው ስራ ከፓርቲ አባል ውጪ የሆኑ ሰዎች በቦታው እንዲሰየሙ ተደርጓል፡፡ በአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ላይም ሰፊ የሆነ የለውጥ ስራ ተከናውኖበታል፡፡ ከላይ የተቀመጡት አጠቃላይ ተደምረው የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አላማና አጀንዳቸውን ወደ ህዝቡ ይዘው እንዲቀርቡ በር የከፈተ ነው፡፡ መገናኛ ብዙሀንም ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታቅበው እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። የኤሌክትሮኒክስና የህትመት መገናኛ ብዙኃን የፈለጉትን አጀንዳ ይዘው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩ ቀድሞ ከነበረው እንዲሰፋ ተደርጓል የሚሉት አቶ ጃፋር፤ በአገሪቱ መድብለ ፓርቲ እንዲስፋፋ ለማድረግ የምርጫ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ባህል እንደሚያስፈልገው ይና ገራሉ። በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ግን እንደዚህ ዓይነት ባህሎች አልተለመዱም። እውነተኛ የሆነ ነፃነት ተሰጥቶ፤ ሀሳብን አቅርቦ በሀሳብ የበላይነት አሸንፎ የመውጣት ልምድ የለም። አሁን የሚታየው በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ሀሳብን አቅርቦ ሀሳብን የመሸጥ ሁኔታዎች ሳይሆን ምርጫ ሲደርስ ብቻ የመንቀሳቀስ ነው:: ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀደም ብለው ስትራቴጂያቸውን ማስተዋወቅ ላይ ድክመት ያለባቸው ሲሆን በውይይቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ::
ለማንኛውም ሰላማዊ ምርጫ የህግ የበላይነት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚያወጡት ሪፖርት ሲታይ ለህግ የበላይነት መከበር መንግስት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኘ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጃፋር፤ በተለያዩ ቦታዎች ሰላም ለማስፈንና የተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት ለመፍጠር የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ህጋዊ አለመሆኑ እንቅፋት መፍጠሩን ይገልፃሉ፡፡ በፓርቲዎች ዘንድ ዴሞክራሲያዊ የሆነ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድ ስለሌለ አሁንም ድረስ ‹‹እኔ ካላሸነፍኩ ዴሞክራሲና መረጋጋት የለም›› የሚሉ መፈክሮች በተለያዩ ቦታዎች በሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎች ላይ እየተንፀባረቁ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው የዴሞክራሲ ባህል አለማደጉን ሲሆን፤ ለረጅም ዓመታት በአፈና ውስጥ የቆየ የፖለቲካዊ ስርዓት የወለደው እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
የመንግስት የውስጥ ለውጥ (የተቋማት ሪፎርም)
ለውጡ ተቋማዊ መሆን አለበት ሲባል በግለሰቦች ላይ የተመረኮዘ መሆን የለበትም ማለት ነው፡፡ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ተቋማት በተቀመጠው ህግና መመሪያ መሠረት መንቀሳቀስና መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ህጉና መመሪያው ሰው ሲቀየር አብሮ የሚቀየር፤ በግለሰቦች ፍላጎት ብቻ የሚሠራ መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም ሥራ በተቋማዊ ደንቡ መሠረት መሰራት አለበት እንጂ ወደኋላ ተመልሶ በሚመጡ ሰዎች ፍላጎት፤ በእነርሱ አስተያየት ወይም ሃሳብ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሌለበት ይጠቀሳል፡፡ ለውጡ ተቋማዊ መሆን አለበት የሚባለው ተቋማት ማሻሻያ ሲደረግባቸው፣ መልክ ባለው መንገድ እንዲሻሻሉ ብቃትና ዕውቀት ባላቸው ሰዎች እንዲመሩ ሲደረግ ነው፡፡ አሁን በአብዛኛው ሹም ሽር እንደሚስተዋለው ተቋማትን በኃላፊነት እንዲመሩ የሚሰየሙ ሰዎች ብቃታቸውና እውቀታቸው ታይቶ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቢኔቸውን በሰየሙበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
እንደ ዶክተር ገብረ ክርስቶስ ገለፃ፤ በቅርቡ በመጡ ፖለቲካዊ ለውጦች ምክንያት መንግስት የውስጥ ለውጦች አድርጓል። በዚህም ጥሩ የሚባል ገፅታ መገንባት ተችሏል፡፡ ተቋማትን እንደ አዲስ ሪፎርም የማድረግ ስራ ከመንግስት የውስጥ ለውጥ አንዱ ማሳያ ተደርጎ መወሰድ ይችላል፡፡የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከፍተኛ የሆነ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም በንቃት የመንቀሳቀስ ሁኔታዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን፤ ውስጣዊ ማነቆዎች እንዳሉ በተለያየ መንገድ ይታያል። ለዚህም በአገሪቱም የተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱትን የሰላም መደፍረሶች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
