ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ዚምባብዌ 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት። ከዚህ ውስጥ 32 ከመቶ የሚሆነው በከተማ ይኖራል። ሁለት ከተሞቿም /ዋና ከተማዋ ሃራሬና ቡላዋዮ/ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ቡላዋዮ በአብዛኛው የኢንዱስትሪ ከተማ ናት።
ከዚምባብዌ ዜጎች መካከል 98 ከመቶ የሚሆኑት የባንቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ዚምባብዌ ጥቂት ነጭ ዚምባቤዊያን ያላት ሲሆን አብዛኞቹም የዘር ሃረጋቸው ከብሪታንያ ይመዘዛል። አልፎ አልፎም የግሪክ፣ የፖርቹጋል፣ የፈረንሳይና የሆላንድ መሰረት ያላቸው ነጮች ይገኛሉ። ከአጠቃላይ የአገሬው ህዝብ ቁጥር 4 ነጥብ 3 ከመቶ የሚሆኑ ነጮች ሲሆኑ 0 ነጥብ 5 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ክልሶች ናቸው። የተለያዩ ሃማኖቶችም ይገኛሉ።
እአአ በ2006 ዚምባብዌ ከአለም ዝቅተኛ የእድሜ ጣሪያ ካላቸው አገራት ግንባር ቀደም ነበረች። በተለይ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መስፋፋት ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይነገራል። በአገሪቱ 21 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 37 ነጥብ 9 ከመቶ የሚሆኑ ዚምባብዌያውያንም በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚምባብዌ በተለይ ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ በርካታ ዜጎቻቸው በድህነት ውስጥ ለማለፍ የተገደደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህ ደግሞ ድርቅና በዚህ የተነሳ የተከሰተው የምግብ እጥረት ዋነኛው ምክንያት ነው። በተለይ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ከምእራባውያን ጋር የገቡትን እሰጣገባ ተከትሎ በአገሪቷ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ለችግሮቹ መባባስ የራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም መረጃዎቹ ያሳያሉ።
ምእራባዊያኑ በወቅቱ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳደሩበት ወቅት ነበር። ከ1830 ጀምሮ ደግሞ እንግሊዞች በዚምባብዌ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አሳደሩ። ከዚያም በ1889 ዚምባብዌ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወደቀች። ከዚያ በኋላም በዚምባብዌ በርካታ ነጮች መሬት በመያዝ አገሪቷን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ።
ይህም እስከ 1965 ድረስ ቀጠለ። ሆኖም በ1965 ዚምባብዌ በከፊል ነጻ ሃገር በመሆን ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ መንገድ ጀመረች። በ1980 ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ነጻነቷን ተቀዳጀች።
ዚምባብዌ እአአ ከ2005 ጀምሮ ድህነትን ለመቅረፍ ሰፊ ዘመቻ አድርጋለች። በተለይ በጥቂት ነጮች ተይዞ የነበረውን መሬት ከነጮቹ በመቀማት ለጥቁሮች በማዳረስ ዜጎች ከመሬት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል። ይህ ተግባራቸው በምእራባዊን ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረውም ለአብዛኞቹ የአገሬው ዜጎች ግን ትልቅ ደስታን የፈጠረ ነበር።
ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ዚምባብዌ በከፍተኛ የሰብኣዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። ለዚህም ዋነኛው መንስኤ በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅና ይህንን ተከትሎ የተፈጠረው የምግብ እጥረት ነው። በዚህም የተነሳ አንድ ሶስተኛው ህዝቧ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገዷል። ይህንን ሰብኣዊ ቀውስ ለመፍታትም የዓለም የምግብ ፕሮግራም 331 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ከተጋለጡ የአፍሪካ አገራት ዚምባብዌ አንዷ ናት። የኣለም የምግብ ፕሮግራም ሃላፊ የሆኑት ዴቪድ ባሴል እንደሚሉት በአገሪቱ በተፈጠረው የድርቅ አደጋ ምክንያት በርካቶች ለረሃብ ተጋልጠዋል። በአንድ ወቅት “የዳቦ ቅርጫት” የሚል ስያሜ የተሰጣት ዚምባብዌ ዛሬ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ተጋርጦባታል::
