መጋቤ አዕምሮ ስንል የከፈትነው ይህ አምዳችን ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ፣ ለአስተሳሰብ ቀረጻ የጎላ ሚና ባላቸው የተለያዩ እሴቶቻችን ዙሪያ የተመረጡ ንግግር አዋቂዎች የሚያቀርቧቸው ነጻ ሃሳቦች የሚስተናገድበት ይሆናል::
በነገራችን ላይ ማለት እግረ መንገድ ማለት ይመስለኛል። እግረ መንገድ የሆነ ነገር፤ አንዳች ነገር ትዝ ሲል ወይም ነገርን ነገር ሲያነሳው የሚቀርብ ብሒል ስለሆነ `በነገራችን ላይ…` ይባላል። ዋና ነገር ያልሆነ ማለትም ነው። እንዲህ ልበል እንጂ፣ የሰው ልጅ ጉዳይ የሆነ ነገር ሁሉ ቀዳሚና ተከታይ ደረጃ ይሰጠው ይሆናል እንጂ፣ ጠቃሚ ነው። ክፉውን ክፉ ነው ማለትም ሆነ፣ ጠቃሚውን ጠቃሚ ነው፤ ማለትም በነገራችን ላይ አይባልም፤ የዋዛ አይደለምና።
ራሱ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ የምንለውም ነገር በምድር ላይ እስካለን ድረስ እግረ መንገድም ነው። ቤት ቢኖረን፣ መኪና ብንገዛ፣ ፋብሪካ ብናቋቁም፣ ሁሉም እግረ መንገድ ነው። የሰማዩን በልባችን ይዘን፣ የምድር የምድሩን እስቲ እንጨዋወት። ስለዚህም፤ ዛሬ “በነገራችን ላይ…“ ባልኩት፣ በዚህ ነጻነት በሚሰጥ አርዕስት ስር ሁሌ በልቤ ስለማትጠፋው ሃገሬ፣ ስለ ክፉዎች ደስታ፣ ስለአንጋፋዎቹ ዜጎቿ፣ ስለሚናፈሰው ቱማታ ፣ ስለ አላካኪና ሰበበኛ ሰዎች፣ ስለአየር ጠባዩ፣ ስለ ስብከት፣ ስለ ክብር፣ ስለ ነጻነት ዋጋ፣ ስለ ወዘተርፈ አነሳሳለሁ።
አንድ ጊዜ አንድ ለቅሶ ለመድረስ ራቅ ያለ ቦታ ሄጄ ነበርና ለማስተዛዘን በተቀመጥንበት አንድ ልጇ፣ የሞተባት ሴት አካባቢ ድንኳን ውስጥ ተቀምጬ፣ የሞትን ሰርክ አዲስነትና ሁሌም ግን የማይለየን አሮጌ ወዳጃችን መሆኑን ነግሬ ትንሽ ትንፋሽ ለመሰብሰብ ያህል ብቻ ለመቀመጥ ወሰንኩ። በዚሁ ቅጽበት ለማስተዛዘን የገባ የሚመስል ሰው ከእኔ ትይዩ የተቀመጠ አንገቱን አስግጎ ጠጋ በማለት “ያን የመሰለ ልጅ እንዴት ሞተ?” በማለት ጀመረ።
ድንገት መጣሁ ብሎኝ ወጥቶ፤…. ትላለች እናት …. ቁርሱንም ሳይበላ… ( ድምጽዋ ከለቅሶ ብዛት ሻክሯል) ድንገት የመጣ የጠገበ የመንግስት መኪና ሾፌር ገጨብኝ።
“ጠርጥሪ…መንግስት በነገር ፈልጎት ይሆን?” ኧረ ተው አንተ ሰው አሁን ይኼ ይገባል፤ ሃዘን ባንገበገባት እናት ፊት እንዲህ ይወራል? ልለው አስቤ ተውኩት። ሰው ግን የተስማማ በሚመስል አስተያየት “እምጵፅ …” እዚህም እዛም ከናፍሮች ጮሁ።
