የአፍሪካ ቀንድ ለአካባቢው ደህንነት በእጅጉ አስጊ በሆነ መልኩ የአለም አቀፍ ኃያላን መንግስታት የባሕር ኃይሎች የተከማቹበት ቀጠና ሆኗል። ቀጠናው አሳሳቢ በሆነ የጸጥታና ደህንነት ችግር ውስጥ ነው ማለት ይቻላል።
ታላላቅ የተባሉት መንግስታት አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይ፤ ሩሲያ፤ ቻይና፤ ጃፓን፤ ኋላ መጤዎቹና ከዚህ በፊት ያልነበሩት ሳኡዲ አረቢያ፤አረብ ኢምሬት፤ ግብጽ፤ ቱርክ ጭምር በጅቡቲ የጦር ሰፈሮች መስርተዋል።
የጅቡቲ መንግስት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እነዚህ ሀገራት በአገሪቷ ላይ ሰፊ ጫና አድርገዋል። ጉዳዩ እኛንም በጥልቀት ያሳስበናል። ለሁሉም ቀጠናው በማንኛውም ሰአት ያልተጠበቀ ግጭት ውስጥ ሊገባ ይችላል። ኢትዮጵያም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የወጪና ገቢ ንግዷን ለመጠበቅ የራሷን ባሕር ኃይል ዳግም ለመመስረት ሰፊ ስራ በመስራት ላይ ትገኛለች።
በጅቡቲ ገደብ የለሽ የተለያዩ ሀገራት የጦር መርከቦች ክምችት መኖርና ፍጥጫው የአፍሪካ ቀንድን የጦር ቀጠና አስመስሎታል። ሁሉም የበላይነቱን ለመያዝ ጥድፊያ ውስጥ ይገኛል። ቀጠናው አደጋ እያንዣበበት በመሆኑ የተለያዩ የውጭ ፍላጎቶች በአፍሪካ ቀንድ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ በያዙት ትንቅንቅ ቀንዱን እየቆለፉት መጥተዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጃፓን ለንግድ ፍሰቷ ወሳኝ የሆነውን በአፍሪካ ውሀዎች ላይ ያላትን ፍላጎት ለማስከበር ያለችበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም ሲል ኒው አፍሪካን ድረገጽ ገልጾአል። አንቨር ቨርሲ እና ጆሴፍ ሀሞንድ በቀጠናው ያለውን ውስብስብ ተለዋዋጭነት / ዳይናሚክስ/ ዘግበውታል፤ እኛም እንዲህ ቃኝተነዋል።
በኒው አፍሪካ ሪፖርት መሰረት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካለፉት ጥቂት አመታት ጀምሮ በአስገራሚ ሁኔታ እጅግ አደገኛ ቀጠና እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል። የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካል ተለዋዋጭነት የስበት ኃይሉ ወሳኝ በመሆኑ ቀድሞ የነበሩና ያልነበሩ አዳዲስ ተጨዋቾች በጣም ክፍልፋይ በሆኑ ትናንሽ ነገሮች ጭምር ግጭት ሊፈጥሩ በሚችሉበት ሁኔታ እንዲከማቹ አድርጓል።
በአለም አቀፍ የነዳጅ ዘይት ንግድ ዋናው የመተንፈሻ መስመር በሆነው በሆርሙዝ ባሕረሰላጤ ቀደም ሲል በሁለት መርከቦች ላይ የተካሄደው ጥቃትና እንደገናም ሁለተኛው ጥቃት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መከሰቱ በአካባቢውና በመንግስታቱ መካከል ያለውን ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ አባብሶታል።
በቅርቡ ኢራን መርከቦቹን ያገተችው በነዳጅ ዘይት የውጭ ንግዷ ላይ ለተጣለባት ማእቀብ የወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ነው ስትል አሜሪካ ትወነጅላለች። የሆርሙዝን ባሕረሰላጤ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የሚለያየው የአረቢያ ባሕረሰላጤ ስፋት ሲሆን ሁለቱንም የሚገዛቸው የጂኦ ፖለቲክስ ተለዋዋጭነት ተመሳሳይ ነው።
በአሁኑ ወቅት ውጥረቱ አይሎአል። አብዛኛው የአለም ሕዝብ በዚህ አስፈሪ ግጭት ሊያስነሳ በሚችል ጉዳይ ላይ ተኝቶበታል። ይህም ገልፉን የአፍሪካ ቀንድንና የአለምን ኢኮኖሚ በከፋ ሁኔታ ሊያወድም ይችላል።
አውሮፓ በተለይም እንግሊዝ የአካባቢውን ኃይል ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለመያዝ እየታገለች ነው። ዶናልድ ትራምፕ በትዊተራቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፍሊፕ ፍሎፕ (እንዘጭ እንቦጭ) ሲሉ ገልጸውታል። በጉዳዩ ላይ ለመናገር የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ ሙሉ በሙሉ ትንፋሽ አጥሮአቸዋል። ይህ የኃያላን ሀገራትና ከዚህ በፊት በቀጠናው ያልነበሩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጦር ኃይሎች በአፍሪካ ቀንድ መከማቸት ቀዝቃዛው ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ሊባል ይችላል።
