ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለአገራቸው ብሄራዊ ባንክ ባስተላለፉት መመሪያ ከውጭ የምግብ ነክ ሸቀጦችን ለሚያስገቡ አስመጨዎች የውጭ ምንዛሪ እንዳይሰጥ እገዳ መጣላቸው የሚታወስ ነው። ይህ ተግባራቸውም የተለያዩ ውዝግቦችና አስተያየቶችን ሲያስተናግድ ከርሟል። አንዳንድ የሚዲያ አካላትና አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ይህ ድርጊት በአገራቸው ያለውን የግብርና ምርት እድገት ለመጨመር ያግዛል ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላጋጠማት ነው የሚሉ አስተያየቶችን ያነሳሉ።
የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያሳየው ግን ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያደረጉበትን ምክንያት በዝርዝር አስቀምጧል። እንደዘገባው ከሆነ የፕሬዚዳንቱ እርምጃ አዲስ አይደለም። ወደስልጣን መንበራቸው ከመጡ እአአ ከ2015 ጀምሮ ሊከተሉት ያቀዱት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሳያ ነው። ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ወደስልጣን በመጡ ማግስት አገራቸው ሩዝና ሌሎች የታሸጉ ምግቦችን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ከውጭ እንዳይገቡ እገዳ ጥለው ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የአገሪቱ የሩዝ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ታውቋል። ያም ሆኖ ግን ይህ አካሄድ ዝቅተኛ አቅም ያላቸውን የአገሪቱን አርሶአደሮች አቅም ያገናዘበ አይደለም በሚል ትችት ሲቀርብባቸው ቆይቷል። ይህንን አቅጣጫ ተከትሎም በአገሪቱ የምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪን አስከትሏል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ለምግብ ዋስትና አሉታዊ ጫና ማሳደሩ ይነገራል።
ከናይጄሪያ ብሄራዊ የስታትስቲክስ ቢሮ የወጣ መረጃ እንደሚሳየው አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው የምግብና መጠጥ ወጪ ከ2015 እስከ 2017 ድረስ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በ2018 ግን በመጠኑም ቢሆን ቀንሶ ታይቷል። ሆኖም አሁን የመጨመር አዝማሚያ በመኖሩ ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ውሳኔ እንደተነሱ ተዘግቧል። መረጃዎቹ እንዳሳዩት ናይጄሪያ በ2015 ከውጭ ለምታስገባቸው ምግቦችና መጠጦች ያወጣችው ጠቅላላ ወጪ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ሲሆን ይህ አሃዝ በ2017 ወደ 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
ናይጄሪያ በዋናነት ስኳር፣ የስንዴ ዱቄት፣ አሳ፣ወተት፣የፓልም ዘይት፣ የአሳማ ስጋ፣ የበሬ ስጋና የዶሮ ስጋ በስፋት በሃገር ውስጥ በማምረት ለገበያ የምታቀርብ ቢሆንም 200 ሚሊየን የሚሆነውን ዜጎቿን ፍላጎት ለማርካት ግን አልቻለችም። በዚህ የተነሳ መንግስት በሃገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች እንዲጨምሩ ፍላጎት አለው። ለዚህ የመረጠው መንገድ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችና አርሶአደሮች ምርታቸውን እንዲጨምሩ ማድረግ ነው። ለዚህም ሲባል እገዳው መጣሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንደተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት /FAO/ መረጃ የናይጄሪያ የሩዝ ምርት እያደገ ይገኛል። ለምሳሌ ከ2013 እስከ 2017 ድረስ በየዓመቱ የ7ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን እድገት የታየ ሲሆን በ2017 ደግሞ 8 ነጥብ 9 ሚሊየን ቶን እድገት ተመዝግቧል። በአንጻሩ ሩዝን ህጋዊ በሆነ መንገድ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ህገወጥ ደላሎችም መብዛታቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
በሌላ በኩል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማገድ አምራቾች ምርት በስፋት እንዲያመርቱ መፍትሄ ይሆናል ወይ የሚሉ በርካታ ወገኖች አሉ። ባለሙያዎችም እንደሚሉት የምግብ ሸቀጦች ላይ እገዳ ማድረግ በተወሰነ ደረጃ ለአገር ውስጥ ምርት መጨመር አስተዋጽኦ ቢኖረውም ዋነኛው መፍትሄ እንዳልሆነ ግን ይተቻሉ።
አይሪስ አይንዴ በናይጄሪያ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመቀነስ ሂደቱ ቀስ በቀስ ሊከናወን ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ አገሪቱ በአንድ ጊዜ የአገር ውስጥ የምርት ፍላጎቷን ማሟላት አትችልም። በዚህ የተነሳ በአገር ውስጥ ምርቶቹ የዋጋ ግሽበት ሊፈጠር ይችላል።
መንግስት ግን አሁን አንድ ነገር ተስፋ አድርጓል። እስከ 500 ሚሊየን ዶላር በኢንዱስትሪው ውስጥ ድጋፍ ማድረግ ከቻለ በየዓመቱ አሁን ያለውን አጠቃላይ 600 ሺህ ቶን ምርት ወደ አምስት ሚሊየን ማሳደግ ይችላል።
የኢኮኖሚክስ ፅንሰሃሳብ እንደሚያስረዳው የምርት አቅርቦት መቀነስ ለዋጋ ጭማሪ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከዚህ በመነሳትም የአገር ውስጥ ምርቱ ከውጭ የሚመጣውን አቅርቦት መሸፈን ካልቻለ የዋጋ ጭማሪ በማስከተል ናይጄሪያውያን ለምግብ አሁን ከሚከፍሉት በላይ እንዲከፍሉ ያስገድዳቸዋል።
ቀደም ሲል በ2015 መንግስት በሩዝ ምርት ላይ ያደረገውን የውጭ ገበያ ንግድ ተከትሎ የ50 ኪሎ ግራም ሩዝ ዋጋ ከነበረበት 24 ዶላር በአንድ ጊዜ ወደ 82 ዶላር መግባቱ ይታወሳል። በኋላ ግን በ2017 ዋጋው ወደ 34 ዶላር ዝቅ ብሎ ነበር።
በሌላ በኩል ናይጄሪያ ምርቷን ማሳደግ ለምን አቃታት የሚሉ ጥያቄዎችም በተደጋጋሚ ይነሳሉ። ለዚህ ምላሽ የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት ናይጄሪያ ለበርካታ አስርት አመታት ኢኮኖሚዋ በነዳጅ ላይ እዲንጠለጠል ማድረጓ ነው። በሌላ በኩል በርካታ አርሶአደሮችን በማሳ ላይ ማየት የተለመደ ቢሆንም በእርሻ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶች መቀነስም ለዚህ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ ለእርሻ የሚሆነውን መሬት በአግባቡ መጠቀም ላይም ክፍተቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። በአገሪቱ አጠቃላይ ከሚለማው መሬት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው አንድ ሶስተኛው ብቻ ነው።