ሰውየው ግን ቀጠለ፤ ”ያሳዝናል፤….. አለና ፤ …….ያን የመሰለ ልጅ ፤ ልጅም አላስተረፈልሽ -አልወለደም አይደል?” “አዎ፣ ሰርጉ በጥር ነበር እኮ….ልጄን … እኔ ደፋ ልበል” አለች፤ ምርር ባለ ድምፀት፣ እናት። “አደባባይ የቆመ እንደሆን እኮ ቁመናው ሲያሳሳ….” ሲል ሰውየው…
እናት፣ ንፍርቅ እያለችና ደረቷን እየደቃች ….ልጄ፣ ልጄ እኔ ድፍት ልበል…! እኔ እናትህ ልቀጠፍ….እህህ… ሰውየው”… አይሆንም አይሆንም …. ፍርድ ቤት ሲቀርብስ ተናግሮ የማይረታ የነገር ብልት አዋቂ…..” እናት… ሳግና ጩኸት በተቀላቀለው ድምጽ…. እንደ አዲስ ለቀስተኛ ከፍራሹዋ ተነስታ እየተንቆራጠጠች “…ማን አላት ብለህ … ልጄ? ማን አላት ብለህ…?” ማለት።
ሰውየው፣ “አይመለስ እንግዲህ መቻል ነው”…ሲል ትክ ብዬ እያየሁት “…በቀትር የመጣኸው፣ ልታጽናናት ነው ልታስጮሃት..” አልኩት። “ተው እንጂ ሰውዬ፤ እንዴ?” ደገምኩበት።
“ለእኔስ ቢሆን ልጄ እኮ ነው…ልጄ አለና …” ቆረጥ አድርጎ ሲያያት እስካሁን ልብ ሳትለው የቆየችው እናት ድንገት ከተቀመጠችበት አፈፍ ብላ ተነስታ “ አንተ የቀትር ጋኔን ውጣልኝ፣ አሁኑኑ…ውጣልኝ “ አለችው።
አንጀቷን በለቅሶ ሲያነፍረው የነበረው ሰውዬ በከንፈሩ ጠርዝ ላይ ፈገግ እያለ፣ እንግዲህ “ቻል አድርጊው፤ እኔ አልገደልኩት….ደግሞም ወደ ፍርድ ቤቱ ሲሮጥ መሰለኝ፤ ችግሩ የገጠመው..ጠበቃው ልጅሽ!” ሲላት በቁጣ ጦፋ እንዳንተ ዓይነቱን ነገረ ሰሪ በችሎት አደባባይ ስለረታህ በሞቱ ትቀልዳለህ ? አላቃሽና ለቅሶ ደራሽ በሙሉ ባንድ ድምጽ ከእዚህም ከእዚያም፣ “ምኑ ክፉ ሰው ነው? ጃል፣ ባለጌ፣ ባለጌ በመድኃኒያለም…ቱ” ማለት ጀመረ። ግን ውግዘቱን ከመጤፍ ያልቆጠረው ሰውዬ ጭራም ባይኖረው ኮሌታውን ወደላይ አጥፎ ጥቁር መነጽሩን ግጥም አድርጎ፣ ሹልክ ብሎ ወጣ። እናትን በልጇ ሞት አስለቅሶ ሄደ ፤ የክፉ ሰዎች ደስታ ከእንዲህ ዓይነቱም ክፉ ድንገት ይቀዳል።
እንዲህ ዓይነት ህቁር የሆኑ (Saddist) ሰዎች በሌላው ሃዘን የሚደሰቱ፣ በሌላው ለቅሶ ከጣራ በላይ የሚንከተከቱ በምድራችን አሉ። እንኳንም ቁጥራቸው አነሰ እንጂ፤ ሲኦልን በምድር ማሰልጠኛ ከፍተው ያለማምዳሉ። በአገኙት እድልና ጊዜ መጥተው የህያው ልብ በሙት ዘመዶቻቸው ለቅሶ የሚያነፍሩ ህመምተኞች በየስፍራው አይጠፉም።
