ሴት የቤተሰብና የትውልድ መሰረት ናት። ሴት የፍቅር መገለጫ ናት፡፡ ደግነትና ሆደ ሰፊነት በሴት ይወከላል፡፡ ለነገሩማ አገርስ በሴት አይደል የምትሰየመው፤ ማህበረሰባችንም ገደብ የሌለውን መውደድና ፍቅር ለመግለጽ ወንዶችን ጭምር በሴት ጾታ አንቺ፤ እሷ ብሎ መጠራራት የተለመደ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሴት የሰላም መገለጫ ናት፡፡ እንዲያውም ይሄንን ሰላማዊ ሁኔታ ለመግለጽ አንዳንድ ምሁራን ዓለም በሴቶች ብትመራ በየቦታው የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንደማይፈጠሩ ያትታሉ፡፡ ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳን ከቦታ ቦታ ቢለያይም በሴቶች ላይ ያለው የተዛባ አመለካከትና አተያይ የፆታ እኩልነት ያለበት የሰለጠነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ ይገኛል፡፡
ምንም እንኳን የሴቶችን እኩልነት በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር መሬት ላይ ያዋሉ አገሮች ቁጥር በዓለም ላይ እየተበራከተ ቢመጣም፤ ለሴቶች ያለው ኋላቀር አመለካከትና አስተሳሰብ በዚህ ዘመንም በስፋት የሚስተዋልባቸው አገሮች አሉ። በተለይ እንደ የመን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ በመሳሰሉ አገሮች በሚደረግ የርዕስ በርዕስ ጦርነት ሴቶችና ህጻናት የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆነው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ማስቀጠል የማይገፋ ዳገት ሆኖባቸው ይገኛል፡፡
ከዚህ ባለፈ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በሆነ አስተሳሰብ በመመራት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወደጎን በማለት፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች ለመብቶቻቸው አደባባይ ወጥተው እንዳይታገሉና ለአገራቸው የበኩላቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ ተደርገው ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ሆነው ይገኛሉ።
ከነዚህ አገሮች መካከል የሴቶች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ተሳትፎ ተገትቶ ሴቶች ለከፋ ችግር ተጋላጭ ከሆኑባቸው አገሮች አንዷ ቫኑዋቱ ናት።ይቺ አገር በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንድም የሴት የፓርላማ አባል የሌላት አገር መሆኖን ቢቢሲ በድረገፁ ከሰሞኑ አስነብቧል።እርስዎም ይሄን ዜና ሲሰሙ ቫኑዋቱ የምትባል አገር አለች እንዴ? የት አካባቢ ይሆን የምትገኝው? ብለው በአዕምሮዎ ጥያቄ ሊያጭርበዎ ይችላል።
በአገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ድሮ በሚባል ሁኔታ ካልሆነ በቀር በአሁኑ ወቅት አንድም የሴት አባል ያልተካተተባት በመሆኑ በሰሞነኛው በዓለም የመገናኛ ብዙሃን ስሟ ገኖ የወጣውና መነጋገሪያ የሆነችው ቫኑዋቱ በደቡባዊ ፓሲፊክ ውቅያኖስ አንድ ሺህ 300 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያሉ 80 ደሴቶችን የያዘች አገር ናት።የአገሪቱ ፓርላማም 52 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ሁሉም እንደራሴዎች ግን ወንዶች ናቸው።
በዚህም ሳቢያ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ በሕግ አውጭው ምክር ቤት ሴቶች እንዲወከሉና የሴቶች እኩልነት ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት የምታደርገው የዚች አገር ዜጋ የሆነችው ያስሚን እንደተናገረችው፤ ለሴቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮችና ጉዳዮች በአገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጭ አካል ውስጥ ሴቶች ውክልና ስለሌላቸው ተግባራዊ አይደረጉም።