ስለናይጄሪያ ሲነሳ አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች በተደጋጋሚ እንደሚነሱ ቢቢሲ በዘገባው አካቷል። የመጀመሪያው ታዋቂ ሙዚቀኞቿ ናቸው። በናይጄሪያ የሙዚቃ ዘርፉ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪም እንደሆነ ይነገርለታል። በተለይ አብዛኞቹ ናይጄሪያውያን እንግሊዝኛን የሚናገሩ በመሆኑ እና ሙዚቀኞቹም በአብዛኛው በዚሁ ቋንቋ የሚያቀነቅኑ በመሆኑ በቀላሉ ወደሌላው ዓለም በተለይ ወደአሜሪካና አውሮፓ ገበያ መግባት አስችሏቸዋል። በዚህ የተነሳም ሶኒን የመሳሰሉ ግዙፎቹ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ አንቀሳቃሽ ተቋማት ቢሮኣቸውን በናይጄሪ እንዲከፍቱ አስችሏቸዋል። ይህ የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ የአፍሪካ ድምጽ ብቻም አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆኑ የሬዲዮ ጣቢያዎችና የምሽት ክለቦች ማድመቂያም ነው።
እነዚህ የናይጄሪያ ሙዚቃዎች በኢንዱትሪው ውስጥ የራሳቸውን ዘውግም እስከመፍጠር አስችሏቸዋል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጋና የሙዚቃ ቡድን ጋር በመዋሃድ የሚያቀርቧቸው አንዳንድ ዘፈኖቻቸው በኣለም ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህ ደግሞ አገሪቱም ከዘርፉ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አስችሏታል።
ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ታዋቂዎቹ ደራሲዎቿ ናቸው። የናይጄሪያ ስም ሲጠራ ለመላው አፍሪካውያን ታዋቂዎቿ ደረሲዎቻቸው እንደነ ዎሌ ሾይንካ እና ቺን አቼቤ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ናይጄሪያ ባህላዊ መገለጫዎቿን ያስተዋወቀችውም በአብዛኛው በድርሰት ስራዎቿ ነው። በተለይ የቺን አቼቤ ስራዎች ለዓለም ጭምር ትልቅ ተምሳሌት የነበሩና በዓለም ማህበረሰብም ጭምር እውቅናን የተቸሩ ናቸው። ቺን አቼቤ ለህትመት ካበቃቸው ስራዎቹ ውስጥ “Things Fall Apart” የተሰኘው ስራው ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።
ይህ የቺን አቼቤ ስራ በተለይ ከቅኝ ግዛት በኋላ የስነፅሁፍ ወርቃማ ስራ እንደሆነ ይገለፃል። ይህ መፅሃፍ በ1958 ከታተመበት ጊዜ ጀምሮም በዓለም ላይ በ57 ቋንቋዎች የታተመ ሲሆን ከ20 ሚሊየን ኮፒ በላይም በመሸጥ ትልቅ ታሪክ ሊሆን ችሏል። ከዚህም ባሻገር ዎሌ ሾይንካ በ1986 የኖቤል ሽልማት ያገኘ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የስነጽሁፍ ሰው መሆን ችሏል።
ንዋውባኒ የተባለች ናይጄሪያዊት ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለመጠይቅ እንደተናገረችው “ናይጄሪያውያን በባህሪያቸው መታየትና መሰማት የሚፈልጉ ህዝቦች ናቸው። በዚህ የተነሳ በዓለም ላይ ከሚነገሩ ትላልቅ የአፍሪካ ተረቶችና ምሳሌዎች ውስጥ የናይጄሪያውያን ታሪክ ጎልቶ ይገለፃል። በነፃነትና ያለፍርሃት የመናገር እንዲሁም ሃሳባችንን የመግለፅ ባህል አለን። በምንሰራቸው ማናቸውም ጉዳዮች የበላይ መሆን እንፈልጋለን” ስትል ተናግራለች።
ናይጄሪውያን በተለይ ከሚታወቁባቸው ጉዳዮችም ውስጥ አንዱ ትረካዎቻቸው ናቸው። በናይጄሪያ ታሪካቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ አፈታሪኮችና የስነፅሁፍ ስራዎች ይገኛሉ። እነዚህን ስራዎች ደግሞ እያንዳንዱ ናይጄሪያዊ ከልጅነቱ ጀምሮ እየተለማመደ እንዲያድግ ትልቅ ባህላዊ ውርርስ ይደረጋል።
ሶስተኛው የናይጄሪውያን መገለጫ ደግሞ የህዝባቸው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ነው። ናይጄሪያ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ ስፍራ ላይ የምትገኝ ሲሆን ከ35 አመታት በኋላ ደግሞ የህዝብ ቁጥሯ ከአሜሪካ እንደሚልቅ ይጠበቃል። በ2047 የናይጄሪያ የህዝብ ቁጥር 387 ሚሊየን እንደሚደርስ ይጠበቃል። ይህ አሃዝ ደግሞ አገሪቱን ከዓለም ሶስተኛዋ ትልቅ አገር ያደርጋታል።