በሐገሬም አንዳንድ ስፍራዎች በተፈጠሩት መፈናቀሎች አክቲቪስት ይባሉ “ማይክቲቪስት” የሆኑ ሰዎች እየመጡ “በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት”፤ እንዲሉ የማይረባ ነገር በየማህበራዊ ሚዲያው እየለፈለፉ የሰውን ልብ ማሳዘን ሥራዬ ብለው ያጧጡፋሉ። እነዚህ ድንኳኑ ውስጥ ከገጠመኝ ክፉ ሰው የሚለዩት ደግሞ ክፉ የሚያወሩባቸው ምስኪኖች እንጀራቸውን እንደ ጠበቃው ልጅ ያልበሉባቸው፣ ደሃዎችና ለፍቶ አዳሪ ወገኖቻችን መሆናቸው ነው። ታዲያ፣ ሲገበዙም፣ እኔ ከተፈናቃዮቹ ጋር የግል ጸብ የለኝም፤ ግን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እስከመጡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ቢነሱ ምናለበት ሲሉ አፋቸውን እንኳን ያዝ አያደርጋቸውም። ወጋሁ፣ በሰው ሃዘን የሚደሰቱ ሰዎችን ሃሳብ !! እግረ -መንገዴን ላጽናና ሄጄ መጽናኛ የሌለውን ሃዘን አዝኜ መውጣቴን ሳስበው እገረማለሁ።
ሰው ለምን በገዛ ወገኑ ለቅሶ ይደሰታል። ምንም ቅሬታ ቢኖረው ቅሬታውንና ሃዘኑን፣ የሚያካካስበት ይቅርታ ከልቡ እንዴት ያጣል። ከዚህ ሃዘን ቤት በሃዘን በተመታ ልብ ወጥቼ መኪናዬ ውስጥ ስገባ እጅግ ምስኪን በሆኑ ሰዎች ሰፈር መግባቴን ያወቅሁት ከለቅሶው ቤት ይልቅ መኪናዋ በ”የኔ ብጤዎች” ተከብባ በማግኘቴ ነው። አያታችን ቤት የሚመጡትን ተመጽዋቾች ሲያይ ታናሽ ወንድሜ “ያንቺ ብጤዎች መጡልሽ” የሚላት ትዝ ይለኛል። እርሷም አያርማትም፤ “የኔ ብጤ” በል፤ ትለዋለች፤ እርሷ ከነገረችው ይልቅ ግን “ያንቺ ቢጤ” ማለቱን አይረሳም።
አንድ መቶ ብር አወጣሁና ይህን ብሰጣቸው ለአምስትም ለስድስትም ይቃመሱታል፤ ብዬ ከኪሴ ሳወጣ፣ አንደኛው በመስኮቱ በኩል እጁን ዘርግቶ “መንዝሬው ልስጥህ” ሲል “ቆሜ ሳካፍል አልገኝም እናንተው ተካፈሉ” ብዬው መኪናዬን ሳስነሳ “ጓ” የሚል ድምጽ ሰማሁ ገና ድሮ ግብግብ ይዘዋል። ለመካፈል ጸብ፣ ለመኖር ጸብ፣ ለመማር ጸብ፣ ለመብላት ጸብ፣ ለመስራት ጸብ፣ ለስልጣን ጸብ፣ ለማገልገል ጸብ፣ ለማምለክም ጸብ የማያጣን ለምንድ ነው፤ እላለሁ። ሁላችንም በበጎውም በክፉውም ነገራችን ላይ መፍትሔ ማምጣት የምንሻው በክስና በግርግር ነው። በሰከነ እና በተረጋጋ መልክ ወደ ምንፈልገው ግብ ከመድረስ ይልቅ በሚፈጠር ግጭት ውስጥ ማለፍ ይሆን ውጤቱን ጣፋጭ የሚያደርገው? ይህንን ከሳሽና ወቃሽ መንፈስ ነው፤ ከምድሪቱ ጠርገን ማጥፋት የሚገባን። በቀጥታ ልቤ በአንድ አፍታ ሁለት ሃዘን ሸምቶ ከዚያ ሰፈር ወጣሁ።
