ሕንድ ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነጻነቷን ካወጀችበት እአአ ከነሐሴ 1947 አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሳዳር ፓታል የተባሉ የሕንድ ፖለቲከኛ ስለ ሁለቱ የህንድና የፓኪስታን ወንድማማች ህዝቦች መለያየት አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ « በሒንዱ እና በሙስሊሞች መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቶ ወደ ጠብና ክፍፍል እንዲያመራ በሁለቱ ወንድማማቾች ትከሻ ላይ የልዩነት ሸክምን የጫነው ማነው? ቢባል ምክንያቶቹ ብሪታንያዎች ናቸው። እስኪ እኔ ብሪታንያን ላንድ ሳምንት እንድገዛ ፍቀዱልኝ። ኢንግላንድ፣ ዌልስ፣ ስኮትላንድ ለዝንተ ዓለም የሚጋጩበትን ጠብ መፍጠር እችላለሁ።» ብለው ነበር ከዛሬ 71 ዓመታት በፊት።
በሌላ በኩል «ዛሬ በእኩለ ሌሊት ዓለም ሲተኛ ሕንድ የነፃነት ብርሐን ለመፈንጠቅ ትነቃለች።» ያሉት የመጀመሪያው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀዋሐራል ኔሕሩ ሕንድ እአአ ነሐሴ 14 ቀን 1947 ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃነቷን በአወጀችበት ጊዜ ነበር። በዚህ ወቅትም የመጀመሪያው የፓኪስታን መሪ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ በበኩላቸው፤ «ሒንዱስታን እና ፓኪስታን ውስጥ የሚመሰረቱት የተረጋጉና ዘላቂ መንግሥታት ወዳጅና ጎረቤት እንደ ሆኑት ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ በመተባበር እንደሚኖሩ ተስፋ አለኝ» ብለው ነበር።
ነገር ግን አበው ውሃን ከምንጩ ወሬን ከመሰረቱ እንዲሉ ሁለቱ አገሮች ከዛሬ ሰባ ዓመት በፊት ነፃነታቸውን ቢያውጁም፤ ነፃነታቸውን ካወጁበት እለት ጀምሮ ሁለቱን ወንድማማቾች በሁለት ጎራ ከፋፍሎ ለዘመናት የሚያባላው ታሪክ እንዲህ ተጀመረ።
የቬኒሲያው ነጋዴና አገር አሳሽ ማርኮ ፖሎ የምሥራቁን ሐብት፣ ባሕል እና ፖለቲካዊ አስተዳደር ለምዕራቡ ካስተዋወቀበት ከሺ ሁለት መቶዎቹ ማብቂያ ጀምሮ፤ አውሮፓዎች ያንን ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ የሚታፈስበትን፤ ማዕድን የሚዛቅበትን፤ ሐርና ጥጥ የሚጋዝበትን ሰፊ ንዑስ ክፍለ ዓለም ለመቆጣጠር ቋመጡ።
ከምሥራቅ ይልቅ ደቡብ አሜሪካ ላይ አገዛዛቸውን የተከሉት የስፓኝና የፖርቹጋል ጠንካራ ክንድ እየዛለ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ጡንቻ ባበጠበት ዘመን፤ የለንደንና የፓሪስ ገዢዎች የቆየ ምኞታቸውን ለማሳካት ወደ ምሥራቅ ሲያማትሩ በቀላሉ የማይጋፉት ጠንካራ ሐይል መኖሩን ተረዱ።
እ.አ.አ ከ1526 ጀምሮ ርዕሰ-መንበሩን ከአግራ እስከ ፋቴፑር ሲኪሪ፣ ከሻሐጃናባድ እስከ ደልሒ እየቀያየረ እስከ አፍጋኒስታን የተዘረጋውን ሰፊ ምድር የሚገዛው የሙስሊሞቹ የሙግሐል ሥርወ- መንግሥት፤ በቅጡ ላልደረጀው አውሮፓዊያን የሚደፈር አልነበረም።