እንደ አቶ ጃፋር አባባል፤ በሁሉም የመንግስት ተቋማት፤ በተለይ ህብረ ብሄራዊነትን ከማስረፅ አኳያ በተቋማት ከከፍተኛ አመራር እስከ ሰራተኛው ድረስ የተወሰዱ የሪፎርም ርምጃዎች አሉ። ሪፎርሙ ጎልቶ የሚታይባቸው በተለይ የደህንነትና የመከላከያ መስሪያ ቤቶች ናቸው። የአገሪቱን ብዝሀነት በሚያንፀባርቅ መልኩ አመራሮች እንዲቀየሩ ተደርጓል። አመራሮቹ ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት እንዲኖርና ለመንግስት የአሰራር ስርዓት ተገዥ የሚሆኑበት አካሄድ እንዲኖርና አጠቃላይ የአገሪቱ ህብረ ብሄራዊነት በሚያንፀባርቅ መልክ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ ተቋማቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀም መሳሪያ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ እንደመሆናቸው ከዚህ እሳቤ እንዲወጡ በህግ አግባብና ዴሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር ተከትለው የሚጣልባቸውን አደራ እንዲወጡ ተደርገው ተደራጅተዋል። በሌላ በኩል፤ ተቋማቱ በባለሙያ የተደራጁ እንዲሆኑና ከፓርቲ ጣልቃ ገብነት ተላቅቀው አገርንና ህዝብን የመጠበቅ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ሰፊ የአቅም ግንባታ ስራ ተከናውኗል፡፡ የዚህም ውጤት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
በተቋማት ውስጥ ያለው የለውጥ ስራ በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥልና በተለይ ወደፊት ውጤቶቹ እየታዩ መሄድ አለበት። የተቋማትን ለውጥ ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ በተጨባጭ አገልግሎት የሚያገኝበት መንገድ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። አሁን ያለው በፅንሰ ሀሳብና በለውጥ ደረጃ ሲሆን፤ ይህ ለውጥ ወደ ተግባር ተለውጦ ገለልተኛ በሆነ መንገድ ቅልጥፍና ያለው አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ በአፋጣኝ መጀመር እንዳለበት አቶ ጃፋር ይጠቁማሉ፡፡
የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት በሚያስጠብቅ መንገድ መስራት አለበት፡፡ በአሁን ወቅት የለውጥ እንቅስቃሴውን በሚቃወሙ ሀይሎች እየተደረገ የሚገኘው ነገር ሆን ተብሎ በመተንኮስ ሰላምና መረጋጋት ለማጥፋት፤ ህዝቡ ተማርሮ “ዴሞክራሲ ይቅርብኝ” እንዲል የማድረግ እንቅስቃሴ እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በጥንቃቄና በብልሀት መያዝ ያለበት ነገር እንደሆነና በአገሪቱ ዴሞክራሲና የህግ የበላይነት አብሮ ማስኬድ እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡ ሁለቱን ጉዳዮች አቻችሎ ማስኬድ የሚቻልባቸው መንገዶች ስላሉ ተቋማት ሪፎርማቸውን አጠናክረው መስራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ፡፡
በውጪው ዓለም የተፈጠረው ተፅዕኖ
የአገሪቱ የውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በውጪ አገራት ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እንድታገኝ አስችሏታል፡፡ እንዲያውም፤ በውጪ የተገነባውን መልካም ገፅታ ያክል በአገር ውስጥ እየተሰራ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ለውጥ በውጪው ዓለም ዘንድ ያመጣው ለውጥ ሲታይ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከአረብ አገራት፤ ከምዕራባውያን፤ እንዲሁም ከጎረቤት አገራት፤ በተለይ ከኤርትራ ጋር የተፈፀመው እርቅ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆን ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ያላትን ስም እንደቀየረው ዶክተር ገብረ ክርስቶስ ያብራራሉ፡፡
በተጨማሪም፤ በአሁን ወቅት በአገሪቱ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ አይደለም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ስጋቶች አሉ፡፡ አገሪቱ በውጪ አገራት ያላት ስዕል በአገር ውስጥ የለም፡፡ አገሪቱ በውጪ አገራት ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነት በአገር ውስጥ መፍጠር መቻል አለበት፡፡ በተወሰነ ደረጃ ቀሪ የሆኑ ስራዎች ስለሚገኙ እነሱን ማጠናቀቅ ይገባል። በውስጥ ያለውን ችግር አቻችሎ በአገር አንድነት ላይ መሰራት እንዳለበትም ይገልፃሉ፡፡
እንደ አቶ ጃፋር አባባል፤ በሁለቱ ዓመታት በተሰሩ ፖለቲካዊ ስራዎች በውጪው ዓለም አኳያ የመጡ ለውጦችን በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ነው፡፡ ሽልማቱ የመጣው በተሰሩ ውጤታማ ስራዎች መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት ማስፈን ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ አገር በሰብዓዊ መብት፤ ጋዜጠኞችን፤ የመብት ተሟጋቾችን እና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ባለማሰር ከፍተኛ መሻሻሎች መጥተዋል፡፡ አጠቃላይ የለውጡ እንቅስቃሴ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በበጎ ጎን የመሸፈኑ ሁኔታ ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቷል፡፡ ይህ አገሪቱ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩባት መሆንዋን አስመስክሯል፡፡ በአሁን ወቅት ያሉትን ለውጦች አጠናክሮ ማስኬድ ከተቻለ በውጪ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር ይቻላል፡፡ የአገሪቱ ህዝብ በዴሞክራሲ እጦትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰው የማይሰደድባት ከሆነች በአፍሪካ ደረጃ የዴሞክራሲና የብልፅግና ተምሳሌት የምትሆን አገር የመፍጠር ጅምር አሳይቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
መርድ ክፍሉ