እየነዳሁ ሳለሁ ግን ልቤ ከእነዚያ ጎስቋሎች ጋር ነው፤ የቀረው። የሀገሬን ሰዎች የነገር አያያዝ፣ የችግር አፈታትና የቅራኔ ጉዞ እግረ መንግዴን እያሰብኩ ፈጣሪዬን አሰብኩት። ሰሞኑን አንዳንድ ጉምቱ ሰዎች ይሁኑ ድርጅቶች በንቀት ሲወነጃጀሉ ብሰማ ክፉኛ ልቤ አዘነ። ከእነርሱ የምንማረው በ”አንቺታ” መጠራራትን ወይስ መከባበርን ? (በተውላጠ ስም መጠራራት የንቀት ሌላው መልኩ መሆኑን ታውቁታላችሁ፤ ቢሆንም ፌሚኒስቶች እንዳይሰሙኝ)
እነዚህ “ፌሚኒስት” የሚባሉት ቡና ቤት ገብተው ማኪያቶና ወንበር “በወንድ ስም ተጠራ” ብለው ይቆጣሉ፤ አሉ። እኔ ግን እናቴን ስለምወድ፣ ዶሮ ወጢት፣ አሮስቶይት፣ ድንች ጥብሲት …ወዘተ ቢባልም አይከፋኝም። መጥበሻይቱን እና ዘይቲቱን አይለውጡብኝ እንጂ። እነዚህ ተናናቂና ተዛላፊ አካላት፣ እነርሱ “የዋሉበት ሸንጎ፣ ዝንብ የገባበት እርጎ” እየሆነ እኮ ነው፤ አንድም ሐሳብ ለእነርሱ ካልተስማማ የማይሰምርበት፣ ወይም የደሃው እርጎ የማይጠጣበት እየሆነ ነውና።
ኢትዮጵያ ሃገራችን በክፉም ሆነ በደግ፣ የምትወደው እየተጣላት፣ የሾመችው እየከዳት ይሂድ እንጂ፣ እርሷ እንደሆነ እንደ ወራጅ ወንዝ በየመስኩ የምትወልደው ታማኝ አጥታ አታውቅም። የክፋት ጉዶች ሲያጋጥሟት፤ ለደህንነቷ የሚጨነቁላት፣ ስግብግቦች ሲፈነጩባት፣ ጠንቃቃዎች የሚበቅሉባት እየሆነች ሳታልፍ፣ እያሳለፈች አለች። የደከመች ትመስላለች እንጂ አልዛለችም፤ የታመመች ትመስላለች እንጂ አልማቀቀችም፤ ታነክስ ይሆናል እንጂ መራመዷን አላቆመችም። የማደጊያ መንገዷ የኩራቷ ምንጭ የሚሆነው ህብረታችንና አንድነታችን እንጂ መሰነጣጠቃችን አለመሆኑን አሳምራ ነግራናለች።
መሻሻሏን ማየት የሚሻ ሁሉ በየተሰማራበት መስክ ያለውን እያካፈለ መጓዝ፤ ዕውቀቱን እየገበረ፣ ሙያውን በድርጊት እያበሰረ መሄድ ይገባዋል። ዘመን በመጣ ቁጥር ግን የነበረችውን ሃገር “አዲሲቱ” እያሉ እነርሱ የሰሯትና ፣ ሲፈልጉ እነርሱ የሚያፈርሷት መምሰልና ማስመሰልን ማቆም አለባቸው። የቀድሞ የምንላቸው ሳይኖሩም የነበረችውን ያህል መጪዎቹ ሳይኖሩም ነበረች፤ ዛሬም አለች፤ እነርሱ ሲሄዱም ትኖራለች። የዛሬ 30፣ 40ና ሃምሳ ዓመት ድርጅታቸው ተፈጠረ እንጂ፤ ኢትዮጵያን አልፈጠሯትም። እኛ ስንሄድ “ኢትዮጵያ አለቀላት” የሚሉት ወገኖቻችን በማስተዋል ቢራመዱ መልካም ነው። አለበለዚያ “የልጅ ቀላቢ፤ አህያ ጋላቢ” መሆናቸው ሊነገራቸው ይገባል። የልጅ ቀላቢ፣ ለእናቱ ምጥ አስተማሪና ጉረኛ ነዋ!!