ይሁንና አውሮፓዊያኖቹ ጠንካራውን የሙስሊሞች ሥርወ-መንግሥት ሰርስረው በመግባት ገዝግዘው የሚጥሉበት ብልሐት፣ ተንኮልና ትዕግስት ሞልቶ ተርፏቸው ነበር። ፖርቹጋሎች፣ ፈረንሳዮችና ሮሞች በንግዱና በክርስትና ስም በመስበክ እንዲሁም በጉብኝት ሰበብ ወደ ቀየው በመዝለቅ በመደለያ ስጦታዎች በማማለል በእዚያ ምድር እግራቸውን ለመትከል ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልቆፈሩት ጉድጓድ አልነበረም ።
ነገር ግን ወደ ምስራቁ ዓለም ለመዝለቅ እንደ ብሪታንያዎቹ የተሳካለት ግን አልነበረም። ብሪታንያዎቹ እ.አ.አ በ1600 የጆን ኩባንያ ብለው የመሠረቱትን ኩባንያ በ17 መቶዎቹ አጋማሽ፤ «የምሥራቅ ሕንድ ኩባንያ» በሚል አዲስ ሥም ሰጥተው ወደዚያ ትልቅ ግዛት አዘመቱት። ጥጥ፣ ሐር፣ ጨው፣ ሻይ ቅጠልን የመሳሰሉ ትናንሽ የፍጆታ ምርቶችን በመነገድ የጀመረው ይህ ትንሽ ኩባንያ የአውሮፓ ተቀናቃኞቹን እየፈነገለ፤ የትልቁን ክፍለ ዓለም ትላልቅ ገዢዎችን እያታለለ እና ሕዝቡን እየከፋፈለ እ.አ.አ በ1858 ተልዕኮውን ከግብ አደረሰ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታላቋ የምስራቁ ዓለም ክፍል ሕንድ በቀጥታ በለንደን ነገስታት እጅ ወደቀች።
በዚህም በወቅቱ የገዢነቱ ሥልጣን በአውሮፓዊያኖች ተወሰደብን ብለው የብሪታንያን ቅኝ አገዛዝ ለመቃወም ቀድመው ያመፁት ሙስሊሞች ነበሩ። ነገር ግን ፀረ-ቅኝ ግዛቱን ትግል የሚመራ እና የሚያስተባብር የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረቱት ሒንዱዎች ሲሆኑ፤ እ.አ.አ በ1885 በቦምቦይ ወይም በሙባይ የተመሠረተው የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ መላውን ሕንዳዊ እንደሚወክል መሥራቾቹ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ከ73 የፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣናት 54ቱ ግን የሒንዱ እምነት ተከታዮች ናቸው። በያኔዋ ሕንድ ብዙ ቁጥር ይዘው ከነበሩት ሙስሊሞች ለፓርቲው ከፍተኛ ሥልጣን የበቁት ሁለት ብቻ ነበሩ። በዚህም እኩል ቅኝ በሚገዙትበትና መታገል በሚፈልጉት አገራቸው በአገራቸው ልጆች የተገለሉ የመሰላቸው ሙስሊሞች ቅሬታ አጭሮባቸው፤ እ.አ.አ በ1906 በባንግላዴሽ ዳሐክ ውስጥ የሙስሊም-ሊግ ያሉትን የፖለቲካ ማሕበር መሠረቱ። የፓርቲው መስራችና ኋላ የመጀመሪያው የፓኪስታን መሪ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ እንዳሉት፤ ፓርቲያቸው ሙስሊሙ የሚያደርገውን ትግል ከማስተባበር ባለፈ ትልቁን ግዛት የመከፋፈል ሐሳብ አልነበረውም ብለዋል።
የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ቅኝ በያዙት አገሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ደከም ያለውን ደገፍ፤ ጠንከር ያለውን ኮርኮም እያደረጉ የሁለቱን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ወደ ጠብ፤ የሁለቱን ኃይማኖት ተከታዮች ወደ ግጭት ይገፏቸው ያዙ። እ.አ.አ ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የሚደረጉ የፀረ ቅኝ አገዛዝ አመፅ፣ አድማና ሰልፎች ሁሉ ፈራቸውን እየለቀቁ በሙስሊምና ሒንዱዎች ጠብና ግጭት ያሳርግ ጀመር።
