ሕንድ እና ፓኪስታን እኤአ 1947 ከታላቋ ብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተው ከአንድ ወደ ሁለት አገርነት ከተለወጡ ማግስት አንስቶ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት አንድም ቀን ሰላም ሆነው አያውቁም። የካሽሚር ግዛት ‹‹ትገባኛለች››ን ዋነኛ ምክንያት የሚያደርገው የኢስላማባድና የኒውዴህሊ ፍጥጫም ሁለቱን ሀገሮች ለሁለት ጊዜያት ያህል ጦር አማዟል፡፡
በእርግጥ ሁለቱ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂ ባላንጦች እአአ በ2003 የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል፡፡ በስምምነቱም ጃሙና ካሽሚር በተባለ ስፍራ ላይ የተወሰነውን ወታደራዊ የድንበር መስመር በመቀበል ከጠብ ለመራቅ ተስማምተዋል፡፡ ይሁንና ዛሬም ድረስ የካሽሚር ውዝግባቸው ያልተዘጋ አጀንዳቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡
ሀገሮቹ በካሽሚር ጉዳይ ሁሌም ስሜተ ስሱ ናቸው፡፡ አንዷ ሌላኛዋን በጭራሽ አታምናትም። አትቀበላትም። በቀጠናው የሁለቱም አገሮች ወታደሮች ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። ፍጥጫቸው ረገብ በሚልበት ወቅት እንኳን ውጥረትና መፈራራት ጠፍቶ አያውቅም። የእርስ በርስ መወነጃጀላቸውም የተለመደ ነው፡፡
ባሳለፍነው አመት ኢምራን ከሃን የሚመራው የፓኪስታን ፓርቲ ምርጫውን በማሸነፍ ከ220 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላትና የኒውክሌር ባለቤት የሆነችውን አገር ለመምራት ስልጣን ሲረከቡ፣የሁለቱ አገራት ቁርሾ ፈር ሊያገኝ አንደሚችል በርካቶች ተስፋ ነበራቸው፡፡
ቀደም ሲል የፓኪስታን ብርቱ የክሪኬት ስፖርት ተጫዋች የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ከሃን፣ በምጣኔ ሐብት ድቀት፤ በድንበር ውዝግብ እንዲሁም በፅንፈኞች ሽብር ክፉኛ የቆሰለችውን፣ በጦርነት ዳሽቃ፣ሰላምና ዜጓቿን የተነጠቀችውን አገር ገፅታ ከመለወጥ በተጓዳኝ ለአመታት እልባት ለናፈቀው የጎረቤታሞቹ ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰሩም ማረጋገጫም ቃላቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
‹‹በክሪኬት ስፖርት ምክንያት ከማንኛውም ፓኪስታናዊ በላይ ህንድን ጠንቅቄ አውቃታለሁ› የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ከሃን፤ በዘመነ ስልጣናቸው ከኒውዴሊህ መንግስት ጋር መልካም ወዳጅነት ለመመስረት ፍላጎታቸው ስለመሆኑም በአደባባይ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል ሰላም እንዲወርድ እንደሚተጉ ቢገልፁም፤ የመሪነቱን ወንበር ከተቆናጠጡ በኋላ ግን ይህን ቃላቸውን ወደ ተግባር የመለወጥ ቁርጠኝነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡
በስልጣን ተዋረድ አንዱ መሪ መጥቶ በሌላው ቢተካም ከፍቅር ይልቅ ጠብ የማያጣው የሁለቱ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂ ባላንጦች ፍጥጫ፣ በተለይ በኢምራን ከሃን የስልጣን ዘመን ይባስ ብሎ እየጦዘ የመጣ ይመስላል፡፡ ባሳለፍነው ጥር ወር በካሽሚር ግዛት ከ40 በላይ የሕንድ ወታደሮች መገደላቸውም በርቀት በተጠንቀቅ ይጠባበቁ የነበሩትን የሁለቱ አገራት ወታደሮች ይበልጥ እንዲፋጠጡ አድርጓቸውም ታይቷል፡፡
በክስተቱ ምክንያት የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከአንገት በላይ መሆን ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ሕንድ ከቀናት በፊት በሕገ-መንግስቷ በአንቀጽ የሰፈረውን ካሽሚር የነበራትን ልዩ መብትና አስተዳደራዊ ስልጣን መሻሯ በጎረቤታሞቹ አገራት መካከል እየተቀጣጠለ በነበረው እሳት ላይ ቤንዚን አርከፍክፎበታል፡፡
