በሁሉም ቋንቋዎቻችን የሚነገሩ ስነቃሎቻችን የተለያዩ ሰብአዊ ርእሰ ጉዳዮችን የማስተናገዳቸው አቢይ ጉዳይ እንግዳ ነገር አይደለም። የትየለሌ ጉዳዮችን ያነሳሉ፤ ይጥላሉም። ከእነዚህ መካከል “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው።”፣”ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት፣ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት።” የሚሉትን መጥቀስ በቂ ነው።
ርእሰ ጉዳያችን ከእናት ሆድ (ማህፀን) ጋር የተያያዘው “ዥንጉርጉር” ነው። ስንቀፅለው ደግሞ “ዥንጉርጉርነት” ይሆናል። ይህ የመቀፀሉ ሂደት በበኩሉ ቃሉን/ፅንሰ ሀሳቡን የበለጠ ገላጭ፣ አመላካችና የበለጠም ትርጉም ሰጪ ያደርገዋል።
“ዥንጉርጉርነት” በየትኛውም መስክና ዘርፍ አለ፤ በወጉ ከሆነ ጤናማ ነው። ገሚሱ የጤና ሲሆን ገሚሱ ደግሞ መርዛማና ገዳይ ነው። “ዥንጉርጉርነት” የትም አለ። በየትኛውም የዓለም ክፍል (ዓለም እራሷ ዥንጉርጉር አይደለች እንዴ)፤ በየትኛውም ክፍለ ዘመን ነበር፤ አሁንም አለ፤ ወደፊትም ይኖራል። ይሁን እንጂ ከሃሳብ ልዩነት ባለፈ የዓለምን መጨረሻ ለማቃረብ የደረሰባቸው ጊዜያት ጥቂቶች ናቸው።
በስነ ፍጥረት መስክ ዥንጉርጉር ሀሳብ እንዲኖርና በአንድ አቅጣጫ ብቻ የነበረውን እይታ ወደ ሁለት የቀየረው ቻርለስ ዳርዊን የሥነህይወት ጥናት (Biology)ን ብቻ ሳይሆን ሀይማኖትን ሳይቀር እየተፈታተነ በርካታ ምሁራንን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ደብር እየተቆጣጠረ እስከ ዛሬ የዘለቀው በ“Natural Selection” ዘመን ተሻጋሪ ስራው በሃሳብ ጥንካሬው እንጂ በሳለው ሾተል፣ በተሸከመው ገጀራ አይደለም። ከላይ እንዳልነው ይህ ሰው የ19ኛው ክ/ዘመን ሰው ሲሆን አዶልፍ ሂትለርንም የሰጠን ያው 19ኛው ክ/ዘ መሆኑን ልብ ስንል የእናት ሆድ ብቻ ሳይሆን የክ/ዘመንም “ዥንጉርጉር” መኖሩን እንገነዘባለን። “ዥንጉርጉርነት”ን ይዘን ዓለምን ብንዞር በርካታ ትንግርት መሳይ ነገሮችን የምናገኝ ሲሆን አፍሪካ ያለውም ተመሳሳይ ነው።
“ዥንጉርጉርነት” በአፍሪካ የሚጀምረው ከባህል፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ መልክአ ምድር ወዘተ ሲሆን ይሄ ጤነኛውና ሰዋዊው የህይወት ክፍል ነው። አስቸጋሪውና ተጠይው “ዥንጉርጉርነት” ግን እነዚህን የተከበሩና የአህጉሪቱ ጌጥ የሆኑ “ዥንጉርጉርነቶች”ን ከስራቸው ነቅሎ ለመጣል ወገቡን በገመድ አስሮ እየሰራ ያለው “ዥንጉርጉርነት” (ሲያቆለጳጵሱት “ሰብአዊ መብት ተማጓች፣ አክቲቪዝም …” በሚል ባልተቀደሰ ስም ይጠሩታል) ሲሆን፤ “ሰው እየገደሉ ይማራል ወይ ነብስ . . .” ያለችው አስናቀች ወርቁን የሚያስታውስ አባባል ይመስላል። ባጭሩ፤ እኛ በስነቃላችን ጥንት ያልነው “የእናት ሆድ …” ዛሬ ላይ የአለምም፣ የአፍሪካም ሆድ ዥንጉርጉር ሆኖ ይገኛል።
ከኢዲ አሚን በተቃራኒው ያሉት የእነ አፄ ሀይለስላሴ፣ ኑክሩሁማ፣ ማንዴላ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ሴዳር ሴንጎር፣ ፀጋዬ ገብረ መድህን ቦብ ማርሌይ፣ ጋርቬይ ወዘተ ታሪክም የአፍሪካ ታረክ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ “ዥንጉርጉርነት” ከየት ሊመጣ ከየትስ ሊገኝ? “ዥንጉርጉር”ነታችን እስከ ለራሳችን ስም እስከማውጣታችን ድረስ ሲልቅ ዛሬም ልክ እንደ የሪፖርት አፃፃፍ ትምህርት ክፍለ ጊዜ “አክቲቭ ቮይስ/ፓሲቭ ቮይስ”ን የማስረዳት ማራቶናዊ ውድድር ውስጥ የተዘፈቅን መሆናችን ነው።