መሐመድ ዓሊ ጂናሕ፣ መሐተመ ጋንዲ እና ጀዋሐራል ኔሕሩ አንድነትን ለመጠበቅ በተደጋጋሚ ያደረጉት የነበረውን ድርድርና ውይይት ትኩረት በመነፈጉ፤ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ ከአንድነት ባሻገር ያለውን አማራጭ ግልፅ አደረጉ።
እርሳቸውም «በሰፊው የሕንድ ንዑስ-ክፍለ ግዛት ከሚኖሩት በርካታ ጎሳና ኃይማኖቶች መካከል ሁለት ዋና ዋና ብሔሮች አሉ። ሒንዱ እና ሙስሊም። በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች አናሳ ሊባሉ አይችሉም። በሕንድ ምዕራባዊና ምሥራቃዊ ቀጣና ብቻ ያለነው ከሰባ ሚሊዮን እንበልጣለን። በነዚህ አካባቢዎች ከሚኖሩት ሒንዶዎች ጋር ሲነፃፀር ቁጥራችን ከሰባ ከመቶ ይበልጣል። ሕንድ በሂንዱስታንና ፓኪስታን ለሁለት እንዲከፈሉ እንፈልጋለን። ለሒንዱዎችም ለሙስሊሞቹም ነፃነትን የሚያረጋግጠው ይሕ ብቻ ነው» በማለት የመፍትሄ ሃሳብ ያሉትን ይዘው ብቅ አሉ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የብሪታንያ ሕዝብ ሀብትና ንብረቱ ቢወድምበትም፤ ልጆች አባታቸውንና ዘመዳቸውን ቢያጡም ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችልን ህዝቡ እንደ ድል አድራጊ ጀግና አድናቆትና ሙገሳ ቸራቸው። ነገር ግን እ.አ.አ በ1945 በብሪታንያ በተደረገው ምርጫ የብሪታንያ ሕዝብ ቸርችልና ፓርቲያቸውን በምርጫው ባለመምረጡ፤ በምርጫው ያሸነፈው የሌበር ፓርቲ መሪ ክሌመንት አትሌ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ተቆናጠጡ። እርሳቸውም ስልጣን በያዙ ማግስት ሕንዶች ነፃ እንዲወጡ በመወሰናቸው፤ እ.አ.አ 1947 ንጉስ ጆርጅ አራተኛ የነፃነት ደንብ የተባለውን ሕግ ለማፅደቅ ጊዜ አልፈጁም ነበር።
ሕጉ ከመፅደቁ በፊት የሕንድ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የጀመሩትን ድርድር እና ውይይት አላቋረጡም ነበር። ነገር ግን እ.አ.አ ግንቦት 1947 አንድነቷን የጠበቀች ሕንድን ለመመሥረት የተደረገው ሙከራ ከሸፈ። ጋንዲ እራሳቸውን ከፖለቲካ ሲያገሉ፤ የሙስሊም ሊግ መሪ መሐመድ ዓሊ ጂናሕ እና የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ ጀዋሐራል ኔሕሩ ሕንድን ለመክፈል ተስማሙ።
ሁለቱ ዋና ዋና ፖለቲከኞች ከብሪታንያ አገረ ገዢ ሎርድ አድሚራል ሉዊስ ጋር ሆነው ነፃነቱም ክፍፍሉም አንድ ቀን እንዲሆን ወሰኑ። እንደ አውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ነሐሴ 14 ቀን 1947 ሕንድ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ ሆና ለሁለት ተከፈለች።
