በኢትዮጵያ ከአስራ ሰባት አመት በፊት በየአመቱ በኤች አይ ቪ ቫይረስ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 81 ሺ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ይህ አሀዝ ወደ 15 ሺ መውረዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቫይረሱ አዲስ ከሚያዙ ከእነዚህ 15 ሺ ሰዎች ውስጥ 47 በመቶ የሚሆኑት በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ ይህም የቫይረሱ ስርጭት በከተሞች ስር እየሰደደ እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ የኤች አይ ቪ ተፅዕኖ ዳሰሳ ጥናት በከተሞች ላይ በማተኮር እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2017 እስከ ሚያዚያ 2018 ለስድስት ወራት ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶች በገጠር ያለው የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭት አነስተኛ መሆኑን የሚያመለክቱ በመሆናቸውና በሃገር አቀፍ ደረጃ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ካለባቸው 610 ሺ 335 ሰዎች ውስጥ ሁለት ሶስተኛው የሚሆኑት በከተሞች የሚኖሩ ከመሆናቸው አኳያ ጥናቱ በከተሞች ላይ ብቻ አተኩሮ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡
ጥናቱ አድሜያቸው ከ15 እስከ 64 ዓመት የሆኑ በ10 ሺ 529 የከተማ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ 20 ሺ 170 ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን፣ የኤች አይ ቪ ህክምና ውጤታማነትን ለመለካትና የኤች አይ ቪ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተደረገውን ጥረት ለማመላከት የሚያስችሉ መረጃዎችን አሰባስቧል፡፡ አዲስ ኤች አይ ቪ በደማቸው የተገኘባቸውን ሰዎች መጠንና በደም ውስጥ ያለው የኤች አይ ቪ ቫይረስ የቀነሰበት መጠን ደግሞ ጥናቱ በመለኪያነት የተጠቀመባቸው አመላካች መረጃዎች ናቸው፡፡
እድሜያቸው ከ 15 አስከ 64 ዓመት ከሆኑና ኤች አይ ቪ ቫይረስ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆኑት አጥጋቢ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ቅነሳ መጠን እንዳላቸው ጥናቱ ያሳየ ሲሆን፣ ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ማስተባበሪያ ፕሮግራም በ2020 እ.ኤ.አ ካስከመጠው የ73 ከመቶ በደም ውስጥ ኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን የመቀነስ ግብ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ጥናቱ በዘርፉ የታዩ ክፍተቶችንና የመጡ ውጤቶችን ከማመላከቱም ባሻገር በኤች አይ ቪ ዙሪያ ያሉ ፕሮግራሞችንና ፖሊሲዎችን ሊደግፉ የሚችሉ ግባአቶችን አስገኝቷል፡፡ እድሜያቸው ከ15 አስከ 64 የሆኑ ኤች አይ ቪ በደማቸው ካለባቸው ወንዶች ውስጥ ኤች አይ ቪ እንዳለባቸው የሚያውቁት 62 በመቶ ወይም ከሁለት ሶስተኛ በታች መሆናቸው በቀጣይ ኤች አይ ቪ በደማቸው ካለባቸው ወንዶች ውስጥ ቫይረሱ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለማስቻል ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚጠይቅ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደሚሉት፤ ጥናቱ የኢትዮጵያ መንግስት በኤች አይ ቪ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በመመርመርና ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ያስመዘገባቸውን ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንም አመላክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ማስተባበሪያ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ2020 ያስቀመጣቸውን የ90-90-90 ግቦች ከማሳካት አንፃር ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውንም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ በተለይም እድሚያቸው ከ15 አስከ 64 ዓመት ከሆኑና በከተማ ከሚኖሩ ኤች አይ ቪ በደማቸው እንዳለ ከሚያውቁ አዋቂ ሰዎች ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እየወሰዱ መሆናቸውም የለውጡ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በከተሞች ከሚኖሩ ኤች አይ ቪ በደማቸው ካለባቸው አዋቂ ሰዎች ውስጥ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ወይም 30 በመቶዎቹ በደም ውስጥ የቫይረስ መጠናቸው ዝቅተኛ ያልሆኑ በመሆናቸው በቀጣይ በደም ውስጥ የቫይረስ መጠንን ዝቅተኛ ለማድረግ በትጋት መስረት ያስፈልጋል፡፡
በጥናቱ የኤች አይ ቪ ምጣኔ በከተሞች 3 በመቶ እንደሆነ መጠቀሱን የሚገልፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ውጤቱ በክልል ሲከፋፈል፣ በፆታ ስብጥር ሲታይና ከተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች አንፃር ሲመነዘር ልዩነት እንደሚኖረው ያስረዳሉ፡፡ ይህም ጥናቱ በተለያዩ መንገዶች መሰራቱ ለግቡ ተጨባጭነትና ስኬት ጠቀሜታ ያለው ግብአት ማስገኘቱን ያሳያል፡፡ ጥናቱ ሁሉንም ማህበረሰብ ማዕከል አድርጎ የተሰራ በመሆኑና ከ25 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንዲካተቱበት መደረጉ የሃገሪቱን አጠቃላይ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ምጣኔን ለማወቅ አስችሏል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ፤በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ በርካታ ተግባሮች ተከናውነው ውጤቶች የመጡ ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ ያለው ቫይረሱን የመከላከልና የመቆጣጠር ሂደት ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ አስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎች በደማቸው ቫይረሱ እንዳለባቸው እንዲያውቁና ህክምናም እንዲያገኙ የተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ከብዙሃኑ ውስጥ ጥቂቶቹን መፈለግ ከፍተኛ ጥንቃቄና ስትራቴጂ ይፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል በነበረው መንገድ መሄድ በቀረው አንድ አመት ውስጥ የሶስቱ ዘጠናዎችን ግብ ለማሳካት ስለማያስችል ጥናቶች ባመጡት ውጤት ላይ በመመርኮዝ መስራት ግቡን ለማሳካት ይረዳል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አይካፕ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ዘነበ መላኩ እንዳስታወቁት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ በከተሞች የሚኖሩ ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸው ኢትዮጵያውያን የቫይረስ መጠናቸውን ለመቀነስና ጤናማ ህይወት ለመኖር የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እየወሰዱ መሆኑን የጥናቱ ውጤት ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸውን ሰዎች መርምሮ ለማግኘትና ህክምና ለማስጀመር የሚደረገው ጥረት ከዚህ ቀደም አንደነበረው ባለመሆኑ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በኤች አይ ቪ ዙሪያ አስካሁን የተከናወኑ ተግባሮች በርካታ ቢሆኑም፣ እስካሁን የተሰራውን ስራ በበቂ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ሀገር አቀፍ ጥናት አልተሰራም፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተሰራው ጥናት በተለይም የሶስቱ ዘጠናዎችን ግብ ለመምታትና ሀገሪቷ ያለችበትን ደረጃ ለማወቅ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፤ በኤች አይ ቪ ዙሪያ የሚነሱ ቁልፍ ጥያቄዎችን ለመመለስም እገዛ ያደርጋል፡፡
ባለፉት አስራ አምስት አመታት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ጥናቱ ማሳየቱን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ሀገሪቱ በቀረው አንድ አመት ውስጥ የሶስቱ ዘጠናዎችን ግብ ከማሳካት አንፃር አሁንም የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ አሳይቷል ይላሉ፡፡ በተለይም በከተማ የሚኖሩ ዜጎችን ቫይረሱ በደማቸው እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለማድረግ በቀጣይ ጠንካራ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ መጠቆሙን፣ ከአሁን ቀደም የነበሩ አሰራሮችን መፈተሸና ማስተካከል እንደሚገባም ማመልከቱን ያብራራሉ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ጥናቱ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለህብረተሰቡ በቂ መረጃ ለመስጠት የሚያስችል ግብአት የተገኘበት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለም በከተሞች ላይ አተኩሮ መሰራቱ በከተሞች ያለውን የኤች አይ ቪ ስርጭት መጠን በዝርዝር እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ በቀጣይ የትኩረት ጉዳዮችን በመለየት ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡ በፆታ ስብጥርም ሴቶች የሚሰጣቸው የኤች አይ ቪ አገልግሎትና ተጠቃሚነታቸው ምን እንደሚመስል ማሳየቱን ይናገራሉ፡፡
ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የማይታወቁ የእድሜ ምድቦችን በተለይም አዛውንቶችና ጨቅላ ህፃናት የሚገኙበትን የኤች አይ ቪ ደረጃ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎችንና በተለይም ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑ ውጤቶችንም አካቷል፡፡ በቀጣይም ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦችን የጠቆመ፣ አሰራሮችንና ስትራቴጂዎችን ለመከለስ አጋዥ ግብአት የተገኘበት ነው፡፡