አዎ፣ በተደጋጋሚ በረሐብ፣ በተደጋጋሚ በድርቅ ስሟ ተነስቷል፤ ሁሉም ረሐቦችና ድርቆች ሲሆኑ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ከእነርሱ በፊት የነበረውን መንግስት እየጠቀሱ፣ “ሃገሪቱን ለረሐብ እና ህዝቡን ለእርዛት አጋልጦ የራስን ልደት ማክበር፤”…(.ደርግ ኃይለሥላሴን) “ሃገሪቱን ለድርቅ አጋልጦ የአብዮት በኣል ማክበር “… (ኢህአዴግ ደርግን) ”14 ሚሊዮን ህዝብ ለድርቅ አጋልጦ …ግን …ረሐብ የለም “ እያሉ ረሃብስ በ77 ዓመተ ምህረት ነበረ፤ እያሉ ማካካስ አያዋጣም። ረሀቡም፣ ድርቁም፣ ስደቱም፣ ድቀቱም የእኛው ነው። ረሐብ እየተበዳደርን ግን ስልቻ እየተቃማን ግማሽ ምዕተ ዓመት ማሳለፋችን ግን የጋራ እውነታችን ነው።
ታዲያ፣ በእነዚህ ጊዜያት ሰሜኑ ደቡብ እየመጣ፤ ደቡቡ ምስራቅ እየወጣ፣ ምዕራቡ ደቡብ እየሄደ አለፍነው እንጂ ምን ሆንን? በዚህ ክፉ ቀን አቁማዳ መገለባበጣችን ምን ነውር አለውና ዛሬ መሬትህን ሊወስድ፣ ማሳህን ሊወርር መጣ፣ እንባባላን። የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች ደግሞ፣ “ወሰደብህና ወረረብህ” እያሉ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በማህበራት ስም አደራጅተው መሬቱን መያዝና ማረስ ብቻ ሳይሆን ባንኩን በማይመለስ ብድር አጨናንቀው ይወስዱበታል። ይሄ-ይሄ ለራስ ሲታይ “ትክክለኛ ምሪት”፣ ይሆንና ለሌላው የእርቦና የአምሾ ጭሰኛ ሆኖ መባተል ግን ገፈፋና ወረራ ነው የሚባልበት፣ የተገላቢጦሹ ክስ ግን ግራ ታጋባለች።
ወገንን ባለጥፋትና ባለልማትም ብለን በመዘርጠጥ ማየትን ትተን መቆም ይገባናል፤ መወነጃጀል የትም አያደርሰንም። የአክሱሙ አንጥረኛ ሻኪሶ ላይ መጥቶ ወርቅ ካላነጠረ፣ የምእራቡ ጋይንት አዲግራት ሄዶ እብነ-በረድ ካልቀረፀ፣ ሶማሌው ጨው ጭኖ መሐል ሐገር ካልሸጠ፣ አፋሩ ፍየል አርብቶ አዲሳባ ላይ ካላሻገረ፤ ወሎዬው ቅቤ ጭኖ ከጎጃም ካልተለዋወጠ፤ ወለጌ ጥምዝ ወርቁን ሐረርጌ ካልሸቀጠ ምኑን ተዛመድን። የአንዱን ሸዌ ልጅ፣ የሲዳማው ጉብል ካላገባ፤ የመቱው ጎበዝ ከቦንጋዋ ቆንጆ ካልወለደ፣ መልካምነትም ካልተገመደ፣ ምኑን ሃገር ተዋሃደ? በየቀያችን አጥር አጥረን በመብት ስም፣ ከተገፋፋን ምኑን ዜጎች ሆንን … የሃጢያት ስርየት የሚመጣው፣ ያለ ይቅርታ የሚወለደውን በደል እየቆጠርን ሳይሆን ለነገ በፍቅር ልብ ስንኗኗር ነው።
ይህንን እያብሰለሰልኩ፣ ሣለ አጠገቤ ካለው የመድሃኒያለም ቤተክርስቲያን የሚተላለፈውን የስብከት ድምጽ ሰማሁና አለፍኩ። መምህሩ ምን እየተናገሩ ይሆን….. የምጓዘው በዝግታ ቢሆንም ሰላምና መግባባትን እየሰበኩ እንዲሆን በመመኘት ነው፤ ያለፍኩት። ቀጥሎ የ”ሰማሪያዊው ቦርሳ” የሚል ጽሁፍ ያለበትን አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ታፔላ አይቼ አለፍኩኝ። በእውነት ሳምራዊው ሰው እንዳደረገው የተጎዳን አይቶ፣ የቆሰለን አክሞ መጠጊያ የሚያበጅ ይሆን ወይስ “የድህነት ጌቶች “ (Lords of Poverty) ተብሎ ተጽፎ በተተረጎመው መጽሐፍ ላይ እንዳሉት እርዳታ ሰብስበው እንደሚጠቀሙት አካላት ይሆኑ – ይሆን ስል አሰብኩኝ። እርሱም እንዲሁ እንደተመኘሁት መልካም እንዲሆን አሰብኩ።