«በታሪክ ብዙም የማይታይ አጋጣሚ ነው። አሮጌውን አልፈን ወደ አዲሱ እንሸጋገራለን። አዲሲቱን ሐገራችንን እንረከባለን። ለረጅም ጊዜ የተጨቆነችው ሐገር በስተመጨረሻው ትንሳኤ አግኝታለች» ሲሉ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀዋሕራል ኔሕሩ አስተጋቡ። በተመሳሳይ ካራቺ ላይም አዋጅና ደስታ ፌስታ ሆነ።
እ.አ.አ ነሐሴ 15 ቀን 1947 ነፃነት ሆነ። ነገር ግን ነፃነቱ ወደ እርስ በእርስ ብጥብጥ ተቀይሮ የማቃጠል፣ የመዝረፍ እና የመግደል ነፃነት ሆነ። እንዲሁም ደልሒ እና ካራቺ በደስታ ሲፈነድቁ፤ ማዕከላዊ ፑንጃብ ግን በእሳት ትጋይ ጀመር።
ግድያ፤ ዘረፋ፤ስደቱ በፑንጃብ ሲያይል፤ ስድስት ሚሊዮን ሙስሊሞች ከዛሬዋ ሕንድ ወደ ዛሬዎቹ ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ተሰደዱ። ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ሒንዱ ከፓኪስታንና ከባንግላዴሽ ወደ ሕንድ ፈለሱ። ጓዝ ለመስበስብ ጊዜ አልነበረም። ሙስሊሙ ከሕንድ፣ ሒንዱ ከፓኪስታን ማቄን ጨርቄን ሳይል እየተግተለተለ ተሰደደ። በዚህ ግርግር አንድ ሚሊዮን ሰው አለቀ።
ነገር ግን ማሃተመ ጋንዲ እ.አ.አ ከ1914 ጀምሮ በሕንድ ሠላማዊ የነፃነት ትግልን ሰብከዋል። የትግል ሥልታቸው አብነት በመላው ዓለም ናኝቷል። ወገናቸው ግን አልተቀበላቸውም። ተከፋፋለ፣ ተላለቀ፣ ተሰደደ።
እርሳቸው አክለውም፤ «ብዙ ጥፋት ደርሶብናል። ብዙ ተፈትነናል። ጠንካራ ትግል አድርገናል። ይሕ ሁሉ ትግልና ፈተና ከዝናቡ ወደ ጎርፉ ለመግባት ነበር? ይሕ አካሄድ ትክክል አይደለም። የተለያየ ኃይማኖት ተከታዮች ነን። ነገር ግን ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። ወንድማማቾች ይተቃቀፋሉ» ሲሉ በሁሉም ጎራ ጽንፍ ለያዙና ጦር ለሰበቁ የሙስሊምና የሕንዱ ወንድማማቾች የሰላም ጥሪያቸውን አቀረቡ።
ነገር ግን የሰማ እንጂ የተቀበላቸው አልነበረም። እንዲያውም በሐይማኖት የሚጋራቸው ሒንዱ ፅንፈኛ ገደላቸው። ምዕራባዊ ፓኪስታን የተባለችው ሙስሊማዊቷ ባንግላዴሽም ከሙስሊማዊቷ ፓኪስታን ተነጥላ ሌላ ነፃ መንግሥት መሠረተች። ሕንድና ፓኪስታንም ባለፉት ሰባ ዓመታት ሰላም እርቋቸው ሰባት ጊዜ ተዋግተዋል። ከሰባቱ ሁለቱ ዋና ዋና ጦርነቶች በካሽሚር ግዛት ሰበብ የተጫረ ነው።
ሙስሊሞች የሚበዙበት የካሽሚር ገሚስ ግዛት በሒንዱዎች እጅ በመቅረቱ ዛሬም ካሽሚር በህንድና በፓኪስታን የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ግጭቶችን የምታስተናግድ የውጥረት ግዛት ስትሆን፤ የህንድ መንግሥት ለካሽሚር ግዛት ልዩ መብት የሚሰጠውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ለመሰረዝ መወሰኑን ለአገሪቱ የህግ አውጭ ምክር ቤት በያዘነው ሳምንት ሰኞ ዕለት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ህንድና ፓኪስታን ወደ ጦር አውድማ ለመግባት ዳር ደርሰዋል ሲል ቢቢሲ በድረገጹ አስነብቧል።