በአገሪቱ በተፈጠረው አየር ንብረት መዛባት ምክንያት አገሪቷ በድርቅ በመመታቷ የምርት መቀነስ ያጋጠመ ሲሆን የምግብ ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በአገሪቱ በተከሰተው የዝናብ እጥረትም የአገሪቱን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጨው ጣቢያ የሃይል ማመንጨት አቅሙ ተዳክሟል። በዚህ የተነሳ አብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ለሃይል እጥረት ተጋልጠዋል።
ሌላው የአገሪቱ ትልቁ ፈተና ደግሞ የዋጋ ግሽበት ነው። በአሁኑ ወቅትም አገሪቱ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ወድቃለች። ባሴል እንደሚሉት አሁን ባለው ሁኔታ ዚምባብዌ አስቸኳይ ድጋፍ ካላገኘች በርካታ ዜጎች ለከፋ የረሃብ አደጋ ይጋለጣሉ።
አገሪቱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ረሃብም ትጎዳለች። ከፊል ማላዊንና ሞዛምቢክን የመታው ከፍተኛ አውሎንፋስም ከ 570 ሺህ በላይ የዚምባብዌ ዜጎችን አጥቅቷል። ይህ ደግሞ በአስር ሺዎች የሚገመቱትን ዜጎች ቤት አልባ አድርጓል።
በርግጥ አገሪቷ ይህንን የተፈጥሮ አደጋ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ከዚህ አንፃር የአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ሚቱሊ ንኩቤ እንዳሉት መንግስት ችግር ለደረሰባቸው ከ757 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የምግብ እርዳታ እያቀረበ ይገኛል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋጋዋ በበኩላቸው ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው አገራቸው ለድርቅ መጋለጧን ይፋ አድርገዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ እየባሰ መጥቷል። የኤሌክትሪክ መቆራረጡም ለአገሪቷ ተጨማሪ ፈተና ሆኗል:: ብዙ ልጆች አሁን የቤት ስራቸውን በሻማ መብራት ይሰራሉ። ይህ ኤሌከትሪክ ሃይል እጥረት ደግሞ ትልቁ ፈተና ነው። በዚህ የተነሳም በርካታ ዚምባብዌያውያን ምግብን ለማብሰል እንጨትን እንደማራጭ እየተጠቀሙ ነው። ይህ ደግሞ በአገሪቷ እየተመናመነ ለመጣው ደን ሌላ ፈተና ደቅኗል።
በህክምና ጣቢያዎችም ቢሆን የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረቱ ትልቅ አደጋን እየደቀነ ነው። አብዛኞቹ የህክምና ጣቢያዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ በሽተኞችን ለማከምም ሆነ ኤሌክትሪክ የሚያስፈልጋቸው የህክምና ቁሳቁሶችን መጠቀም እንዳልቻሉ ያማርራሉ።
በነዚህ ችግሮች የተነሳ አብዛኞቹ ዚምባብዌያውያን በአገሪቱ በተከሰተው ችግር እያማረሩ ይገኛሉ። በተለይ በዘመነ ሙጋቤ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም እንዲህ የከፋ ችግር አላጋጠመም ነበር የሚሉ ወገኖች በዝተዋል።
በተለይ ሙጋቤ ለአመታት በነጮች ተይዞ የነበረውን መሬት ቀምተው ለጥቁሮች ካከፋፈሉ በኋላ አብዛኞቹ ጥቁሮች ለራሳቸው የሚሆን ምርት በማምረት የተሻለ ገቢ ማግኘት በመቻላቸው በነበረው አሰራር እና በመንግስት ደስተኞች ነበሩ። ይህ ግን አሁን ታሪክ እየሆነ ነው።
እነኚያ ባለውለታቸውም በአሁኑ ወቅት በሲንጋፖር በህክምና እርዳታ ላይ ይገኛሉ። ሙጋቤ በወሰዱት በዚያ እርምጃ ዚምባብዌ ለችግር መዳረጓን የሚናገሩ ፖለቲከኞችም አልጠፉም:: ለዚህ እንደምክንያት የሚያቀርቡት ደግሞ አገሪቷ ከምዕራባውያን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ባልተላቀቀችበት ሁኔታ እንዲህ ከነጮቹ ጋር እሰጣገባ ውስጥ መግባታቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል መሬቱ ለጥቁሮቹ በመሰጠቱ ለአገሪቱ ህዝብ የሰጠው ፋይዳ እምብዛም እንደሆነም የሚናገሩ አሉ። ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት መሬትን በጣጥሶ ለአርሶ አደሮች መስጠት ግብርናው በተበታተነ ሁኔታ እንዲካሄድ በማድረጉና ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ድርቅ ሲያጋጥም ችግሩ እንዲባባስ ትልቅ ምክንያት ሆኗል። በዚህ የተነሳ ነው አሁን ላይ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም አብዛኛው የአገሬው ህዝብ ለችግር የተጋለጠው የሚል ምክንያት ያቀርባሉ።
