የመደመርን ተግባራዊ ፋይዳና ወቅታዊም ሆነ ሀገራዊ ብሎም አህጉራዊ መፍትሄነት ለመረዳት ቃሉን ከቃልነት ባሻገር ውስጡ ታጭቆና ተሰድሮ ያለውን ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ መመርመርና መረዳትን አጥብቆ ይጠይቃል።
በእኔ እሳቤም በመደመርና ባለመደመር ድምር ውጤት መሃል ያለውን ልዩነት የብርሃን የጨለማ ያህል እጅጉን ስፊ ነው። ፍቅር ፣ሰላምና አንድነትን የሚያመጣ የመደመር ስሌት የእኩል ይሆናል ውጤቱ ዘረኝነትን፣ መንደርተኝነትን፣ ሌብነትንና ሌቦችን በመቀነስ ሁለንተናዊ ለውጥ ሰላምን፣ነፃነትን እኩልነትን፣ አንድነትን፣ ብልፅግናንና ዕድገትን መጨመር ነው። ከዚህም በላቀ መከባበር፣ መዋደድ፣ትዕግስት ፣አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነትም ነው።
ያለመደመር ቀመር እኩል ውጤት ከይቅርታ ይልቅ ለቂም የፈጠነ ነው። ከእርቅ ይልቅ በቀልን መምረጥ ነው። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን ከሰላም ይልቅ ጠብን ማስቀድም ነው። አክራሪ ብሄርተኝነት፣ የጎሳ ቡድንተኝነት፣ መንደርተኝነት፣ ድህነት፣ ጉስቁልና፣ መከፋፈልና መፈራረስ ነው።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ፍቅር ፣ሰላምና አንድነት በሚያመጣ የመደመር ስሌት የእኩል ይሆናል ውጤቱ ምን እንደሆነ ጠንቅቆ ገብቷቸዋል። በመደመር ጽንሰ ሃሳብ በጋራ መግባባት በይቅር መባባልና እርቅን መሰረት በማድረግ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ገልጠዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና በአመራር ቡድናቸው የተጀመረው ይህ የለውጥ እንቅስቃሴም በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት ለሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋን አጭሯል፡፡ በነገ ላይ የተስፋ ስንቅን እንድንቋጥርም ምቹ ጥርጊያ ሆኗል።
አሁን ላይ የዶክተር ዓብይ እሳቤ ከነበረበት ፅልመት አውጥቶ ወደ ብርሃን እንደሚያደርሰው የኢትዮጵያ ህዝብ ተረድቷል። ተገነጣጥሎና ተለያይቶ መኖሩ ምንም ትርፍ እንደማያስገኝለት ጠንቅቆ ማወቅ ጀምሯል። ከቀደሙት ዓመታትና ካለፉት ወራት በተሻለ ዛሬ ላይ እንቢኝ ለአክራሪ ብሄረተኛ፣እንቢኝ ለዘረኛ፤ እንቢኝ ለሌባ ማለትም ጀምሯል። የጠፋበትን አንድነት አግኝቷል። ደክሞ ያገኘውን አንድነት አጥብቆ መያዝ ጀምሯል። አገሪቱም በህዝቡ ያላቋረጠ አንድነታዊ መሻትና ፍላጎት ወደ መረጋጋት መጥታ የሰላም ፍሬን ማጨድ ጀምሯለች።
በመደመር ጽንሰ ሀሳብ በጋራ መግባባት በይቅር መባባልና እርቅን መሰረት በማድረግ አዲስ የለውጥ ጉዞም ከራሳችን ተርፈን ጎረቤት ማስታረቅ፤ ማስተቃቀፍና ማፋቀር ችለናል። በዚህ ተግባራችንም ዓለምአቀፍ አድናቆት ይቸረን ጀምሯል። ቀደም ሲል ጀርባቸውን የሰጡን ዛሬ ላይ በውዴታ ፊታቸው ወደ እኛ አዙረዋል።
ይህ ማለት ግን የመቀነስ ቀመር ድምር ውጤት አራማጆች አሁንም ቢሆን አቋራጭ የስልጣንና የሀብት ጥማታቸውን የማርካት ሩጫ ጨርሶ ተወግዷል ማለትን የሚያስደፍር አይደለም። የመደመር ውጤት የሆነውን ለውጥ ለመቀልበስ፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመደመርን መርህና ተግባር የሚቃረኑ ሰንኮፎች ጨርሶ አልጠፉም።