የሕንድ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አሚት ሻህ፤ መንግስታቸው ለካሽሚር ልዩ መብት የሚሰጠውን የህገመንግሥቱን አንቀፅ 370 መሻሩንና የካሽሚር ግዛት ከአገሪቱ ጋር አንድ አድርጎ ለማስተዳደር ማቀዱን መግለጻቸውም ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ አሸጋግሮታል፡፡
አንቀጹ ካሽሚር የራሷን አዋጆች የማዘጋጀትና ሌሎችንም ውሳኔዎችን የማሳለፍ ልዩ አስተዳደራዊ ሥልጣንና መብቶች የሚሰጥ ነበር፤ ከመከላከያ፣ የውጭ ግንኙነት፣ ፋይናንስና ኮሚዩንኬሽን ውጪ ጉዳዮች ውጪ ግዛቲቱ የራሷን ሕግጋት የማውጣት ስልጣን የሚያጎናጽፍ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መንግስት ይህን አንቀፅ በአብላጫ ድምፅ በመሻር ከእንግዲህ ‹‹አስተዳድረዋለሁ›› ባለው የካሽሚር ግዛት በርካታ ወታደሮችን ማሰማራቱና በግዛቲቱም የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉም በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ አድናቆትን አትርፎበታል፤ እርምጃው የሞዲ ጥንካሬ ማሳያ ተደርጎም ተወስዷል፡፡
የካሽሚር ግዛት ነዋሪዎች በአንፃሩ ውሳኔውን በብርቱ አውግዘውታል፡፡ ስሜታዊነት የታከለበት ጠንካራ ተቃውሞንም አስከትሏል፡፡ በተለይ በካሽሚር ግዛት የሚገኘው በጃሙ አካባቢ ላይ ለረዥም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ ስታቀርብ የቆየችውን የፓኪስታን መንግስት በእጅጉ አስቆጥቶታል፡፡
የኢስላማባዱ መንግስት ይሕ ስሜቱን በሚያንፀባርቅ መልኩም አፍታም ሳይቆይ ከሕንድ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመቀነስ የንግድ አጋርነቱን ማቋረጡን አስታውቋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ እስከ መጠየቅም ደርሷል፡፡ ጉዳዩን ወደ ተመድ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤትም ወስዶታል፡፡
የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻሕ መሐመድ ቁረይሽ ››በዚህ ጉዳይ አንደራደርም›› ብለዋል፡፡ በፓኪስታን የነፃነት ቀን ክብረ በአል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሀንም የጎረቤታቸውን ውሳኔ በማብጠልጠል አገራቸው አስፈላጊ ከሆነ ለወታደራዊ ፍልሚያ ዝግጁ ስለመሆኗ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ጡዘቱን ይበልጥ አስፈሪ አድርጎታል፡፡
በህንድ 73ኛ አመት የነፃነት ቀን ክብረ በአል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው ውሳኔውን ድንቅ አፈፃፀም በሚል በማሞካሸት አገሪቱን አንድ በማድረግ እድገት ለማምጣት በእጅጉ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል። የመንግሥታቸውን ውሳኔ የነቀፉትን ሁሉ ወደ ጎን በመተው የካሽሚር ጣጣ የአገራቸው የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞችም የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂ አገራቱ ፍጥጫ የሚያስከትለውን አስከፊ ጥፋት ከወዲሁ ከማስገንዘብ ባለፈ የጎረቤታሞቹ ፍልሚያ ሌሎች ሀይሎችን ጭምር ሊያፋልም እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