እንዲሁም በአገሪቱ ያሉ ምክር ቤቶች ሁሉም በወንድ የአካባቢ አለቆች የሚመራ ሲሆን፤ ለፓርላማ አባልነት በእጩነት የሚቀርቡትን የሚጠቁሙትም እነርሱው ናቸው።በመሆኑም ሴቶች ለፓርላማ በእጩነት የሚቀርቡ አባላትን መጠቆም ስለማይችሉ የአገሪቱ የፓርላማ አባላት ወንዶች ብቻ የሆኑት በዚህ ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።
275 ሺህ ሕዝብ ባላት ቫኑዋቱ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችና ወንጀሎች ከፍተኛ እንደሆኑ የገለፀችው ያስሚን፤ በአገሪቱ ከሦስት ሴቶች አንዷ አስራ አምስት ዓመት ሳይሟላት ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባት ተናግራለች።
ያስሚን አክላም፤ በእስር ላይ ከሚገኙ ታራሚዎች 60 በመቶ የሚደርሱት ወንዶች ወሲባዊ ወንጀል የፈፀሙ ሲሆኑ፤ 90 በመቶው በሴቶች ላይ የሚያጋጥሙ ወሲባዊ ጥቃቶች በሚያውቋቸውና በቅርብ ሰዎች አማካኝነት የሚፈፀሙ ናቸው ትላለች።
“በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩት በወንዶች ነው።እጩዎችንም እራሳቸው ይጠቁማሉ፤ የሚወዳደሩትም እነርሱው ስለሆኑ እነርሱው ይመረጣሉ።በዚህም ፓርላማው ሙሉ ለሙሉ በወንዶች ይያዛል” ሲሉ የመጀመሪያዋ የቫኑዋቱ ሴት የቀድሞ የፓርላማ አባል የነበሩት ሊኒ ይናገራሉ።
የቀድሞዋ የፓርላማ አባል አክለውም በሕግ አውጭው ምክር ቤት ውስጥ የሴቶች አለመኖር በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን ገልፀዋል።ለዚህም በቤት ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀምን ጥቃት የሚመለከተውና እስካሁንም በአግባቡ ተግባር ላይ አልዋለም የሚሉትን የቤተሰብ ጥበቃ ሕግ ለማውጣት ዘጠኝ ዓመት እንደፈጀ በምሳሌነት አንስተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በቫኑዋቱ የሚገኙ ሴቶች በፆታዎች መካከል ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠን እንዲያበቃ እና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ተጽዕኖዎችንና የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቀረት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን፤ በፖለቲካው መስክ ያለውን የወንዶች የበላይነት ለመለወጥ በእድሜ ጠና ያሉ ሴቶች ተሰባስበው ሴቶች ብቻ አባል የሆኑበት ፓርቲ መስርተዋል።
በቀድሞዋ የፓርላማ አባል ሄልዳ ሊኒ የሚመራው ይህ ፓርቲ፤ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ሴቶች እንደሚሳተፉ ያሳወቁ ሲሆን ከአገሪቱ ፓርላማ መቀመጫዎች ግማሹ ለሴቶች ብቻ እንዲደረግ ከወዲሁ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ አንፃር የወንዶች የበላይነት በስፋት በሚታይባት ቫኑዋቱ፤ ወንዶች ሴቶች ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ የመውሰድና የማስተዳደር አሠራር የተለመደና በስፋት የሚታይ ነገር መሆኑን ቢቢሲ በዘገባው ያሰፈረ ሲሆን፤ አብዛኛው ሕዝቧ በድህነት ውስጥ የሚኖርባት ይህች አገር ዕድገት ለማምጣት የምትፈልግ ከሆነ በፆታዎች መካከል ያለውን የሰፋ ልዩነት መፍትሄ ልታበጅለት እንደሚገባ ዓለም ባንክ ለዚች አገር ምክሩን ጀባ ብሏል።ይላል።
ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት ፓርላማ ያላት ቫኑዋቱ ብቻ ሳትሆን በዓለማችን ሌሎች ሁለት አገራትም በምክር ቤታቸው ውስጥ አንዲትም ሴት በአባልነት የማይገኝ ሲሆን፤ እነዚህ በዓለማችን በፓርላማቸው ውስጥ ሴት የምክር ቤት አባላት የሌላቸው አገራት ቫኑዋቱን ጨምሮ ሦስቱም በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ያሉ ደሴቶች ናቸው።ሁለቱ አገራትም ማክሮኔዢያና ፓፑዋ ኒው ጊኒ ናቸው።
በአንፃሩ በዓለም ላይ በፓርላማቸው ውስጥ ከግማሽ በላይ ሴት እንደራሴዎች ያሏቸው አገራት ሦስት ብቻ ሲሆኑ፤ እነርሱም አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ 61 በመቶ ሴት የፓርላማ አባላትን በመያዝ ከዓለም ቀዳሚ ስትሆን፤ ኩባ 53 ነጥብ 2 በመቶ እና ቦሊቪያ 53 ነጥብ 1 በመቶ ሴት የፓርላማ አባላትን በፓርላማቸው በማካተት ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 10/2011
ሶሎሞን በየነ