ቀደም ሲል በኤች አይ ቪ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች ህብረተሰቡና የጤና ባለሞያው በቀላሉ የሚረዳቸው እንዳልነበሩ የሚናገሩት ሚኒስትሩ፤ የዚህ ሃገር አቀፍ አዲስ የጥናት ውጤት ግን መገናኛ ብዙሃን፣ ጤና ባለሞያዎችና ህብረተሰቡ በቀላሉ ሊገነዘቡት በሚችል መልኩ የተዘጋጀ ነው ይላሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ፤ ከ0 አስከ 14 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ጨቅላ ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ ያለው የኤች አይ ቪ ምጣኔ 0 ነጥብ 3 ወይም 19 ሺ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፤ ይህም ክፍተት ያመለካተ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በተመሳሳይም ከ 50 አስከ 64 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎችም የቫይረስ ምጣኔያቸው ክፍተት የሚታይበት መሆኑን ጥናቱ እንደሚጠቁም አሳይቷል፤ በመሆኑም በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በሶስቱ ዘጠናዎች ላይ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም፣ በተለይም በከተሞች ውስጥ የሚኖሩና ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ያውቁ ሰዎች መጠን አሁንም በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በቀጣይ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለባቸው እንዲያውቁ ጠንካራ ስራዎችን መስራትን ይጠይቃል፡፡ ጥናቱ በእድሜ፣ በፆታ፣ በቦታና ከበሽታው ጫና አኳያ ባመላከታቸው መረጃዎች አማካኝነት የሚፈለገውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ መመርመር ያስፈልጋል፡፡
የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፅገሬዳ ክፍሌ አንደሚናገሩት፤ ጥናቱ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮችንና በሃገር አቀፍ ደረጃ አስካሁን የተከናወኑ ተግባሮችን አፈፀፃም አሳይቷል፡፡ በቂ የጤና ተቋማትና አገልግሎት ባልነበረበት ሁኔታ ባለፉት አመታት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎችንና ውጤቶችንም ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ የመጡ ውጤቶችን ለማስቀጠልና ቀጣይ ስራዎችን ለማከናወን በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ ከቀድሞው በብዙ መልኩ እንደሚለይ ተናግረው፣ ኤች አይ ቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚጠይቅ ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የውጪ ሃገር ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱና በሃገሪቱ ሃብት የማንቀሳቀስ ስራው ባለፉት አመታት በደንብ እየተሰራበት አለመሆኑን ተከትሎ ባለው ውስን ሃብት የመከላከሉንና የድጋፍና እንክብካቤ ስራውን ለመስራት ጥናቱ ጥሩ መረጃዎች የተገኙበት ነው፡፡ በተለይም በክልል የሚገኙ ከተማዎች ሃብታቸውን ለበሽታው መከላከል ስራ በምን መልኩ ማንቀሳቀስ እንዳለባቸው አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ በሃገር አቀፍ ደረጃ በምን መልኩ ተቀናጅቶ ቢሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም ጥናቱ አመላክቷል፡፡
ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እነማን እንደሆኑ ጥናቱ መለየቱንም ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፣ ይህም ተጋላጮቹ ላይ በማተኮርና ከሚመለከታቸው የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ተቀናጅቶ ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡ ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ ተቀዛቅዞ የነበረውን የኤች አይ ቪ ኤድስ የመከላከል ስራ አዲስ ንቅናቄ በመፍጠር ለማስቀጠል ሰፊ ስራዎችንም መስራት እንደሚጠይቅ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል ይላሉ፡፡
አስራ አንድ የአፍሪካ ሃገራት ማለትም ካሜሩን፣ ኮትዲቯር፣ ኢሳዋቲኒ (የቀድሞ ስዋዚላንድ)፣ ሌሴቶ፣ ማላዊ፣ ናሚቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዝምባቡዌ የማህበረሰብ አቀፍ የኤች አይ ቪ ተፅእኖ ዳሰሳ ጥናት ውጤታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ይህ ጥናትም ከእነዚህ ሀገሮች ጥናት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ማስተባበሪያ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ2020 ያስቀመጣቸውን የ 90-90-90 ግቦች ለማሳካትና በ2030 የኤች አይ ቪ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
አስናቀ ፀጋዬ