አለማችንን የሚዘውሩ አገራት የሁለቱን አገራት ፍጥጫ ተከትሎ ከማን ጎን ሊቆሙ ይችላሉ የሚለውም ወሳኝ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የዋሽንግተን ፖስቱ ባርክሃ ዱት የብላድሚር ፑቲንዋ ሩሲያ ከኒውዴህሊ ጎን መቆሟን አሳውቃለች፣ ከህንድ ጋር በድንበር የምትወዛገበው ቻይና በበኩሏ የኢሳላማባድን መንግስት መደገፍ መርጣለች›› ሲል አስነብቧል፡፡
በእርግጥም ቻይና የካሽሚርን ጉዳይ ወደ ጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት አድርሳዋለች፡፡ ምክር ቤቱም እእአ ከ1964 በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የሁለቱን አገራት የካሽሚር ጉዳይ በዝግ ስብሰባ ለመመልከት ተገዷል፡ ፡ በስብሰባው ሕንድም ሆነች ፓኪስታን ጉዳዩን ከማባባስ እንዲቆጠቡ በመጠየቅ «የጃሙ እና ካሽሚር እጣ-ፈንታ በሰላማዊ መንገድ ሊወሰን ይገባል» የሚል አቋሙን አሳይቷል፡፡
ሞስኮና ቤጂንግ የየቅል ምርጫቸውን ካደረጉ ዋሽንግተን ‹‹ለማን ትወግናለች›› ተብሎ መጠየቁም አይቀር ነው፡፡ የአሜሪካና የፓኪስታን ግንኙነት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጥብቅና አንዳቸው ለሌላቸው የሚያስፈልጉበት ቢሆንም፣ ከዶናልድ ትራምፕ መምጣት በኋላ ግን ይህ ግንኙነት በእጅጉ ተቀዛቅዟል።
ለወትሮ አንዳቸው ለሌላቸው አስፈላጊ የነበሩት አገራትም አይንሽን ለአፈር ተባብለዋል። በተለይ የትራምፕ አስተዳደር በቢሊየን ዶላር የሚተመነውን የደህነንት ድጋፍ መሰረዙ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ በኢስላማበድ ላይ የነበረውን ጥገኝነቱን ስለ ማቋረጧ በቂ ምልክት ተደርጓል።
በእርግጥ ዶናልድ ትራምፕ ለሕንድ እጃቸውን በመዘርጋት በፓኪስታን መንግስት ላይ መኮሳተራቸው ለኒውደህሊ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህም ግንኙነት ከአመት በኋላ መልኩን የቀየረ እየመሰለ ሲሆን፣የዋሽንግተንና ኢስላማባድ ግንኙቱነት ግን መልካም በሚባል እርምጃ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ እስከሆነ ደግሞ የነጩ ቤተ መንግስት አስተዳደር በሁለቱ አገራት ፍጥጫ ላይ የሚያሳድረው ጫና መመጣጠኑ የግድ ነው፡፡ የዋሽንግተኑን መንግስት ወደ ፓኪስታን እንዲያደላ የሚያስገድዱ አጀንዳዎች ሰለመኖራቸውም የፖለቲካ ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡
ኢስላማባድ በአፋጋኒስታን ድንበር በካሽሚር አዋሳኝ በርካታ ወታደሮችን ለማሰማራት አስባለች መባሉ ወደ መጨረሻ ምእራፍ ተሸጋግሯል በተባለው የአሜሪካና ታሊባን የሰላም ድርድር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለህንድ ፍቅር ቢኖራቸውም፣የሁለቱ አገራት ፍጥጫ ኢስላማባድን እንዲያስቀድሙ ሊያስገድዳቸው ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል፡፡
ከኒውርክ ታይምስ ጋር ቆይታ ያደረጉት በዩናይትድ ስቴትስ የፓኪስታን አምባሳደር አሳድ ማጂድ ከሃን በበኩላቸው፣ የካሽሚርና አፍጋኒስታን አጀንዳ ፈፅሞ ግንኙነት እንደማይኖረው ጠቅሰው፣ፓኪስታንም ለታሊባን ሰላም ድርድር ስኬታማነት የማትከፍለው መስዋዕትነት እንደሌለ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከባላንጣዎቹ ጎን የሚሰለፉት አገራት እያደር በተለዩበት በዚህ ወቅት በሁለቱ ሀገሮች ድንበር ላይ ወታደሮች መታኮሳቸውና አምስት የሚሆኑት ሕይወታቸውን ማጣታቸው በበርካቶች ዘንድ የኒውክሌር ታጣቂዎቹ ራሳቸውን ለጦርነት እያሟሟቁ ስለመሆኑ እንዲታመን ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ጸሐፊ ሎርድ ብራውን ከቢቢሲ ሬዲዮ 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉትም ሁለቱ አገራት ጡንቻ ለመፈታተሸ በእጅጉ ተቃርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 14/2011
ታምራት ተስ ፋዬ