በሌላም በኩል ናይጄሪያ ትልቋ የወጣቶች አገር በመባልም ትታወቃለች። ለዚህም አንዱ ማሳያ ከአጠቃላይ ህዝቧ 40 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧ እድሜው ከ14 አመት በታች መሆኑ ነው። ይህ ትልቅ የሰው ሃብት ደግሞ ለአገሪቱ ትልቅ ሀብት እንደሆነ ይነገራል። የአገሪቱ ወጣት ሃይሎች ያለው ኢኮኖሚ ለወጣቱ የሚመጥን ስራ እድል መፍጠር ላይ ችግር እንዳለበት ቢናገሩም በርካቶች ግን ወደውጭ አገር በመሄድ ይሰራሉ። በዚህም ናይጄሪያ በውጭ አገር ከሚኖሩ ዜጎቿ በርካታ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር እንድትሆን አስችሏታል።
አራተኛው ጉዳይ ትልቅ የነዳጅ ሃብት እና አነስተኛ የኤሌክትሪካ ሃይል አቅርቦት ያላት አገር መሆኗ ነው። ናይጄሪያ በአንድ በኩል ካላት ትልቅ የነዳጅ ሃብቷ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በናይጄሪያ ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥና ማነስ ትልቅ የምሬት ምንጭ ነው። በሌላ በኩልም ለኢንዱስትሪ አለማደግ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖም አሳድሯል። በናይጄሪያ ትላልቅ ከተሞች ከአምስት ቤቶች አራቱ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሲሆኑ በገጠር ደግሞ ከሶስት ቤቶች አንድ ብቻ ነው የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያገኘው።
ናይጄሪያ ከአፍሪካ ትልቋ ነዳጅ አምራች አገር ናት። በየዕለቱም አራት ሚሊየን በርሜል የነዳጅ ዘይት ታመርታለች። ይህ ግን አስተማማኝ አይደለም። የነዳጅ ሃብቷ በአጭር ጊዜ ሊያልቅ እንደሚችል ባለሙያዎች ይተነብያሉ።
ሌላው የናይጄሪያ መገለጫ አሸባሪ ቡድኖች የሚያደርሱባት አደጋ ነው። የናይጄሪያ ስም ሲነሳ ቦኮሃራም የሚባለው የሽብር ቡድን አብሮ ይነሳል። በተለይ ከጥቂት አመታት በፊት በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቶ የነበረው ይህ ቡድን በ2014 ከሰሜን ምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ከቺቦክ ትምህርት ቤት 200 ልጃገረዶችን ከትምህርት ቤት ወስዶ የኣለም መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። ከዚህም ባሻገር ናይጄሪያ ካላት ትልቅ ኢኮኖሚ አንጻር ይህንን ቡድን ለመቋቋም ያደረገችው ጥረት አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል።
በርግጥ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ናይጄሪያ በዚህ ቡድን ላይ ከፍተኛ የበላይነት መያዝ እንደቻለች ብዙዎች ይመሰክራሉ። ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ያም ሆኖ ግን ቦኮሃራም አሁንም ቢሆን ከአካባቢው ብዙም አልራቀም። ጥቃት የማድረስ አቅሙም ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም።
በአጠቃላይ ናይጄሪያ በአንድ በኩል በዚህና መሰል ችግሮች ውስጥ የምትገኝ አገር ስትሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ ትላልቅ አቅምና እድሎች ያላት የተስፋ አገር እንደሆነችም ብዙዎች ይመሰክራሉ። ለስኬቷ ደግሞ መንግስት እየተከተለ ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው የሚነገረው።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 20/2011
ወርቁ ማሩ