ባለፈው ማክሰኞ የተከበረው የገና በዓል ዕለት ካጋጠመኝ ልጀምር:: ሰዓቱ ማታ ነው:: ከላምበረት መናኸሪያ በዋናው መስመር ወደ ጉርድ ሾላ እየወረድኩ ነው:: በመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉ ምግብና መጠጥ ቤቶች ሁሉ በባህል ዘፈኖች ደምቀዋል:: በቡድን በቡድን ሆነው የሚሄዱ ሰዎች ንግግር ሞቅ ያለ ቢሆንም ያው በዓል ስለሆነ አልገረመኝም::
አንድ ወጣት ግን ከሚዛኑ ውጭ እየተንቀሳቀሰ ከአንድ ግቢ በር ላይ ቆማ ስልክ የምታወራ ሴት ሄዶ እጇን ያዘው:: ስልክ ለመንጠቅ አይደለም፤ ፆታዊ ትንኮሳ መሆኑ ነው:: እየተጨቃጨቁ ሳለ በአቅራቢያ ካለ ሬስቶራንት በር ላይ ሻይ ቡና የሚሉ ወንዶች ገፈታትረው አባረሩት:: ልጁ እየተወለጋገደ ወደታች ወረደ፤ እኔም ጉዞዬ በዚያው መስመር ስለነበር እግረ መንገዴን የልጁን ሁኔታ መከታተል ጀመርኩ:: የጉርድ ሾላው ዋና መስመር ሊገባ ትንሽ ሲቀረው አንዲት ብቻዋን የምትሄድ ሴት ሄዶ አንገቷን አቀፈው:: እንደምንም ገፈታትራው ስትሄድ አሁንም ይደርስባታል:: ከዚችኛዋ ጋር የከፋ ግጭት ውስጥ ሳይገቡ አመለጠችው::
ልጁ ሙሉ ጤነኛ ነው (ስካር እንደ ጤና ጉድለት ካልታየ በስተቀር):: ሙሉ ጤነኛ ነው ያልኩበት ምክንያት የአዕምሮ ችግር ያለባቸው ሰዎች በአካላዊ ገጽታም ሆነ በአለባበስ ስለሚያስታውቁ ነው:: የዚህ ወጣት ችግር ስካር ብቻ ነበር::
ከቆይታዬ በኋላ ወደቤት ስመለስ ደግሞ ይሄኛው አጋጠመኝ:: የአንድ አካባቢ (በዚህ ሁኔታ አካባቢውን መግለጽ ልክ መስሎ ስላልታየኝ ነው) መገለጫ የሆነ የባህል ልብስ የለበሱ ሦስት ወጣቶች እየሄዱ ነው:: ሰዓቱ ወደ ምሽት 3፡00 እየተጠጋ ስለሆነ ብዙም መንገደኛ የለም:: እነዚህ በጋራ የሚሄዱ ወጣቶች በመንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ ይሳደባሉ:: ተሰዳቢው ሁሉ በስካር ሃይል መሆኑን ስለተረዳ ከምንም አልቆጠራቸውም፤ መልስ የሚሰጣቸውም የለም:: እንዲህ አይነት የስካር ጣጣዎችን እያየሁ ወደ ቤቴ ገባሁ::
እርግጥ ነው ስካር ሁሌም የምናየው ነው:: ታዲያ ምኑ ያስገርማል ያሰኝ ይሆናል፤ ግን በበዓል ቀን እንዲህ አይነት ነውር ነገር እንዴት አያስገርምም? ኢትዮጵያዊነት የኩራት መለያ ነው የሚባል የባህል ልብስ ለብሶ አስነዋሪ ነገር ማድረግ አያሳፍርም? ያንን አካባቢስ እንዴት ሊወክል ይችላል? ሲቀጥል ደግሞ ስካር የሚበዛውም በበዓል ቀን ነው:: ለምሳሌ ያ ያገኘውን ሴት ሁሉ ሲጎትት የነበረ ወጣት አይነት ሌላ ቀን አጋጥሞኝ አያውቅም:: የሌላ ቀኑ ስካር ልክ ያለው ነው:: በነገራችን ላይ ስካር ልማዳቸው ያልሆነ ሰዎች የሰከሩ ዕለት ሁሌም ከሚሰክሩ ሰዎች በላይ ያስቸግራሉ:: እነዚህ ብዙ ጊዜ የማይሰክሩ ሰዎች ደግሞ የሚሰክሩት በበዓል ቀን ነው::
ሌላው የበዓል ገፅታ የዚህኛው ፍጹም ተቃራኒ ነው:: ይሄውም ሁላችንም በመገናኛ ብዙኃን እንደምናየው ከጎዳና ተዳዳሪዎችና ከአቅመ ደካሞች ጋር በዓልን ማሳለፍ ነው:: እዚህ ላይ አንድ ነገር እናንሳ:: ይሄን በጎ አድራጎት ብዙ ሰዎች ይተቹታል:: ምክንያታቸው ደግሞ ዓመት በዓል ብቻ ጠብቆ የሚደረግ ነው የሚል ነው:: በሁለት ምክንያት ትክክል አይመስሉኝም:: አንደኛ፤ በአመት አንድ ጊዜ እንኳን ማድረግ ምንም ካለማድረግ አይሻልምን? እርግጥ ነው ሁሌም ቢደረግ ጥሩ ነበር፤ ግን በበዓል ቀን እንኳን ማድረግ እንዴት አያስመሰግንም? ሁለተኛ፤ የበዓል ቀን ከሌላው ቀን ይለያል:: እነዚህ ጎዳና ላይ የወጡ ሰዎች ወይም በህመምና በዕድሜ መግፋት ምክንያት ከቤት የዋሉ ሰዎች በአንድ ወቅት እኛ የምናደርገው የሚያደርጉ ነበሩ:: የበዓል ቀን ያ ትዝ ይላቸዋል:: በየቤቱ በግና ዶሮ እንደሚታረድ ያውቃሉ:: ታዲያ የዚያን ቀን የሚሰማቸው ስሜት ከሌላው የአዘቦት ቀን ጋር እኩል ነው? ሌላውም ሰው ቢሆን እኮ የሚጫወተውና የሚያርደው ዓመት በዓል ጠብቆ ብቻ ነው፤ ስለዚህ በበዓል ቀን አቅም ከሌላቸው ሰዎች ጋር ማሳለፍ ምኑ ይተቻል? እንዲያው ባንችል እንኳን የሚችሉትን ሰዎች ባንወቅስ! ለእነዚህ ተቺዎች ‹‹ችሎታህን የማያመሰግኑ ሰዎች በውሃ ላይ ስትራመድ ቢያዩህ ‹ዋና ስለማይችል ነው› ይሉሃል›› የሚለው አባባል ምንኛ ገላጭ ነው!
በዓላት እንዲህ አይነት ሁለት ገፅታ ነው ያላቸው:: አንደኛው ገፅታ፤ አጉል ብክነት የሚበዛበት:: ይባስ ብሎ ደግሞ የጤና መታወክ የሚያጋጥምበትና ግጭት ውስጥ የሚከት:: ምንም እንኳን አንዳንዶች እየተበደሩም ቢሆን የሚያደርጉት የገንዘብ ብክነቱን ‹‹ለበዓል ያልሆነ ታዲያ!›› ብለን እንለፈው፤ ግን የማይተካው የጤና ጉዳይስ? ያለ ልክ የሚበላውና የሚጠጣው በበዓል ቀን ነው:: አደጋ የሚያጋጥመው የበዓል ቀን ነው:: መግቢያ ላይ የገለጽኩት አይነት ጋጠወጥነትም የሚያጋጥመው የበዓል ቀን ነው::
በዓል ግን በባህሪው ዘመድ ከዘመድ የሚገናኝበት፤ ወግና ባህል የሚታይበት፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚሰሩበት ነው:: አቅም ለሌላቸው ሰዎች እንኳን በጉጉት የሚጠበቅ ቀን ነው:: በዚያን ቀን ሁሉም እንደ አቅሙ የሚደሰትበት ነው::
በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት አላቸው:: በተለይም ሃይማኖታዊ ይዘታቸው ደግሞ ስነ ምግባርን የሚቀርጽና በጎ አድራጎትን የሚያስተምር ነው:: ችግሩ ግን ከሃይማኖታዊ ይዘታቸው ውጭ እየሆኑ ነው:: ያ ድርጊት ግን የሃይማኖቱን አስተምህሮት ለማያውቅ የሃይማኖቱም ባህሪ ሊመስል ይችላል:: መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በብሔራዊ ቴአትር አንድ መድረክ ላይ ሲናገሩ የሰማሁት ነገር ነበር:: ‹‹ጫት በእስልምና ሃይማኖት ይፈቀዳል ወይ›› ብዬ አንድ ሙስሊም አባት ጠየቅኩ አሉ፤ ያገኙት ምላሽ ጫት የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮት እንዳልሆነ ነው:: እርሳቸውም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሰባኪ እንደመሆናቸው ስካር እጅግ ነውር እንደሆነ ተናገሩ:: እንዲህ ነው እንግዲህ የሃይማኖቱ አስተምህሮት:: ጫትን የእስልምና መገለጫ፤ መጠጥን የኦርቶዶክስ መገለጫ ያስመሰልነው እኛ እንጂ የሃይማኖቱ ባህሪ አይደለም::
በባህላዊ ይዘታቸውም ቢሆን ስነ ምግባርን የሚቀርጹና ባህልና ወግን የሚያስተዋውቁ ናቸው:: እንዲህ አይነት አኩሪ ስነ ምግባር የሚቀረጽባቸውንና በጎ አድራጎት የሚደረግባቸውን ሃይማኖታዊ በዓላት አስነዋሪ ድርጊት አናድርግባቸው! ፌሽታም ሆነ መጠጡም በልክ ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