የለውጡን ፍጥነትና ስኬታማነት በየደረጃው በመረዳትና በመገምገም ተገቢውን ተሳትፎ ከማድረግና ሂሳዊ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ «እኛ ከሌለንበት» የሚሉ ከአፈርኩ አይመልሰኝ ልክፍት የፖለቲካ ሰብዕና ሰለባ የሆኑ፤ ግላዊ የልዩ ፍጡርነት ስሜት (false or wrong self perception) ሰለባዎች ዛሬም አሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ተለያይቶ እንዲያስብና ተግባብቶ እንዳይኖር ፅኑ ፍላጎት ያላቸው የዚህ አሳቤ አራማጆች በመንደረተኛነት ስሜት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ፍላጎታቸውም የሚመኙትን ስልጣን ለመቆናጠጥ የህዝብ ማሰቢያ ላይ የበላይነትና የበታችነት ወላፈን በመዝራትና ስሜት በማነሳሳት ንዴት ማስታጠቅና እንዳሻቸው ህዝቡን እየዘረፉ ሀብት ማከማቸት ነው። ለእነርሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም፣ ነፃነት፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ ብልፅግናና እድገት ምናቸውም አይደለም።
መሻታቸው ፖለቲካዊ ሃሳብና መፍትሄ ከማመንጨት ይልቅ ሥልጣን ለመያዝ መናፈቅ፣ መመኘትና መጎምዠት ነው። ከዚህም አልፎ በጎሳና በጎጥ ተደራጅተው በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ፀብ በመዝራትና ጥላቻን በመስበክ ማበጣበጥና የህዝቡን ሰላም ማደፍረስ ነው።
እነኚህ መንደራዊ ሹማምንቶች በድብቅ በሚያስተላልፉት መልዕክትም ሆነ የማህበራዊ ድረ ገፅ አንድ አካል ፌስ ቡክ እለት በእለት በሚፅፉት ፅሁፍ ህዝብን በማናቆር ድርና ማግ ሆነን የተሰፋንበትንና የተቆራኘንበትን የአንድነት ሰንሰለት መበጣጠስ ከተሳካላቸውም ሀገሪቱን ማፍረስ ነው።
በዚህ እኩይ ተግባራችው አንዳንድ ቦታ በሚያስነሱት ሁከት እኩይ ዓላማቸው ተያይዞ የነደደ ቢመስላቸውም እስከአሁን ድረስ ግን የተለሙት ትልም እውን ሊሆንላቸው አልቻለም። ደግም ሆነ ክፉውን ዘመን በጋራ የተሻጋገረውና ተዋዶ፣ ተጋብቶ፣ ተስማምቶና ተፋቅሮ የኖረው ህዝብ በሀገሩ አንድነት አጥብቆ ስለሚያምን በመሻታቸው ከፍታ በመራዥ ሃሳባቸው ሊነዳላቸው አልቻለም።
በእርግጥ እነዚህ የእፉኝት ልጆች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት ሲሰብኩ፤ይሄን እንደ ድክመትና የህግ የበላይነት ያለመኖር አድርገው በመቁጠር በፈፀሙት እኩይ ተግባር በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች በህዝብና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ዜጎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ መተኪያ የሌላት ህይወታቸውንም ተነጥቀዋል።
ይሁንና በመደመር የይቅርታና የፍቅር መርህ የህግ የበላይነት የለም ማለት ግን አልነበረም። ምንም እንኳን የለውጡን ውጤት «ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ» በሚል ልጓም አልባ ስሜታዊነትና ተጓዳኝ ተግባር ብዙዎች በራሳቸው መንገድ ሲጓዙ ቢታዩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንፃሩ ለውጡን ሰላማዊና ከወንጀል የነፃ ለማድረግ ብሎም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎችን በትዕግስት ሰርተዋል።
የለውጥ ጊዜው አጭር ቢሆንም በስፋቱና በጥልቀቱ ግን በሀገራችን ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ስር ነቀል የአመራርና የአሰራር ለውጥና ማሻሻያዎች ከማድረግ ጀምሮ መሰረታዊ ለውጦችን ተግብረዋል። ከሚያስተዳድሩት ህዝብ ጋር በመሆን በተለይ በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር በይፋ ማጋለጥ ችለዋል። ቃል ለገቡለት ህዝብ በመደመር ቀመር የእኩል ይሆናል ውጤትን በአደባባይ ማስመስከር ጀምረዋል።