በሱዳን ያለው ሁኔታ በባሕልና በጂኦግራፊ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የተያያዘና በሰሜንም ከእስላማዊ መንግስታት ጋር መገናኘቱ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል። የሱዳን ሠራዊት በአስከፊ ሁኔታ ተቃውሞ ባቀረቡ ሲቪሎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሞአል። የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር መንግስት ወደሌሎች የውጭ ኃይሎች ሳኡዲአረቢያ ፤ አረብ ኢምሬት ግብጽና እንዲሁም ምእራባውያን አጋሮች ሙሉ በሙሉ ለሞራልና ማቴሪያል ድጋፍ ሲል ፊቱን ከማዞሩ በፊት ከሲቪል ኃይሎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ መሆኑ መልካም ነው፤ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ተስማምተው ረቂቅ ሕገመንግስት አውጥተዋል።
የመንን ለማውደም ሳኡዲ አረቢያ ከኢራን፤ ቱርክ፤ ኳታር በተለይም ሩሲያና ምናልባትም ቻይና በትብብር ለሚያደርጉት ዘመቻ ሱዳን ግዙፍ ሠራዊት አቅራቢ መሆኗ አሳሳቢ አድርጎታል። ይህ የተለያዩ ሀገራት የጦር ኃይል በአፍሪካ ቀንድ ተፋጦ መከማቸቱ ለአፍሪካ እንደ አንድ ነጻ አህጉር የሚሰጠው ትርጉም ግዙፍ ነው። ጉዳዩ በእጅጉ አሳሳቢ በመሆኑ ትንሽም ቢሆን በአፍሪካ ሕብረትና በግል በከፍተኛ ደረጃ ውይይቶች ተካሂደዋል። ብዙ የአፍሪካ ተመልካቾች የማስጠንቀቂያ ደወል በመደወል ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ክልል ያለው እምቅ ሁኔታና እድል ግዙፍ ፍንዳታ ሲያስከትል ሁለት መሪዎችን ብቻ ነው የበለጠ የሚያስጨንቀው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድና የጃፓኑን ጠ/ሚር ሺንዞ አቤን በቅርቡ የአሜሪካንና የኢራንን ውጥረት ለማርገብ ቴህራን ጎራ ብለው ነበር።
ጃፓን በራሷ የጃፓን ፓስፊክ ሕግ በተጨማሪም ባለው የመሰባሰብና የጦርነት ሁኔታ ጭምር ደስተኛ አይደለችም። ሁኔታው ጃፓንን በአፍሪካ ቀንድ እንግዳ ተዋናይ አድርጓታል። በቀንዱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የኃያላን ሀገራት የባሕር ኃይል ክምችት በመኖሩ ጃፓን ውስን ኃይል ቢኖራትም በድንገተኛ ሁኔታ ተጨማሪ መሆን አትችልም። ትኩረቷ ግን ከፍተኛ ነው።
ለሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በአደገኛ የጦርነት ስጋት ቀለበት ውስጥ ይገኛል። የጃፓን የባሕር መከላከያ ኃይል በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል። ምን እንደሚመጣ፤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለማይታወቅ።
በሚያዝያ አጋማሽ በሕንድ ውቅያኖስ መካከል የየመን መርከብ በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች በኃይል ከተወረረችና ከተያዘች በኋላ የሶማሌ ሽፍታዎች የወሰዷትን መርከብ ዋነኛ (እናት መርከብ ) አድርገው በመጠቀም በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ተሰማርተው በነበሩ ሁለት የስፔን መርከቦች ላይ ማጥቃት ሰንዝረዋል።
የመርከቧ በሚያዚያ 19 መያዝ የመጀመሪያው የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የፈጸመውን ትልቅ ጉዳይ ያሳያል። ከ2017 እኤአ በፊት መርከብ በሶማሌ የባሕር ወንበዴዎች ተጠልፎ ይህንኑ እንደ እናት መርከብ እየተጠቀሙ ተጨማሪ ማጥቃቶችን የሚሰነዝሩበት ሁኔታ አልነበረም። በባሕር ወንበዴዎች የተያዘው መርከብ በአውሮፓ ሕብረት የባሕር ኃይል ሚያዚያ 23 እንዲለቀቅ ሲደረግ 5 ተጠርጣሪ ወንበዴዎች ታስረዋል። በርካታ ታጋቾች ተለቀዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የባሕር ላይ ወንበዴዎች መቀነስ ብዙ ሀገራት በአካባቢው የሚያደርጉትን ዘመቻ እንዲያቆሙ አድርጎአል። ኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት) የራሱን ጸረ-የባህር ላይ ወንበዴዎች ዘመቻ የዘጋው በ2014 (እኤአ) ነው።
ቢሆንም የጃፓን የባሕር መከላከያ ኃይል (ማሪን ዲፌንስ) ጃፓን በአካባቢው ባላት ቁርጠኝነት የተነሳ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል። በዚህ አመት የጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ “ ጃፓን በሶማሊያና በኤደን ባሕረሰላጤ እያደገ የመጣው የባሕር ላይ ውንብድና ያሳስባታል” ሲል አስፍሮአል። .
