የጃፓን መንግስት ባለፈው ወር የቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ወደ ደቡብ ኮሪያ እንዳይላኩ የሚያደርግ አዲስ ማዕቀብ ጥሏል። እነዚህ ቁሳቁስ ሳምሰንግና ኤል ጂን ጨምሮ ሌሎችም የደቡብ ኮሪያ ግዙፍ ኩባንያዎች ለሚያመርቷቸው ቴክኖሎጂዎች ዋነኛ ጥሬ እቃ በመሆናቸው ውሳኔው ለሴኡል አስደናጋጭ ሆኖም ነበር።
በማዕቀቡ መሰረት ማንኛውም የጃፓን ምርት አምራች ድርጅት ግብአቶቹን ወደ ደቡብ ኮርያ ከመላኩ አስቀድሞ ለቶኪዮ መንግስት ማሳወቅና ይሁንታውን ማግኘት ግድ ይለዋል። የሲኤን ቢሲዋ ፀሃፊ የን ኒ ሊ ይህን አስመልክታ እንደዘገበችው ውሳኔ ኩባንያዎቹ ወደ ደቡብ ኮሪያ ሊልኩ የሚፈልጓቸውን ምርቶች ከዘጠና ቀናት በፊት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።ጃፓን ከዚህ ውሳኔዋ በስተጀርባ ብሔራዊ ደህንነትን በምክንያትነት ትጠቅሳለች።
በቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር ለማጥበቅ መወሰኗ ግን በሁለቱ አገራቱ መካከል የንግድ ውዝግብ እንዲከሰት እያደረገ ነው ሲሉ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ናቸው።
ምንም እንኳን ደቡብ ኮሪያ ለጃፓን የኤክስፖርት ጥብቅ ቁጥጥር የአፀፋ ምላሽ ባትሰጥም፣የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን ግን የአገራቸው ኩባንያዎች ለንግድ ጦርነቱ ዝግጁ እንዲሆኑና የተከለከሉትን ግብአቶች በአገር ውስጥ ስለማምረት እንዲያስቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በርካታ ደቡብ ኮሪያውያን በአንፃሩ ከመንግስታቸው ቀድመው ‹‹አስተማሪ ምላሽ ነው››ያሉትን ፈፀመዋል። አደባባይ በመውጣት ጠንካራ ተቃውሟቸውን ከማሰማት አልፈው፣የጃፓን ምርቶችን ምርትና አገልግሎቶችን ላለመግዛትና ላለመጠቀም ወስነዋል።
በእርግጥ ካሳለፍነው አመት ጀምሮ የሁለቱ አገራት ግንኙነት የመሻከር ምልክቶች ታይተውበታል። የዚህ መነሾውም ‹‹ጃፓን እአአ ከ1910 እስከ 1945 ለ35 አመታት ኮርያን በቅኝ ግዛት በያዘችበት ወቅት የኮሪያ ሰራተኞችን በግዳጅ የጉልበት ሥራ አሰርታለች፤ ለዚህ ተመጣጣኝ ካሳ ይገባናል›› በሚል በሴኡል በኩል የተነሳ ቅሬታ ነው። ጃፓን ይህ ጉዳይ እአአ በ1965 ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ በመሰረቱበት ወቅት በተደረሰ ስምምነት መሰረት ተገቢውን ማላሽ ማግኘቱን በመጥቀስ ጥያቄውን ውድቅ አድርጋዋለች።
ደቡብ ኮሪያ ግን በስምምነቱ መሰረት በተሰጣቸው ምላሽ ደስተኛ እንዳልሆኑ ይገለፃል። ምንም እንኳን የሰራኞቹ የካሳ ጥያቄ ለወቅታዊው ንግድ ውዝግብ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ በበርካታ ወገኖች ባይታመንም በሴኡል ህዝቦች ዘንድ በታየው የቅሬታ ስሜት ላይ የኤክስፖርት ቁጥጥሩ ውሳኔ መደመሩ በአደባባይ ወጥተው ጠንካራ ተቃውሞ ለማንሳታቸው ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል።