መንግስታዊና ህዝባዊ ሃላፊነት ወደጎን በመተውና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ አስከፊ ምዝበራ የፈፀሙ ብቻም ሳይሆን የዜጎችና የቡድኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በግላጭ ሲጥሱ የነበሩትን አካላት የህግ መርህን በመከተል በማስረጃ መያዝ ተችሏል።
መንግስት ለህዝቡ ቃል በገባው መሠረት ሰብአዊ መብት የጣሱ፣ሀገርን የዘረፉና የዚህችን ሀገር መፃኢ ተስፋ ለማጨለም የተንቀሳቀሱ አካላትን እንዲሁም የሰኔ 16ቱን ጥቃት ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን በማቀነባበር የተጠረጠሩትን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ ተግቶ እየሰራ፤ ማንኛውም ሰው ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይችልና ከሀገሪቱ ህግና ህገ መንግስት በላይ እንዳልሆነ እያስመስከረ ይገኛል።
ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት ጥቂትና ለውጥ የማይዘልቃቸው የልዩ ፍጡርነት ስሜት (false or wrong self-perception) ሰለባ ግለሰቦች ከደመ-ነፍስ ስሜት ወጥተውና ምክንያትን ተመርኩዘው ከማየት ይልቅ አይን ባወጣው ዘረፋ በህግ ተጠርጥረው የተያዙና በፍለጋ ላይ ለሚገኙ ሌቦች ከለላ የመስጠትና ፈፃሚዎቹን የማደን ተግባርን ከብሄር፣ፓርቲ ወይም ተቋም ጋር ለማያያዝ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
«ለምን እየሰረቅንንና እየዘረፍን አንኖርም?» የሚል አሳፋሪና ህሊና ቢስ ሙግት የሚገጥሙት እነዚህ የእፉኝት ልጆች፣ ሌብነታቸው ሲጋለጥ« እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አስተሳሰባቸው ከብሄር ጋር ከተያያዘ ጥቃት ጋር ለማስተሳሰር የማያስኬድ ጉዞን ለመራመድ አንድ እግራቸውን ሲያነሱ ታይተዋል።
በዚህም መንግስታዊና ህዝባዊ ሃላፊነት ወደጎን በመተው ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ኢትዮጵያን ከዘረፏት ካስለቀሷት ከገረፏት እና የድህነት መስቀል ላይ ቸንክረው ያስቀሯት ሌቦች ከሰሩት ወንጀል በማይተናነስ መልኩ ነውረኛ ወንጀል መፈፀማቸው ሊሰመርበት ይገባል።
በእርግጥ ለውጡ የመጣላቸው ሳይሆን የመጣባቸው እነዚህ አንጃዎች ጨለማው እንዲቀጥል ካላቸው ፍላጎት መሰል ጉዞን ምርጫቸው ማድረጉ አይደንቅም። ይሁንና አንድ በጥንቃቄ አግባብ መታወቅ ህዝቡም መረዳት ያለበትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫም እንዳረጋገጡት ወንጀለኛ ወገንም፣ ብሔርም፣ዘርም ሆነ ሞራል የለውም፡፡
ከዚህም ባሻገር አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በመግለጫቸው «ወንጀለኛ የማንም ብሔር ተወካይ አይደለም፣ የሚወክለው ራሱን ብቻ ነው» ማለታቸውን እንዲሁም ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙሃን በተላለፈው የሜቴክ ዶክመንተሪ ላይ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ «ለህዝብም ለብሄርም ብሎ የሚዘርፍ የለም፤ የሚዘርፈው ለራሱ ነው፣ ዘራፊ አገርም ሞራልም የለውም» ሲሉ መናገራቸውን መለስ ብሎ ማጤን እጅጉን አስፈላጊ ነው።