በስነቃላችን “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው።” ሲባል የተገለፀው ተምሳሌታዊ ፍልስፍናው ቀላል አይደለም። በጥበበ-ቃላት እያንዳንዱ ነገር ወይ በተናጠል ወይ በጋራ/ቡድን የሚወክለው ነገር አለው፤ ወካይ/ተወካይ አለ ማለት ነው። ተምሳሌታዊነት ማለት አንድ እራሱን ያልሆነ አካል ሌላውን እንዲገልፅ የሚደረግበት የላቀ ጥበባዊ ተግባር ነውና እዚህ ስነቃል ውስጥ ደግሞ ይህንን ሚና እንዲጫወት የተመረጠው ቃል “እናት” የሚለው ሲሆን ፍካሬያዊ ፍቺውም “ከወላጅ እናት ሆድ/ማህፀን” አልፎ “የአገር ሆድ/ማህፀን” ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ “ዥንጉርጉርነት” በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አለ ማለት ነው። “እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ/ . . .”ም ተብሏል። “ቀይ” እና “ነጭ” ቀለሞችን መለያችን አድርገን ተላልቀናል። ይህ ሁሉ ምንም ማለት ሳይሆን ያው “ዥንጉርጉርነት” ነው። አስቀድመው “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው” እንዳሉት ማለት ነው።
በዘመናዊ ሥነ-ግጥም ስራዎች ውስጥ ቀድሞና ጎልቶ የሚገኘው ዮፍታሄ ንጉሴ አንድ ተቃርኖን ያስተናገደበት ስንኝ አለችው፤
አወይ የኔ ነገር እንዲያው ተለባብሶ፣
መስቀል ተሰላጢን ዘፈንና ለቅሶ።
የምትል ነች። ይህች ሁለት ግዙፍ ግን ደግሞ እጅግ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች የተስድተናገዱባት ግጥም መልእክቷ ጥልቅ፣ ተምሳሌትነቷ ከዚህ መለስ የማይባል ዓለም አቀፍ ነው።
“መስቀል ተሰላጢን”ም ሆነ “ዘፈንና ለቅሶ” የሚሉት ቃላት ተቃራኒዎች ናቸው። “መስቀል” ሀይማኖታዊ ሲሆን መዳኛም ነው። “ሰላጢን” ጦር፣ (በዛሬው አጠራር ገጃራ) መግደያ መሳሪያ ነው።
በግጥሙ መሰረት ከሁለት አንዱን መያዝ ችግር የለውም። ችግሩ ሁለቱንም መያዝና ሁለቱንም ነኝ ማለቱ ላይ ነው “መስቀል ተሰላጢን”። ድምፃዊት አስናቀች ወርቁን “ሰው እየገደሉ ይማራል ወይ ነብስ . . .” እንዳለችው ነው። እንዴት ሰው ሰው እየገደለ ዲሞክራት ሊሆን፣ የመብት ተሟጓች ሊሆን፣ ወካይ ሊሆን፣ አገር ሊያቀናና ወገንን ሊታደግ ይቻለዋል? “መስቀል ተሰላጢን ዘፈንና ለቅሶ” ካልሆነ በስተቀር።
ኢትዮጵያዊነት “ዥንጉርጉርነት” መሆኑ በታላቁ መጽሐፍም ተገልጿል። አስገራሚው ነገር እሱ አይደለም። አስገራሚው ነገር ከዚህ መለኮታዊ አገላለፅ በተቃራኒ የሆነ “ዥንጉርጉርነት” መፈጠሩ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ ዘር እየተቆጠረ ባንድ እጃቸው ህገመንግስት፣ በሌላኛው ገጀራ በያዙ ወገኖች በግፍና አሰቃቂ ሁኔታ መግደል የተጀመረባት አገር መሆኗ በቂ ማስረጃ ነው – “መስቀል ተሰላጢን”። በአገሪቷም እየተሰሙ ያሉት ድምፆች “ዘፈንና ለቅሶ” መሆናቸውን እየሰማንና እያየን፣ እኛም ከሁለቱ የአንዱ አካል ሆነን እየተሳተፍን እንገኛለን።
እውነቱ ግን ይህ አይደለም። እውነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ መጋቢት 2010 ወደ መንበረ ስልጣናቸው ሲመጡ የተናገሩት ነው። እሱም፤
አማራው በካራማራ ለሀገሩ ሉአላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል። [. . .] እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንምት ኢትዮጵያ ነን።
የሚለውና በወቅቱ ብዙዎችን እጅግ ያማለለ፣ አንዳንዶችንም ለሲቃ፣ አልፎ አልፎም ለእንባ የዳረገ፣ የዘር ፖለቲካ አስተሳሰብን የደፈቀና አንድነትን የሚያፀና ተደርጎ የተወሰደው ንግግራቸው ነው።
ባጭሩ ባሁኑ ወቅት፤ በዚህች ሰዓት እኛ ኢትዮጵያዊያንን ያጋጠመን ክፉ ጉዳይ ቢኖር ይሄው ስነቃላችን “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው”፤”ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት፣ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት።” እና ባለቅኔው ዮፍታሄ “መስቀል ተሰላጢን ዘፈንና ለቅሶ” ያሉት ነውና ሁሉንም ጊዜ ይፍታው (ቦ ጊዜ ለኩሉ) እንላለን። እስከዛው ግን እንደዘፈኑ ነው “እንተባበር!”
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 3/2012
ግርማ መንግሥቴ