
ከመቶ ሃያ አራት ዓመታት በፊት ፋሺስት ጣሊያን በአምባገነኑ ቤኒቶ ሞሶሎኒ እየተመራ ኢትዮጵያን ወረረ። ምስጋና ለማይዘነጉት ጀግኖቹ አርበኞቻችን ይግባና ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ሞሶሎኒና ግብረአበሮቹ ብዙም ሳይደላደሉ ከአገር ቤት በቅሌት ተባረሩ። ይህም ታላቅ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ በርካቶቹ የአፍሪካ አገራት የነፃነት ቀናቸውን ሲያከብሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ የድል በዓል ለማክበር አበቃቸው። አልፎ ተርፎም ይህ ታላቅ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ ዛሬም ድረስ በወርሃ የካቲት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለመዘከር በቅቷል።
124ኛው የአድዋ ድል በዓል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ሲከበርም የድሉ መሪ አፄ ምኒልክ በበቀሉባት ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ በበዓሉ ዋዜማ የጎዳና ላይ የስምንት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በማካሄድ ጀግኖች አርበኞች ተዘክረዋል።
‹‹ኑ ለእምዬ ምኒልክ ክብር እንሩጥ›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ውድድር ከአርባ ሺ በላይ ህዝብ እንደተሳተፈ የውድድሩ አዘጋጅ ‹ፋን ኢትዮጵያ የስፖርት አገልግሎት› ድርጅት የገለፀ ሲሆን በውድድሩ ጀግኖች አርበኞችና የአርበኞች ልጆች፣ ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። በነጭ የመሮጫ ካኔቴራ ‹‹ለኢትዮጵያ አንድነት እንሩጥ›› በሚሉ መልዕክቶች የደመቁት የውድድሩ ተሳታፊዎች በተለይም ወጣቶች በውድድሩ ከመዝናናት ባለፈ የአድዋ ታሪካዊ ድል የአገር አንድነት ዋልታና ማገር በመሆኑ ለዚህ ውድ ሕይወታቸውን ከከፈሉ አባቶች ከልዩነት ይልቅ አንድነትን መማር እንደሚገባ ለማንፀባረቅ ሞክረዋል።
ሰሜን ሸዋ ለአትሌቲክስ ምቹ ከሆኑ የአገራችን አካባቢዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን በርካታ አትሌቶች ከተለያዩ ክለቦች ተፎካካሪ መሆን ችለዋል። በዚህም በሴቶች መካከል በነበረው ፉክክር የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛዋ በላይነሽ ውበቴ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፣ የግል ተወዳዳሪዋ ከበቡሽ ይስማው ሁለተኛ ሆና ፈፅማለች። ትዕግስት ገዛኸኝ ከፌዴራል ፖሊስ ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቀች አትሌት ነች። በተመሳሳይ በወንዶች የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አትሌት የሆነው ቢምረው አወቀ ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ዳዊት ሃብቴ ከተመሳሳይ ክለብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። መንገሻ ፀጋዬ ከአንጎለላና ጠራ ወረዳ ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈፅሟል።
በቀድሞዋ የስምንት መቶ ሜትር ኮከብ አትሌት ፋንቱ ሚጌሶ የተቋቋመው ‹ፋን ኢትዮጵያ የስፖርት አገልግሎት› ድርጅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ከተሞች የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን እያካሄደ ይገኛል። የተለያዩ ወቅታዊ ነገሮችን መነሻ በማድረግ የጎዳና ላይ ውድድሮችን በተለያዩ ከተሞች የሚያካሂደው ፋን ኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን ከማፍራት ባሻገር ለበርካታ አትሌቶች የውድድር እድሎችን ለመፍጠር በማሰብ ውድድሩን እንዳካሄደ ገልጿል። በተለይም የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች እምብዛም በማይካሄድባቸው ከተሞች ትኩረት በማድረግ አትሌቲክስን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ በመፍጠር በህብረተሰብ አቀፍ ስፖርት(ማስ ስፖርት) እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ
ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አሳውቋል።
በሃዲያ ሆሳዕና፣አርባ ምንጭና ሀላባ ከተሞች በቅርቡ የተለያዩ የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድሮችን በስኬት በማድረግ በርካታ ህዝብ አሳትፎ ተወዳጅነትን እያገኘ ያለው ፋን ኢትዮጵያ ውጤታማና ወጣት አትሌቶችን ከክለቦች ጋር ከማገናኘት ባለፈ ዓለም አቀፍ የውድድር እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች አትሌት ፋንቱ ጠቁማለች። ፋን ኢትዮጵያ ብዙም ባልተለመደው የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ደፍሮ በመግባት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ የገለጸችው አትሌት ፋንቱ ካለፉት ውድድሮች ልምድ በመቅሰም ወደፊት የሚያካሂዳቸውን ውድድሮች በተሻለ የጥራት ደረጃ ለማከናወን ጥረት እንደሚያደርግም አስረድታለች። መሰል ውድድሮች በየዞኑ እና ወረዳው ማካሄድ ቢቻል፤ ህዝቡ ስፖርቱንና አትሌቶችን በባለቤትነት ስሜት በመደገፍ የተለያዩ አካባቢዎችን የአትሌቶች መፍለቂያ ማድረግ እንደሚቻልም አትሌት ፋንቱ ጠቁማለች።
ፋን ኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የሚያደርጋቸው ውድድሮች ከስፖርታዊ ኩነትነቱ ባሻገር ሰላም፣ፍቅርና አንድነትን የተመለከቱ መልዕክቶች የሚተላለፉበት ቢሆንም ውድድሩን ስፖንሰር በማድረግ በአጋርነት የሚሰሩ ድርጅቶች እንደሌሉ የተናገረችው አትሌት ፋንቱ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ ከተሞች ውድድሩን ለማሳደግ ያሳዩትን ጥረት በመጥቀስ ምስጋና አቅር ባለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
ቦጋለ አበበ