በእርግጥ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ይሁንና አንድ ሊታወቅ የሚገባውና ማብራሪያ የማያስፈልገው እውነት ቢኖር ሌባ እራሱን ችሎ ሌባ ነው። የሌቦቹን ነውረኛ ተግባር ከብሄርና ከፓርቲ ጋር በማስተሳሰር የሚኬድ ጉዞም መዳረሻው ጥፋት ብቻ ነው።
ከእያንዳንዱ ብሔረሰብ ውስጥ ብዙ መልካም ዜጎች እንዳሉ ሁሉ ሀገር ዘራፊ ሌቦችም አሉ። ዋናው ነገር በህግ መነጽር ተፈትሸውና ተለቅመው እስኪወጡ ድረስ መታገስ ብቻ ነው። የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልም በመሰል ውዥንብር ከመታለል ወጥተን ሌባ የሚወክለው አመሉን ብቻ መሆኑንና ተግባሩ የግለሰቡ ህመሙም የሁላችን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
በመሰለኝ እሳቤ ቶሎ ብለን ለውጡን ወደ መጠራጠር የምንሄድ ከሆነ በመሰረቱ ትክክል አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ለውጡ ይዞት የተነሳው ትልቅ ራዕይና አላማ በመደመር ቀመር የእኩል ይሆናል ውጤት ዘረኝነት መንደርተኝነት አልያም ሌብነትና ሌቦችን በመቀነስ በሁለንተናዊ ለውጥ ሰላም፣ ነፃነት እኩልነት አንድነት ብልፅግናና እድገት መጨመር መሆኑ ሁሌም ቢሆን በአእምሯችን ሊመጣ ይገባል። ከሁሉም በላይ በመደመር ቀመር የእኩል ይሆናል ውጤት የማይገባቸው ወይም ደግሞ ገብቷቸውም የማይዋጥላቸው የ«እኛ ከሌለንበት» አንጃዎች ለውጡን ለመገዳደር እንደማይተኙ መረዳት ያስፈልጋል። ለዚህም ችኮላ አደገኛ መሆኑን መገንዘብና የምንፈልገው ነገር ዛሬውኑ ካልተደረገልን ከሚል ሙግት ራሳችንን ማራቅም ግድ ይለናል።
ውጤቱን «ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ» ከሚል ልጓም አልባ ስሜታዊነት ወጥተን ገንቢ በሆነ ሂሳዊ አመለካከት critical and constructive way of thinking የመነሻችን፣የሂደታችንና የመዳረሻችንን ምንነትና እንዴትነት በአግባቡ መረዳትም ግድ ይለናል።
በመደመር ቀመር የእኩል ይሆናል ውጤትን ለማግኘት ከስሜታዊነት እየወጣንና በሰለጠነ፣ቅንነትን በተላበሰ፣በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የዕለት የዕለቱን ወይም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የነገውንና የትውልደ ትውልድን እጣ ፈንታ አርቀን በመመልከት ለውጡን በገንቢ ሂሳዊ አቀራረብና በመፍትሄ ጠቋሚነት መደገፍ ይኖርብናል።
እስከዛሬ በመጣንበት መንገድ እየተባላን እየተናከስን በጎሳ እየተቧደንን ከተጓዝን ያው ጨለማ ውስጥ እንዳክራለን። እናም ዛሬም ሆነ ነገ ጠንቀቅ ብሎ እነኚህን ለዘመን ዘመናት ተፋቅሮ ተዋዶ በኖረ ህዝብ መሀከል ዙፋናዊ ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ ፀብን እየዘሩ ጥላቻን እያጎረሱ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ወዲያ ወዲህ የሚንከላወሱትን የእፉኝት ልጆች ጀርባ ልንሰጣቸው ይገባል። ለውጡ የመጣባቸው መሆኑንና ጨለማው እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸውም በመረዳት የእኩይ ተልዕኳቸው ማስፈጸሚያ እንዳንሆን ማስተዋልና ጥንቃቄን መታጠቅ ግድ ይላል።
ኢትዮጵያችን በመደመር ቀመር በየእኩል ይሆናል ውጤት ትሩፋቶች ታጅባ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እንድትለወጥ፣ እንድትሻሻልና እንድታድግ ከፈለግን አሁን እንደጀመርነው እንቢኝ ለዘረኞች እንቢኝ ለሌቦች በሚል አንድነት የጋራ እድገት ወደ ተባለ ጅረት ልንወስዳትም ጊዜው አሁን ነው።
እዮብ