ጃፓን ጀርመንን፣ ብሪታኒያን፣ አሜሪካን ጨምሮ 27 አገሮችን በንግድ አጋርነት ይዛ የቆየች ስትሆን፣ደቡብ ኮርያም ከእነዚህ ሀገሮች አንዷ ናት። የሰሞኑ የጃፓን ውሳኔ ግን ኮሪያን ከህብረቱ እስከ መሰረዝ ሊሸጋገር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል። ይህ ከሆነ ደግሞ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሸጋገሩ ተገምቷል።
ይህን ቀድመው የተረዱ በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካና ኢኮኖሚ ምሁራን በእስያ ግዙፍ ሀብታም ሀገራት መካከል የተከሰተው የንግድ ውዝግብ ኢኮኖሚያዊ ይሁን ጂኦፖለቲካዊ ጉዳቱ አስከፊ መሆኑን በመጥቀስ፣ ችግሩ በጊዜ መፍትሄ ሊቀመጥለት ይገባል ሲሉ መጎትጎታቸውን ይዘዋል።በኢኮኖሚው በኩል በተለይም በዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ ገበያ ላይ ከባድ መዘዞች ሊከተሉ እንደሚችሉም እየተጠቆሙ ናቸው።
የኤቢሲ ኒውሱ ኤሪን ሃንድሊ፣‹‹በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ፍጥጫ በስማርት ስልኮች፣በኮሚፒውተርና በሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ የዋጋ መናር ሊያስከትል ይችላል›› ሲሉ አስነብበዋል።የደቡብ ኮርያው ግዙፍ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግም ገና ከወዲሁ የንግድ ጦርነት ግለቱ እንደደረሰው ተጠቁሟል።
የሲ ኤን ቢሲው ፀሓፊ ግርሲ ሾ የሁለቱ አገራት ፍጥጫ ከወዲሁ የንግዱን ምህዋር እያናጋው ስለመሆኑ አትታለች። በእርግጥም ፍጥጫው ከወዲሁ በርካታ አየር መንገዶች በረራቸውን እንዲያስተካክሉ አንዳንዶቹም እንዲሰርዙ ሲያስገድድ ተስተውሏል።
የኮርያ አየር መንገድም ከፈረንጆቹ መስከረም 3 ቀን ጀምሮ ከደቡብ ኮርያዋ ቡሳን ወደ ጃፓኗ ሳፖሮ የሚያደርገውን በረራ እንደሚያቋርጥ አስታውቋል። ወደ ጃፓን የሚያደርጋቸውን በርካታ በረራዎች ለመሰረዝ ወይም አገልግሎቱን በአነስተኛ አውሮፕላኖች ለመስጠት ስለማሰቡም የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
በአቭየሽን ኢንዱስትሪው የተስተዋለው ኪሳራም በእስያ ሀገራት መካከል የተከሰተው የንግድ ጦርነት በጊዜ መቋጫውን የማያገኝ ከሆነ አገራቱ በተለይም በቱሪዝሙ መስክ የነበራቸውን መስተጋብር በመበጣጠስ በሚሊየን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ጉብኝታቸውን እንዲሰርዙ በማስገደድ አገራቱ ከዘርፉ የሚያገኙትን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያሳጣቸው መገመት ቀላል ነው›› ተብሏል።፡
ይህን ያስተዋለውና መቀመጫውን በጃፓን ያደረገው የዊዝደም ትሪ ኩባንያ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አማካሪ ጄስፔር ኮል ፣የእሲያ አገራት የንግድ ፍጥጫ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን በማንገጫገጭ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚያስከትል በመጠቆም፣ጉዳቱም ሁለቱንም ሊመለከት እንደሚችል ለሲኤንቢሲ ጠቁሟል።