እኛስ ስለሌላው ወገናችን ምን ክፉ እያሰብን፣ ምን ክፉ እየተናገርን፣ ምን ክፉ እያደረግን ይሆን? ብለን መጠየቅ የተገባ ነው፤ ይህንን ማጤን አለብን። ሁላችንም ወደ ውስጣችን ማሰብ ስንጀምር፣ ራሳችንን መመርመር እንጀምራለን። ውስጣችንን የመረመርንም ሰዎች፣ የችግራችን መፍትሔ አካሎች ለመሆን አናመነታም። የአንዳንዶቻችን ችግር ግን ችግራችንን ሁሉ በሌላው ላይ በማላከክ ራሳችንን ንፁህ የማድረግ አባዜ የተጠናወተን መሆናችን ነው።
ሰበበኞችና አላካኪ ሰዎች እውነተኛ ችግራቸውን ከመቀበል ይልቅ የችግራቸውን ምንጭ ደጅ ላይ ይለጥፉታል። ነውራቸውን ሌላ ሰው ላይ ያላክካሉ፤ ሆስፒታል ቢሄዱ ያልዳኑት ህክምናውን ባለመከታተላቸው ሳይሆን፣ በሃኪሙ ስህተት ፣ፈተና ቢወድቁ በመምህሩ ክፋት፣ ከሚስታቸው ቢጣሉ በነገር አያያዛቸው ድክመት ሳይሆን በአማታቸው መሰሪነት፣ ዕድገት ባያገኙ በአለቃቸው፣ (አንዳንዴ ያጋጥማል) መጥፎነት፣ ነው።
በሓገርም ጉዳይ እንዲህ ያጋጥማል። በኢትዮጵያ ላይ ያኮረፉ ሁሉ ያኮረፉት በራሳቸው ነው። እንዲህ አላደረገችልኝም፤ እንዲህ በድላኛለች፤ ይህንንና ያንን ከልክላኛለች እያሉ ከሚሰጡት ይልቅ የሚቀበሉትን እያሰቡ የሚቀሩና መብት ፈላጊ ግዴታ አልባዎች ስለሆኑ፣ ወይ በዝምታ ጥፋቷን ይጠባበቃሉ፤ ካለዚያም ከአጥፊዎቿ ጋር ድንበር ተሻግረው ይተባበራሉ። ክፋቱ ለለውጥ መምከራቸው አይደለም፤ የባዕድ ሃሳብ ይዘው አብረው መዶለታቸው ነው።
ወደ መኝታዬ ሳልፍ ሃገሬን አሰብኳት። እንዴት ትሆን ይሆን ? ራስ ወዳዱ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ ባዩ፣ ሰበበኛና አላካኪው፣ ነጻ አውጭ ነኝ ባዩ፣ “እሄዳለሁ” ባዩ፣ እመጣለሁ ባዩ፣ አኩራፊው፣ አድፋጩ፣ አልማጩ፣ ናቂው ተናቅሁ ባዩም፣ ወዘተርፈ ተቀላቅለው እንደ እኔ ወደመኝታቸው ያልፋሉ ወይስ በደንብ አልታመሰችም፤ በሃይል አልተጎዳችም፤ ገና ይቀራታል፣ ብለው ለጥፋቷ ሴራ ይሰራሉ።
የሚያዋጣን ግን ለእርሷ የሚገባትን እየሰጠን ከእርሷ የምንቀበለውን ስንሰራው ነው። የተቀባይነት መንፈስ አሳሪም፣ አጭበርባሪም ነው። ከሌሎች የሚጠብቁ ሁሉ ምስኪኖች ሲሆኑ የማይጠብቁ ግን ብሩካን ናቸው። በራሳቸው ወጥተው ይገባሉ፤ ኢትጵያንም ወደ ብርሃን አቅጣጫ ያዞሯታል፤ በሌላው የማያላክኩ ሰዎችም ጽኑኣን ናቸው፤ እውነት ከእነርሱ ጋር ናትና የእውነትን ምሬት ፊት ለፊት ይጋፈጧታል። በነገራችን ላይ….እ.. በደንብ እንዳነበባችሁት እርግጠኛ ነኝ። አስተያየት ካላችሁ በአዲስ ዘመን በኩል ይደርሰኛል፤ ፃፉልኝ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