ከዚህም ባሻገር የዚምባብዌ ዶላር በደረሰበት የዋጋ ግሽበት ምክንያት ከዓለም አቀፉ ገበያ መታገዱ ይታወቃል። ብዙዎች ይህንን ጉዳይ ከነባራዊው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ያያይዙታል። አብዛኞቹ ዚምባብዌያውያን ዜጎች ይህ የሆነው በእንግሊዝና ወዳጆቿ ሴራ እንደሆነ ይገምታሉ:: በዚህም የተነሳ የዚምባብዌ ዶላር በዓለም ላይ ትልቁን የዋጋ ግሽበት ያስተናገደ ገንዘብ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ በዚምባብዌ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተንሰራፍቷል። የስራ አጥ ቁጥሩም ጨምሯል:: ይህ ደግሞ ለበርካታ ዜጎች ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል::
ይህንን ችግር ለመፍታት መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። የሙጋቤን እርምጃዎች እንደማይደግፉ የሚነገርላቸው አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ምዋንጋጋዋም ቢሆኑ ችግሩን ለመፍታት አቅሙ አንሷቸዋል እየተባለ ነው። በተለይ በነበረው ችግር ላይ አሁን አሁን የተባባሰው የተፈጥሮ አደጋና የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ድርቅ ለመንግስታቸው ፈተና ሆኖባቸዋል።
በዚምባብዌ የደረሰውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቅረፍ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የቦንድ ኖቶችን ማሳተም ነበር። ይህ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተቀባይነት ባይኖረውም ችግሩን በጊዜያዊነት እንደሚቀርፍም ባለሙያዎች ተንብየው ነበር::
ነገር ግን ይህም ቢሆን የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አላስገኘም። በዚህ የተነሳም በአገሪቱ የጥቁር ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቷል:: ዚምባብዌም በአብዛኛው የገንዘብ ኖት የማይዘዋወርባት አገር ሆናለች። የአገሪቱ ገበያ በአብዛኛው በካርድ ላይ የተመሰረተ የተንቀሳቃሽ ገንዘብ ልውውጥን ያካሂዳል።
በዚህ የተነሳ ባለፈው የካቲት ወር ላይ የአገሪቱ የቦንድ ኖቶች እና የኤሌክትሮኒክስ ገንዘቡ ምልክታቸውን የማደስ ስራ ሰርተው ነበር። ይህም የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር የዘየዱት መላ ነው።
በዚምባብዌ የመጣው የገንዘብ ቀውስ በተለይ እአአ ከ2008 ጀምሮ ነው እየተባባሰ የመጣው። መረጃዎች እንደሚሳዩት በሃምሌ 2008 የአገሪቱ አመታዊ የዋጋ ግሽበት በማይታመን ሁኔታ እስከ 231 ሚሊየን ከመቶ ደርሶ ነበር። በህዳር ወር 2008 ደግሞ ግሽበቱ ከ80 ቢሊየን ከመቶ በላይ ሲደርስ ባለስልጣቱ ይህንን ሪፖርት ማድረግ ተሰላቹ።
የሸቀጦች ዋጋ በየቀኑ በብዙ እጥፍ የሚጨምርበት ሁኔታም ነበር። በወቅቱ ምንም እንኳን ህጋዊ ባይሆንም በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ከጥቁር ገበያ የሚያገኙትን የአሜሪካ ዶላር ያከማቹ ነበር። ነጋዴዎችም የውጭ ምንዛሪ ላይ ትኩረት ማድረግ ጀምረው ነበር። በዚህ የተነሳም መንግስት የውጭ ምንዛሪዎች በገበያ ላይ እንዳይውሉ እገዳ እስከመጣል የደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የቻይና ዋንን እና የህንድ ሩፒን ጨምሮ በርካታ የገንዘብ ኖቶችም በዚምባብዌ ገበያ ታግደው ቆይተዋል።
ሰሞኑን ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው ደግሞ የአገሪቱ ከተሞች የቧንቧ ውሃ የሚደርሳቸው በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ሆኗል። ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዚምባብዌ ማዘጋጃ ቤት ካጋጠሙት ፈተናዎች ውስጥ ትልቁ ነው። ከዚህም ጎን ለጎን የውሃ ጥራት ማነስ ትልቁ ፈተና ነው።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ውሃን ለማጣራት የሚያስችሉ ኬሚካሎችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ አለመኖሩ ነው። ይህ የኬሚካል ግዢ በወር እስከ ሶስት ሚሊየን ዶላር ወጪን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚሞከር አልሆነም። ዘገባው የቢቢሲ፣ አልጀዚራና ሲኤንኤን ነው።
አደዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011
ወርቁ ማሩ