በእስያ ግዙፍ ሀብታም ሀገራት መካከል የተከሰተው ይህ የንግድ ውዝግብ ከሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በላይ ጂኦፖለቲካዊ ኪሳራው እንደሚበልጥ የሚያስገነዝቡ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካና ኢኮኖሚ ምሁራንም በርክተዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የናሽናል ሪቪው ፀኃፊ ቴይለር ዲነርማን ‹የሁለቱ አገራት ፍጥጫ በአሜሪካና በቀጠናው ደሕንነት ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ ከባድ ስለመሆኑ አስነብቧል።በሰሜን ምስራቅ እሲያ በሚደረገው ወታደራዊ ደህንነት ጥበቃ ላይ ያለውን ጥምረት እንደሚያፈርስም አመልክቷል። ይህም ከሁለቱም አገራት ጋር ወዳጅ የሆነችው በኢኮኖሚም ሆነ በደህንነት ጉዳዮች ላይ በጥምረት የምትሰራው አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ ሳያደርጋት እንደማይቀር ተጠቁማል።
በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አንድሪው ዮ፣ በ‹‹ፎሬን አፌርስ›› ላይ ባሰፈረው ሰፊ ትንታኔ በሴኡልና በቶኪዩ መካከል የተነሳው ፍጥጫ በአለም አቀፉ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ዘንድ የሚሰጠው ትርጉም የላቀ ስለመሆኑ አስነብቧል።
ጉዳዩ በተለይ ዋሽንግተን በእሲያ ምድር በምተከተለው ፖሊሲና ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳደር ያመላከተው ፀሃፊው‹.ፍጥጫው አፋጣኝ እልባት ካላገኘ የኢኮኖሚ ብቻም ሳይሆን የትራምፕ አስተዳደር በሰሜን ኮሪያና በኢንዶ ፓስፊክ የሚከተለውን ፖሊሲ እንደሚፈታተነው አብራርቷል።
ምንም እንኳን በሁለቱ አገራት መካከል የተለኮሰውን እሳት በማጥፋት በኩል ዩናይትድ ስቴትስ እሳት የማጥፋት ሩጫ በሚፈለገው ልክ ሆኖ አልታየም። ዋሽንግተን ውዝግቡን ለመፍታት በምትችለው ሁሉ እንደምታግዝ ስለማስታወቋም ተጠቁሟል።፡
የንግድ ጦርነቱ በሚያስከትለው ኪሳራ ተጎጂዎች የመኖራቸውን ያህል ተጠቃሚዎችም ስለመኖራቸው የሚያመላክቱም አልጠፉም።ይህን እሳቤ በመንተራስ ሰፊ ትንታንውን በ‹‹ዚስ ዊክ ኢን እሲያ›› ላይ ያሰፈረው ሊ ጆኦንግ ሆ ‹‹የሁለቱ አገራት የንግድ ውዝግብ በተለይም ለቻይና በዲፕሎማሲውም በሆነ በኢኮኖሚው መስክ የሚያስፈነድቅ የብስራት ዜና ነው ብሎታል።፡
በኢኮኖሚው መስክ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በተለይ ግዙፉ ሁዋዌ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያመላከተው ፀኃፊው፣በዲፕሎማሲውና በጂኦ ፖለቲክሱ ደግሞ ሁሌም ቢሆን በአይነ ቁራኛ የምትከታተለው የፓስፊክ ቀጠናዋ የጃፓን፣ደቡብ ኮርያና የአሜሪካ አጋርነት ጫና ውስጥ እንደሚወድቅ አስነብቧል።
የንግድ ውዝግቡ ጦስ ሁለቱን አገራት ብቻ ሳይሆን ወትሮም ቢሆን አቅማቸውን ለመለካካት ዳር ዳር እየተባባሉ የሚገኙት አሜሪካና ቻይናን ሳይቀር ጎትቶ የሚስገባ መሆኑን በርካታ ፖለቲካ ምሁራን ይጠቁማሉ።ምሁራኑ ኪሳራው ከኢኮኖሚ በላይ የሆነው የንግድ ውዝግብ ሳይውል ሳይድር መቋጫውን እንዲያገኝ መጎትጎታቸውኝ ቀጥለዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011
ታምራት ተስፋዬ