ከ2012 (እኤአ) ጀምሮ ትርጉም ባለው ደረጃ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የሚያደርጉት ጥቃቶችና ጠለፋዎች ቀንሰዋል። ጃፓን ይህን የምትመለከተው ለዘረፋና ለውንብድና የሚያበቃው መሰረታዊ ምክንያት በቦታው ላይ እንዳለ ነው። ለጊዜው ቀንሶ የሚታየው ውንብድና ተመልሶ ቦታውን ሊይዝ ይችላል። ጃፓን ጸረ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ዘመቻውን በ2009 (እኤአ) ስትጀምር የኤደን ባሕረ ሰላጤና የአፍሪካ ቀንድ ባሕሮች በአመት 200 የውንብድና ተግባሮችን ያስተናግዱ ነበር።
በ2011 በአረብ ስፕሪንግ የተነሳውን ሕዝባዊ ማዕበል ተከትሎ ከሁሉም ጊዜዎች በላቀ ሁኔታ የባሕር ላይ ውንብድና ተስፋፍቶ በማደግ በአመት ቁጥሩ 237 ደርሶ ነበር። ከጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜና ምንጮች በተገኘው መረጃ መሰረት ባለፈው አመት 3 ብቻ የባሕር ላይ ውንብድናዎች ነበሩ።
ጃፓን በአካባቢው በጥበቃ ላይ አሰማርታቸው የነበሩትን 2 ዲስትሮየር የጦር መርከቦች በ2016 (እኤአ) ወደ አንድ አውርዳለች። በጉዳዩ ላይ ቁርጠኝነቷን በመጠበቅ ተልዕኮዋን ወደ ሌሎችም ዘርፎች አስፍታለች። ጃፓን ሁለት ፒሲ 3 የባሕር ኃይል ቅኝት አውሮፕላኖችን የዘመቻው አካል አድርጋ በአካባቢው አሰማርታለች። በጅቡቲ በ2011 (እኤአ) በመሰረተችው ጦር ሰፈር 200 የሚጠጉ ጃፓናውያን ይኖራሉ።
በጃፓን ራስ ተከላካይ ኃይሎች ከተቋቋመው ወታደራዊ ጦር ሰፈር ጀርባ ያለው ምክንያት ግልጽ ነው። ጃፓን ለአለም አቀፍ የባሕር ዘመቻዎች ድጋፍ እንድታደርግ ማስቻል ነው። ከ2013 (እኤአ) ጀምሮ ሶስት ጃፓናውያን አዛዦች የሕብረ ብሔራዊው ኃይል አዛዦች በመሆን በጸረ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ዘመቻ የባሕር ኃይል መርከቦችን በመጠበቅ ሰርተዋል።
ባብል መንደብ ለጃፓን አለም አቀፍ ንግድ ዋነኛው መስመር ነው። ጃፓን የነዳጅ ፍላጎቷን ከመካከለኛው ምስራቅ ዘይትና ጋዝ ላኪዎች የምታስገባው በዚሁ መስመር ነው። ጃፓን የአፍሪካን ውሀ የምትጠብቀው የነጻና ግልጽ ኢንዶ ፓሲፊክ ስትራቴጂክ ራዕይ አካል በማድረግ ነው። ይህም አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገልጹት ለቻይና የመቀነት መንገድ ግንባታ (ቻይና ቤልት) ተነሳሽነት አማራጭ ለመሆን ነው።
የኤሽያን ባሕርና የሕንድ ውቅያኖስን አቋርጠህ ወደ ናይሮቢ ስትመጣ አፍሪካና ኤሽያን የሚያገናኘው የባሕር መስመሩ እንደሆነ በደምብ ትረዳለህ ሲሉ የጃፓኑ ጠ/ ሚነስትር ሽንዞ አቤ በ2016 (እኤአ) ናይሮቢ ላይ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ በተለያዩ ሀያል አገራት ፍላጎት እጅጉን የበረታበት አካባቢ ነው። ቀጠናው በዋናነት ለሚዋሰኑት አገራት ጥቅም መቆም አለበት የሚል አቋም ቢኖርም ዋና ጥቅም ተጋሪዎቹ ግን ተዋሳኞቹ አለመሆናቸው በአካባቢው ትኩረት ስቧል። ጥቅም እና ጉዳት እየተመዘነ ለተጎራባች አገራት ተቆንጥሮ የሚሰጠው ጥቅም ግን አሁንም በአካባቢው ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011
ወንድወሰን መኮንን