ህንድ ለምታስተዳድራት የካሽሚር ግዛት የሰጠችውን ልዩ ህገ መንግሥታዊ መብት ለመሰረዝ መወሰኗን በተመለከተ የሕንድ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አሚት ሻህ እንዳብራሩት፤ የፈዴራል መንግሥቱ ለካሽሚር ልዩ መብት የሚሰጠውን ድንጋጌ የያዘውን የህገመንግሥቱን አንቀፅ 370 ለመሰረዝ ወስኗል። በዚህም ህንድ በአብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብ የሚኖርበትን የካሽሚር ግዛት ከአገሪቱ ጋር አንድ አድርጋ ለማስተዳደር ማቀዷን ገልጸዋል።
አንቀፁ በድንጋጌው አወዛጋቢዋ የካሽሚር ግዛት የራሷን አዋጆች የማዘጋጀትና ሌሎችም የነጻ ውሳኔ ልዩ መብቶችን የሰጣት ቢሆንም፤ አሁን የፌዴራሉ መንግሥት በወሰነው ውሳኔ መሰረት አንዱ አንቀፅ ተሰርዞ ቀሪው የህገ መንግሥቱ ድንጋጌ በሙሉ በካሽሚርና በጃሙ ግዛት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፤ ካሽሚርና ጃሙ በሕንድ አስተዳደር የሚጠቀለሉ ይሆናሉም ተብሏል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ የፌዴራሉ መንግሥት የአንቀፁን መሰረዝ ይፋ ከማድረጉ በፊት የካሽሚር ግዛት መሪዎች በቁም እስር ላይ መሆናቸውና በግዛቷም የቴሌኮም አገልግሎቶች መቋረጡ ተገልጿል።
የህንድ መንግሥት ይፋ ያደረገውን ውሳኔ ተከትሎ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ በፓኪስታን የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ የሁለቱ ጎረቤታሞቾቹ የኒውክለር ጦር መሳሪያ ባለቤቶች ፍጥጫ ወደ ጦርነት ለማምራት ከጫፈ ደርሷል።
ህንድ የካሽሚር ግዛትን ልዩ ራስ ገዝ አስተዳደር ስርዓትን መንጠቋን ተከትሎ የፓኪስታን ጦር ሃይል ኢታማዦር ሹም ጀነራል ቀመር ሸሪፍ እንደተናገሩት፤ የፓኪስታን ጦር ለካሽሚር ህዝብ መብትና ነፃነት ድጋፍ ለማድረግ የትኛው ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ለመጠቀምና እስከመጨረሻ ድረስ ለመጋደል ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን በበኩላቸው፤ ‹‹የሕንድን ጠብ አጫሪነት ዓለም ይስማልኝ›› ሲሉ ፓርላማቸውን ሰብስበው ለዓለም ህዝብ አስተጋብተዋል። እርሳቸውም ሰፊውን የሙስሊም ማህበረሰብ ወደ ህንድ እንዲጠቃለል ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለሆነ በጸጥታው ምክር ቤት ለመታገል መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
የሁለቱ አገራት ጎረቤት የሆነችው ቻይና የሕንድን ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው ስትል ያጣጣለችው ሲሆን፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን በካሽሚር እና በቀጣናው ፀጥታ ዙሪያ ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሃን ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
ሶሎሞን በየነ